ኢትዮጵያ በአፍሪካ እጅ ኳስ ኮንፌዴሬሽን የዞን 5 ፕሬዚዳንት በመሆን ተመረጠች። ኮንፌዴሬሽኑ ከሰሞኑ ባካሄደው ጉባኤ ኢትዮጵያ ውክልናውን ማግኘቷንም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
በአፍሪካ እጅ ኳስ ኮንፌዴሬሽን ስር ከሚገኙት ዞኖች መካከል የዞን 5 አባል ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ በፕሬዚዳንትነት የተመረጠችው ከቀረቡት እጩዎች መካከል ምርጫውን አሸንፋ ነው። የፕሬዚዳንትነት ስፍራውን የያዙትም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍትህ ወልደሰንበት ናቸው።
ኮንፌዴሬሽኑ ጉባኤውን በበይነ መረብ ያካሄደ ሲሆን፤ በእጩነት አንድ ኢትዮጵያዊ እንዲሁም ኡጋንዳዊ ቀርበው ነበር። በተደረገው የድምጽ አሰጣጥም ዶክተር ፍትህ ወልደሰንበት ተፎካካሪያቸውን ስድስት ለሶስት በሆነ ብልጫ የበላይነቱን በማስመዝገብ አሸንፈዋል። በዚህም ላለፉት ሶስት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ሲመሩ ከቆዩት ኡጋንዳዊቷ ሺላ ሪቻርድ የአመራርነቱን ስፍራ መረከባቸውን ፌዴሬሽኑ በድረገጹ አስነብቧል።
የአፍሪካ እጅ ኳስ ኮንፌዴሬሽን በስሩ 7 ዞኖች ያሉት ሲሆን፤ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ዞን 5 በሚል ይታወቃል።
ይህ ዞን ከፍተኛውን የአባላት ቁጥር የያዘ ነው፤ 11 ሀገራት በዞኑ ይጠቃለላሉ። ሀገራቱም ኢትዮጵያ፣ ብሩንዲ፣ ጅቡቲ፣ ግብጽ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ ናቸው። በዚህ ምርጫ ላይ በማሸነፍ ፕሬዚዳንት በመሆንም ዶክተር ፍትህ የመጀመሪያው ናቸው።
ይህ ዞን ከፍተኛውን የአባላት ቁጥር የያዘ ነው፤ 11 ሀገራት በዞኑ ይጠቃለላሉ። ሀገራቱም ኢትዮጵያ፣ ብሩንዲ፣ ጅቡቲ፣ ግብጽ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ ናቸው። በዚህ ምርጫ ላይ በማሸነፍ ፕሬዚዳንት በመሆንም ዶክተር ፍትህ የመጀመሪያው ናቸው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 22/2014