በቅርቡ ታድሶና ዘመናዊ ገጽታን ተላብሶ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው የአበበ ቢቂላ ስታዲየም 15ኛውን የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ (ሲቲ ካፕ) በማስተናገድ ላይ ይገኛል። የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፤ የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች ወደ ውድድር ዓመቱ ከመግባታቸው አስቀድሞ ይህንን ውድድር ያዘጋጃል። ወደ ዓመታዊው ውድድር የሚያንደረድራቸው ይህ ከተማ አቀፍ ዋንጫ ክለቦች ከእረፍት መልስ አቋማቸውን የሚገመግሙበትና የተጫዋቾቻቸውንም አቅም የሚፈትሹበት በመሆኑ ተወዳጅነትን አፍርቷል።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተጀመረው በዚህ ውድድር ላይም ከረጅም ጊዜ በኋላ ደጋፊዎች በስታዲየም ተገኝተው ክለቦቻቸውን እንዲያበረታቱ ተፈቅዶላቸዋል። በኮቪድ 19 ስጋት ምክንያት ከፊል ደጋፊ ብቻ በስታዲየም እንዲገባ በተፈቀደበት በዚህ ውድድር፤ የስታዲየም መግቢያ ቲኬት አቆራረጡ ከመዘመኑ በተጨማሪ በአዲስ እና የተሻለ ጥራት እየተካሄደ መሆኑን ለመገንዘብ ይቻላል። እስከ መስከረም 30/2014ዓ.ም በሚቀጥለው ውድድር ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
ከተጀመረ 5 ቀናት ያስቆጠረው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ (ሲቲ ካፕ) ዛሬ ከሰዓት በኋላ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። በምድብ አንድ የተደለደሉት ክለቦች ሁለተኛ ጨዋታቸውን ሲያደርጉ፤ የመጀመሪያው ጨዋታ አሸናፊዎቹ ጅማ አባጅፋር እና መከላከያ ኢትዮጵያ ቡናን እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማን ያስተናግዳሉ። በዚህም መሰረት የመጀመሪያው ጨዋታ በስምንት ሰዓት አዲስ አበባ ከተማን ከጅማ አባጅፋር ያገናኛል።
በመክፈቻው ጨዋታ በመከላከያ 2 ለምንም የተሸነፈው ወደ ፕሪምየር ሊጉ በድጋሚ ያደገውአዲስ አበባ ከተማ፤ ከሌላኛው አሸናፊ ጅማ አባጅፋር ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ቀላል እንደማይሆንላቸው ይጠበቃል። ይሁን እንጂ አዲስ አበባዎች ካለፈው ጨዋታ ልምድ በመውሰድ ወደ ዛሬው ጨዋታ የሚገቡ ከሆነ እንዲሁም ግብ በማስቆጠር በኩል ተሽለው ከተገኙ ነጥብ አስቆጥረው ሊወጡ ይችላሉ። ጅማዎች በበኩላቸው በቀደመው ጨዋታ እንደታየው ሁሉ በተቃራኒ ቡድን ግብ በመድረሱ የተሻሉ ከሆኑ አሸናፊነታቸውን አስጠብቀው የመውጣት ዕድላቸው የሰፋ ይሆናል።
በ10 ሰዓት የሚካሄደው ሁለተኛው ጨዋታ ደግሞ በመከላከያ እና ኢትዮጵያ ቡና መካከል ይደረጋል። በመጀመሪያው ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ የበላይ በመሆን ሶስት ነጥብ ይዘው የወጡት መከላከያዎች የዛሬው ጨዋታ ቀላል እንደማይሆንላቸው ይጠበቃል። የአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ቡድን ከዚህ ጨዋታ ነጥብ ይዞ ለመውጣት ወደ ሜዳ የሚገባ ሲሆን፤ በአንጻሩ ከአንድ ዓመት በኋላ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተመለሰው ጦሩ ቀላል ቡድን እንደማይሆን ይጠበቃል።
በየጨዋታው ኮከብ ተጫዋች በመምረጥ የዋንጫ ሽልማት በሚሰጥበት በዚህ ውድድር እስካሁን አራት ተጫዋቾች ተመራጭ ሆነዋል። በአዲስ አበባ እና በመከላከያ መካከል በተካሄደው ጨዋታ ለራሱና ለክለቡ ሁለት ግቦችን ከመረብ በማዋሃድ ጦሩን አሸናፊ እንዲሆን ያደረገው አዲስ ፈራሚው የመከላከያ ተጫዋች ቢኒያም በላይ፤ የጨዋታው ኮከብ በመሆን ሽልማቱን ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ እጅ ወስዷል። በዕለቱ በተካሄደው ሌላኛው ጨዋታ ደግሞ ለጅማ አባጅፋሮች ሁለተኛውን ግብ ያስቆጠረው አጥቂው ዳዊት ፈቃዱ ኮከብ ተጫዋች በመባል ተመርጧል።
ባህርዳር ከተማ ብልጫውን በወሰደበት ጨዋታ ደግሞ አስደናቂ አቋም ያሳየውና ተደጋጋሚ ሙከራዎችን በማድረግ አንድ ግብ ከመረብ ያገናቸው ኤርትራዊው አጥቂ አሊ ሱለይማን ኮከብ ተጫዋች ሆኗል። በሌላኛው ጨዋታም የቅዱስ ጊዮርጊሱ አማካይ ሃይደር ሸረፋ ኮከብ ተጫዋች በሆን ተመርጦ የዋንጫ እና የ12ሺ ብር ሽልማቱን ከዕለቱ የክብር እንግዳ ተረክቧል። ይህም ኮከብ ተጫዋቾችን በመምረጥ የዋንጫ እና የገንዘብ ተሸላሚ የማድረግ ሂደት በየጨዋታው የሚቀጥል ይሆናል።
ከትናንት በስቲያ በምድብ አንድ በተካሄዱት ጨዋታዎች ባህርዳር ከተማ አዳማ ከተማን 3 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ሲያሸንፍ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስም በተመሳሳይ ፋሲል ከተማን 3 ለምንም በሆነ ውጤት ረቷል። በዚሁ ምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች ነገ ቀጥለው የሚደረጉ ሲሆን፤ ስምንት ሰዓት ባርዳር ከተማ ከፋሲል ከተማ ይጫወታሉ። በ10 ሰዓት ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ አዳማ ከተማን ይገጥማል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 19/2014