ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የተካሄደውንና በርካታ መራጮች ድምፅ የሰጡበትን ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ተከትሎ መስከረም 24 ቀን 2014ዓ.ም አዲሱ የመንግስት ምስረታ ይካሄዳል ተብሎ እየተጠበቀ ነው። ብልፅግና ፓርቲም መንግስት ለመመስረት የሚያስችለውን ድምፅ በማግኘቱ መስከረም 20 የሚካሄደው ቀሪ የፓርላማ እና የክልል ምክር ቤት ምርጫ ውጤት ሳይጠበቅ አዲስ መንግስት መመስረት እንደሚችል ማረጋገጥ ተችሏል።
ከስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በፊት ብልፅግና ፓርቲ ምርጫውን ማሸነፍ ከቻለ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላትን በመንግስቱ መዋቅር ውስጥ የተለያዩ የስራ ሃላፊነት ሰጥቶ እንደሚያሳትፋቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አስታውቀው እንደነበር ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀፅ 74 -የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣንና ተግባር በሚለው ስር፣ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባሎችን ከሁለቱ ምክር ቤቶች አባላት ወይም ለስራው ብቃት ካላቸው ሌሎች ግለሰቦች መካከል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በእጩነት አቅርቦ ሹመታቸውን ያስጸድቃል›› ይላል።
ለመሆኑ በአዲስ የመንግስት ምስረታ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማሳተፍ እንዴት ይታያል?፣ ማሳተፍ ሲባልስ እስከምን ድረስ ነው? እንዴት ሊያሳትፋቸው ይችላል? እገሌ እንዳይከፋው እገሌም እንዳይቀርበት በሚል ነው? ወይንስ የሚሉና ሌሎችንም ጥያቄዎች በማንሳት እንዲመልሱልን የተለያዩ ምሁራንን አናግረናል።
በፈረንሳይ ፓሪስ ‹‹school of advanced studies in social sciences Paris –/EHESs/የፒኤች ዲ ተማሪ የሆኑት ጌታነህ ውድነህ ‹‹ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ተከትሎ መንግስት ለመመስረት የሚያስችለውን ድምፅ ያገኘው የብልፅግና ፓርቲ አዲስ በሚመሰረተው መንግስት የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን አሳትፋለሁ ማለቱም እጅግ በጣም የሚደነቅ እና የሚበረታታ ነው›› ይላሉ።
ከፓርቲ ግለኛ ፖለቲካ ወጣ ባለ መልኩ የመንግስት ካቤኔ አባል ማድረግ በአፍሪካ ምድር እምብዛም የተለመደ እንዳልሆነ የሚያስገነዝቡት አቶ ጌታነህ፣ ውሳኔው በጣም ተስፋ ሰጪ እና በተለይም የፍላጎት ግጭትን ከመቀነስ አንጻር ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ያነሳሉ። መንግስትም የተሻለ መሰረት እንዲቀመጥ ብሎም እድሜው እንዲፀና የማድረግ አቅሙም ግዙፍ ስለመሆኑ ይጠቁማሉ። ብሄራዊ መግባባት የመፍጠር አቅሙ በተለይም አንገብጋቢ የሆነውን የሰላም ጥያቄ በመመለስ ረገድ ጉልህ አበርክቶ እንደሚኖረው ያሰምሩበታል።
ውሳኔው የሚበረታታ ቢሆንም መንግስት ከተፎካካሪ ፓርቲና ግለሰቦች ጋር አብሮ ለመስራት እጁን ሲዘረጋ፣ በተለያዩ የአቋም ልዩነት ምክንያቶችም ሆነ ከብዛታቸው አንጻር ሁሉንም ለመጨበጥአይቸገርም ወይ የሚል ጥያቄ ከተለያዩ ወገኖች መነሳቱ አይቀርም። በተለይ በአሸባሪነት ከተፈረጁ እና በሽብር ወንጀል ከተከሰሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ድርጅቶች ጋር እንዴትስ አብሮ ሊሰራ ይችላል? የሚለውም እጅግ ወሳኝ ጥያቄ ሆኖ ይቀርባል።
ይህን እሳቤና ስጋት የሚጋሩት አቶ ጌታነህም፣ በተለይ አሳታፊ የማድረጉ ተግባር በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ላይ ያልተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንዴት ይመለከታቸዋል የሚለው አሳሳቢ መሆኑን ያስረዳሉ።
በተለይ ከአዲስ አበባ ውጭ በሌሎች አካባቢዎች በአገራዊ ምርጫው ላይ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳታፊ እንዳልነበሩ የሚያስታውሱት ምሁሩ፣ በቀጣይም የእነዚህን ፓርቲና ግለሰቦች ሃሳብ እንዴት ማስታረቅ ይቻላል? የሚለው ወሳኝ ጥያቄ እና ከባድ ፈተና እንደሚሆንም ይጠቁማሉ። በዚህ ረገድ መንግስት ከባድ ሃላፊነት እንዳለበትም ያስገነዝባሉ።
ይሁንና በተለያዩ የአቋም ልዩነት ምክንያትም ሆነ ከብዛታቸው አንጻር ሁሉንም ለመጨበጥ አይቸገርም ወይ የሚለው ጥያቄም ለእሳቸውም ያልተመለሰ ጥያቄ ነው። ‹‹መንግስት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ይሰራል ማለት ከሁሉም ጋር ይሰራል ማለት አይደለም። ይህም ፈፅሞ የማይቻል እና የማይሞከር ነው›› የሚሉት ምሁሩ፣ የህዝብ ይሁንታን አግኝቶ አገር የመምራት ሃላፊነት የወሰደ መንግስት የራሱን ካቢኔ ማዋቀር ፣የፈለገውን የመምረጥና የመሾም ሙሉ መብት እንዳለውም አጽእኖት ይሰጡታል።
መንግስት እውቀትና ብቃቱ አለው፤ ፖሊሲና ስታራቴጂዬን ያስፈፅምልኛል፤ የተሻለ አቅም ስላለው አብሮኝ መስራት ይችላል፤ ብሎ ያሰበውን ግለሰብ ወይንም ፓርቲ ከፈለገው ቦታ መርጦ ማምጣት እንደሚችል የሚያስገነዝቡት አቶ ጌታነህ፣ ‹‹መንግስት አሳታፊ ይሆናል ማለት ሁሉንም ሰብስቦ ስልጣን ይሰጣል ማለት አይደለም። ይህን ማሰብም ትልቅ ስህተት ነው›› ይላሉ። ከመካከላቸው የፈለገውን የመምረጥ ሙሉ ስልጣን እንዳለውም ፈፅሞ መረሳት እንደሌለበት ያሰምሩበታል።
የኢዜማ ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ በዚህ ሃሳብ ይስማሙበታል። አቶ ግርማ ፣ በዚህ በጭንቁ ጊዜ የተለያየ አመለካከት ያላቸው ፓርቲዎችም ሆኑ ቡድኖች አገሪቱን ከተደቀነባት አደጋ ለመታደግ ያለምንም አመለካከት ልዩነት በጋራ ቆመው መመከታቸው በታሪክ መዝገብ በደማቅ ቀለም የሚጻፍና ሊበረታታ የሚገባ መሆኑን ያነሳሉ።
ለአገር አንድነትና ዘላቂ ሰላም ሲባል የተለያየ አመለካከት ቢኖራቸውም ስለ አገራቸው ተቆርቋሪ ከሆኑ ኃይሎች ጋር መወያየትና በሀገሪቱ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ እና ወሳኝ እንዲሆኑ ማድረግ ለአገሪቱ መጻዒ እድል ወሳኝ ጉዳይ ስለመሆኑ አፅእኖት ይሰጡታል።
‹‹አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ከአገር አፍራሾቹ በስተቀር ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር አብሮ ይሰራል የሚል እምነት አለኝ›› የሚሉት አቶ ግርማ፣ ይሁንና አሁንባለው ነባራዊ ሁኔታ አገር ለማፍረስ አቅደው እየሰሩ ካሉት አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ጋር ድርድር ማድረግ እንደማያስፈልግ አፅእኖት ይሰጡታል።
ይሁንና አሸባሪ ድርጅቶቹ ከእብደታቸው ታቅበው ለፈጸሙት ጥፋት ተጠያቂ የመሆን ሃላፊነት ካላቸው እንዲሁም ወንጀለኞችን አሳልፈው የሚሰጡ ከሆነ ነገሮችን በጥልቀትና በብስለት ማየት እንደማይከፋም ሳይስገነዝቡ አላለፉም።
የህግ ባለሙያው ኪያ ፀጋዬ፣ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የተካሄደውና በርካታ መራጮች ድምፅ በሰጡበት ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያ ህጋዊ የሆነ ቅቡልነት ያለው መንግስት እንዲኖራት ማድረጉን ያስታውሳሉ። ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ምርጫው ላይ በሰለጠነ መንገድ በመሳተፍ ውጤትን በፀጋ በመቀበል የኢትዮጵያ ጠላቶች እንደተመኙትና እንደጠበቁት እንዳይሆን በማድረጋቸው ትልቅ አክብሮት ሊሰጣቸው እንደሚገባም ያስገነዝባሉ።
‹‹የዚህ ምርጫ ውጤት የሆነው አዲሱ መንግስት በመዋቅሩ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ማሳወቁ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ ነው፣ ውጤቱም ለፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት በተለይም ለአገር ሁለንተናዊ ሰላም እና እድገት ትልቅ እንድምታ አለው›› ይላሉ።
አንድ ፓርቲ ብቻ ጠቅላይ አሸናፊ ሆኖ የአገር ጉዳይ በአንድ ፓርቲ ትከሻ ላይ ብቻ መውደቅ እንደሌለበትና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ውስጥ ሃሳብ ፣ እውቀትና ልምድ ያላቸውን ሰዎች ማሳተፍ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን የሚያስገነዝቡት የህግ ምሁሩ፣ ገዚው ፓርቲ አሁንም ቢሆን አገርን ሊጠቅም የሚችል እና አገርን ማእከል ያደረገ በተሻለ ደረጃ ሊያገለግሉ ይችላሉ የሚባሉ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት እና አመራሮችን በተለያዩ የመንግስት ማዋቅር ውስጥ ማስገባቱንና ግለሰቦችም አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን ይጠቁማሉ።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ እንዲሁም የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስን በዋቢነት ያቀርባሉ። ከዚህ ባሻገር የተለያዩ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችንና አባላት በተለያዩ ተቋማት ላይ ቦርድ አመራር ሆነው እያገለገሉ መሆናቸውንም ያነሳሉ። ይህም የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት እንዳለ ሆኖ ተፎካካሪም ሆነ ገዢ መንግስት አንድ በሚያደርጋቸው ጉዳዮች ላይ ተቀራርበው መስራትና መተባበር እንደሚችሉ ጥሩ ማሳያ መሆኑን ይጠቁማሉ።
ይህ ማለት ግን ከሁሉም ጋር መስራት እንዳልሆነ የሚስማሙት አቶ ኪያ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለ ፓርቲ እና ምርጫ ተሳትፎ ከተወራ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በቀጥታ እውቅና እና ሰርተፍኬት የተሰጠው መሆን እንዳለበት ያስገነዝባሉ።
በተለይ ህወሓት እና ሸኔን የመሳሰሉ ድርጅቶች በምርጫ ቦርድም ህጋዊ ፓርቲ እንዳልሆኑ የተወሰነባቸው ናቸው፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ሽብርተኛ ብሎ ፈርጇቸዋል›› የሚሉት የህግ ምሁሩ፣ ይህ እንደመሆኑም ከእነዚህ ፓርቲዎች ጋር መስራት እንዲሁም በመንግስት መዋቅር ውስጥ ተሳታፊ ማድረግ የማይሞከር መሆኑ ያስማማቸዋል። ‹‹በአሁኑ ወቅት በጣም ፅንፍ የሆነ ዋልታ የረገጠ ፖለቲካ አስተሳሰብ ቦታ እንደሌለው እየታየ ነው። የዚህ እሳቤ አራማጆችም ከፖለቲካ ሜዳው ውጪ እየሆኑ ናቸው›› ይላሉ።
ፓርቲዎች ተሳታፊ በማድረግ ሒደት የተመዘገቡትን ሁሉም እንደ ፀበል መርጨት ብሎም ሁሉንም ማስደሰትም እንደማይቻል አፅእኖት የሚሰጡት የህግ ምሁሩ፣ ለዚህም የተለያዩ የአሳታፊነት መስፈርቶች ማስቀመጥ ግድ እንደሚል ነው ያመላከቱት።
ግለሰቦች በቦታው ላይ ሲሾሙ ለአገር ምን አስተዋጽኦ ያደርጋል፣ የሚለውን ቅድሚያ ተሰጥቶታል ወይ፣ እንዲሁም ትምህርት እና ልምዱስ እንዴት ነው የሚለው መታየት እንዳለበት ነው ያሰመሩበት። አሳታፊነቱ ህዝብን ማእከል ያደረገና በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የድጋፍ መጠን፣ ታሳቢ ማድረግ እንዲሁም አገር አቀፍ ለሆኑት አገራዊ ቦታዎች፣ ክልላዊ ለሆኑት በተመሳሳይ ማድረግ እንደሚቻል ነው ያስረዱት።
ህዝቡ አዲስ ከሚመሰረተው መንግስት ምርጥ የተባለ ከአድሎ እና ከሙስና የፀዳ አገልግሎትን እንደሚጠብቅ የሚያስገነዝቡት የህግ ባለሙያው፣ ‹‹በአሸናፊው ፓርቲ ውስጥም፣ የብልፅግና አባል ስለሆነ፣ ካርዱን ስለያዘ ወይንም ለፓርቲው ታማኝ ስለሆነ ብቻ ትላልቅ አገራዊ ቦታዎችን መያዝ የለበትም፣ ይልቅስ በግልፅ የሚታይ አቅም እና አበርክቶው ሊገመገም ይገባልም ነው›› ያሉት።
አስተያየት ሰጪዎቹ ለአገር አድነትና ዘላቂ ሰላም ሲባል የተለያየ አመለካከት ቢኖራቸውም ስለ አገራቸው ተቆርቋሪ ከሆኑ ኃይሎች ጋር መወያየትና በሀገሪቱ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ እና ወሳኝ እንዲሆኑ ማድረግ ለአገሪቱ መፃኢ ዕድል ወሳኝ ጉዳይ ስለመሆኑ ተስማምተውበታል።
ይሁንና ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ተሳታፊ የማድረግ ተግባር ኮታ ሳይሆን ብቃትን መሰረት ማድረግ እንዳለበትም የፀና እምነት አላቸው። አሳትፊነቱም ፓርቲና ግለሰብን ሳይሆን ህዝብ እና አገርን ለማስደሰት መሆን እንዳለበትም ጠቁመዋል። አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ድርጅቶችም ፈፅሞ መካተት አይኖርባቸውም የሚለው የአስተያየት ሰጪዎቹ ምክረ ሃሳብ ሆኖም ተመላክቷል።
አዲስ የሚመሰረተው መንግስት አገሪቱ በአሁኑ ጊዜ ካጋጠሟት የተለያዩ ፈተናዎች አንጻር ብዙ የቤት ስራዎች ይጠበቅበታል። የትኛውም መንግስት ቀዳሚ ተግባር የህግ የበላይነትን በማስጠበቅ ሰላምን ማስፈንና የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ በመሆኑ የሚመሰረተው መንግስትም ቀዳሚ አጀንዳ በአገሪቱ ላይ ሰላም ማስፈንና የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ሊሆን እንደሚገባም ባለሙያዎቹ አስምረውበታል።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን መስከረም 18/2014