የኦሮሞ ማህበረሰብ በየአመቱ በድምቀት ከሚያከብራቸው በዓላት አንዱ ኢሬቻ ነው፡፡ ኢሬቻ በየአመቱ በመስከረም ወር ከመስቀል በዓል ቀጥሎ ባሉት ቅዳሜና እሁድ በሆራ ፊንፊኔ እና በሆራ አርሰዲ ይከበራል፡፡ የበዓሉ መከበር ዋነኛ ዓላማም ምስጋናና ምልጃ ነው፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ላገኘው ፀጋና በረከት፣ ሰላምና ደስታ፣ ጤናና ዕድሜ፣ ፍቅርና ክብር፣ ብርሃንና ተስፋ እንዲሁም ከዘመን ወደ ዘመን በሰላም ላሸጋገረው አንድ አምላኩ/ ለዋቃ ጉራቻ/ በኢሬቻ ምስጋና ያቀርባል፤ ለወደፊቱም ይማፀናል፡፡
ኢሬቻ የምርቃት፣ የተማጽኖ፣ የዕርቅ፣ የይቅርታ፣ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የወንድማማችነትና የእህትማማችነት፣የምስጋና እና የበረከት በዓል ነው። እሬቻ መነሻው እና መድረሻው የመከበሩም አልፋ እና ኦሜጋ ሰላምና ፍቅር ነው፡፡
ክረምት አልፎ ጸደይ መምጣቱ፣ ጨለማ አልፎ በብርሃን መተካቱ፤ አይቀሬ ክስተቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ክስተቶች ደግሞ ለሰው ልጅ ምን ያህል ዋጋ እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ ለዚህ ረቂቅ የተፈጥሮ ስጦታ ደግሞ ፈጣሪን አለማመስገን ንፉግነት ካልሆነ ሌላ ምንም ሊሆን እንደማይችል ኦሮሞ ያምናል፡፡ በዚህ የተነሳ ነው ይህንን ሁሉ ፀጋ ለሰጠው ዋቃ ጉራቻ ምስጋናውን የሚያቀርበው፡፡
ኢሬቻ የሚከበረው ውሃ በሚገኝበት ስፍራ ሲሆን እርጥብ ሳር መያዝም የበዓሉ አካል ነው፡፡ ይህ የሚሆነው በምክንያት እንደሆነ አባገዳዎች ይገልጻሉ፡፡ አባገዳዎች እንደሚሉት ውሃ ከፈጣሪ የተሰጠ ረቂቅ የሰው ልጅ የህይወት መሰረት ሲሆን በምድርም፣ በምድር ውስጥም ሆነ ከምድር በላይ የሚገኝ ፀጋ ነው፡፡ እርጥብ ሳርም እንዲሁ በፈጣሪ የተሰጠ ፀጋ ሲሆን የህይወትን ቀጣይነት የሚመሰክር ትልቅ ተምሳሌት ነው፡፡
ኢሬቻ ይህ ተፈጥሮአዊ ሕግ ሳይዛነፍ ዓመታዊ ዑደቱን ጠብቆ እንዲቀጥል ለማመስገንና ለመለመን የሚከበር ድንቅ በዓል ነው። የተራራቀው ሊቀራረብ፤ የተጠፋፋው ሊሰባሰብ፤ የደፈረሰው ሊጠራ፤ የጨለመውም ሊበራ እለቱ ሲደርስ አመስጋኙ የኦሮሞ ህዝብ በፍጹም ምስጋና እና እልልታ ከመልካው ዳርቻ ይገናኛል፡፡
በሌላም በኩል ኢሬቻ ንፅህና ነው። በኦሮሞ ማህበረሰብ ዘንድ ቂም ይዞ ፀሎት፣ ሳል ይዞ ስርቆት አይታሰብም፡፡ በመሆኑም ከምስጋናና ከተማፅኖ በፊት ልብ ንጹህ መሆን አለበት፡፡ በንጹህ ልብ ፈጣሪውን የሚለምን ኦሮሞ የወደቀውን ያነሳል፡፡
ኢሬቻ ሁሉም ሃይማኖትና፣ የእድሜ ደረጃና አመለካከት ያላንዳች ልዩነት የሚሳተፍበት የብዝሀነትና የአንድነት መድረክ ነው። በበዓሉ ላይ ልዩነት እንደውበትና ጥንካሬ ተወስዶ የኦሮሞ አንድነት፣ ይወደሳል፣ ይዘመራል፣ ይገነባል፣ ይታደሳል፣ ይጠነክራል። የአንድነት፣ የፍቅር፣ የወንድማማችነት፣ የመቻቻል ቃል ኪዳን ይገባል፤ ይታደሳል። የበለጠ አንድነት ይፈጠራል፤ ከዘመን ወደ ዘመንም ይሻገራል፡፡
የክረምት ወራት ከባድ ጊዜያት ናቸው፤ ብዙ ተግዳሮቶች ያጋጥማሉ፤ ወንዞች ይሞላሉ፤ ደራሽ ውሀ ሰውና እንስሳ ይወስዳል፤ በረዶ ይጥላል፤ መብረቅ ይወርዳል፤ ጨለማው ብርቱ ነው፤ ጨረቃ፣ ከዋክብትና ጸሐይ በጥቁር ደመና ይጋረዳሉ፤ ከወንዝ ማዶ ካሉት ዘመዶች ጋር መገናኘት ይቋረጣል፤ ገበያ መሄድ ይከብዳል። የበጋ ወቅትም ብዙ ተግዳሮቶች አሉት፤መሬት በድርቀት ይሰነጣጠቃል፤ ዛፎች ቅጠሎቻቸው ይረግፋል፤ የግጦሽ ሳር ይደርቃል፤ ከብቶች ይከሳሉ፤ አውሎ ንፋስ ይበረታል። እነዚህ ፈታኝ ሁኔታዎች ግን አላፊዎች ናቸው፤ ተስፋ የሚያስቆርጡ የዓለም ፍጻሜ አይደሉም።
አገራችን ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ እንዲሁ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ እድሜዋን ያለፈችባቸው ወቅቶች በፈተና የታጀቡ ነበሩ፡፡ በኋለኛው ዘመን እንኳ ብንመለከት በውጭ ሃይሎች የደረሰባት የወረራ እና የትንኮሳ ሙከራዎች ብዙ ናቸው፡፡ ህዝቦቿ በድርቅና በተፈጥሮ መዛባት የተነሳ ለረሃብ የተጋለጡባቸውና የሌላውን እጅ ያዩበት ወቅትም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ሆኖም አንዳቸውም ኢትዮጵያን አላሸነፉም፡፡ ኢትዮጵያውንያን እነዚህን የፈተና ወቅቶች ሁሉ በአንድነት በመጋፈጥ አልፈዋቸዋል፡፡
ባለፉት ሶስት አመታት ደግሞ ኢትዮጵያ አንገቷን ቀና አድርጋ ለመራመድ የሚስችላትን ጎዳና ማየት ስትጀምር እነዚህ ፈተናዎች ዳግም አቆጥቁጠው የብዙዎችን አንገት አስደፍተዋል፡፡ በነዚህ የፈተና ወቅቶች በርካታ ዜጎቻችን ከጎናችን ተቀጥፈዋል፤ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ተሰደዋል፤ በሃገራቸው በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት ከብዷቸው በስጋት መኖር ግድ ሆኖባቸዋል፡፡
ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ባሳለፍነው አመት ያጋጠሙን ፈተናዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ የከፉ እንደነበሩ የምናስታውሰው ነው፡፡ አሸባሪው ህወሓት በከፈተብን ጦርነት ሃገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ በከፍተኛ ሁኔታ ለችግር ተዳርጋለች፡፡ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀምም የውጭ ጠላቶቻችን ሊበታትኑን ከመቼውም ጊዜ በላይ አሰፍስፈው የጠበቁበት ጊዜ ቢኖር ያሳለፍነው አመት ነው፡፡
ነገር ግን በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ ጠላቶቻችንን ተስፋ የሚያስቆርጡ፣ የሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንን አንገት ቀና የሚያደርጉ የተስፋ ብርሃኖችም የፈነጠቁበት አመት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛውን ዙር ውሃ ሙሌት በስኬት ያጠናቀቅንበትና ስኬታማ ምርጫ አካሂደን መንግስት ለመመስረት የተጓዝንበት አመት መሆኑ በፈተና ውስጥም ጣፋጭ ፍሬዎች ማፍራት መቻላችንን የሚያሳዩን ናቸው፡፡
ክረምት አልፎ ጸደይ ሲመጣ በኢሬቻ ለፈጣሪ ምስጋና እንደምናቀርበው ሁሉ፤ ይህ ጊዜም አልፎ የብልፅግና ፍሬ የምንቋደስበት ጊዜ ቅርብ መሆኑን አመላካች ነው፡፡ በሽግግር ወቅት ደግሞ ፈተናዎች ይበዛሉ። ያለመተማመን፤ ተጠራጣሪነት፣ ጨለምተኝነት፤ ሕገ ወጥነት ያጋጥማሉ። በዚህ ወቅት የኢሬቻ የአምልኮ ፍልስፍና የሚያስተምረን ከውጣ ውረዶቹና ከፈተናዎቹ ባሻገር ተስፋ መኖሩን ነው፤ የተሻለ ዘመን፣ የተሻለ አገር እንደሚኖረን ማሰብ ያስፈልጋል፤ ለዚህም በጽናት በተስፋ፣ በጋራ፣ በመቻቻል እና በወንድማማችነት መንፈስ እንቁም፡፡
አዲስ ዘመን መሰከረም 23 ቀን 2014 ዓ.ም