የስፖርት ሚናው በርካታ ቢሆንም ለሶስተኛው ዓለም ግን ትርጓሜው በእጅጉ ላቅ ያለ ነው፡፡ ኋላ ቀር በምትባለው አህጉረ አፍሪካ በማህበራዊ፣ በባህል፣ በፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን እያበረከተ ያለ ነው፡፡
አፍሪካውያን የስፖርቱ ተዋናዮች በሁለት ሊከፈሉ ይችላሉ፤ ይኸውም በሀገራቸው ስፖርት ተሳታፊ የሆኑ እንዲሁም ባህር አቋርጠውና ከሀገራቸው ርቀው በሌሎች ሀገራት ስፖርት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ በሚል፡፡ በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሀገራቸው ርቀው በሌሎች ሀገራት ስፖርት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ አፍሪካውያን ለሀገራቸው መልካም ገጽታ ግንባታ አስተዋጽኦ ከማበርከታቸው ባለፈ፤ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ያላቸው አበርክቶም ከፍተኛ ነው፡፡
አፍሪካ በስፖርተኞች ምንጭነት የታደለች አህጉር ስትሆን፤ በ50 ዓለም አቀፍ የስፖርት ማህበራት ውስጥ ንቁ ተሳትፎም አላት፡፡ በተለይ የሚታወቁት ስፖርቶች ደግሞ እግር ኳስ፣ የመምና የጎዳና ላይ ሩጫ፣ ክሪኬት እንዲሁም የራግቢ ስፖርቶች ነው፡፡ በፓራሊምፒክ ስፖርትም አፍሪካ ብቃት ያላቸው ስፖርተኞች ምንጭ መሆናቸውን የስፖርት ማህደሮች ያመላክታሉ፡፡
እግር ኳስ
ይህ ስፖርት በአህጉሪቱ ከታወቀ 200 ዓመታትን ማስቆጠሩን በጽሁፍ የተገኙ መረጃዎች ያስነብባሉ፡፡ ይህ ስፖርት በተለይ ከቀኝ ግዛት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ያደገና የተስፋፋ ሲሆን፤ እጅግ ተዘውታሪና ተወዳጅ ስፖርት ሆኖ እስካሁንም ድረስ ዘልቋል፡፡ የምዕራብ እና መካከለኛው አፍሪካ ሀገራት በተለይ በኳስ ስፖርቶች የብቃት ማዕከል መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በአውሮፓ ያሉት በቁጥር የበዙ አፍሪካውያን ተጫዋቾች ለዚህ ማሳያ ሲሆኑ እንደ ዓለምዋንጫ ባሉ ውድድሮችም አዝናኝ ጨዋታ በማሳየት ጭምር ተፎካካሪዎች ናቸው፡፡ ደቡብ አፍሪካ እአአ በ2010 የዓለም ዋንጫን እንድታዘጋጅ በዓለም አቀፍ ደረጃ እግር ኳስን ከሚመራው ተቋም (ፊፋ) ማግኘቷ በእርግጥም በስፖርቱ ያላትን ቦታ የሚያመላክት ነው፡፡
እግር ኳስ በመላው አህጉሪቷ ባሉ ሀገራት ሊባል በሚችል ደረጃ የሚዘወተር ስፖርት ከመሆን አልፎ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችንም አስገኝቷል፡፡ ሀገራቸውንና ራሳቸውን በመልካም ከመወከላቸው አልፈው በሚያገኙት ገቢ ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን የሚወጡ ስፖርተኞች ቀላል የሚባሉ አይደሉም፡፡ ሌሎች ታዳጊ ወጣቶችም እነርሱን በመመልከት ወደ ስፖርቱ በመግባታቸው ስፖርቱ በአህጉሪቱ ባህል የሆነ ሲሆን፤ አንድ የገቢ ምንጭና የስራ ዘርፍ በመሆንም እያገለገለ ይገኛል፡፡ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ተጽእኖ በማሳረፍ ረገድም የአፍሪካን ያህል ሚናውን ያሳየበት የለም ሊባል ይችላል፡፡
አትሌቲክስ
ሌላኛው ተወዳጅና በአህጉሪቱም ተዘውታሪ ስፖርት ነው፡፡ ከአፍሪካውያን የአኗኗር ሁኔታ ጋር ተያይዞ በርካቶች ወደዚህ ስፖርት የመግባት ዝንባሌ አድሮባቸዋል፡፡ በሁሉም የአትሌቲክስ ስፖርቶች አፍሪካውያን ተወዳዳሪ ቢሆኑም ምስራቅ አፍሪካ በተለይም እንደ ኬንያ፣ ኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ ያሉ ሀገራት በተለይ በማራቶንና ሌሎች የጎዳና እንዲሁም የመም ውድድሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀዳሚዎቹ ሀገራት ናቸው፡፡ ከሩጫው በሚገኘው ገቢም በርካቶች ከራሳቸው አልፈው ለወገኖቻቸው የስራ እድል በመፍጠር ለሀገራቸው የውጭ ምንዛሬ ምንጭ በመሆንም ከፍተኛ ሚና እንዲጫወቱ እያስቻለ ነው፡፡
ቅርጫት ኳስ
በዚህ ስፖርትም ከሀገራቸውና አህጉራቸው አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃም ተወዳዳሪ የሆኑ በርካታ አፍሪካውያን ሀገራት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ይህ ስፖርት እአአ ከ1960ዎቹ ጀምሮ የታወቀ ሲሆን፤ በጊዜ ሂደት ተወዳጅነቱና ተዘውታሪነቱ አድጓል፡፡ ስፖርቱ በተለይ በታዳጊና ወጣቶች ዘንድ ተወዳጅ በመሆኑ በአፍሪካ አብዛኛዎቹ ሀገራት ባሉ ትምህርት ቤቶች የቅርጫት ኳስ ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን መመልከት የተለመደ ነው፡፡ ግብጽ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ናይጄሪያ ደግሞ በስፖርቱ ከሀገራቸው ባለፈ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይም ስመ ጥር የሆኑ ስፖርተኞችን ማፍራት ችለዋል፡፡ ዲኬምቤ ሞቱቦ እና ሃኬም ኦልጆዎን ደግሞ ለዚህ ምሳሌ የሆኑ ተጫዋቾች ናቸው፡፡
ክሪኬት እና ራግቢ
ይህም ስፖርት በአብዛኛው ሊባል በሚችል ሁኔታ በአፍሪካ ሀገራት የሚዘወተር ቢሆንም በተለይ በኬንያ እና ዚምቧቡዌ ቁጥሩ ከፍ ያለ ነው፡፡ በደቡብ አፍሪካም ያደገና የተስፋፋ እንዲሁም በወንዶች እና በሴቶች ክለቦችን ከማቋቋም አንስቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እስከመሆን የተደረሰበትም ነው፡፡
ሌላኛው ስፖርት ራግቢም በተመሳሳይ በአፍሪካ ታዋቂና ተዘውታሪ በመባል በቅድሚያ ከሚጠቀሱት ስፖርቶች መካከል ነው፡፡ ጋና፣ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ናሚቢያ ደግሞ በዚህ ስፖርት ይበልጥ ታዋቂ ናቸው፡፡ በአህጉሪቱ ብቻ እስከ 600 ሺ የሚሆኑ የራግቢ ተጫዋቾች መኖራቸውም ይነገራል፡፡ የዚህ ስፖርት ተወዳጅነት በአህጉር አቀፍ ደረጃ ፌዴሬሽን እንዲመሰረት ከማድረግ ባለፈ በዓለም አቀፉ ማህበር ውስጥም 37 የሚሆኑት አባል ሀገር በመሆን ሊመዘገቡ ችለዋል፡፡ ስፖርቱ በሚዘወተርባቸው በእነዚህ ሀገራት ውስጥም በየዓመቱ በርካታ ውድድሮች ይደረጋሉ፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 23/2014