አገራት ከዓለምአቀፍ ተቀፍ ተቋማትም ሆነ ከአገራት ጋር የሚያደርጓቸው ግንኙነቶችም ሆኑ የሚሰሯቸው ስራዎች በመርህና በህግ የሚመሩናተጠያቂነትም ያለባቸው ናቸው። ዓለምአቀፍ ህግና መርሆዎችን መነሻ በማድረግም በኢትዮጵያ በርካታ የልማትና የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ተቋማት ተሰማርተው ይገኛሉ። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ በዓለምአቀፍ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ የውጭ አገር ዜጎች ከተሰማሩበት ዓላማ ውጪ ህገወጥ ተግባር ላይ ሲሰማሩ፤ የአገርና ህዝብን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ በሚጥሉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሲገቡ ማየትና መስማቱ እየተደጋገመ መጥቷል።
በተለይ አሸባሪው ቡድን ከማዕከላዊ መንግስት ተገፍቶ ትግራይ ከመሸገና የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ መንግስት የህግ ማስከበር እርምጃ ውስጥ ከገባ በኋላ፤ አንዳንድ በዓለምአቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ የውጭ አገር ዜጋ ሰራተኞች ለአሸባሪ ቡድኑ በመወገን የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችን ከማቅረብ ጀምሮ ኮሪደር ለማስከፈት የሚያስችሉ ብርቱ ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል። የኢትዮጵያን ስምና ዝና የሚያጠለሹ ተግባራትንም ሲያከናውኑ ቆይተዋል።
ይህ ተግባር ደግሞ ከዓለምአቀፍ ህግና መርሆዎች የተቃረነ፤ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ገብቶ የመፈትፈት እና ከተሰማሩበት ዓላማም ያፈነገጠ ስለመሆኑ በመጥቀስ፤ መንግስት በተደጋጋሚ “ከስህተታችሁ ታረሙ” የሚል ጥሪም፣ ማሳሰቢያም ሲሰጥ ቆይቷል። ከዛሬ ነገ ይታረማሉ በሚልም የበዛ ትዕግስት አሳይቷል። ይሁን እንጂ ከመታረም ይልቅ ችግሮችን ወደ ማባባስ፤ በሰብዓዊነት ሽፋን የአገርና ህዝብን ወደችግር ለማስገባት የሚያደርጉትን ተግባር አጠናክረው ሲቀጥሉ ተስተውሏል።
ከብዙ ትዕግሰት በኋላ “ትዕግስትም ልክ አለው” እንደሚለው ብሂል ጊዜው ሲደርስ ሊታረሙ ያልቻሉ በዓለምአቀፍ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ እና በህገወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ ሰባት የውጭ አገር ዜጎች በ72 ሰዓት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ ትዕዛዝ አስተላልፏል። ይህ ደግሞ የአገር ሉዓላዊነት መገለጫ ከመሆኑም በላይ የህዝብ ሰላምና ደህንነት ከሚያሳስበው የአንድ ሉዓላዊት አገር መንግስት የሚጠበቅ ትክክለኛ እና ተገቢነት ያለው እርምጃ ነው።
ምክንያቱም መንግስት ምንም እንኳን ለተቋማትና ዓለምአቀፍ መርሆዎችና ህጎች ተገዢ ቢሆንም፤ ይሄንኑም አክብሮ ከአጋር አገራትና ተቋማት ጋር እየሰራ ቢገኝም፤ እነዚህ ተቋማትና አገራት በሰብዓዊ ድጋፍ ስራ ላይ የሚያሰማሯቸው ግለሰቦች ከእነዚህ ዓለምአቀፋዊና ተቋማዊ መርሆዎችና ህጎች ባፈነገጠ መልኩ በአገር ጉዳይ ጣልቃ ሲገቡ ዝም ሊባሉ ሳይሆን፤ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ የግድ ይሆናልና።
ይሁን እንጂ ይሄን ውሳኔ ተከትሎ ከዓለምቀፍ ተቋማትና ከምዕራባውያኑ የሚሰማው መግለጫ እጅጉን የሚያሳዝን፤ የሚያስተዛዝብ ሆኗል። ምክንያቱም እነዚህ አገራትና አካላት ለእውነት የሚደነግጡበት የሞራል ልዕልና ቢኖራቸው ኖሮ የሰብዓዊ ድጋፍ ጭነው ትግራይ የሄዱ መኪኖች አለመመለሳቸው ሲነገር ሊደነግጡ ይገባ ነበር፤ ለህዝቡ እንዲደርስና ለህጻናት እንዲውል ወደክልሉ በእርዳታ የገቡ ኃይል ሰጪ ምግቦች አሸባሪው ቡድን ላሰማራቸው ታጣቂዎች ሲውሉ ሊደነግጡ ይገባ ነበር፤ መደንገጥ ካለባቸው አሸባሪው ቡድን በአማራ እና በአፋር ክልሎች ላይ ንጹሃንን በገፍ ሲጨፈጭፍ፣ እንስሳትን ሳይቀር በጥይት ሲገድል፣ የዜጎችን ሀብት ንብረት ሲዘርፍና የመንግስት ተቋማትን ሲያወድሙ ሊደነግጡ ይገባ ነበር።
ዛሬ ከመርህና ህግ ባፈነገጠ ውጪ ለሰብዓዊነትና የልማት ስራን ሽፋን አድርገው ለአሸባሪው ቡድን ሲሰሩና በአገርና ህዝብ ሰላምና ህልውና ላይ አደጋ በሚፈጥሩ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን ከአገር እንዲወጡ ሲወሰን የመንግስት እርምጃ አስደንግጦናል ብሎ የመግለጫ ጋጋታ ማሰማትና ጫና ለማሳደር መሞከር በራሱ ከመርህም፣ ከህግም ያፈነገጠ ነው። ማንም ይሁን ማን ከመርህና ህግ ውጪ ሲንቀሳቀስ ሊጠየቅ እና ተገቢው የእርምት እርምጃ ሊወሰድበት ግድ ነውና።
ኢትዮጵያ ነጻና ሉዓላዊት አገር ናት፤ መንግስቷም ለዜጎቹ ክብርና ሰላም የሚቆረቆር፤ ለአገር ሉዓላዊነት መከበርም የሚሰራ ነው። በመሆኑም ይሄን ተገቢና ህጋዊ እርምጃ ተቃውሞ መቆም በራሱ በኢትዮጵያ ላይ ለማሳደር የተፈለገውን የተቀናጀ ጫና በግልጽ የሚያሳይ ነው። በእነዚህ አገራትና ተቋማትም ሆነ በሌሎች አካላት ሊታወቅ የሚገባው ግን ኢትዮጵያ ሉዓላዊትና ነጻ አገር መሆኗ፤ መንግስት የወሰደው እርምጃም በመርህና በህግ የተመራ ተገቢና ትክክለኛ መሆኑን፤ ይልቁንም ሌሎች ትምህርት ሊወስዱበት የሚገባ መሆኑን ነው!
አዲስ ዘመን መስከረም 22/2014