ኢትዮጵያ ስፖርትን ጨምሮ በበርካታ ጉዳዮች ፈር ቀዳጅ ሃገር መሆኗን ታሪክ ያሳያል።አህጉር አቀፍ የስፖርት ማህበራትን በመመስረትና መምራትም ስመ ጥር የሆኑ የስፖርት ባለውለታዎችንም መጥቀስ ይቻላል።ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ በአህጉር አቀፍ ደረጃ የነበራት መሪነትና የውክልና ስፍራ አሁን በእጅጉ የቀነሰ መሆኑ ግልጽ ነው።በእርግጥም በሃገር ውስጥ በስፖርቱ ያለው አደረጃጀትና ወጥ የሆነ አሰራር አለመኖሩ በዓለም አቀፍ ስፍራዎች ጎልቶ ለመውጣት ላለመቻሉ መነሻዎች መሆናቸው ይታያል።የዘርፉ ባለሙያዎች በዓለምና አህጉር አቀፍ የስፖርት ማህበራት እንዲሁም የስፖርት ተቋማት ጥረትና ተሳትፎ ማድረግ ለስፖርቱ እንዲሁም ለሃገር መልካም ገጽታ ግንባታ ተገቢ መሆኑንም ይመክራሉ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ጥቂት የስፖርቱ ሰዎች በአህጉር አቀፍ መድረኮች ላይ ስማቸው ሲጠቀስ እየተስተዋለ
ነው።ከሰሞኑም ሁለት ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች በአህጉር እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ቦታ ማግኘታቸው
ተሰምቷል።ሁለቱ ባለሙያዎች ዶክተር ድረስባቸው ኃይሌ እና አቶ ይርሳው ዘውዴ ሲሆኑ፤ የወከሉት ተቋም ደግሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የጸረ አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤትን ነው፡፡
ዶክተር ድረስባቸው ኃይሌ በዓለም አቀፉ የጸረ አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ (WADA) ውስጥ የቴክኒካል ኮሚቴ አባል ሲሆኑ፤ ቀደም ሲል ጀምሮ አባል በመሆን በብቃት እያገለገሉ ይገኛሉ።በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የፊዚዮሎጂ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ድረስባቸው፤ ለረጅም ዓመታት በስፖርት አበረታች መድሃኒት ዙሪያ ጥናቶችን በመስራት ይታወቃሉ፡፡
ኮሚቴው 10 አባላት ሲኖሩት አብዛኛዎቹ ከአሜሪካ፣ አውሮፓ እና አውስትራሊያ የተወጣጡ ናቸው።ዶክተር ድረስባቸው ደግሞ ከእነዚህ መካከል ብቸኛው አፍሪካዊ በመሆን በኮሚቴው ተካተዋል።በተቋሙ ካሉ ኮሚቴዎች መካከል አንዱ የሆነው ይህ ኮሚቴ፤ ከስፖርት አበረታች ቅመሞች ምርመራ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ በማስቀመጥ፣ በመምከርና አስተያየት በመስጠት ተሳታፊ ይሆናል።
ሌላኛው በአህጉር አቀፍ ደረጃ ውክልና ያገኙት ባለሙያ አቶ ይርሳው ዘውዴ የአፍሪካ የዳኝነት ፓናል (Africa Continental Result Management Panel) አባል ናቸው።የዚህ ፓናል አባላት የህግ እውቀት ያላቸው ባለሙያዎች ሲሆኑ፤ ፓናልም በአፍሪካ ደረጃ የሚፈጸሙ የስፖርት አበረታች ቅመሞች የህግ ጥሰቶችን በመመልከት ዳኝነት የሚሰጥ መሆኑን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡
ጽህፈት ቤቱ በአገር ውስጥ የስፖርት አበረታች ቅመሞችን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ ይሰራል።ከዚህ ተግባሩ በተጨማሪም በዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በንቃት በመሳተፍ፣ የበኩሉን ሚና ለመጫወት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ግንኙነቱንም ለማጠናከር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራም ይገኛል።በዚህም መሰረት በተቋሙ የሚያገለግሉ ባለሙያዎች በዓለም አቀፍ ተቋማት ውክልና እንዲያገኙ በተደረገው ጥረት ይህ ውጤት ሊገኝ መቻሉን የጽህፈት ቤቱ መረጃ
ይጠቁማል።በቀጣይም ይህንን ዓለም አቀፍ ተሳትፎ የማጎልበት ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥልም ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ የጸረ አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤት በድጋሚ ከተቋቋመ ጥቂት ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቋማዊ አቅሙን በማጎልበት እና የአሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋት ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የተሸጋገረ ተቋም
ነው።በዚህ ውስን ጊዜም ትምህርትና ስልጠና እንዲሁም ምርመራና ቁጥጥርን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ማከናወን ችሏል።በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር ተሞክሮ ሊሆኑ የሚችሉ ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል።በአትሌቲክስ ስፖርት ታዋቂ የሆነችው ኢትዮጵያም በአትሌቶቿ ውጤታማነት ምክንያት ከሚነሳበት ጥርጣሬ እንዲሁም በዓለም አቀፉ ተቋም ከተጣለባት ልዩ ትኩረት ነጻ ለመውጣትም ችላለች።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 17 ቀን 2014 ዓ.ም