በዓለም አቀፉ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት በተቀዛቀዘው የአትሌቲክስ ስፖርት፤ የቶኪዮ ኦሊምፒክ መካሄዱ በድጋሚ እንዲነቃቃ አድርጎታል። ከኦሊምፒኩ በኋላም ጥቂት ውድድሮች ይሰረዙ እንጂ በርካታዎቹ በድጋሚ አትሌቶችን በመምና በጎዳና ላይ ወደ ማወዳደር ተመልሰዋል። ካለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ የሆኑት የማራቶን ውድድሮች እየተካሄዱ ይገኛሉ። ከፉክክር ርቀው የቆዩት ታላላቅ አትሌቶችም በድጋሚ በጎዳና ላይ ሩጫዎች እየታዩ ነው።
በጉጉት ከሚጠበቁትና ታላላቅ አትሌቶች ከሚሳተፉባቸው ማራቶኖች መካከል አንዱ የሆነው የለንደን ማራቶንም በወረርሽኙ ምክንያት ያለፈው ዓመት ቢሰረዝም፤ ዘንድሮ መካሄዱ ተረጋግጧል። ይህ ሩጫ በመጋቢት ወር የሚካሄድ ዓመታዊ ውድድር ቢሆንም በወቅቱ በእንግሊዝ የኮቪድ 19 ክትባት ለሕዝቡ ባለመዳረሱ ምክንያት ወራትን አሳልፎ በመጪው እሁድ መስከረም 23 ቀን 2014 ዓ.ም የሚደረግ መሆኑም ታውቋል። ይህ ውድድርም ከኮሮና ወረርሽኝ መከሰት በኋላ 50ሺ ሰዎች የሚሳተፉበት ግዙፍ የጎዳና ላይ ውድድር እንደሚሆንም ነው የሚጠበቀው። ለዚህም ከባለሙያዎች ጋር በመሆን አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል።
በስፍራው ከሚካሄደው ውድድር ባሻገር በኢንተርኔት በሚደረገው (ቨርችዋል) ውድድርም በተመሳሳይ ዕለትና ሰዓት ይጀመራል። በዚህም ሩጫ ላይ ከ37ሺ ሰዎች በላይ ተሳታፊ እንደሚሆኑም ነው መረጃዎች የሚያመላክቱት። በአትሌቲክስ ስፖርት ታዋቂና ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑአትሌቶች ተካፋይ ሲሆኑ፤ ያለፈው ውድድር ዓመት (2019) ቻምፒዮናዎች በድጋሚ ለሌላ ድል የተዘጋጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ያለፈው ዓመት የለንደን ማራቶን ቻምፒዮና የሆነው ኢትዮጵያዊው አትሌት ሹራ ቂጣታ በድጋሚ በውድድሩ ላይ የሚካፈል መሆኑ ተረጋግጧል። በ2019ኙ ውድድር አሸናፊ የነበረው ሹራ፤ በቅርቡ በተካሄደው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ሃገሩን በርቀቱ የወከለ ቢሆንም እንደተጠበቀው ውጤታማ አለመሆኑ የሚታወስ ነው። በወቅቱ ውድድሩ የተካሄደበት ሳፖሮ የተባለው ስፍራ ሙቀት ከባድ በመሆኑ ምክንያት ውጤት ሳይመጣ መቅረቱም ነበር የተጠቀሰው።
በዚህ የማራቶን ተሳትፎው ግን አትሌቱ ለሌላ አሸናፊነት መዘጋጀቱን ነው ያስታወቀው ‹‹በኦሊምፒኩ ውድድሩን በማቋረጤ ተበሳጭቻለሁ፤ ይህ የሆነው የአየር ሁኔታውን መቋቋም ባለመቻሌ ነው። ከቶኪዮ አንጻር በኢትዮጵያ ብርዳማ የአየር ሁኔታ በመሆኑ፤ አተነፋፈሴን ከባድ አድርጎብኝ ነበር። ለለንደን ማራቶን ግን በተስተካከለ የጤና ሁኔታ በድጋሚ እገኛለሁ። የቦታው ባለ ድል ለመሆንም በአግባቡ ተዘጋጅቻለሁ። ያለፈው ዓመት አሸናፊነቴ የማይረሳ ነበር፤ ታላቅ ደስታንም ፈጥሮልኛል። ከእኔ ባለፈም ቤተሰቦቼንና አገሬን ላኮራ ችያለሁ። በዚህ ዓመት ደግሞ ካለፈው በተሻለ ፍጥነት ውድድሬን ለማጠናቀቅና ታሪካዊ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጁ ነኝ›› ማለቱን ራነርስ ወርልድ የተሰኘው መጽሔት አስነብቧል።
ሹራ የስፍራው ሻምፒዮን በመሆኑ በድጋሚ አሸናፊ የመሆኑ ሰፊ ቅድመ ግምት ይሰጠው እንጂ፤ ከእርሱ የፈጠነ ሰዓት ያላቸው ሌሎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተሳታፊም ናቸው። እነርሱም ብርሃኑ ለገሰ፣ ሞስነት ገረመው፣ ሙሌ ዋሲሁን፣ ሲሳይ ለማ እና ክንዴ አጣናው ናቸው።
በማራቶን የሴቶች ክብረወሰን ባለቤቷ ኬንያት አትሌት ብሪጅድ ኮስጊ በለንደን ማራቶን ሶስተኛ ድሏን ለማስመዝግብ ማቀዷም ታውቋል። እአአ በ2019 የቺካጎ ማራቶንን 2፡14፡04 በሆነ ሰዓት በመግባት የዓለም ክብረወሰንን የግሏ ያደረገችው አትሌቷ፤ በቶኪዮ ኦሊምፒክ የብር ሜዳሊያ አጥልቃለች።
ተሳትፎዋን ተከትሎም አትሌቷ ‹‹በድጋሚ በለንደን ማራቶን መሳተፌ ደስተኛ አድርጎኛል፤ ምክንያቱም የምወደው ውድድር ነው። ያለፈው ውድድር በጣም መልካም ነበር፤ አሁንም ወደ መልካም አቋም ተመልሻለሁ። በተከታታይ ለሶስተኛ ዓመት አሸናፊ የመሆን ፍላጎትም አለኝ›› ማለቷ በዘገባው ተመላክቷል።
በዚህ ውድድር ላይ ከኬንያዊቷ አትሌት ባሻገር ስድስት የሚሆኑ ታዋቂ አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን፤ ሁሉም ከ2ሰዓት ከ20 ደቂቃ በታች የሆነ ሰዓት ያላቸው መሆኑም ታውቋል። ኢትዮጵያውያኑ የማራቶን አትሌቶች ብርሃኔ ዲባባ እና ሮዛ ደረጄም ለኬንያዊቷ አትሌትም ፈተና እንደሚሆኑ ነው የሚጠበቀው። ደጊቱ አዝመራው፣ ዘይነባ ይመር፣ ትዕግስት ግርማ፣ አሸቴ በቀለ እና አለም መንግስቱም መሳተፋቸውን ያረጋገጡ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 18/2014