ኢትዮጵያውያን በወሳኝ የዘመቻ ወቅት ላይ ናቸው። ጀግኖች አባቶች ያስረከቧቸውን ነጻነቷ የተጠበቀ ሀገር ላለማስደፈር እጅ ለእጅ ተያይዘው ሀገራቸውን ከከሀዲዎችና ተላላኪ ባንዳዎች ለመታደግ “የሀገራቸውን ህልውና ለማስጠበቅ መቼም የትም በምንም “ በሚል ቁርጠኝነት ሆ ብለው እየተንቀሳቀሱ ናቸው ።
በተለይም በትውልዶች የመስዋእትነት ታሪክ ህያው ሆና ለኖረችው ሀገራችን ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በመሆን የህልውና ስጋት የሆነውን አሸባሪው ህወሓት ግብአተ መሬት ለመፈጸም እና ዘላቂ ሀገራዊ እፎይታ ለመፍጠር ዜጎች በአራቱም አቅጣጫ ለሀገር የክብር ሞት ለመሞት ወደ ግንባር በመትመም ላይ ይገኛሉ።
ቡድኑ ለ27 ዓመታት በኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመው ግፍ ፣ በሀገራዊ ለውጡ ዓመታትም መቀሌ በመመሸግ በተላላኪዎቹ አማካኝነት በመላ ሀገሪቱ ህጻን፣ ሴት፣ ሽማግሌ ሳይል ንጹሃን ዜጎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ያስጨፈጨፈበት እውነታ ፣ በሀገሪቱ የቁርጥ ቀን ባለውለታ በሰሜን እዝ ላይ የፈጸመው ክህደት የዜጎችን ልብ ክፉኛ ሰብሮታል።
“ጦርነት ባህላዊ ጨዋታዬ ነው፤ 80 በመቶ ያህሉን የሀገሪቱን የመከላኪያ አቅም በእጄ ይዣለሁ፤ በሚል ያልተገባ እብሪትና ክህደት ለያዥ ለገላጋይ አልመች ብሎ የነበረው ይህ አሸባሪ ቡድን በህግ ማስከበር ዘመቻው በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስ ጥ እብሪ ት ውድቀትን እንደምታስከትል በተጨባጭ መማር ችሏል ።
የተመሰረተበት የአስተሳሰብ መሰረቱ ከስህተቱ እንዳይማር ፍጹም ተግዳሮት የሆነበት ቡድኑ ከቀደመው ስህተቱ መማር አቅቶት በውሸትና ከዚህ በሚቀዳ ፕሮፖጋንዳ ይትግራይን ህዝብ ስቃይን እያረዘመው ሲሆን፣ በቀቢጸ ተስፋ በሚያካሂደው ከንቱ ጦርነትም የትግራይን ጨቅላዎች እየማገደ ይገኛል። እንደ እብድ ውሻ እየተክለፈለፈ በአማራና አፋር ክልል ወረራ በመፈጸም ንጹኃንን እየጨፈጨፈ፣ ሀብታቸውን እየዘረፈና እያወደመ ይገኛል።
በማይካድራ በንጹኃን ዜጎች ላይ የፈጸመው የጅምላ የዘር ጭፍጨፋ አልበቃህ ብሎት፤ በአጋምሳ፣ በጭናና በቆቦ በርካታ ንጹኃን ዜጎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሏል። በአፋር ክልል በጋሊ ኮማ በመጠለያ የሚገኙ ከአንድ መቶ በላይ ህጻናትን ጨምሮ ከሁለት መቶ ሃምሳ በላይ ንጹኃን ዜጎችን በከባድ መሳሪያ ጨፍጭፏል።
በቡድኑ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት የውጭ ወራሪ እንኳ ይፈጽመዋል ተብሎ የሚገመት አይደለም። እናቶች የወላድ ወግ ተከልክለው በጫካ እንዲወልዱ ግድ ሆኖባቸዋል። ህጻናት አዛውንቶችና እናቶች ከጥቃቱ ለማምለጥ ብዙ ተፈትነዋል። ልጃገረዶችና እናቶች በአሸባሪ ቡድኑ ጀሌዎች እናታቸው አባታቸው ፊት ተደፍረዋል።
አርሶ አደሩ እንደ አይን ብሌኑ የሚቆጥሯቸውን ከብቶች የቡድኑ አባላት እያረዱ በልተዋቸዋል፤ የዘረፏቸው፣ በጥይት ደብድበው የገደሏቸው ከብቶችም አያሌ ናቸው። በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማትና ሌሎች የመንግስት ተቋማት ተዘርፈው ወደ ትግራይ ተጭነዋል፤ የተቀረው ንብረታቸው ሰነዳቸው እንዲወድም ተደርጓል።
ይህን አረመኔያዊ ድርጊት በአደባባይ በጠራራ ጸሀይ እየፈጸመ የሚገኘው ይህ አሸባሪ ቡድን ፣ ከምእራባውያኑ እና ከታሪካዊ ጠላቶችችን በሚያገኘው ድጋፍና በሚደረግለት ጥብቅና ከድርጊቱ ከመቆጠብ ይልቅ በድርጊቱ ገፍቶበታል።
ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገር ልጅ የሰጡትን የተለያዩ እድሎች እና የሰላም አማራጮች ከአቅመቢስነት የመነጨ አድርጎ በመውሰድ የሄደበት የእብሪት መንገድ ከሱ አልፎ የትግራይ ወገኖቻችንን ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍሉ አድርጓል፤ እያደረገም ይገኛል።
ከዚህ የተነሳም ኢትዮጵያውያን የዚህን ቡድን ግብአተ መሬት ማፋጠን ለችግሮቻቸው ሁል አልፋና ኦሜጋ መሆንን በመረዳት በእልህ መንቀሳቀስ ከጀመሩ ውለው አድረዋል። ቡድኑን በሚገባው ቋንቋ በማናገር በእብሪት የዘራውን ፣ በብዙ መከራ እንዲያጭድ እያደረጉት ነው ።
ከቡድኑ ጋር የሚደረገው ጦርነት ፍትሀዊ በመሆኑ መላው ህዝባችን ለሰራዊቱ ጠንካራ ደጀን እየሆነ ይገኛል፤ ወጣቱም ሀገር ተረካቢ እንደመሆኑ መጠን ከአባቶች የተረከበውን ሀገር ለማስጠበቅ ከፍ ባለ የሀገር ፍቅር ስሜት መከላከያን ከመቀላቀል ባለፈ በየግንባሩ ተሰልፎ የጀግና ሞት እየሞተ ነው። እናቶች ልጆቻቸውን ስመው ወደ ማስልጠኛ እየላኩ ነው።
ህዝባችን ይህንን አሸባሪ ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አስወግዶ ፊቱን ወደ ልማትና ከልማት ወደሚገኝ ከፍታ ለማዞር የደረሰበት ውሳኔ ብቸኛው የችግሩ መፍቻ ቁልፍ እንደሆነ ይታመናል። ከፍጥረቱ ጀምሮ ሊገራ በማይችል የተበላሸ አስተሳሰብ ሀገርና ህዝብን ዋጋ ሲያስከፍል ለቆየው ቡድን ብዙ እድል ተሰጥቶታል፤ ከዚህ በላይ ሌላ እድል መስጠት የተበላሸ አስተሳሰቡን የመቀበልና የማበረታታት ያህል ይቆጠራልና ቡድኑን ለአንዴም ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ የግድ ነው።
አዲስ ዘመን መስከረም 18/2014