መንግስት በፍጥረታዊ ባህሪው የህዝብ ኃላፊነት ያለበት የአስተዳደር መዋቅር ነው። በተለይም በለውጥ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ በሚገኙ ሀገሮች የመንግስት ኃላፊነት ከተለመደው በብዙ መልኩ ከፍ ያለ እንደሚሆን፤ ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት መፍጠርም ትልቁ የቤት ስራው ነው።
በአንድ በኩል የቀደመው አሮጌው የፖለቲካ ሥርዓት የፈጠረውን የተበላሸ አስተሳሰብና አስተሳሰቡ የወለደውን ያልተገባ ድርጊት ለማስቆም ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለውጡ ይዞት የመጣውን ተራማጅና አራማጅ አስተሳሰብ አቅም ፈጥሮ በአሸናፊነት እንዲቆም የሚደረገውን ተፈጥሯዊ ትግል ከፍ ባለ ኃላፊነትና ከዚህ በሚመነጭ ዲ ሲፕሊን የ መምራት ሃላፊነት አለበት።
በተለይም በብዙ ሴራዎች የህልውና አደጋ በተጋረጠባቸው ሀገራት በህዝብ ይሁንታ የሚሰየም መንግስት ከሁሉም በላይ ሀገርን እንደ ሀገር የመታደግ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ የመንግስትነት ባህሪውም ሆነ የኃላፊነት ደረጃ የሚሰላው ሀገርን እንደ ሀገር ለማስቀጠል ባለው አቅም እና ቁርጠኝነት ነው።
ይህ ደግሞ ችግሮችን ከምንጫቸው በአግባቡ መረዳትን ፤ ለችግሮቹም ዘላቂና አሳታፊ መፍትሄዎችን ማበጀትን፤ መላውን ህዝብ የችግሮች መፍትሄ አድርጎ ማንቀሳቀስን ፤ ከተለመደው የፖለቲካ መንገድ ወጣ ብሎ የመጓዝንና አዲስ የፖለቲካ ባህል መፍጠርና ማለማመድን ፤ ከሁሉም በላይ ሀገርን አሸናፊ የሚያደርግ የፖለቲካ አመራር መስጠትን የሚጠይቅ ነው።
በሀገራችን ከሶስት ዓመት በፊት በመላው ህዝባችን የለውጥ መንፈስ ወደ ስልጣን የመጣው የለውጥ ኃይል ሀገርን እንደሀገር ለመታደግ ፤ የህዝባችን የዘመናት ጥያቄ የሆነውን የዴሞክራሲ ሥርአዓ ግንባታ በጠንካራ መሰረት ላይ ለማዋቀር የሄደበት ርቀት እና ከለውጡ ማግስት ጀምሮ እንደ ሀገር ያጋጠሙንን ተግዳሮቶች አሸንፎ ለመውጣት ያሳየው ቁርጠኝነት የህዝብ ይሁንታ አግኝቶ መንግስት ለመሆን ቀናትን እየጠበቀ ነው።
የለውጥ ኃይሉ ባለፉት ሶስት ዓመታት ሀገርን እንደ ሀገር ለማስቀጠል ፤ ለዚህ የሚስማማ አዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብ በማስተዋወቅ ፤ በብዙ ትዕግስትና ሆደ ሰፊነት የተጓዘበት የለውጥ መንገድ በግብታዊነት ያጣናቸውን መልካም የለውጥ አጋጣሚዎች መካስ የሚያስችል የአዲስ ታሪክ ጅማሬ እንደሆነ በብዙዎች ይታመናል።
ከዚህም በለይ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ለውጡን ለመቀልበስ ከውስጥም ከውጭም ተናበው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ባሰቡትና ባቀዱት መልኩ የጥፋት ተልዕኳቸው ፍሬ እንዳያፈራ የለውጥ ሃይሉ ከመላው ህዝብ ጋር የፈጠረው መናበብና ህዝብን ዋነኛ የለውጡ ሃይል አድርጎ መጓዙ ላስመዘገበው ሀገራዊ ስኬት ትልቅ አቅም ፈጥሮለታል።
ሀገር እንደ ሀገር አበቃላት የሚሉ ሟርቶች አደባባይ በሞሉባቸው ፤ ሀገር ለማፍረስ እስከ ሲኦል እንሄዳለን የሚል የባንዳዎች የአመጻ ድምጽ ከፍ ባለ እብሪት በአደባባይ በድፍረት በተስተናገደበት፤ ዓለምአቀፍ የመገናኛ ብዙሃን በግልጽ ወገንተኝነት የአሸባሪው ህወሓት የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ሆነው በተሰለፉበት ፤ ተግሳጾችና የማዕቀብ ማስፈራሪያዎች የዕለት ተዕለት ድምጽ በሆኑበት ሁኔታና ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በዓለም አቀፍ መድረኮች ማሟሻ በሆነችበት ፈታኝ ወቅት የለውጥ ሃይሉ ስለሀገርና የሀገር ጥቅም ያሳየው ቁርጠኝነት የነገ ታሪካችን ትልቁ ትርክት እንደሚሆንም ይታመናል።
የለውጥ ኃይሉ ባለፉት ሶስት ዓመታት ሀገርን እንደሀገር የተፈታተኑ ችግሮችን በጽናት ታግሎ ከማለፍ ባለፈ እንደ ሀገር የጀመረውን አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ግንባታ ወደ ማይቀለበስ ደረጃ ለማድረስ እና ሀገርን እንደ ሀገር ለማሻገር በህዝብ ዘንድ የተሰጠው የመንግስትነት ይሁንታ በቀጣይ ብዙ ተግዳሮቶች የሚጠብቁት እንደሚሆን ከመጣንበት መንገድ ለመገመት የሚቸግር አይሆንም።
ከዚህም ባለፈ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎችን በተጠናከረ መንገድ ወደ ስኬት ለማሻገርም ለለውጥ ኃይሉ የተሰጠው የመንግስትነት ይሁንታ እንደ መልካም አጋጣሚ የሚታይ ነው። ይህንን አጋጣሚ ወደሚጨበጥ ስኬት በመለወጥ በህዝብ ልብ ውስጥ የተሻለ ስፍራ እና የላቀ ታማኝነት ለማግኘት ከፍ ባለ የኃላፊነት መንፈስ መንቀሳቀስን ይጠይቃል።
የለውጥ ኃይሉ በህዝብ ባገኘው ሰፊ ይሁንታ መንግስት መሆኑ የጀመራቸውን የለውጥ ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የህዝብን የለውጥ መሻት ወደሚጨበጥ የታሪክ ምዕራፍ ለመለወጥ የሚያስችል ታሪካዊ እድል ፈጥሮለታል። ይህንን ዕድል በጀመረው የህዝብና የሀገር ተቆርቋሪነት መንፈስና የለውጥ ኃይልነቱን በተጨባጭ ማስመስከር ፤ ከሁሉም በላይ ሀገርን እንደ ሀገር የማሻገር ከፍ ያለ ሃላፊነት መወጣት ይጠበቅበታል።
የሚመሰረተው መንግስት ይህንን ሃላፊነት መሸከም የሚያስችል ቁመና ሊኖረውና መመዘኛውም ከዚህ ኃላፊነት የሚመነጭና ለዚሁ የተገዛ ሊሆን ይገባል ። ይህንን ለማድረግም የለውጥ ኃይሉ ከመጣበት እልህ አስጨራሽ መንገድ አንጻር ሊከብደው የሚችል አይሆንም!
አዲስ ዘመን መስከረም 21 ቀን 2014 ዓ.ም