ኢትዮጵያውያን መረዳዳትን ፣ መተሳሰብን ከሦስት ሺህ ዓመታት በፊት የኖሩትና ዛሬም ቢሆን እየተገበሩ ያሉ ህዝቦች ናቸው። ኢትዮጵያዊነት በብዙ ነገሮች መተሳሰር እንደሆነም የሚነሳው ለዚህ ነው። በተለይም ችግሮች በአጋጠሙ ወቅት ይህ እውነት ጎልቶ ይታያል። ለዚህም ማሳያው አሁን ያለንበት እውነታ ነው።
ብዙዎች በአሸባሪው ህወሀት ከሀብት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ የሞቱ ቤተሰቦቻቸውን አስከሬን ሳይቀብሩም አካላቸው ጎሎ ነፍሴ አውጭኝ ያሉ ጥቂት አይደሉም። የወገኖቹ መጎዳትና መጎሳቆል ያሳሳበው ህዝብ ግን ከወደቁበት አንስቶ ቤቱን ጭምር በመስጠት አስጠልሎ ዛሬን እየኖሩ ነገን እንዲያልሙ አድርጓቸዋል።
ኢትዮጵያውያን ዘመንን የተሻገሩት፣ ችግርን ያለፉት በእነዚህ ምክንያቶችም ነው። የኢትዮጵያዊነት ባህላችን በስነ ቃላችን ሳይቀር ‹‹ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታል›› በሚል ተከትቦ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየውም ለዚህ ነው። ትውልዱም በዚህ እሴት እየተገነባ በመሄዱም በችግር ወቅት ሳይቀር አንዱ ለአንዱ ደራሽ እንዲሆን አድርጎታል።
ይህን ማህበራዊ እሴታችንን ለማጥፋት እንዳንችል ብዙ መርዝ ተረጭቶ እንደነበር ይታወሳል። መርዙም መቃቃሮችን ፈጥሮ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ‹‹አንተ አታስፈልገኝም፣ ውጣልኝ›› መባባሉ ከዚህ መርዝ የመነጨም እንደነበር ሁሉም ይረዳዋል። በተለይም አሸባሪው ህወሓት የህዝባችንን አብሮ የመኖር ዘመናት የተሻገረ እሴት ለማጥፋት የቱን ያህል በክፋት እንደተጓዘ ለመላው ህዝባችን የሚሰወር አይደለም።
ለዘመናት ተቻችለው፣ ተከባብረው ፣ ተጋብተውና ተዋልደው የኖሩ ህዝቦችን በከፋፋይ የጥፋት ትርክቶች ወደ ግጭት ለመውሰድ የሄደበት የሴራ መንገድ የቱን ያህል መርዘኛ እንደነበር ግልጽ ነው። በዚህም ሴራው ደግሞ ሀገርና ህዝብን ዋጋ አስከፍሏል። አሁንም በምንም ሊለካ የማይችል ዋጋ እያስከፈለው እንደሆነ ለመላው ህዝባችን የቆየ ትዝታ አይደለም። በቡድኑ የጥፋት ሴራ ብዙዎች ህይወታቸውን አጥተዋል ፣ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል ፣ ለስደትና ለአካል ጉዳተኝነትም ተዳርገዋል።
ቡድኑ በገዛ ሴራው ተጠልፎ በህዝብ አመጽ ከስልጣን ከተወገደ ማግስት ጀምሮም ቢሆን በስልጣን ተስፈኝነት መንፈስ በፈጠራቸው ግጭቶችም ሀገርና ህዝባችንን ብዙ ዋጋ አስከፍሏል። ይሁን እንጂ ለራሱ በፈጠረው የተዛባ የእብሪት ትርክት በለኮሰው እሳት እየተለበለበና እየተቃጠለ ይገኛል። ይህ የሆነው ደግሞ የቡድኑን የእብሪት ጉዞ ለመቀልበስ መላው ህዝባችን ከዳር አስከ ዳር ሆ ብሎ በመነሳት ችግር ውስጥ ገብቶ የነበረውን ሀገራዊ አንድነቱን ማደስና በአዲስ ታሪካዊ የአንድነት ምዕራፍ ውስጥ መገኘቱ ነው።
አሁን በጠላቶቻችን ያጋጠመን ተግዳሮት በህብረታችን እንዲፈታ ሁሉም የበኩሉን እያደረገ ነው። ይህ ሁኔታ ደግሞ አንድነት እንዲያብብ እድል ሰጥቷል። ህዝባችንንም ወደ ሀገራዊ ስጋት መፍታት ውስጥ እንዲገባ መርቶታል። ስለሀገሩ የሚጠበቀውን ሁሉ ለመክፈል እንዲዘጋጅና ከመቼውም ጊዜ ባላይ ከፍ ባለ መነሳሳት ውስጥ እንዲገባም አድርጎታል። ህይወቱን ጭምር ለሀገሩ ለመስጠት ቁርጠኛና ያለ ወትዋች ለአገሩ መከታ የሚሆን ወጣትም ፈጥሯል። በዚህም የተፈናቀሉ ወገኖቹን ከመርዳት ጀምሮ የጸጥታ ሃይሉን በስፋት እየተቀላቀለ ይገኛል።
መላው ህዝባችን በተባበረ ክንድ ቡድኑ በሀገር ላይ የፈጠረውን ጽልመት በመግፈፍ የፈነጠቀውን የተስፋ ብርሃን ለማጎልበትና እጣ ፈንታውን በተሻለ ብርሃን ውስጥ ለመምራት በቁርጠኝነት ተነስቶ እየተንቀሳቀሰ ነውም።
“የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ነው “ እንደሚባለው እኔ እብስ አንተ ተባብለን ሀገራችንን ከፍ ወዳለ ስፍራ ለማድረስ በቁጭት መንቀሳቀስ በሚገባን በዚህ ወቅት አሻባሪው ቡድን ከፍ ባለ ስግብግብነት በተቃኘው አስተሳሰቡ ለሀገር ጠንቅ ሆኗል። በገዛ ሀገሩና ወገኖቹ ላይ እያደረሰ ያለው ጥፋት ሆነ ሀገር የማፍረስ ሴራ እኛን ብቻ ሳይሆን ዓለምንም አስደንቋል። ነገር ግን አስተዋይ ህዝብ በመኖሩ ይህንን ሴራውን ለማክሸፍ ብዙ ነገሮች እያደረገ ነው። ለዚህም በዋናነት የሚጠቀሰው የፈጠረው አንድነት ሲሆን፤ ለጀመርነው የብልጽግና ጉዞ አልፋና ኦሜጋ እንዲሆን አቅጣጫን ያስተካክላል። ይህንን ደግሞ እንደምንኖረውም ይታመናል።
አሸባሪው ቡድን የፈጠረውን ሀገር የማፍረስ ስጋት የጀመርነውን አንድነት አጠናክረን መቀጠል ከቻልን ድባቅ እንደሚመታ እሙን ነው። ለዚህ ደግሞ ለሀገሩ በጎ ህሊና ያለው ዜጋ ያስፈልጋል። በሙሉ ባለው እውቀቱና አቅሙ የሚሰለፍ ሰውንም ይጠይቃል። ስለሆነም ይህንን አይነት ሰው የምንሆንበት ተገቢው ወቅት አሁን ነው።
ቡድኑ ላለፉት 40 ዓመታት የዘራውን የክፋት ዘር ወደ ሚቀጥለው ትውልድ በአስተሳሰብ ሆነ በተግባር እንዳይሸጋገር ሁሉም ዜጋ እራሱን ከተዘራው የክፋት ዘር የማጥራት ግለሰባዊ የዜግነት ግዴታ አለበት ። ዛሬ ላይ ያለን አንድነት ከዚህ በላይ ማበብ አለበት። በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ወደ ቀደመው የመተሳሰብ እና የመረዳዳት መንገዳችን ልንመለስ ይገባል። ይህ መንገዳችን ነው በተሻለ ጎዳና ወደ አሰብነው የብልጽግና ህይወት ሊወስደን የሚችለው።
ለዚህም ሁሉም ዜጋ በተሰጠው መክሊት በቁርጠኝነት ሊንቀሳቀስና ሊያገለግል ይገባል። ከያኒው በጥበባዊ ሥራው፣ ባለሀብቱ በገንዘቡ፣ ጉልበት አለኝ የሚለው ደግሞ በጉልበቱ እንዲሁም እውቀትና ሙያው ያለው በተሰማራበት መስክ በሃላፊነት መንፈስ አገሩን ካለችበት ችግር ማውጣት ይጠበቅበታል።
ኢትዮጵያዊነት ጽናት ነው። ለማሸነፍ መጓዝም ነው። ድል ሳይያዝ ወደኋላ የሚባል ነገር የለም። በዚህም አሁን እየተፈተነው ያለውን ፈተና በጽናታችን ተሻግረን ፍሬውን የምንቀምስበት ቀን ሩቅ አይሆንም።
አሁን በአሸባሪው ህወሓት የጥፋት ተግባር ደስታውን የተነጠቀ ፤ ከቤት ንብረቱ የተፈናቀለ ሁሉም በኢትዮጵያዊነቱ እየኮራ ቀዬው ላይ ሆኖ የአዲስ ብስራቱን ዜና በጆሮው እየሰማ ፤ በዓይኑ እያየ የሚያዜምበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። ሰላም!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መስከረም 18/2014