በአውሮፓ ታላላቅ ከሆኑት ማራቶኖች መካከል አንዱ እንዲሁም በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃ ከተሰጣቸው ስድስት የጎዳና ላይ ሩጫዎች መካከል አንዱ የለንደን ማራቶን ነው።ከነገ በስቲያ ለ41ኛ ጊዜ በሚካሄደው በዚህ ውድድር ላይም በርካታ ታዋቂ አትሌቶች እንዲሁም 50ሺ ሰዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑበትም ተረጋግጧል።ይህም በዓለም ላይ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ የሚካሄድ ትልቁ የአትሌቲክስ ውድድር ያደርገዋል።
በውድድሩ ተሳታፊ እንደሚሆኑ አስቀድሞ ከታወቁት የርቀቱ ዝነኛ አትሌቶች መካከል አንዱ የዓምናው አሸናፊ ሹራ ቂጣታ ተጠቃሽ ነው።በዚህ ማራቶን እአአ ከ2003 ጀምሮ የአውሮፓውያንና የአሜሪካ አትሌቶች የበላይነት አብቅቶ በአፍሪካውያን የበላይነት ተተክቷል።የአንጋፋውን አትሌት ገዛኸኝ አበራን የመጀመሪያ አሸናፊነት ተከትሎ በቦታው በርካታ የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች እየተፈራረቁ በበላይነት ርቀቱን ፈጽመዋል።ከእነዚህ መካከል ጸጋዬ ከበደ እአአ በ2010 እና 2013 አሸናፊ የሆነ ኢትዮጵያዊ ነው።በዘንድሮው ውድድር ለአሸናፊነት ከፍተኛ ግምት ያገኘው ሹራ ውድድሩን በድል የሚያጠናቅቅ ከሆነም በቦታው ተከታታይ ድል ያገኘ ሌላኛው አትሌት ይሆናል።
በለንደን ማራቶን በማሸነፍ ታሪክ ቀዳሚዎቹ ኬንያውያን አትሌቶች ናቸው።በተከታታይ በማሸነፍ በተለይ የሚታወቀው ደግሞ የርቀቱ የዓለም ክብረወሰንባለቤቱ ኢሉድ ኪፕቾጌ ነበር።አትሌቱ እአአ ከ2015 ጀምሮ (እአአ ከ2017 በቀር) ለአራት ዓመታት የስፍራው ቻምፒዮን በመሆን ታዋቂ ነው።እአአ በ2019 ቻምፒዮን ሲሆንም ርቀቱን 2:02:37 በመሮጥ ሲሆን፤ ይህም የዓለም ክብረወሰን ባለቤት የሚለውን ክብርም ደርቦለታል።
በቀጣዩ ዓመት ግን ኢትዮጵያዊው አትሌት ሹራ በቦታው አሸናፊነቱን አስመስክሮ በኬንያውያን የበላይነት የተያዘውን ድርሳን ወደ ሌላ የፉክክር ገጽ እንዲዞር ምክንያት ሆኗል።ባለፈው ዓመት በዚህ ውድድር ኢትዮጵያ በታላቁ የረጅም ርቀት አትሌቷ የርቀቱን የበላይነት የዓለም ክብረወሰንን በመስበር ጭምር ታሳካለች
የሚል ሰፊ ቅድመ ግምት አግኝታ ነበር።ይሁን እንጂ ተጠባቂው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በጉዳት ምክንያት ተሳትፎ እንደማያደርግ በማሳወቁ አሸናፊነቱ ዳግም የኬንያውያን አትሌቶች ይሆናል በሚል ተገመተ፤ ይሁንና ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሹራ ቂጣታ ግን ክብረወሰኑን ባይሰብርም 2:05:58 በሆነ ሰዓት ሮጦ ድል በማድረግ ሀገሩን ሊያስጠራ ችሏል።
ይኸውም አትሌቱን በርቀቱ አዲሱ ተጽእኖ አሳዳሪ ይሆናል በሚል በስፋት እንዲጠበቅ አድርጎታል።በወቅቱ ባስመሰከረው ድንቅ ብቃት ምክንያትም በቶኪዮ ኦሊምፒክ የማራቶን አሸናፊነትን ይጎናጸፍ ይሆናል የሚል ቅድመ ግምቱን ከወሰዱ አትሌቶች መካከል ተካቶ ነበር።ይሁንና በውድድሩ ስፍራ የአየር ሁኔታና በነበረበት ጉዳት የታሰበውን አሸናፊነት ሊያሳካ አልቻለም።
በኦሊምፒኩ ማግስትም በለንደን ማራቶን ሮጦ ዳግም ድል ለማድረግ ማቀዱ ይታወቃል።ነገር ግን ከሰሞኑ የተሰማው ጉዳት እንዳለበት የሚያመላክተው ዜና በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ በውድድሩ እንዳይሳተፍ ሊያደርገውና በተጠበቀው ፉክክርም ላይታይ ይችላል የሚል ስጋትን አሳድሯል።ይሁንና የ25ዓመቱ አትሌት ሹራ ቂጣታ ጉዳቱን ተቋቁሞ በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ከእንግሊዟ ዋና ከተማ ለንደን መድረሱ ታውቋል።
ጥቂት ችግሮች ቢኖሩበትም፤ አሁንም ግን አሸናፊ ሊያደርገው የሚችለውን ዝግጅት አጠናክሮ መቀጠሉንም ዘ ኢንተርናሽናል ኒውስ የተባለው ድረገጽ አስነብቧል።አትሌቱ ስለ ሁኔታው ሲያስረዳም ‹‹ከኦሊምፒኩ አስቀድሞ በጥሩ ሁኔታ ዝግጅት ሳደርግ
ነበር የቆየሁት፤ ኦሊምፒኩ ሁለት ሳምንት ሲቀረው ግን የቋንጃ ጉዳት አጋጠመኝ።ይህም ከፍተኛ ጫና ውስጥ ከቶኝ ነበር።አሁን ግን መልካም ሁኔታ ላይ ስለምገኝ በእሁዱ ሩጫ ላይ እሳተፋለሁ›› ሲል ማረጋገጫውን ሰጥቷል፡፡
አትሌቱ ተሳታፊነቱን ያረጋግጥ እንጂ በውድድሩ ላይ መሳተፉ እንደተገመተው አሸናፊ እንዳይሆን ሊያደርገው ይችላል የሚለውን ስጋት ተከትሎም፤ ጉዳቱ ከአሸናፊነት ሊያቆመው እንደማይችል የሚያመላክት ምላሽ ሰጥቷል። በምላሹም ‹‹የቋንጃ ጉዳቱና እርሱን ተከትሎ የሚመጣው የህመም ስሜት ቀላል የሚባል አይደለም።ችግሩ በተለይ በፈጣን ሩጫ ወቅት የሚከሰት ነው።ቢሆንም ከዚህ ቀደም እንዳደረኩት አሸናፊ ሆኜ ውድድሩን ለማጠናቀቅ ጥረት አደርጋለሁ›› ማለቱን ዘገባው አትቷል፡፡
በዚህ ውድድር ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ብርሃኑ ለገሰ አሸናፊ ይሆናል በሚል ይጠበቃል።አትሌቱ እአአ በ2019 የበርሊን ማራቶን 2:02:48 የሆነ ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ አሸናፊ ነበር።ሌላኛው አሸናፊ ሊሆን ይችላል በሚል የሚጠበቀው አትሌት ደግሞ ኬንያዊው ኢቫንስ ቺቤት ሲሆን፤ በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በውድድሩ ፈተና እንደሚሆኑ አልሸሸገም።አትሌቱ ‹‹ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ከኋላ ሆነው ሲሮጡ ቆይተው 200 እና 300 ሜትር ሲቀረው አፈትልከው በመውጣት ይታወቃሉ።ይህም ውድድሩን ከባድ ያደርገዋል፤ በመሆኑም በጥንካሬ ፈተናውን መወጣት ይጠበቃል›› ሲልም አስተያየቱን አንጸባርቋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 21/2014