ብዙዎች የሚያውቋቸው በጎበዝ ሰራተኝነታቸውና በአይበገሬነታቸው ነው። በተለይም በፓርላማ ላይ ያልመሰላቸውን አሻፈረኝ የሚሉ በመሆናቸው ብዙ ጊዜ በግምገማ እንደሚደበደቡ ይናገሩላቸዋል። ከዚያ በፊት በነበሩበት የአመራርነት ህይወትም እንዲሁ ያሰቡትን ከማሳካት ወደኋላ የማይሉ እንደሆኑ ይነገራል። በትምህርት ህይወታቸውም ቢሆን ህጻን እያጠቡ ሳይቀር የሚማሩና ተጠቃሽ ተማሪ የሆኑ እንስት ናቸው።
ስድስት ልጆቻቸውንና ባለቤታቸውን አስተምረው ራሳቸውንም ለሁለተኛ ዲግሪ ያበቁም ናቸው። በዚህ ህይወታቸው ውስጥ የነበሩ ውጣውረዶች ደግሞ ብዙዎችን የሚያስደምምና የሚያስተምር ነው። እኛም ለዛሬ የ‹‹ህይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳችን ያደረግናቸው ይህ ተሞክሯቸው ብዙዎችን እንደሚገነባ በማሰብ ነውና ወይዘሮ ፀሐይ ደምሴን ተዋወቋቸው ስንል ጋበዝናችሁ።
ብቸኛዋ ሴት
ቤተሰቡ እናትና አባት ተጨምሮ አራት ናቸው። ልጆቹ ብቻ ደግሞ አንድ ወንድና አንድ ሴት ሲሆኑ፤ እርሳቸው ብቸኛ ሴት ልጅ ለመሆን አስችሏቸዋል። በእርግጥ ሴት ይባሉ እንጂ በአኗኗር የወንድ ልጅ ህይወትን ነው ያሳለፉት። ምክንያቱም ውሏቸው ከአባታቸው ጋር ነው። በዚህም የቤት ውስጥ ሥራ ሰርተው አያውቁም። ግብርናውን ጨምሮ የውጭ ሥራ ግን እርሳቸውን የሚያክላቸው አልነበረም። ጨዋታቸውም ቢሆን ከወንዶች ጋር ነው። በረኛ እስከመሆን ድረስ የእግር ኳስን የሚጫወቱም ነበሩ። በዚያ ላይ ፈረስ መጋለብ ልዩ ችሎታቸው ነው። በዚህ ግን እናት በጣም ይናደዱባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
ታናሽ ወንድማቸው የእርሳቸው ተቃራኒ ነው። ውሎው ከእናቱ ጋር ስለነበር የሴት ሥራ የሚባል አይቀረውም። እናቱን የሚደግፈው እርሱ ነው። እናም እናት ‹‹ምን አለበት ጾታችሁን ብትቀያየሩ›› ይሏቸው እንደነበርም አይረሱትም። ግን በሌላ ጎኑ የሚመሰገኑበት ነገር እንደነበር ይናገራሉ። ይህም በደርግ ጊዜ ሁሉም ወደ ዘመቻው በአመራበት ወቅት መሬቱ ጦም እንዳያድር የጎረቤቱን ጭምር እያስተባበሩ ሲሰሩ የነበሩት እርሳቸው ናቸው። አጥራቸው የፈረሰ ሰዎች ሳይቀር የሚያጥሩትም እርሳቸው ነበሩ። ስለዚህም ሴት ብትሆንም እንደወንድ አገልግላናለች የማይላቸው ጎረቤት አልነበረም። እናታቸውም ሆኑ አባታቸው ደግሞ በዚህ ተግባራቸው በጣም ያመሰግኗቸው እንደነበር አጫውተውናል።
ትውልዳቸው በቀድሞ ሸዋ ክፍለ አገር ሰላሌ አውራጃ ውስጥ ያያጉለሌ ወረዳ ሳድኒ ለሚ በሚባል ገበሬ ማህበር ውስጥ ነው። እስከ አምስተኛ ክፍል ድረስ በዚያ ቆይተዋል። በዚህም የፈለጉት ነገር እየተሟላላቸውና ነጻነት ተሰጥቷቸው ነው ያደጉት። በተለይ የማይረሱት ነገር ከአባቶች እግር ስር ቁጭ ብለው ታሪኮችንና የሽምግልና ሥርዓቱን እንዲያዩ የሚደረገው ምንም እንኳን ወንዶች ብቻ ቢሆኑም እርሳቸው ግን ከአባታቸው አይለዩምና ማንም አይከለክላቸውም። በዚያ ላይ አባታቸው የተከበሩ ባላባት በመሆናቸው እርሳቸው ያሉት ይሆናልና ባለታሪካችን በነጻነት የፈለጉት ቦታ ላይ እንዲሳተፉ መፈቀዱን ነው።
ይህ አባቶች እግር ስር መቀመጥና ማደጋቸው በህይወታቸው ላይ ብዙ አሻራን እንዳኖረ የሚናገሩት ወይዘሮ ፀሐይ፤ አስተዋይ ልጅ፣ ታዛዥ ልጅ፣ ቀልጣፋና አገር ወዳድ ልጅ የሆኑት በሚሰጧቸው መመሪያዎች መሰረት መስራት በመቻላቸው እንደሆነ ያስታውሳሉ። ጥቃትን የማይወዱ፣ አንሶ መታየትን የሚጸየፉ ያደረጋቸውም ይህ ታሪክ ሰሚነታቸው እንደነበርም ይናገራሉ።
በባህሪያቸው ተደባዳቢ ሲሆኑ፤ ከዚህ የተነሳ ‹‹ነብሯ›› የሚል ቅጽል ስም ወጥቶላቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። በምክንያት የሚያምኑና ዝብ ብሎ ለማሳመን ሲጥሩ እሽ የማይሉም ናቸው። ማስመሰልና ችሎ ማደርም አይችሉበትም። ሁሉን ፊት ለፊት መናገር መለያቸው ነው። በዚህም የልጅነት ፍላጎታቸው በጊዜው ትርጉሙን ባያውቁትም ማናጀር መሆን
እንደነበር ያስረዳሉ። በእርግጥ ለዚህ ምክንያታቸው ፍራንሲስ የሚባለው የእንግሊዝኛ መምህራቸው ሲሆን፤ ከትምህርት ቤቱ ለየት የሚሉና ብዙዎቹን የሚመሩ እንደሆኑ ስለሚነግራቸው የተፈጠረባቸው ልዩ ፍላጎት ነው።
በትምህርት ተስፋ አይቆረጥም እንግዳችን በጣም ጎበዝ ብቻ ሳይሆኑ አርቆ አሳቢም ናቸው። መሆን የሚፈልጉትን ለመሆን ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም። እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ድረስ የመማር ህልም ያላቸው ናቸው። ያንን ለማድረግ ደግሞ ዛሬ ድረስ ይታትራሉ። በእርግጥ ብዙም የቀራቸው አይደሉም።
ምክንያቱም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ይዘዋል። ይህም ቢሆን በቀላል እንዳልተገኘ ግን ይናገራሉ። በተለይም ቅድሚያ ለልጄ በማለታቸው የትምህርት ጉዟቸው በፈለጉት ሰዓት እንዳይጠናቀቅ እንዳደረጋቸው ያወሳሉ። ከዚህ ጎን ለጎን ያለእድሜ ጋብቻና የቤተሰብ ሃላፊነትም እንዲሁ ትምህርታቸው ላይ ፈተና ከሆኑባቸው ጉዳዮች ተጠቃሽ ናቸው።
እንግዳችን ልጆች ከማንኛውም ሰው የተለየ እንክብካቤን ይሻሉ። ምክንያቱም ታዳጊ በመሆናቸው ብዙ የሚረከቡት ነገር አለ። በተለይም መልካም ስብዕናና አገር ወዳድነት እንዲሁም ለሌሎች መኖርን ከእነርሱ በላይ ሊማረው የሚገባ አካል የለም ብለው ያምናሉ። በዚህም ከባለቤታቸው በፊት ከምግብ ጀምሮ ቅድሚያ የሚሰጡት ለልጆቻቸው እንደነበር አይረሱትም። በትምህርት በኩልም ቢሆን ልጆቻቸውን ካስተማሩ በኋላ ባለቤታቸውን አስተምረዋል።
ከትምህርት ጋር የተገናኙት ለሁለት ሩብ ጉዳይ በእግር ተጉዘው በሚያገኙት በያያጉለሌ ወረዳ ፍታል ከተማ ፍታል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ክፍል ተምረውበታል። በጣም ጎበዝና ሁሉም መምህራን የሚወዷቸው አይነት ተማሪ ሆነውም ነው ያሳለፉበት። ነገር ግን ከዚያ በላይ በቦታው መቀጠል አልቻሉም። ምክንያቱም በሴትነታቸው ምክንያት ብዙ ፈተና ይደርስባቸው ነበር። በተደጋጋሚ ሊጠልፏቸው ሲሉ ቤተሰቦቻቸው እያስጣሏቸውም ነው የቆዩት። እንዲያውም ጥይት እስከመተኳኮስ የደረሰ ጸብ ውስጥ ተገብቶ እንደነበርም አይረሱትም። ስለዚህም አባት ከዚያ ርቀው እንዲማሩ አደረጉ። በዚህም ጉዟቸው ቤት ተከራይተው ከትንሹ ወንድማቸው ጋር በመሆን ፍቼ ከተማ ላይ መማራቸውን ቀጠሉ።
በፍቼ ሁለት ቁጥር ትምህርት ቤት ስድስተኛ ክፍልን የተከታተሉ ሲሆን፤ ከሰባት እስከ 12ኛ ክፍል ደግሞ በፍቼ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በትምህርት ቆይታቸው በጣም ጎበዝ ተማሪ ሲሆኑ፤ መምህራንም ሆኑ ተማሪዎች የሚጠቅሷቸው ናቸው። በዚህም ከፍተኛ ውጤት በማምጣት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን መቀላቀል ችለዋል። ነገር ግን ትምህርቱን መቀጠል አልቻሉም። ምክንያቱም ወልደው ልጃቸውን ለባለቤታቸው ትተው ስለሄዱ ብዙም ሳይቆዩ ልጁ ታመመ። ስለዚህም መልቀቂያ ወይም ዊዝድሮ (Withdraw) ሞልተው ልጃቸውን ለማዳን ባለቤታቸው ወደሚሰራበት ቦታ አቀኑ።
የሚገቡበት ጊዜ ከመድረሱ በፊት ቁጭ ከማለት ብለው ሥራ ተወዳደሩ። አልፈውም ማስተማር ጀመሩ። ለዚህ የሚሆን ትምህርትም በመምህራን ስልጠና ተቋም (Teachers’ Training Institute – TTI) ቲ.ቲ.አይ ተምረዋል። ወደ ዩኒቨርሲቲ የመግቢያ ጊዜያቸው ሲደርስ ደግሞ ሁለተኛ ልጃቸውን በማርገዛቸው መግባት አቃታቸው። ስለዚህም ሥራውን ዝም ብለው ቀጠሉት። መማሩን ግን ማቆም አልሆነላቸውምና ህጻኑ አደግ ሲልላቸው ዳግም ወደ ትምህርት ተመለሱ። ትምህርቱ ደግሞ በክረምት ያገኙት የትምህርት እድል በመሆኑ በደንብ ተጠቅመውበታል። በኮተቤ መምህራን ኮሌጅም በከፍተኛ ማእረግ በዲፕሎማ በባይሎጂ ትምህርት መስክ መመረቅ ቻሉም።
‹‹እኛ ስንማር አይደለም ኢንተርኔት መብራት አልነበረም። ጥናት ከታሰበ በፋኖስ ነው። በዚያ ላይ ልጅ አለ፤ ባልም የሴቷን እንክብካቤ ይፈልጋል። ስለዚህም ቤቱ እንዳይጎል ሃላፊነቴን እየተወጣሁ፤ በፋኖስ እያነበብኩ ጉብዝናዬን ሳልቀንስ ዛሬ ላይ ደርሻለሁ። በተለይ 12ኛ ክፍል ተፈታኝ ሆኜ የወለድኩበት ጊዜ ላይ በመሆኔ ውጤቴ ከሌሎች እንዳያንስ ልጁን በቀኝና በግራዬ እያዟዟርኩ በማቀፍና በማጥባት አጠና ነበር። ልጄ በጣም ሃይለኛ በመሆኑም እንቅልፍ ሳላይ የማድርበት ጊዜ ብዙ እንደነበር አረሳውም። ይህ ደግሞ ትዕግስትና ህልም ስላለኝ ታልፏል። ›› ይላሉ።
ወይዘሮ ፀሐይ ዊዝድሮ ከሞሉ በኋላ ወደ ዩኒቨርሲቲው አልተመለሱም። ሰርቶ እየበሉ ልጆቻቸውንና ቤተሰቡን ማኖርን በመምረጣቸው ከቲ.ቲ.አይ ጀምረው እንዲማሩ ሆነዋል። በዚህም የተለያዩ ሥራዎችን ከሰሩ በኋላ ነው ዲፕሎማ፣ ዲግሪና ሁለተኛ ዲግሪ እያሉ ትምህርታቸውን የቀጠሉት። እንደውም የፍቼ ከተማ አፈ ጉባኤ ሆነው እየሰሩ ሳለ ነበር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ለመማር የተወዳደሩት።
ዲፕሎማቸውን በመንግስት የትምህርት እድል አግኝተው ቢማሩም ዲግሪያቸውን ለመማር ግን ምንም አይነት እድል አልነበራቸውም። በዚህም መማር የህይወት ለውጥ እንደሆነ ያምናሉና በራሳቸው ለመማር አልፋ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በርቀት በማኔጅመንት የትምህርት መስክ ተማሩ። መማር ልምዳቸው የሆነው እንግዳችንም ክረምት ላይ ተመርቀው መስከረም ላይ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን እንዲማሩ ተወዳደሩ ተባሉ። እድልቀናቸውናም ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ገቡ። በአርባን ማኔጅመንት በከፍተኛ ውጤት መመረቅ ቻሉም።
በእስካሁን ቆይታቸው ለመማር የሚያስችሉ ምንም ሁኔታዎች እንዳልነበራቸው ያጫወቱን ባለታሪካችን፤ መቼም ቢሆን ህልሜን ሳላሟላ አልቀመጥም ይላሉ። በዚህም ሦስተኛ ዲግሪያቸውን እንደሚማሩ ነግረውናል።
ሥራና ፈተናው
12ኛ ክፍል እየተማሩ ሳለ ነበር የመሰረተ ትምህርት ዘማች ሆነው ጉረኔ የተባለ ቦታ ለማስተማር የዘመቱት። በዚህም ብቻቸውን ሲመላለሱ በተደጋጋሚ ጅብ ይገጥማቸው ነበር። በተለይ መጀመሪያ ሳያውቁት የሆኑትን መቼም አይረሱትም። እግሬ አውጪኝ ብለው እስከመሮጥ ደርሰዋልም። ነገር ግን ምንም እንዳልሆኑና አንድ ገበሬ እንዳስጣላቸው ያስታውሳሉ።
ቀጣዩ ያስተማሩበት ቦታ ደብረ ሊባኖስ አካባቢ የሚገኘው ቃሲም ትምህርት ቤት ሲሆን፤ አምስት ዓመታትን በቦታው ላይ ቆይተዋል። ባለቤታቸውን አስተምረው ካስመረቁ በኋላ ደግሞ እርሱ ከተማ በመግባቱ የተነሳ ወደ ደብረ ጉራቻ፣ ኩዩ ወረዳ እንዲዛወሩ ሆኑ። ኩዩ ትምህርት ቤትም ማስተማር ጀመሩ። ዘጠኝ ዓመትም አስተምረዋል። በአጠቃላይ በመምህርነት 14 ዓመታትን አሳልፈዋልም። ከዚያ በኋላ ደግሞ ወደ አመራርነቱ ነው ያቀኑት።
ወደ አመራርነት የከተታቸው ነገር በሪሳ ጋዜጣ ላይ በብዕር ስም ብሶታቸውን አውጥተው የጻፉት ሥራቸው ነው። በእርግጥ በወቅቱ ጥሩ ጸሐፊ አልነበሩም። የመናገር ያክል ተናደው ስለነበር ውስጣቸውን ለመግለጽ ሞከሩበት እንጂ። ይህ ግን አመራሩን ሙሉ ለሙሉ አስደንግጦት ነበር። ለሴቶች የሚሟገት ሰው መፈለግ ነበርናም ብዙ መረጃቸዎችን እርሳቸውን የሚገልጽ ጽሁፉ ላይ ነበረበትና በቀጥታ እንዲያገኙዋቸው ሆነ። እውነቱም ታወቀ። በዚህም ለሴቶች ጉዳይ ተጠሪነት እንዲመረጡ አደረጋቸው።
የነገሩን መነሾ ሲያነሱም እንዲህ ነበር ያሉን ‹‹የስምንተኛ ክፍል ፈተና ለመፈተን ምርጫ ሲከናወን የምናስተምረው ሴቶች እያለን እኛን በመተው ተጠቃሚዎቹ ወንዶች እንዲሆኑ አደረጉ። ብንከሳቸውም ነገሩ ስህተት ነው ለሚቀጥለው ይስተካከላል ተባልን። በዚህም ሁላችንም ታመምን፤ ሳይበልጡን እንዲበልጡን የሚሰጣቸው እድል በጣሙን አበሳጨን። በዚህም ብዕሬን አነሳሁና ‹ለሴቶች መታገል ፖለቲካ አይደለም› በሚል ጹሁፍ ጻፍሁ›› ይላሉ። ይህ ደግሞ ፍቼ ዞን ላይ ግራር ጃርሶ የሚባል ወረዳ ሴቶች ጉዳይ ሃላፊ ሆነው ለመሾማቸውም መነሻ ሆኗል።
ግራር ጃርሶ ወረዳ ላይ የመጀመሪያዋ የሴቶች ጉዳይ ሃላፊ እንደነበሩ የነገሩን ወይዘሮ ፀሐይ፤ መዋቅሩ ገና ያልተጀመረ በመሆኑ እንደ ኦሮምያም ጭምር በወረዳ ደረጃ አዲስ ፖዚሽን የያዙ መሆናቸውን አጫውተውናል። ለዚህ ደግሞ ማሳያው መዋቅሩ ባለመኖሩ ክፍያቸው በትምህርት ጽህፈት ቤት አማካኝነት መሆኑ ነው። ተጠያቂነት እንዳይኖርም የትምህርት ቤቱ ምክትል ሱፐርቫይዘር አድርገው እንደሾሟቸው ያስታውሳሉ።
ቀጥለውም ቢሆን ሹመቱ አለቀቃቸውም ነበር። ከፍ ተደርገው በትምህርት ጽህፈት ቤቱ ውስጥ የዞኑ ሴቶች ጉዳይ ሃላፊ ሆነው ሰርተዋል። ከስድስት ወር የሥራ ላይ ቆይታ በኋላ ደግሞ በተመሳሳይ ከሴቶች ሥራ ሳይወጡ የዞኑ ሴቶች ማህበርን በሊቀመንበርነት እየመሩ ለረጅም ዓመታት አገልግለዋል። በዚህ ቆይታቸው ለየት ያለ ተግባርም እንዳከናወኑ አይረሱትም። ለሴቶች ለውጥ ብዙ ለፍተዋል። ከእነዚህ መካከልም የሰላሌ ሴቶች ልዩ ባዛር ያዘጋጁበትና ብዙዎችን ተጠቃሚ ያደረጉበት አንዱ ነው። ሌላው አይሴማ የሚባል የሴቶች ማህበር በሟጮዋቸው የገነቡትን ቤት የዞኑ ፍትህ ቢሮ ወስዶ አልሰጥም በማለቱ በህግ ተጠያቂ በማድረግ አስመልሰው ቢሯቸው ጭምር እንዲሆን በማድረግና ቀሪውን በማከራየት ማህበሩን ተጠቃሚ ያደረጉበት ሁኔታም ተጠቃሽ ነው።
እንግዳችን የፍቼ ከተማ አስተዳደር አፈ ጉባኤም ነበሩ። ከትምህርት በፊት ሁለት ዓመት ከትምህርት በኋላ ደግሞ አንድ ዓመት አገልግለውበታልም። የተማሩት ትምህርት የከተማ አስተዳደር በመሆኑ የከተማው ከንቲባ እንደሚሆኑ አምነው ነበር። ቀደም ሲል በአፈጉባኤነት የሰሯቸው ሥራዎች በኦሮምያ ጭምር ተሸላሚ ያደረጋቸው ስለነበር ወደዚያ እንደሚያድጉም ተስፋ አድርገው ነበር። ነገር ግን ይህንን እድል ሴት በመሆናቸው ሳሰጧቸው ቀሩ። በዚህም ዘላለም የሌሎች ሃሳብ አስፈጻሚ መሆኑን አልፈለጉትምና የዞኑ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሃላፊ በመሆን ሥራቸውን ቀየሩ። ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ደግሞ የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት ምክትል ሃላፊ ሆነው ሰሩ። ከዓመት አገልግሎት በኋላ ለፓርላማ በመመረጣቸው ቀጥታ ወደ ፓርላማ ገብተው ሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ውስጥ ለስድስት ዓመት ያህል እንዲያገለግሉ ሆነዋል።
‹‹ሶሳይቲ ፎር ውመን›› የሚባል ድርጅት ፍቼ ላይ ገብቶ እንዲሰራ ያደረጉና ብዙ ሴቶችን ዛሬ ድረስ ተጠቃሚ እንዲሆን ያስቻሉት ወይዘሮ ፀሐይ፤ የድርጅቱ የቦርድ ምክትል ሰብሳቢ በመሆን ያገለግላሉም። ከሁሉም በላይ ሰራሁ የሚሉት ደግሞ በማዕዴን ላጋራ ላይ የመጀመሪያ መልስ የሰጡት እርሳቸው መሆናቸውን ነው። በዚህ ጥሪ ከባለሀብቶችና ከሴቶች በመሰብሰብ ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማድረግ የቻሉ ናቸው። አሁንም ቢሆን በኮሚቴ ደረጃ ስለተዋቀረ ትንሽ ብር አለ። ተጨማሪ እንቅስቃሴ በማድረግ ለድሆች የሚደርሱ መሆናቸውንም አጫውተውናል።
በቀጣይ ማንም አዛዥ ናዛዥ ሳይኖርባቸው በራሳቸው የሚንቀሳቀሱበትን ተግባር ለመከወን አስበዋል። ይህም የበጎ አድራጎት ሥራ ሲሆን፤ በተለይም ዋና ህልማቸው ሴቶችን ማገዝ ነውና በእዚያ ላይ ትኩረታቸውን ያደርጋሉ። ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ላይም እንዲሁ የመስራት እቅድ አላቸው። ለዚህ ያነሳሳቸው የሀመርን ብሔረሰብ ማየታቸው ነው። በዚህም ለችግረኞች እንትረፍ በሚልም እየተንቀሳቀሱ ረጂዎችን እያፈላለጉ እንደሆነና ፕሮፖዛል በማዘጋጀት ላይ እንዳሉ አጫውተውናል።
ምክረ አዲሱ መንግስት
‹‹በቀደመው የፓርላማ ጉዟችን በተለይም በ2008 እና 2009 ዓ.ም ላይ ብዙ ፈተናዎች ነበሩብን። ሲኦል ውስጥ እንዳለሁ ይሰማኝም ነበር። ለዚህ ደግሞ መነሻው ብቻችንን የኢህአዴግ ፓርቲ አባላት መሆናችን ነው። ይህም ሆኖ ለውጡ ሲመጣ ግን ብዙ ነገሮች ተለውጠዋል። ነባር አሰራሮች ቢኖሩም መነጋገር እንደተጀመረ አይቼበታለሁ። ለዚህ ደግሞ ፓርላማው ሲመሰረት ጀምሮ ሲታገሉ የቆዩ ወጣቶች፣ ህዝቡና አንዳንድ ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። ለዓመታት ከነበርንበት ፈተና አውጥተውናል። ነገር ግን አዲሱ መንግስት ሲመሰረት አሁንም ብዙ ነገሮች መለወጥ እንዳለባቸው አምናለሁ። ›› የሚሉት ወይዘሮ ፀሐይ፤ የአስተሳሰብ ለውጥ ላይ መስራት ያስፈልጋል። ምክንያቱም አቀማመጣችን ጭምር በብሔር ነበር። ይህ ደግሞ ሥራችንም ወዴት ሊያጋድል እንደሚችል በግልጽ ያሳያል። ስለሆነም አዲሱ መንግስት ትኩረቱን ሊያደርግበት የሚገባው ጉዳይ አንዱ ይህ መሆን አለበት።
ሌላው ምርጫው ከቀደመው እኛ ተወዳድረን ከገባንበት የታሰበውን ያህል ባይሆንም ተፎካካሪ ፓርቲዎች የተካተቱበት ነው። እነርሱን መጠቀምና እንዲሟገቱ መፍቀድ ላይ ትልቅ ሥራ መስራት ይጠበቅበታል። ምክንያቱም መንግስትን ከስህተቱ የሚመልሱ ሊሆኑ ይችላሉና። የሃሳብ መንሸራሸሩም የተሻለ ሃሳብ ለማምጣት ያስችላልም። ስለሆነም ማድረግ ይገባዋል። በተመሳሳይ የፓርላማ ጽህፈት ቤት አሰራርም ሙሉ ለሙሉ መቀየር አለበት። ምክንያቱም አመራሩም መመሪያውም መቀየር ካልቻለ የቀደመው ፓርማ ሂደት የማይቀጥልበት መንገድ አይኖርም።
የአባላቱ ተግባርና ሃላፊነት ተብሎ የተቀመጠው ነገር ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የሚያሰራ አይደለም። በእጅ አዙር ጭምር አመራሩ የሚሰራበትን ሁኔታም የሚፈጥር ነው። ይህ ደግሞ አሁንም ድረስ የዘለቀ በመሆኑ እነዚህ ህጎችና ተግባራት በደንብ መፈተሽና መታየት አለባቸው። የዶክተር አብይ መንግስት ይህንን አስቦ መስራት ይኖርበታል። በእርግጥ አሁን የተመረጡት አባላት እሺ የሚሉ አይደሉም። እኛም መጀመሪያ አካባቢ ያን አይነት ባህሪ ነበረን። ነገር ግን በህጉ ጫና ሲደረግብን እሺ ወደማለቱ ገብተናል። እናም አሁን የሚመሰረተው መንግስት ይህንንም ታሳቢ አድርጎ መንቀሳቀስ እንዳለበት ያስገነዝባሉ።
አሁን ወደ ፓርላማ የሚገቡ ከእኛ የማይለዩ የድርጅቱ አባላትም ቢሆኑ ማድረግ ያለባቸው ነገር አለ። ከቀደመ አስተሳሰብ ያልተላቀቀ ብዙ ነገራቸውን ይዘው መግባትና በዚያ መመራት የለባቸውም። ምክንያቱም የቀደመው አሰራር ብዙ ነገሮቻችንን ቀምቶናል። ህዝባችንንም እንዳናገለግለው ገድቦናል። ስለሆነም እንደስሙ አዲስ ሆነን በአዲስና አገርን በሚያስቀድም አስተሳሰብ ለመስራት ቁርጠኛ መሆን፣ መታገል አለባቸው። በምክንያት እንቢ የሚሉ አባላትም መሆን ይጠበቅባቸዋል። የቢሮክራሲው አሰራር ሙሉ ለሙሉ እንዲቀረፍም የተቻላቸውን ያህል መስራት ይኖርባቸዋልም ብለዋል።
አዲሱን መንግስት ሌሊት ድረስ ቆሞ ህዝብ የመረጠው በምክንያት ነው። ከዚህ በኋላ ዝም ብሎ የማየት አቅሙ አይኖረውም። ጊዜያዊ የሰብዓዊ መብታችን ይከበርልናል እንጂ ዘላለማዊ እነርሱን ይዘን እንዘልቃለን ብሎም አይደለም የመረጣቸው። ስለዚህም ተመራጩ ዝም ተብሎ እንደማይታለፍ አምኖ ለህዝብ የሚመጥን ሥራ መስራት አለበት። እሺ ሲባል ምክንያታዊ ባለመሆኑ አገራችን 30 ዓመት ሙሉ ችግር ተሸክማ እንድትኖር ሆናለች። ዛሬም ያልፈታነው ችግር የመጣው በዚህ ምክንያት ነው። ስለሆነም አዲሱ መንግስት የተከማቹ ችግሮችን በቁርጥ እርምጃ ማስወገድ ይኖርበታልም ባይ ናቸው።
አዲሱ መንግስት ቢወስደው ብለው ያነሱት ሌላው ጉዳይ ፓርቲ ስለወደደው ሳይሆን ህዝብ ስለወደደው ብቻ የሚመረጥ መሪና አመራር በእያንዳንዱ ቦታ ላይ መቀመጥ መቻል አለበት የሚለውን ነው። በዘመድ አዝማድ መሿሿም የትም እንደማያደርስ መረዳት ያስፈልጋል።
ቤተሰብ
‹‹የእኔ ስኬታማ መሆን የባለቤቴ ልፋት ያመጣው ነው። እርሱ የፈለኩትን ቀድሞ ያውቃል፣ እንዳደርገውም ይገፋኛል። ምቹ ሁኔታዎችን ሳይቀር የሚፈጥርልኝ ስጦታዬ ነው። ›› የሚሉት ባለታሪካችን፤ ለዚህ ሁሉ መንስኤው በልጅነታቸው ተዋደው መጋባታቸው ነው። ገና በተማሪነት ህይወት ላይ እያሉም በጉርብትና ተከራይተው ሲማሩ ነው ትውውቃቸው ጠንክሮ ለዛሬ ህይወታቸው ያበቃቸው። ስድስት ልጆችን አፍርተውም እርስ በእርስ በመተጋገዝ ልጆቻቸውን ብቻ ሳይሆን ራሳቸውንም አስተምረዋል። ለልጆቻቸውም አርአያ ሆነዋል።
መልዕክተ ፀሐይ
አሁን እንደ አገር እያንዳንዱ ሰው ቢኖረው ብለው የሚመኙት መልካም እልህን ነው። በዚህ እልህ መልማት፣ ችግርን ማለፍ ይቻላል። ሌሎችንም ማሻገር ያስችላል። ለዚህ ማሳያው መጀመሪያ የሚቀጠር ወታደር ጠፋ ሲባል ሆ ብሎ በመነሳቱና ብሔር ሳይለይ ዘመቻውን መቀላቀሉ ቦታ እንዲጠፋ አድርጎታል። ይህንን ያመጣው ደግሞ መልካም እልህ ነው። ስለሆነም አንድ ያደረገንን መልካም እልህ አጥብቀን በመያዝ ከችግራችን ልንወጣበት ይገባል የመጀመሪያው መልዕክታቸው ነው።
መልካም ኃሳቦች ሁልጊዜ ፈተና ይበዛባቸዋል። ነገር ግን መቼም ቢሆን አይወደቅባቸውም። ምክንያቱም በእነርሱ ውስጥ እድል አለ። ደህንነትም ይገኛል። ልምላሜና ሌላን ማሻገሪያም በእነርሱ ውስጥ ይኖራል። እነርሱ የውስጥ ፈውስን ማግኛም ናቸው። እናም ሰዎች ይህንን ይዘው ቢጓዙ ህይወታቸውን አረንጓዴ ያደርጋሉ። በተለይም በዚህ ጊዜ ይህ ወርቃማ እድል ሊያመልጣቸው አይገባም። እናም አሁን የመጣውን ችግራቸውን ለማለፍ ምስጢሩ መልካም ኃሳቦችን መያዝ፣ ለሌሎች ማካፈልና በእነዚህ ኃሳቦች መራመድ እንደሆነም ይናገራሉ።
ሌላው ያነሱት ኃሳብ እያንዳንዱ ሰው ንግግሩን ስልታዊ ማድረግ እንዳለበት ነው። ዛሬ አገርን ለመታደግ ንግግር ስልታዊ ማድረግ ያስፈልጋል ባይ ናቸው። ስልታዊ ንግግር ስንጠቀም የሰዎችን ስሜት ስለምንቆጣጠር ብዙዎችን ከመቃቃር እናድናለን። ምክንያቱም አሁን ባለው አገራዊ ወቅታዊ ሁኔታ ሰው ያለፈውን መቁጠር ላይ በመሆኑ ለነገ የሚያስቀምጠው ቁርሾ እየተበራከተ ነው። ስለሆነም አመራርም ሆነ ህዝቡ አስቦና አስተውሎ እንዲሁም አመዛዝኖ ካልተናገረ ተጨማሪ የሚከፍለው ዋጋ ይመጣል። በመሆኑም ብዙ ሥራ ተሰርቶ የቀደመው መጥፎ ትርክት ካልጠፋ በስተቀር አሁን ያለንበት ሁኔታ ላይ ንግግርን ስልታዊ አለማድረግ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ያደርገናል። ስለዚህ ሰዎች ባለፈው ላይ ላለመጨመር መጠንቀቅ አለባቸው። ለአገር የሚበጀውን ብቻ መርጠው መናገርን ሊያስቀድሙ ይገባል መልዕክታቸው ነው።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መስከረም 23/2014