በ2 በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ (ሲቲ ካፕ) በሁለቱም ምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ እና ነገ የሚካሄዱ ይሆናል። ዛሬ 8 ሰዓት ላይ የመጀመሪያው ምድብ መከላከያን እና ጅማ አባጅፋርን ያገናኛል፤ በ10 ሰዓት ደግሞ ኢትዮጵያ ቡና ከአዲስ አበባ ከተማ ይጫወታሉ። ነገ ደግሞ 8 ሰዓት ላይ ፋሲል ከተማ ከአዳማ ከተማ እንዲሁም በ10 ሰዓት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከባህርዳር ከተማ የሚጋጠሙ ይሆናል።
በ15ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ዛሬ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታ ይካሄዳል። ከመጀመሪያው ምድብ ጅማ አባጅፋር እና መከላከያ ከምድባቸው አልፈው ወደ ግማሽ ፍጻሜው መግባታቸውን ያረጋገጡ ቡድኖች ቢሆኑም በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ይገናኛሉ።
በዚህ ምድብ ዘንድሮ በድጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የተመለሱት ሁለት ክለቦች (መከላከያ እና አዲስ አበባ ከተማ) መኖራቸው የሚታወቅ ነው። ይሁንና ጦሩ አቅሙን አጎልብቶ ዳግም ወደ ሊጉ ተፎካሪነት መመለሱን የሚያረጋግጥ ብቃት አሳይቷል ፤ አዲስ አበባ ከተማ ግን አካሄዱን ዳግም እንዲቃኝ ያደረገውን ውጤት አስመዝግቧል። የከተማዋ ክለብ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታውን ከጅማ አባጅፋር ጋር ቢያደርግም የ 1ለ 0 ሽንፈት ገጥሞታል።
በምድቡ ሌላኛው ጨዋታ ደግሞ ኢትዮጵያ ቡና ሁለተኛ ሽንፈቱን በመከላከያ የ1 ለ 0 ውጤት ተቀብሎ ከዋንጫ ጉዞው መሰናበቱን አረጋግጧል። ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ ለ4 ጊዜያት የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫን ያነሳው ኢትዮጵያ ቡና የውድድሩ ድምቀት በመሆን ቢታወቅም በዘንድሮው ውድድር ግን ድል ሊቀናው ባለመቻሉ ከምድብ ጨዋታው በጊዜ መሰናበቱ ታውቋል። በዛሬው የምድቡ ጨዋታም መውደቃቸውን ያረጋገጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከአዲስ አበባ ከተማ ሲጫወቱ፤ የምድብ አላፊዎቹ መከላከያ እና ጅማ አባጅፋር ፉክክር ተጠባቂ ሆኗል።
ከሁለተኛው ምድብ ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ቀጣዩ ዙር መሸጋገሩን አረጋግጧል። ከትናንት በስቲያ ከአዳማ ከተማ ጋር ጨዋታቸውን ያደረጉት ፈረሰኞቹ በሃይደር ሸረፋ የፍጹም ቅጣት ምት በመሸነፋቸው 6 ነጥብ ማስመዝገብ ችለዋል። ይህም ቅዱስ ጊዮርጊስን ወደ ጥሎ ማለፉ እንዲቀላቀል አድርጎታል። ነገ በሚኖረው ጨዋታ ከምድቡ ሁለተኛ ሆኖ ለማለፍ የተሻለ እድል ካለው ሌላኛው ክለብ ባህርዳር ከነማ ጋር የሚጫወት ይሆናል። በዚህ ውድድር ድል ያልቀናው አዳማ ከተማ ደግሞ በዛሬው ጨዋታ ማሸነፍ ከቻለ ከምድቡ የማለፍ እድሉን ከሚያመቻቸው ፋሲል ከተማ ጋር ይገናኛል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚህ ውድድር ለበርካታ ጊዜያት አሸናፊ በመሆን የበላይነቱን ይዟል። የ6 ጊዜ ባለድሉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለሶስት ዓመታት በተከታታ ዋንጫውን የግሉ የማድረግ ታሪክ አለው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 22/2014