ህይወት ባሰቧት መንገድ የማትሄድ መልከ ብዙ ነች። ጥቂቶች ህልማቸውን እውን ያደርጋሉ። ባሰቡት የህይወት መስመር ትልቅ ደረጃ ላይ ለመድረስ አስበው በተለያዩ ምክንያቶች ከጉዟቸው ተደነቃቅፈው መንገድ ላይ የሚቀሩ በርካቶች ናቸው። በአንድ ወቅት ዳጎስ ያለ ገንዘብ ሲያንቀሳቅሱ የነበሩ ቱጃር ነጋዴዎች ወይም አራሽ አፋሽ የነበሩ ታዋቂ ገበሬዎች በሌላ ጊዜ የእለት ጉርስ እንኳ አጥተው ሲቸገሩ ልናይ እንችላለን። ለማግኘትም ለማጣትም ምክንያቶች ይኖራሉ። ሁል ጊዜ መነሻ ያደረግነውን የህይወት መሰላል እንደረገጥን አንቆምም፤ ወደ ላይ እንወጣለን፤ እላይ ደርሰንም እንደተንጠለጠልን አንቀርም። በህይወት መሰላል ላይ ከታች ወደ ላይ፤ ከላይ ወደ ታች፤ መውጣት መውረድ የተለመደ ነው። ዋናው ቁም ነገር ሁሌም እራሳችንን ለማኖር የምናደርገውን ጥረት አለማቆም ነው። ሁሌም በስራ ላይ፤ ሁሌም ራስን ችሎ ለመኖር በመጣር ላይ መገኘት ነው።
የዛሬው ባለታሪካችን ሙሉጌታ ዘውዴ ይባላል። የልጅት ምርጫውና ፍላጎቱ ወታደር ሆኖ የሀገሩን ሉዓላዊነት ማስከበር ነበር። እንዳሰበውም ገና በለጋ እድሜው የቀድሞው የኢትዮጵያ ወታደር በመሆን በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ላይ በመሳተፍ ለሀገሩና ለወገኑ ላቡንና ደሙን አፍስሷል። በኋላም የደርግ መንግስት ስልጣኑን ለቆ ኢህአዴግ ስልጣን ሲቆናጠጥ በጠላትነት ተፈርጆ ከውትድርና ይሰናበታል። ኋላ ግን በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ጊዜ መንግስት ሊጠቀምበት ስለፈለገ ብቻ ዳግም ይጠራዋል። ከጦርነቱ መጠናቀቅ በኋላም ለሁለተኛ ጊዜ ይሰናበታል። ከውትድርና ሲሰናበት ባዶ እጁን ወደ ሀገሩ የመሄድ ሞራል አጥቶ እዚሁ አዲስ አበባ ህይወቱን ለመምራት ለበርካታ ዓመታት ጥሯል።
ይህ ሰው ዛሬ የ55 ዓመት ጎልማሳ ነው። መኪና እያጠበ በሚያገኛት ሳንቲም የእለት ጉርሱንና የመኝታውን እየቻለ ይኖራል። ባለታሪኩ ከዚህ በፊት ለሀገሩ ለከፈለው መስዋዕትነት እውቅና የሰጠው አካል ባይኖርም ለሀገሩ ታማኝ ሆኖ ማገልገሉ እያኮራው ኖረ እንጂ አላስቆጨውም። ዛሬም ህግ በማስከበር ዘመቻው የቀረበውን የመንግስት ጥሪ ሰምቶ መከላከያ ሰራዊትን ለመቀላቀል ቢሄድም የሜዲካሉን ሳያሟላ ቀርቶ ሊቀር ችሏል። ቆፍጣናው ወታደር ከ15 ዓመት በላይ መኪና እያጠበ ህይወቱን ለመምራት ጥሯል። ሳይደላው እየኖረ ያለው የቀድሞ ወታደር ዛሬም ከራሱ በፊት ሀገሩንና ህዝቡን ያስቀድማል። ያለፈባቸውን እና አሁን ያለበትን ሁኔታ ልናስቃኛችሁ ወደድን።
ጊዜው 1976 ዓ.ም ነው። የደርግ መንግስት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ከሻቢያ እና ወያኔ ጋር እያደረገ ላለው ጦርት የብሄራዊ ውትድርና ግዳጅ አውጆ የመጀመሪያ ዙር ምልምል ወታደሮችን ወደ ማሰልጠኛ ማስገባት ጀምሯል። ግዳጁ እድሜያቸው ለውትድርና የደረሱ ወጣቶች የሚገኙበትን ቤት ሁሉ ያንኳኳ ነበር። ቢያንስ ከአንድ ቤት አንድ ሰው ጥሪውን የመቀበል ግዴታም ነበረበት።
ያኔ ሙሉጌታ በድሮው አጠራር ሀረር ክፍለ ሀገር አሰበ ተፈሪ ከተማ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ነበር። ትምህርት ቤት ሄዶ ከመምጣት እና ከሰፈር ጓደኞቹ ጋር ኳስ ከመጫወት ውጭ የሚያወቀው ነገር የለም። አንድም ቀን ካደገባት ከተማ እርቆ የሄደበት አጋጣሚ አልነበረም። ነገር ግን ወታደር የመሆን ፍላጎት ነበረው። የቀበሌው መስተዳድር ከቤተሰቡ አንድ ሰው ብሄራዊ ጥሪውን መቀበል እንዳለበት አስገዳጅ ሁኔታዎችን ሲጥል ሙሉጌታ ታላላቅ ወንድሞቹን አስቀርቶ ዘመቻውን መቀላቀል ይፈልጋል። እድሜው አስራ ሳባት ዓመት አካባቢ ይሆናል።
ምንም እንኳን የሀገሩን ጥሪ ተቀብሎ መዝመቱ ቢያስደስተውም ያደገባትን አሰበ ተፈሪ ከተማና ቤተሰቦቹን ተሰናብቶ መሄድ ውስጡን ረብሾታል። ያም ሆኖ ህልመኛው ወጣት ከሃሳቡ ፍንክች ሊል አልፈለገም። ከመሰል ጓደኞቹ ጋር ጥሪውን ተቀብሎ የጉዞውን ቀን ይጠባበቃል። የመጨረሻው ቀን ደርሶ ምልምሎቹ ወደ ማሰልጠኛ ለመግባት መኪና ተሳፍረው የአሰበ ተፈሪን ከተማ መልቀቅ ሲጀምሩ አስፋልት ላይ የተኮለኮሉት የከተማዋ ነዋሪዎች እጃቸውን እያውለበለቡ የተሰናበቱትንና እናቱ ሲያለቅሱ የነበረው ሁነት ሁሌም ያስታውሰዋል።
ሙሉጌታ የመጀመሪያ ዙር ብሄራዊ ውትድርና ስልጠናውን ካጠናቀቀ በኋላ ግዳጁን ለመወጣት ወደ ግንባር ይሰማራል። ግንባር ባሳለፋቸው ሁለት ዓመታት በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ላይ መሳተፉን ይናገራል። በወሎ፣ በጎንደር፣ በትግራይ፣ በኤርትራ በረሃማና ተራራማ አካባቢዎች እየተዟዟረ በወቅቱ ከነበሩት ሽምቅ ተዋጊዎች ጋር ይፋለማል። በወር ሃያ ብር የኪስ ደሞዝ እየተሰጠው በታማኝነት የተጣለበትን ግዳጅ መወጣቱን ይቀጥላል። የሁለት ዓመት ግዳጁን አጠናቆ በክብር ከተሰናበተ በኋላ ወደ ትውልድ አካባቢው በሰላም ይመለሳል።
ሙሉጌታ ቤተሰቦቹ ጋር ገብቶ ለሁለት ዓመት ያህል ያቋረጠውን ትምህርት ከዳር ለማድረስ ደፋ ቀና በሚልበት ሰዓት የሀገሪቱ የሰላምና የጸጥታ ጉዳይ እየከፋ መምጣቱን ተከትሎ ለዳግም ግዳጅ ይጠራል። ወትሮም ለሀገሩ ዘብ የመቆም ፍላጎት የነበረው ወጣት ዳግም ጥሪውን ተቀብሎ አሰበ ተፈሪን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተሰናብቶ ይዘምታል። ሙሉጌታ ዳግም የቀረበለትን ጥሪ ተቀብሎ ሲዘምት እንደመጀመሪያው የተሰጠውን ግዳጅ አጠናቆ ወደ ቤቱ ለመመለስ አልነበረም።
መደበኛ ሰራዊቱን በመቀላቀል ቋሚ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባል ለመሆን ወስኖ ነበር። ኢትዮጵያን በውትድርና የማገልገል ፍላጎት የነበረው ሀገር ወዳድ ወጣት አጋጣሚውን ተጠቅሞበት አሰላለፉን ይቀይራል። ከዚያም በሶስተኛ ክፍለ ጦር ውስጥ መደበኛ ወታደር በመሆን ትግሉን ይቀጥላል። በከባድ ውጊያዎች ላይ በመሳተፍ በርካታ ድሎችን መጎናጸፉን ይናገራል። በዚህ መሃልም እግሩ ላይ መጠነኛ ጉዳት ይደርስበታል። ኋላ ግን የሰሜኑ ውጊያ በአሻጥሮች እየተበላሸ ሲመጣ ጠላት አቅም ማግኘት ጀመረ የሚለው ሙሉጌታ ህወሓት አዲስ አበባን ለመቆጣጠር ወደ መሃል ሀገር ግስጋሴ ሲያደርግ አምቦ ላይ እስከተካሄደው የመጨረሻው ውጊያ ድረስ በኮሎኔል ተመስገን ጫላ አመራር ሰጪነት እንደተዋጋ ይገልጻል።
ኢህአዴግ ሀገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ በቅርበት ያገኛቸውን የቀድሞ የኢትየጵያ ወታደሮች ሰብስቦ የተሀድሶ ስልጠና ትወስዳላችሁ በሚል ደዴሳ ማሰልጠኛ ማዕከል እንዳስገባቸው ይናገራል። ሙሉጌታ ከሁለት ወር የተሀድሶ ስልጠና በኋላ ከዴደሳ ወደ አዲስ አበባ ይመጣል። እርሱና ሌሎች የተበተኑ የቀድሞ ወታደር ባልደረቦቹ በረንዳ እያደሩ ከተባበሩት መንግስታትና ከለጋሽ ድርጅቶች የሚደረግ እርዳታን መጠባበቅ ይጀምራሉ። ለስድስት ወር ያህል ስንዴና ሃምሳ ሃምሳ ብር ከተሰጣቸው በኋላ ድጋፉ ይቋረጥባቸዋል። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ታዲያ ልብሳቸው በላያቸው ላይ ይበጫጨቃል፤ መሳፈሪያ ተብላ የተሰጠቻቸው ገንዘብም ታልቃለች። የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የምግብና የአልባሳት ድጋፍ እያደረጉላቸው ወራትን በረንዳ እያደሩ ማሳለፋቸውን ሙሉጌታ ይናገራል።
በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳለ የእናቱን መሞት ይሰማል። ጉስቁልናው ትልቅ የሞራል ውድቀት የፈጠረበት ያ ቆፍጣና ወታደር ወደ ሀገሩ የመመለስ ተስፋው ይሟጠጣል። ጉሮ ወሸባ እያለ ወደ ቤቱ የመመለስ ተስፋ ይዞ ከሀገሩ የወጣው ሙሉጌታ ተጎሳቁሎ መመለስ አሳፍሮት ያገኘውን ስራ በመስራት እራሱን አሻሽሎ መመለስ በማሰብ ወደ ስራ ይሰማራል። እዚህና እዚያ እየተሯሯጠ የጉልበት ስራዎችን በመስራት በሚያገኛት የእለት ገቢ ምግቡንና የመኝታውን እየቻለ ኑሮውን በአዲስ አበባ ያደርጋል። የተለያዩ የጉልበት ስራዎችን እንደሰራ የሚናገረው ሙሉጌታ በዋናነት ግን ልደታ ክፍለ ከተማ ከባልቻ አባነፍሶ ሆስፒታል ከፍ ብሎ ባለው ጎዳና የሚቆሙ መኪኖችን በማጠብ ህይወቱን እንደገፋ ይገልጻል።
ሙሉጌታ ከ15 ዓመት በላይ መኪና እያጠበ የኖረበትን ሁኔታ እንዲህ ያስረዳል። ‹‹ሁልጊዜ ማለዳ አንዲት ባልዲ፣ ጨርቅና ስፖንጄን ይዤ ወደ ቆሙ መኪኖች እሄዳለሁ። ባለቤቶቹ እንዳጥብ ከፈቀዱልኝ አጥቤ የሚሰጡኝን ሳንቲም እቀበላለሁ። ከአስር ዓመት በፊት ለአንድ መኪና ከአምስት እስከ አስር ብር ይከፈለኝ ነበር። አሁን ግን እስከ ሃምሳ ብር ድረስ ይሰጡኛል። ሲቀናኝ ሁለትም ሶስትም መኪና ላጥብ እችላለሁ። አንዳንዴ ግን በቀን ይቅርና በሁለት ቀንም አንድ መኪና ላላጥብ እችላለሁ። እንግዲህ ከማገኛት ገንዘብ ላይ ለመኝታዬ በቀን ሃያ ብር እየከፈልኩኝ እኖራለሁ። ድሮ የቀን ሰራተኞች ተሰብስበን ለምናደርበት ቤት ከአምስት እስከ አስር ብር ነበር እየከፈልን የምናድረው፤ አሁን በቀን ከሃያ እስከ ሃያ አምስት ብር እንከፍላለን። የኑሮ ውድነቱ እየተባባሰ ስለመጣ ሰርቼ ገንዘብ መጨበጥ አልቻልኩም። እራሴን ሳልለወጥ አልሄድም በሚል ከትውልድ ሀገሬም ከዘመዶቼም ተለያይቼ ቁጭ ብያለሁ። አንዳንድ ጊዜ እንዲህ አይነት ህይወት ከመግፋት ይልቅ እንደ ጓደኞቼ ከእነ ክብሬ መስዋዕት ብሆን ኖሮ እላለሁ›› ይላል ብሶተኛው የቀድሞ ወታደር።
ሙሉጌታ በትዝታ ወደ ኋላ ተመልሶ ያለፈ ታሪኩን ያጫውተኝ ቀጥሏል። እኔም በተመስጦ እያዳመጥኩት ነው። ‹‹ለነገሩ የቀድሞ ወታደሮችን ክብር ያዋረደው ወያኔ ነው። ከአንዴም ሁለት ጊዜ ክዶናል። በ1983 ዓ.ም የሀገሪቱን ወታደሮች እንደወንበዴ ቆጥሮ ከበተነን በኋላ የራሱን ተዋጊዎች አጭቆ የሀገር መከላከያ ሰራዊት እገነባሁ ብሎ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ድራማ ሰርቷል። የሚገርመው ነገር ያኔ የበተነውን የኢትዮጵያ ወታደር በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ጠርቶ ሀገሩን እንዲታደግ ግንባር አሰለፈው። የሞተው ሞቶ የተረፈው ተርፎ ከተመለስን በኋላ አሁንም ለሁለተኛ ጊዜ በተነን። እንግዲህ ሁለት ጊዜ ከድቶናል ማለት ነው›› ይላል ሙሉጌታ።
‹‹በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት እኔ የተደረገልኝን ጥሪ ተቀብዬ ብላቴ የተሃድሶ ስልጠና ካደረግኩኝ በኋላ በቀጥታ ጾረና ግንባር ነበር የገባሁት። ብዙ ጓደኞቼ ሲሰዉ እንደ አጋጣሚ ተርፌ መጣሁ። የወያኔ መንግስት ከተጠቀመብን በኋላ ለእግረኛ ምድብተኞች ስድስት ሺ ብር እየሰጠን አሰናበተን። ወደ ውትድርና ህይወት መቀላቀሌ ደስ ሲለኝ እንደገና ሞራሌን ገድሎ ሲለቀኝ ተመልሼ የቀን ስራ እየሰራሁ ለመኖር ተገደድኩኝ። የቀድሞ ወታደሮች ግፍ ተፈጽሞብናል። ለእናት ሀገራችን ዘብ ለመቆም በወጣን እንደጠላት እየታየን ብዙ በደል ደርሶብናል። ዛሬ ሀገሬ ያለችበትን ሁኔታ ስሰማ በጣም እናደዳለሁ። አሁንም ሀገርን ለማዳን በተደረገው ጥሪ መከላከያ ሰራዊትን ለመቀላቀል ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝ። ሄጄም ለመመዝገብ ሞክሬ ነበር። ነገር ግን የጤና እና የአቅም ውሱንነት ስላለብኝ ሜዲካሉን ማለፍ አልቻልኩም።
ወጣቶች በዚህን ሰዓት ወታደር ሆነው ሀገርን ከውጭ ጠላቶችና ከውስጥ ባንዳዎች መታደግ እንዳለባቸው ይሰማኛል። ይህ የዜግነት ግዴታ ነው። የወያኔ ገዢዎች በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ያላቸው የበላይነት ካከተመ በኋላ መከላከያ ሰራዊትን የሚቀላቀሉ ወጣቶች እድለኞች ይሆናሉ ብዬ አምናለሁ። መንግስት የሀገራቸውን ክብርና የህዝባቸውን ሰላም ለመጠበቅ ሲሉ መስዋእት ለመሆን ለተሰለፉ ዜጎች ክብር ሊሰጣቸው ይገባል። አሁንም ቢሆን መንግስት በየጎዳናው የወደቁ የቀድሞ ወታደሮችን በመሰብሰብ ለውትድርና ሙያና ለወታደሩ ውለታ ያለውን ክብር ማሳየት ይኖርበታል›› ይላል ሙሉጌታ።
ቀደም ሲል የነጻ ህክምና ያገኝ እንደነበር የሚናገረው የቀድሞ ወታደር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይደረግለት የነበረው የህክምና ድጋፍ በመከልከሉ እየከፈለ እንደሚታከም ተናግሯል። እኛም ስለሀገራቸው ክብር ላባቸውን እና ደማቸውን አፍስሰው የተበተኑ የቀድሞ የኢትዮጵያ ወታደሮች ድጋፍና ክብር በመስጠት ውለታቸውን ማስታወስ ይገባል በማለት ተሰናበትን። ቸር እንሰንበት።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን መስከረም 22/2014