የእናትነትን፣ እህትነትን፣ ልጅነትንና የትዳር አጋርነትን ፀጋ የተጎናፀፉት ሴት ልጆች በሕብረተሰብ ውስጥ ያላቸው ውክልናና ኃላፊነት ድርብርብ ነው። የሀገርና የወገን አጋርነታቸውና አለኝነታቸውም የዚያኑ ያህል ይገዝፍና ይጎላል። ሩቅ ሳይኬድ አሁን በወቅታዊ የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ እየሰጡት ያለው ምላሽ ብቻ ለዚህ አስተዋጿቸው ማሳያ ይሆናል።
እንዲህም ሆኖ ሴቶች ከወንዶች በበለጠ በየትኛውም ሁኔታ የሚከሰቱ ተፈጥሯዊም ሆኑ ሰው ሠራሽ ችግሮች ተጋላጭና ተጎጂዎች ናቸው። የሴቶች፣ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አድነው አበራ እንደሚናገሩት በተለይ ሀገራችን በውጪም በውስጥም ጠላቶች ሴራ ከገባችበት አጣብቂኝ ጋር ተያይዞ በነበረውና እስከ አሁንም ባላባራው ችግር የመጀመርያዎቹ ገፈት ቀማሾች ሴቶች ናቸው። የጥፋት ኃይሉ በመቀናጀት ወረራ በፈፀመባቸው የአማራና የአፋር ክልሎች ብቻ የተጎዱትን ሴቶች ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። በተለይ ባለፈው 2013 ዓ.ም ክረምት መግቢያ አካባቢ መንግስት እርሻ እንዲታረስ ብሎ የወሰደውን ተኩስ የማቆም ጥሪ ለጥፋት ተግባሩ ያዋለው የጥፋት ኃይል በሕይወትና በንብረት ላይ የፈፀመው ውድመትና ጥፋት አያሌ ሴቶችን ተጎጂ አድርጓል።
ዳይሬክተሩ ከምግብ ዋስትናና ስጋት መከላከል ኤጄንሲ የተገኘውን መረጃ ዋቢ አድርገው እንደገለፁት ከትግራይ ክልል ጋር በነበረው ግጭት ምክንያት ብቻ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለመፈናቀል ተዳርገዋል። ከተፈናቀሉት ዜጎች መካከል አብላጫውን የሚይዘው የሴቶቹ ቁጥር ነው። በመተከልና በሰሜን ሸዋ ዞኖችም በተመሳሳይ በከፍተኛ ደረጃ የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆኑት ሴቶች ናቸው። ከተፈናቀሉት 24ሺህ ህፃናት መካከልም ለአስከፊ ጥቃት የመጋለጥ ሰፊ ዕድል ያላቸው ሴት ህፃናት አብላጫውን ቁጥር ይይዛሉ።
በአፋር ክልል የሚገኙ ሴቶች ዕጣ ፈንታ ከአማራ ክልል ባልተናነሰ ለመፈናቀል የተዳረገ ነው። ለአብነትም ከተፈናቀሉት ዜጎች መካከል ከ19ሺህ በላይ ለአቅመ ሄዋን የደረሱ ሴቶች ይገኙበታል። ሦስት ሺህ 61ዱ ነፍሰ ጡር ሴቶች መሆናቸውንም መረጃዎች ይጠቁማሉ። 39ሺህ 793ቱ ወይም 52 በመቶው ደግሞ ህፃናት ሲሆኑ በዚህም ውስጥ ያለው የሴት ህፃናት ቁጥር ከፍተኛውን መጠን ይይዛል። ሴቶች የመፈናቀል ብቻ ሳይሆን ከሞት ባሻገር የመደፈር፣ አካል ጉዳተኛ የመሆን፤ እንዲሁም ህፃናትን፣ የጦርነቱ ሰለባ የሆኑ አካል ጉዳተኞችን፣ አረጋዊያንንና አቅመ ደካሞችን የመንከባከብ ሸክምም ተጨምሮ ተጭኖባቸዋል።
በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶችም የስነ ልቦና ችግር ሰለባዎችም ሆነዋል። ለከፋ የስነ ልቦና ችግር የተጋለጡት ሴቶች ቁጥር ከ16ሺህ በላይ መሆኑን መረጃዎች ያመለከቱ ሲሆን፤ ብርቱ የስነ ልቦና ድጋፍን የሚሹ መሆናቸውም በጥናት ላይ መመልከቱን ዳይሬክተሩ አቶ አድነው ይጠቅሳሉ። ሴቶችና ህፃናት ላይ የደረሱባቸውን አፀያፊና ስነ ልቦናዊ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደ ሀገር በርካታ ድጋፎችን ለማድረግ ተሞክሯል።
ማይ ካድራና መተከልም ድጋፍ ከተደረገባቸው ቦታዎች ይጠቀሳሉ። እንደ ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ተቋምም ሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሚደርስ የብር ድጋፍ የተደረገበት ሁኔታ አለ። በዚህ ዓይነት የቀውስ ወቅትም ሆነ በማንኛውም ጊዜ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶችን ለዘለቄታው ለመከላከል ይቻል ዘንድም ከፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን ግብረ ኃይል ማቋቋም ተችሏል። በዚህ ዓመትም ይሄን ተቋም በክልሎች የማስፋት ሥራዎች ይሰራሉ።
ሴቶች ይሄ ሁሉ ጉዳትና ጥቃት ሳይበግራቸው ወዲህ በስንቅ ዝግጅቱ፤ ወዲያ በህልውና ዘመቻው በመሰለፍ ሀገር የማዳን ርብርብና ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሴቶች እንቢኝ ለሀገሬ ብለው ከወንድሞቻቸው ጎን በመሰለፍ ግንባር ዘምተዋል። ሰፊ ቁጥር ያላቸው ሴቶችም እነዚህን ሴቶች ለመቀላቀል የሚያስችላቸውን ትምህርት ለመቅሰም
በየማሰልጠኛ ጣቢያው በመከተም ስልጠና በመውሰድ ላይ ይገኛሉ። በሊግ፣ በሴቶች ፌዴሬሽንና በተለያየ መልኩ በተዋቀሩ አደረጃጀቶች ገብተው እየተንቀሳቀሱ ያሉ በርካታ ሴቶች እንደ በሶ፣ ዳቦ ቆሎ፣ ቆሎና ሌሎች ስንቆችን ለዘመቻው በማዘጋጀት ደጀን ሆነው አጋርነታቸውን በማስመስከር ርብርብ እያደረጉ ይገኛሉ። ሰራተኛ ሴቶችም በሥራ ገበታቸው ላይ ከማገልገል ባሻገር ጉልበታቸውን፣ የወር ደሞዛቸውን፣ ደማቸውን ለግሰዋል።
የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ አድነው አበራ እንደሚናገሩት ታድያ ርብርባቸውና ድጋፋቸው በትግራይ ክልል መንግስት ላይ ከተወሰደው ሕግን የማስከበር ዘመቻ ይነሳል። ከዚህ ጀምሮ በቅርቡ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና ከተማዋ ደሴ ላይ ተገኝተው የሚኒስቴር መስርያ ቤቱ ከፍተኛ ኃላፊዎች ለከተማው ከንቲባ ካስረከቧቸው 26 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ አልባሳት፣ ምግቦችና ቁሳቁሶች ጋር ሲደመር ከዘጠና ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት በማሰባሰብ በአሸባሪው ህወሓትና ተላላኪዎቹ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ባደረሰው ወረራና ጥቃት እንደ ሀገር ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ አድርገዋል።
በተለይ በብርቱ ተጎጂ ለሆኑት ለሁለቱ ክልሎች እስከ አለፈው ጷግሜን ወር መጠናቀቂያ ከገቢዎችና ጉምሩክ ሚኒስቴር ጋር በተደረገው ትብብርና የሥራ ድጋፍ የተለያዩ አልባሳትንና ምግብ ነክ ድጋፎችን በማሰባሰብ፣ በገንዘብ ሲተመን፣ ለስንቅ ዝግጅቱ የዋለ የጉልበት ዋጋቸውን ሳይጨምር ፣ በብዙ ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ መደረጉንም አቶ አድነው አስታውሰዋል።
ድጋፉ. እንደ ተቋም በሚወክላቸው የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴርና ከሌሎች ተቋማትና አደረጃጀቶች ጋር በመቀናጀት .በተቀናጀ ሁኔታ እየተተገበረ የመጣ ነው። ትግበራው ከትግራይ ክልል ውጪ ሲዳማን ጨምሮ በዘጠኙም ክልሎች ከክልል እስከ ወረዳና ቀበሌ ያሉ የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ቢሮዎችና ጽሕፈት ቤቶች ያካትታል። በዚህ መልኩ በተለይ በአማራና አፋር ክልሎች ግጭቶችን መሰረት በማድረግ ታክስ ፎርስ በማቋቋም በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል። የተሰሩት ሥራዎች በአጭርና በረጅም ጊዜ እርምጃ በሁለት ጎራ በመከፈል ተለይተው የተከናወኑ ናቸው።
ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር በአጭር ጊዜ እርምጃ ከተለያዩ ተቋሞች ጋር በመቀናጀት ተጎጂዎቹ ምግብ ነክና ቁሳዊ ድጋፎችን እንዲያገኙ ያደረገበት ሁኔታ አለ። ከሴቶች ውጪ 15 ሺህ ለአቅመ አዳም የደረሱየሕብረተሰብ ክፍሎችም የድጋፉ ተቋዳሾች ሆነዋል። በጥፋት ኃይሎች የወደሙ አካባቢዎች ያሉ ተቋሞችንም መልሶ የማቋቋም ሥራ ተከናውኗል። በተለይ ከእነዚህ ውስጥ በአማራና አፋር ክልሎች የሚገኙ፣ ጉዳት የደረሰባቸውንና የወደሙ የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ቢሮዎች፣ ጽሕፈት ቤቶችና በየደረጃው ያሉ ተቋሞችን መልሶ ለማቋቋም የተከናወነው ተግባር ይጠቀሳል።
ሁሉም ሥራ የተሰራው ከሚመለከታቸው አጋሮችና ድርጅቶች ጋር በመቀናጀትም ነው። ከዚህ በተጨማሪም በድጋፉ የቅድመ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ክልሎች የለየ ነው። አማራ ክልል በተለያየ ምክንያት የጥፋት ኃይሉ ለሚፈጥረውና ለፈጠረው ችግር የበለጠ ተጋላጭና ተጎጂ በመሆኑም፤ አፋር ክልልም በሰው ሰራሽ ብቻ ሳይሆን በድርቅና ጎርፍ በመጋለጡ ትኩረትና ቅድሚያ ማግኘታቸውንም ዳይሬክተሩ ገልፀዋል። ድጋፉ በሶማሌ፣ በቤንሻንጉል፣ በጋንቤላ፣ በኦሞ ወንዝ ባሉና በሌሎች የቅድመ ቅድሚያ ትኩረት የሚሹ ተብለው በተለዩ
አካባቢዎች ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ተናግረዋል። ከተቋማቸው ጀምሮ የመንግስት ሰራተኛውና ወጣቱ በተለይ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን እንዲቆምና ሴቶችን እንዲደግፍም ጥሪ አቅርበዋል።
እንደ ሴቶችና ህፃናት ተቋም ለዚህ ጥሪ እሷን ጨምሮ ጾታ ሳይለይ ሁሉም ሠራተኛ ምላሽ መስጠቱን የገለፀችልን የስምሪት ኃላፊዋ ወጣት ዓለም ዮሴፍ ነች። ወጣቷ እንዳከለችልን ሠራተኛው ደምና የአንድ ወር ደሞዙን ለግሷል። ይሄም ብቻ ሳይሆን መከላከያ ሠራዊትና ከጎኑ ለመሰለፍ የዘመቱት በጦር ግንባር ከሚሰሩት ሥራ ጎን ለጎን እሱም በየሰፈሩ ሾልኮ የገባውን ከቀበሌ እስከ ወረዳ፣ ዞንና ክልል በመደራጀት አጥብቆ መቆጣጠር እንደሚገባው መክራለች። ይሄን ለስኬት ለማብቃት ሴቶች በተለያየ አደረጃጀት ውስጥ መግባት እንዳለባቸውም ገልፃለች። በተለያዩ ቦታዎች በሚደረጉ የስንቅ ዝግጅቶችም ትሳተፋለች። በበኩሏ ከሥራ ውጪ በሆኑት ቅዳሜና እሁድ ቀናት በዚህ መልኩ ጭምር ተሳትፎ በማድረግ ሀገሯንና ወገኗን ከጥፋት ኃይሎች እኩይ ተግባር እየታደገች እንደምትገኝ አጫውታናለች።
በዚሁ ተቋም የሰው ሀብት ዳይሬክቶሬት ባለሙያ የሆነችው ወጣት አለሚቱ በሪሁን ‹‹በፈቃደኝነት የአንድ ወር ደሞዜን ለመከላከያ ሠራዊት ለግሻለሁ። እንዲሁም በየሦስት ወሩ ደም በመለገስ ላይ እገኛለሁ›› ብላናለች። ወጣቷ እንዳከለችው ሴቶች ለወቅቱ ችግር ምላሽ እንዲሰጡ ለሠላም ያላቸውን አስተዋጾ እንዲያበረክቱ የሚያስገድድ ጊዜ ላይ ነው የምንገኘው። ከዚህ አኳያ እንደ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር እንደ ሀገርም እየተሰራ ነው። አሸባሪው ህውሃትና ኦነግ ሸኔ ከአንዳንድ የውጪ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት በዜጎች ላይ የተለያዩ ጥቃቶችን አድርሰዋል።
ጥቃቱን ተከትሎ የተፈናቀሉ ወገኖች አሉ። አብዛኞቹ ሴቶችና ህፃናት ናቸው። በመሆኑም በጥቃቱ የደረሰውን ችግር በመቅረፍም ሆነ ጥቃቱ እንዳይደርስ ቀድሞ በመከላከል ትልቁን ሚና መጫወት የሚገባቸውም ሴቶችና ወጣቶች ናቸው። ሚኒስቴር መሥርያ ቤቱ ችግሮችን በተገቢው መንገድ የሚቀንስ ድጋፍ ለማድረግ የበቃው ይሄን ይዞ ወደ ሥራ በመግባቱ ነው ብላለች። በሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር መሥርያ ቤት ጠንካራ አመራሮች መኖራቸውም አበርክቶውን ማጉላቱን ጠቅሳለች። በቅርቡ ከ100 ተፅዕኖ ፈጣሪ የአፍሪካ ሴቶች አንዷ የሆኑትን የሴቶችና ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ ፊልሰን አብዱላሂንም አብነት በማድረግ ሀሳቧን አሳርጋለች።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን መስከረም 18/2014