የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በነዋሪዎቹ ከሚነሱበት ቅሬታዎች መካከል አንዱ ከሕዝቡ ብዛት ጋር የሚመጣጠን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ አለመኖሩ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በስፖርት ኮሚሽኑ አማካኝነት አዳዲስ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን በመገንባት እንዲሁም የነበሩትን በዘመናዊ መልክ በማሳደስ ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ እየሰራ ይገኛል።
የአስተዳደሩ ስፖርት ኮሚሽን በየካ ክፍለ ከተማ ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ ጨፌ ሜዳ እየተባለ ይጠራ የነበረውን ሜዳም ደረጃውን በጠበቀና ለአካባቢው ነዋሪዎችም ምቹ በሆነ መልኩ አስገንብቶ በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም በማስመረቅ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆን አድርጓል። ይህ ሜዳ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንዲሁም ለተለያዩ ክለቦች ግብዓት የሚሆኑ ተጫዋቾችን በብዛት ካፈሩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች መካከል አንዱ ነው፤ ታዳጊዎች የእግር ኳስ ክህሎታቸውን የሚያሳድጉበት ቦታ ነው።
ኮሚሽኑ አስቀድሞ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ለማስገንባት ካቀዳቸው ዞናል ስታዲየሞች መካከል አንዱ በዚህ ጨፌ ሜዳ ላይ የሚገነባ ነበር። ይሁን እንጂ ቦታው እንደታቀደው ስታዲየም ለማስገንባት የሚያስችል ባለመሆኑ (ለስታዲየም የሚያስፈልገው ወደ 32ሺ ስኩዌር ካሬ ሜትር ቦታ ሲሆን፤ የተገኘው ደግሞ 23ሺ ስኩዌር ካሬ ሜትር በመሆኑ) የእቅድና የዲዛይን ለውጥ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ከኮሚሽኑ የተገኘ ማስረጃ ይጠቁማል። በዚህም መሰረት ባለው ቦታ መሰራት የሚችለው የማዘውተሪያ ስፍራ የአካባቢውን ተፈጥሯዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ እንዲሁም በሕጉ መሰረት በሜዳው አጠገብ ከሚያልፈው ወንዝ 15ሜትርበመራቅ ተገንብቷል። በዲዛይን ክለሳ ምክንያትም ቀድሞ በአራት ወራት ለማጠናቀቅ የታሰበው ግንባታ ከእቅዱ ውጪ ጥቂት ጊዜያትን የወሰደ ነበር።
ግንባታው የሚያጠቃልለው ደረጃውን የጠበቀ የእግር ኳስ ሜዳ፣ የ3በ1፣ የመሮጫ ትራክ፣ የፉት ሳል ሜዳዎችን እንዲሁም የመጸዳጃና መታጠቢያ ቤቶችን ሲሆን፤ ከ25 ሚሊዮን ብር በላይም የፈጀ መሆኑም ታውቋል። ይሁን እንጂ ይህ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ በአሁኑ ወቅት አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው በከፊል መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ይጠቁማሉ። የኮንክሪት ሜዳው ለአገልግሎት ተከፍቶ ወጣቶች እየተጫወቱበት ቢሆንም፤ የተቀባው ቀለም የመላላጥ እንዲሁም ውሃ የማቆር ሁኔታ እያሳየ ይገኛል። በቀይ አሸዋ የተሰራው የመሮጫ ትራክም በአግባቡ ባለመገንባቱ ምክንያት በተፈለገው ልክ የሚያገለግል አልሆነም። መሮጫው እግር የሚያሰምጥ እና የማያንቀሳቅስ በመሆኑ፤ በአግባቡ መስተካከል አሊያም በድጋሚ መሰራት እንዳለበትም ነው ተጠቃሚዎቹ የሚጠቁሙት።
ዋናውና ለእግር ኳስ ማዘውተሪያ የሚሆነው የሳር ሜዳ በክረምቱ ምክንያት እስካሁን ጥቅም ላይ አልዋለም፤ በቅርቡ ሳሩ ታጭዶ ለአገልግሎት እንደሚውል እየተጠበቀ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በሜዳው የግራ ክፍል ያለው አጥር በተገነባ በአጭር ጊዜ ውስጥ በጎርፍ ምክንያት ተንዷል። ሜዳው በወንዙ በኩል ግንብ ሊሰራለት ቢገባም በአሰራር ጉድለት ምክንያት ሥራውን ማስጀመር ባለመቻሉ ፈርሷል። በመሆኑም ኮሚሽኑ ይህንን ለማሳደስ ለተጨማሪ ወጪ የሚዳረግ ከመሆኑ ባለፈ አጥሩን ለማስተካከል እና በወንዙ በኩል ግንቡን ለመገንባት የሚገቡት ማሽኖች እና መኪኖች ሜዳውን ሊያበላሹት እንደሚችሉም ስጋታቸውን ያንጸባርቃሉ።
ጨፌ ሜዳ በተፈጥሮው ረግረጋማ ስፍራ ላይ በመኖሩና ውሃ የሚያመነጭ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ይህ ዓይነቱ ችግር ሊያጋጥም እንደሚችል እሙን ነው። ነገር ግን በግንባታው ወቅት የተለያዩ አማራጮችን ለመጠቀም መሞከሩን አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከወራት በፊት በስፍራው ተገኝቶ በሰራው ዘገባ አመላክቷል። ይኸውም ውሃ በሚመነጭባቸው ስፍራዎች ላይ ቱቦ በመቅበር ውሃው ውስጥ ለውስጥ ከሜዳው እንዲወጣ እንዲሁም መሃል ሜዳ ላይ ውሃ እንዳይይዝና ከዚህም ይልቅ ወደ ጎንና ጎን እንዲፈስ የማድረግ አማራጮችን ለመጠቀም መቻሉንም በኮሚሽኑ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ልማትና ፋሲሊቲ ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ባዩ በወቅቱ ገልጸው ነበር። በመሆኑም ሜዳው በበጋ ብቻም ሳይሆን በክረምትም እንዲያጫውት ለማድረግ ውሃ ማስረግ በሚያስችል መልኩ የተገነባ መሆኑም ነው በወቅቱ የተብራራው።
በእርግጥ የወንዙ ውሃ ወደ ሜዳው እንዳይገባ ከተቀመጡት አማራጮች ባሻገር ውሃውን የሚገድብ ግንብ መስራት ካልተቻለ ሜዳው በተለይ በክረምት ወራት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ኮሚሽኑም ስጋቱን ጠቁሞ ነበር። ነገር ግን ሜዳው እንደተጠበቀው ሳይሆን በአጭር ጊዜ ችግሮች እየታዩበት ይገኛል። በመሆኑም እንደ ኮሚሽኑ ሆኖ ግንባታውን በበላይነት የሚመራውና የሚቆጣጠረው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮንስትራክሽን ቢሮ ስለሁኔታው ማብራሪያ እንዲሰጥ ሙከራ ቢደረግም ሊሳካ ባለመቻሉ በዘገባው ማካተት አልተቻለም።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 20/2014