ኢትዮጵያውያን ለድህነት ፣ ለፍትህና ለዴሞክራሲ እጦት የዳረጓቸውን አምባገነን ሥርዓቶች ለመጣል ያልከፈሉት ዋጋ የለም። አንዱን አምባገነናዊ ሥርዓት ጣልነው ሲሉ ሌላ አምባገነን እየበቀለ በአምባገነኖች መዳፍ ለመውጣት ሲታገሉ ኖረዋል።
ከሶስት ዓመት በፊት እውን እስከ ሆነው ሀገራዊ ለውጥ ድረስ የዘለቀውም ይሄው ነው። አንዱን አምባገነን ሥርዓት ሲጥሉ አመጣነው ያሉት አምባገነን ሲሆንባቸው ነው የኖሩት። በዚህ የተነሳም ድህነቱም የዴሞክራሲና ፍትህ እጦቱም ተጣብቷቸው ለረጅም ዘመን ቆይቷል።
ለዘመናት የከፈሉት መስዋእትነት ፍሬያማ ሆኖ ሀገራዊው ለውጥ ሲመጣም ሲናፍቁት የኖሩት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን እንደሚሆን በማመን ድጋፋቸውን ከዳር አስከ ዳር አረጋግጠዋል። በሀገር ቤት ህዝቡ በሰላማዊ ሰልፍና በመሳሰሉት መንገዶች ድጋፉን አረጋግጧል። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ተመሳሳይ ድጋፍ ችረውታል። በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በውጭ ሀገሮች ባደረጉት ጉብኝት ዲያስፓራው ድጋፉን በስፋት አሳይቷል።
ለውጡ በማረሚያ ቤት የሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች አንዲፈቱ፣ በስደት ላይ ያሉ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ፣ መሳሪያ አንስተው የትጥቅ ትግል ላይ የነበሩትም መሳሪያቸውን አስ ቀምጠው ሰላማዊ ትግሉን እንዲቀላቀሉ አድርጓል።
የለውጡ መንግስት በገባው ቃል መሰረት ከለውጡ ግቦች አንዱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ማረጋገጥ እንደመሆኑ የዴሞክራሲ አንዱ መገለጫ የሆነው ምርጫ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር እውን ተደርጓል። መቼውንም ባላጋራ ተለይቷት የማታውቀው ሀገራችን በገዛ ጉያዋ የበቀሉ ከሀዲዎችና እድገቷን የማይመኙ የውጭ ሃይሎች ምርጫውን ለማሰናከል ያልፈነቀሉት ድንጋይ ባይኖርም ምርጫው እነሱ እንዳሰቡት ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ባሰቡት መንገድ በስኬት ተጠናቅቆ በምርጫው ኢትዮጵያ አሸንፋለች።
አሁን ደግሞ በምርጫው ያሸነፈው ፓርቲ አዲስ መንግስት የሚመሰርትበት ወሳኝ ምእራፍ ላይ ተደርሷል። በአሁኑ ወቅት የክልል መንግስታት መንግስት እየመሰረቱ ሲሆን፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት፣ የአዲስ አበባ ከተማ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መንግስት መስርተዋል ፣ሌሎች ክልሎችም በተመሳሳይ ሰሞኑን ይመሰርታሉ። የክልል መንግስታት በካቢኔያቸው አሸናፊው ፓርቲ በገባው ቃል መሰረት የተፎካካሪ ፓርቲ አባላትን በካቢኔያቸው እያካተቱ ይገኛሉ። በሀገር ደረጃ የመንግስት ምስረታው በሚቀጥለው ሰኞ ይካሄዳል። በዚህም ሀገሪቱ ህዝብ በመረጠውና ይሁንታ በሰጠው አካል ወደ መተዳደር ትገባለች። የኢትዮጵያውያን የዘመናት ጥያቄም በዚሁ መቋጫ ያገኛል። በሀገር ደረጃም እንዲሁ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት በካቢኔ ውስጥ እንደሚካተቱ ይጠበቃል። ይህም ሀገሪቱ ከፉክክር ወደ ትብብርናአብሮ መስራት እየተሸጋገረች መሆኑን ያመላከተ ትልቅ የለውጥ ምዕራፍ ይሆናል።
ሀገሪቱና ህዝቧ ለእዚህ ታላቅ ድል የበቁት በርካታ ፈተናዎችን አልፈው ነው። ከለውጡ ወዲህ ያሉትን ፈተናዎች ብቻ ብንመለከት እንኳን ምርጫው ያስፈራቸው አካላት ከውጭ ኃይሎች ጋር በመሆን ተላላኪ መንግስት ለመፍጠር ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም። እነዚህ ኃይሎች ምርጫው እንዳይሳካ ያልከፈቱት የዘመቻ ግንባር የለም። የሽብር ሴራ፣ ማእቀብ፣ ማስፈራራት ከዘመቻ ግንባሮቹ መካከል ይጠቀሳሉ። ኢትዮጵያውያንና መንግስታቸው ግን እነዚህን ፈተናዎች በስልት አልፈዋቸዋል። በዚህም ሀገራቸው ኢትዮጵያ ምርጫውን እንድታሸነፍና አዲስ መንግስት እንድትመሰርትም አድርገዋል።
በዚህ ድል ውስጥ መላ ኢትዮጵያውያን ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የግል ተወዳዳሪዎችና ሌሎች የሀገሪቱን መልካም ጉዞ የሚፈልጉ ወገኖች ሁሉ አስተዋጽኦ አድርገዋል። በቀጣይም ሊሆን የሚገባው ይሄው ነው። ምርጫው እንዲሳካ፣ መንግስት አቅዶ የተንቀሳቀሰባቸው ፕሮጀክቶች ሁሉ ስኬታማ እንዲሆኑ አስተዋጽኦ ሲያደርግ የቆየው መላ ህዝብ፣ ከሚመሰረተው መንግስት ጋር እጅና ጓንት ሆኖ መስራት ይጠበቅበታል።
መንግስት ያለ ህዝብ ምንም ነው። ጠንካራ የህዝብ ተሳትፎ የሌለበት መንግስት ደግሞ የህዝብን ጥያቄ መመለስና ያሰበውን ማሳካት ይከብደዋል። በተለይም በዚህ ወቅት ሀገሪቱ ከገጠሟት ፈተናዎች አኳያ ሲታይ በቀጣይም ጠንካራ የህዝብ ተሳትፎን ይፈልጋል።
ባለፉት ሶስት የለውጡ ዓመታት በተለያዩ መንገዶች ህዝቡ ያደርግ የነበረው ተሳትፎ የህዝብ ተሳትፎ ለመንግስት ያለውን ፋይዳ በሚገባ ያመላከተ ነው። ግንባታው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያለፈው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አሁን ላለበት ወሳኝ ምዕራፍ የደረሰው በህዝብ የነቃ ተሳትፎ ነው። የአንድነት፣ የእንጦጦ ፓርኮች ግንባታ ጠንካራ የህዝብ ተሳትፎ የተደረገባቸው ናቸው።
ኮሮና በሀገራችን በተከሰተበት ወቅት መላው ህዝብ እና ባለሀብቶች በመረዳዳት በኩል ያደረጉት አስተዋጽኦ ሁሌም ሲጠቀስ ይኖራል። ለሀገር መከላከያ በገንዘብና በዓይነት ተደረገው ድጋፍ፣ አሸባሪው ህወሓት በራሱም በተላላኪዎቹም ያፈናቅላቸውን በመርዳትና መልሶ በማቋቋም፣ በምገባ መርሀ ግብር፣ በአቅመ ደካሞች የመኖሪያ ቤት እድሳት ፣ወዘተ ህዝብ ንቁ ተሳትፎ ማድረጉ የመንግስትን ሸክም ትርጉም ባለው መልኩ ማቃለል አስችሏል። ይህ ብቻም አይደለም የህዝብን ተሳትፎ ወሳኝነት በሚገባ ያመላከቱም ናቸው።
ይህ ሁሉ ህዝብ ተይዞ የማይወጣ አቀበት የማይወረድ ቁልቁለት እንደሌለ ያመለክታል። አዲሱ መንግስት ይህን የህዝብ ተሳትፎ በሚገባ መጠቀም ይኖርበታል። ህዝቡም ይህን ተሳትፎውም በቀጣይም አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። ሀገራችን በልማት ገና ያልተራመደች ናት፤ ከዚህም ከዚያም ልታገኝ የምትችለው ብድርና እርዳታ ተላላኪ መንግስት ለመመስረት የሚፈልጉ መንግስታት እየወሰዱ በሚገኙት ማእቀብ ብዙም የሚያወላዳ አይሆንም። ያላት አቅም ህዝቧን ይዛ መስራት ብቻ ይሆናል።
ህዝቡ ሲጠይቅ የኖረው ልማት ፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እና ፍትህ እውን ሊሆን የሚችለው አዲስ መንግስት ስለተመረጠ ብቻ አይደለም። በለውጡ ባለፉት ዓመታት እንዳረገው ሁሉ ህዝብ ከመንግስት ጋር አብሮና በንቃት መስራት ሲችል ነው።
የህዝብ አቅም መተኪያ የሌለው ስለመሆኑ ከለውጡ መንግስት በላይ የሚናገር አይኖርም። ህዝብ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እያለም በሀገር ጉዳይ የሚቆጥበውና የሚሰስተው እንደማይኖር በተጨባጭ ተረጋግጧል። በህዝብ ይሁንታ ወደ ስልጣን የመጣው አዲሱ መንግስት የህዝቡን የዘመናት ጥያቄ ለመመለስ የተጀመረውን ጥረት ከግብ ለማድረስ አሁንም ከህዝቡ ጋር ለመስራት ትልቅ ግምት መስጠት ይጠበቅበታል። ህዝብ ተይዞ የማይሻገሩት ወንዝ፣ የማይወጡት ተራራ የማይወርዱት ቁልቁለት እንደሌለ ለተረዳ መንግስት ደግሞ ይህን ማድረግ እንደማይከብደው ግልጽ ነው!
አዲስ ዘመን መስከረም 20/2014