አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ የአፍሪካ መዲና፤ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ፣ የትንሿ ኢትዮጵያ መገለጫ ከተማ ናት። የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ጉዳዮች ቁልፍ ስፍራ በመሆኗ ልዩ ትኩረትን የምትሻ፣ የዓለም አቀፍ ተቋማትና ዲፕሎማቶች መቀመጫ ጭምር ናት።
ይሁን እንጂ አዲስ አበባ እንዳላት ትልቅ ስፍራ እና አስፈላጊነት የስሟን ያህል ሆና አልቆየችም። በኢኮኖሚውና በማህበራዊ ጉዳዮች ረገድ ለነዋሪዎቿ ምቹ ነበረች ብሎ ለመናገር አያስደፍርም። በመልካም አስተዳደር፣ በአገልግሎት አሰጣጥ የነበሩት ችግሮች ጎልተው የወጡና ብዙዎችን ያሳዘኑ ነበሩ።
አዲስ አበባ የሁሉም መቀመጫ ትሁን እንጂ ሁሉንም እኩል የምታስተዳድር ከተማ ፍትህና ርትዕ የሰፈነባት ከተማም አልነበረችም ። በመሆኖም ሥራ አጥነት፣ የመኖሪያ ቤት እጥረት፣ የመሰረተ ልማት፣ የትራንስፖርት አለመሟላት እና ሌሎች አዲስ አበባን ቀፍድደው የያዙ ችግሮች ናቸው።
ይሁን እንጂ የለውጡ አስተዳደር ባለፉት ሦስት ዓመታት ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ በዓይን የሚታዩ፣ በእጅ የሚዳሰሱ ከሀገራችንም አልፎ ሌሎችን ጭምር የሚያስደምሙ መልካም ተግባራትን ማከናወን ችሏል። የእንጦጦ ፓርክ፤ የአንድነት ፓርክ፣ ቤተመጽሐፍ ግንባታ፣ የመስቀል አደባባይ እና ሌሎችም ግዙፍ ፕሮጀክቶች ሁሉ ባለፉት ሦስት ዓመታት ተሰርተው ለአገልግሎት በቅተዋል። የገቢ ምንጭም ሆነዋል። የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።
በባዶ ሆድ ትምህርት መማር ያቃታቸውን ሁሉ የምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ እንዲሆኑና ትምህርታቸውን በችግር ምክንያት እንዳያቋርጡ አድርጓል። የአቅመ ደካማና አረጋውያን ቤቶችን በበጎ ፈቃድ አድሶ ፀሐይና ዝናብ እንዳይፈራረቅባቸው ታድጓል። ሌላም… ሌላም። ይሄ በቂ ነው ባይባልም ‹‹አዲስ አበባን እንደስሟ አዲስ እናደርጋለን›› በሚል በተያዘው ጠንካራ አቅጣጫ እና በተወሰደው ቆራጥ አመራር አስገራሚና አስደናቂ ውጤቶች ታይተዋል። አሁንም ተጠናክረው ቀጥለዋል።
ዛሬ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በራሳቸው ድምጽ የሚያስተዳድሯቸውን፣ ይመሩናል፤ ይሆኑናል ያሏቸው አካላትን ያካተተ ምክር ቤት ተቋቁሟል። አዲሱ አስተዳደር ለሕዝቡ በገባው ቃል መሰረት ሊሰራ ከተማችንን ብሎም ሀገራችንን ለመቀየር በቆራጥነት መነሳሳቱን አሳውቋል። የዚህን ውጤት ለማየት የከተማው ነዋሪዎች በጉጉትና በተስፋ እየተጠባበቁ ይገኛሉ።
አዎ ! ከተመረጠው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባላት ብዙ የምንጠብቃቸው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፍትሀዊና ዴሞክራሲያዊ ጉዳዮች አሉ። ከእነዚህም አንዱ ከመኖሪያ ቤት ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ ነው። እንዲሁም ከተማዋን ሰቅዞ የያዘውን መሬትና ከመሬት ጋር ተያይዞ ያለውን ብልሹ አሰራር መፍታት፣ መልካም አስተዳደርን ማስፈን፣ የኑሮ ውድነት ማስወገድ፣ በትራንስፖርት ዘርፉ ያለውን ችግር መቅረፍና ከተማዋን በሁሉም መስኩ ለነዋሪዎቿ ፍትሃዊና ምቹ ማድረግ ከከተማው አስተዳደር የሚጠበቅ ነው።
በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በከተማችን የመመረጥ ዕድሉን ያገኘው አንድ ፓርቲ ብቻ አይደለም። የአሸናፊነት ድምጽ ያገኙም ያላገኙም የግል ተወዳዳሪዎች እና የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች አሉ። በመሆኑም የከተማ አስተዳደሩ የመረጠውንም ያልመረጠውንም ሕዝብ በእኩልነትና በሀቅ ማገልገል ይጠበቅበታል። ለከተማው ብሎም ለሀገር ሰላም፣ አንድነት፣ ዕድገትና ልማት፣ ለነዋሪዎች ደህንነት ተግቶ መስራት እንዲሁም የሕዝብ አገልጋይነትን በተግባር ማረጋገጥ ያስፈልጋል። የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት አዲስ አበባን እንደስሟ አዲስ፣ ለነዋሪዎቿ የማትጎረብጥ፣ ችግሮቿን አስወግዳ በብልጽግና ጎዳና ላይ የምትራመድ ማድረግ ይጠበቅበታል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ከተማዋን የመሩ ኃላፊዎች በገቡት ቃል መሰረት ቃልን በተግባር አውለው አሳይተዋል። ሀገር ባልተረጋጋበት፣ የውስጥና የውጭ ጠላት ጫና ባየለበት፣ ተፈናቃዩና ተንከራታቹ በበዛባት፤ በየአቅጣጫው እርዳታና ድጋፍ በሚያስፈልግበት ወቅት ደከመን ሰለቸኝ ሳይሉ ሌሊት ተቀን ሰርተው አሰርተዋል። ይሄ በጣም የሚያስመሰግን፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይሳካል ተብሎ የማይጠበቅ ድንቅ የፕሮጀክቶች አፈፃጸምም አሳይተዋል።
በቀጣዩ አምስት ዓመታት ደግሞ በሕዝብ የተመረጠው ምክር ቤት በሙሉ ልብና የሥራ ተነሳሽነት ትልልቅ ሥራዎችን ከፍፃሜ አድርሶ እንደሚያሳይ ይታመናል። አዎ! ምክር ቤቱ አዲስ አበባን ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግር ይጠበቃል። አዲስ አበባን እንደ ስሟ አበባ ብቻ ሳይሆን ብርሃን ሆና ማየት የሁሉም ዜጋ ፍላጎት ነው። ለዚህ ደግሞ ከአዲሱ ምክር ቤት የሚጠበቀው ብዙ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባዋል!
አዲስ ዘመን መስከረም 19/2014