በዓለም ታሪክ ውስጥ የረጅም ዘመን ታሪክ ባለቤት ከሆኑ ጥቂት ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ ነች። እንደ ሀገርም ከፍ ያሉ ስልጣኔዎች ባለቤት እንደነበረች የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ። የሀገራችንን ትላንታዊ መልክ ለማናውቅ ይሄ እውነታ ግር ሊለን ይችላል። እውነቱ ግን ዛሬም ወደፊትም እውነት ነው።
እኛ በታላቅ ምድር ላይ የተፈጠርን ታላቅ ህዝቦች ነን፡፡ በኩሩ፣በስልጡን እና በጀግና ማህጸን እቅፍ ውስጥ የበቀልን የዚህ ዓለም ጌጦች ነን፡፡ የሰው ልጅ መገኛ ምድር ልጆች ነን።
ኢትዮጵያዊነት የኩራት ምንጭ ነው፡፡ ከዘፍጥረት እስከ ትናንት እና አሁን ድረስ ብዙ ቦታ ላይ በማይታመን ትልቅነት ውስጥ የነበርን ነን፡፡ በየትኛውም መመዘኛ ብታዩት የሀገራችን የስልጣኔና የእውቀት ምህዳር በድሮነት ውስጥ አለ፡፡ አሁን ላይ በብዙ ነገራቸው የዓለምን የስልጣኔና የኢኮኖሚ በትር ይዘው የሀያልነት ማእረግ ያገኙ ሁሉ አንድ ወቅት ላይ ታሪክ ያልነበራቸው ከነጭራሹኑ ሀገር ለመባል ያልበቁ ነበሩ፡፡
በሌላ ቋንቋ ከእኛ ኋላ የተፈጠሩ፣ ከእኛ ኋላ ሀገር የሆኑ ናቸው እያልኳችሁ ነው፡፡ እኔና እናንተ በጥንት አባቶቻችን አጥንትና ደም ለዚች ዓለም የስልጣኔ ብርሃንን የለኮስን በኩራን ነበርን፡፡ የስልጣንና የአለቅነትን ጫንቃ የያዝን፤ የቅድመ ዓለም ፋና ወጊዎች ነበርን፡፡ በትልቅ ዓለም ላይ ትልቅነትን የከተብን በኩረ ዘፍጥረቶች ነበርን፡፡ በምንምነት ውስጥ አክሱምን ሰርተናል፡፡ በምንምነት ውስጥ ላሊበላን አንጸናል፡፡ በምንምነት ውስጥ ለሰው ልጅ እሳቤ የማይቻሉ ታላላቅ ገድሎችን ለብቻችን ተወጥተናል፡፡ ታዲያ ከዚህ በላይ ምን ትልቅነት አለ? ከዚህ በላይ ምን ፍጹምና ይገኛል? ትላንት ላይ ሁሉም ቦታ ነበርን፡፡
ትላንት ላይ ተዐምር የሰሩ እጆች የእኛ ነበሩ፡፡ ትላንት ላይ ከሁሉ የበረቱ ክንዶች የእኛ ነበሩ፡፡ በምንምነት ውስጥ ከምድር አልፈን ከህዋ አካላት ላይ ስልጣኔአችንን ያሳረፍን ታላቅ ህዝቦች ነበርን፡፡ ትልቅ ነበርን፡፡ ብዙዎች ያጨበጨቡልን ብዙዎች እኛን ለመሆን የሚመኙ የዛኛው ትውልድ ምልክቶች ነበርን፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ለብዙ ሀገራት የስልጣኔ ምንጭ ሆና የሰነበተች ቢሆንም ዛሬ ላይ ግን በብዙ ችግሮች ውስጥ የምትገኝ ሀገር ሆናለች፡፡ ከፊትና ከኋላዋ ብዙዎች የተነሱባት ጊዜ ላይ ነን፡፡ የጥንቱ የአባቶቻችን አንድነትና ህብረት ግድ የሚልበት ሰዓት ላይ እንገኛለን፡፡ በትላንት ውስጥ ያለችውን የአባቶቻችንን ኢትዮጵያ ዳግም ለመፍጠር የአሁኑ ትውልድ ምን እየሰራ እንደሆነ ማጤን ይገባዋል፡፡
የትላንትናዋ ኢትዮጵያ ዝም ብላ የተፈጠረች፣ ዝም ብላ ስልጣኔን ያገኘች ሳይሆን በአባቶቻችን የአንድነት ክንድ፣ የህብረት እሳቤ የተፈጠረች ናት፡፡ ዛሬ ላይ ትልቅ ነበርን ብለን አፋችንን ሞልተን በኩራት የምንናገረው ትልቅ ሀገር ባስረከቡን አባቶቻችን ብርታት ነው፡፡ ብኩርናችንን ይዘን እንቆይ ዘንድ እኛ የዛሬው ትውልድ የአባቶቻችንን እውነት መከተል ይኖርብናል፡፡
የአባቶቻችን እውነት ምን ነበር? የአባቶቹ እውነት የገባው ወጣት ዛሬ ላይ ታሪክ ከማውራት ወጥቶ ታሪክ እንደሚሰራ አልጠራጠርም፡፡ የአባቶቹን እውነት የተረዳ ትውልድ ዛሬ ላይ ለልጆቹ የምትሆንን ሰላማዊ ሀገር ለመፍጠር አቅም ያንሰዋል ብዬ አላስብም፡፡ የአባቶቻችን እውነት አንድነት ነበር፡፡ የአባቶቻችን እውነት ፍቅር ሰላም ነበር፡፡ የአባቶቻችን እውነት መተሳሰብ ነበር፡፡
የአባቶቻችን እውነት ፈርሀ እግዚአብሔር ነበር፡፡ የአባቶቻችን እውነት ኢትዮጵያዊነት ነበር፡፡ የእኛስ እውነት ምንድነው? ዛሬ ላይ እንደ ህይወት መርህ የምንከተለው እውነታችን ምን ይሆን? የምንማረው፣ የምንሰራው፣ አግብተን የምንወልደው ለምንድነው? ወጣት የሆነው፣ እንደ ዜጋ የምንጠራው ለምንድነው? የተፈጠርነው፣ ሰው የሆነው ለምንድነው? ይሄን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ ያስፈልጋል፡፡
ለዓለም ስልጣኔን ያስተማረች፣ የብርሃን ችቦ ሆና ለሰው ዘር ሁሉ የበራች ሀገር ዛሬ በህዝቦቿ አንድነት ማጣት ልዕልናዋን ስትነጠቅ ማየት ያማል፡፡ የትላንት አባቶቻችን ባልሰለጠነ ዓለም በባዶ እግራቸው እየሄዱ ነው ታላቅነትን የሰጡን፡፡ ግን ፍቅርን ያውቁ ነበር፡፡ ከሁሉም ትልቁን እግዚአብሔርን ይፈሩ ነበር፡፡
እኛ የዛሬዎቹ የአባቶቻችን የቀና መንገድ እያለ ክፋት በዋጀው በሌሎች መንገድ የምንሄድ ነን፡፡ ልባችንን ከፍቅር፣ እጃችንን ከስራ አቀያይመን በትችትና በወቀሳ የቆምን ነን፡፡ እውነት ነው ትልቅ ነበርን ትልቅ የሆነው ግን ተለያይተን ስለቆምን በዘርና በብሄር ስለተከፋፈልን አይደለም፡፡
የትልቅነታችን ምንጭ አንድነታችን ነበር፡፡ የትልቅነታችን መሰረት ህዝባዊነት ነበር፡፡ የአባቶቻችንን ሀቅ እንውረስ ስል እማጸናችኋለሁ፡፡ አሁን ካለንበት ክፉ ሀገራዊ መልክ እንወጣ ዘንድ፣ አሁን ካለንበት ድህነትና ኋላ ቀርነት እንወጣ ዘንድ በጽድቅና የሚኖሩትን የአባቶቻችንን ነፍስ መጋራት ይኖርብናል፡፡ የአባቶቻችን የትላንት መልክ በእኛ በልጆቻቸው ላይ መመለስ አለበት፡፡
ጣሊያንን ያንበረከኩ የትላንት ጥምር እጆች ዛሬም ያስፈልጉናል፡፡ ግብጽና እንግሊዝን ያንበረከኩ የህብረት ክንዶች ያስፈልጉና፡፡ ድልን የሚጽፉ፣ ብስራት የሚናገሩ አንደበቶች እንሻለን፡፡ በዓለም አደባባይ ያጀገኑን፣ ስማችንን በወርቅ ቀለም ያጻፉ ትላትናዊ ብዙ መልኮች አሉን፡፡ እኚህ ሀበሻዊ መልኮች ዛሬም ያስፈልጉና፡፡ ሊወሩን ባኮበኮቡ፣ አንድነታችንን ጠልተው ጥርሳቸውን በነከሱንን ጠላቶቻችን ላይ መደገም አለብን፡፡
የነገ ትልቅነታችን ያለው በዛሬአችን ውስጥ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ለነገ ስንቅ የሚሆኑ መልካም ተግባራትን በመከወን ራሳችንን ለትልቅነት ማዘጋጀት ይኖርብናል፡፡ ነገ ለምንናፍቀው ሀገራዊ ልዕልና ስንል ዛሬን በዋጋ መኖር ግድ ይለናል፡፡ ትልቅ ነበርን እያልን ታሪክ ከማውራት ወጥተን ታሪክ ወደ መስራት መሸጋገር የዛሬው ትውልድ የቤት ስራ መሆን አለበት፡፡ ከትላንት እስከዛሬ ታሪክ ስናወራ ገድል ስንዘክር ኖረናል አሁን ግን ታሪክ ወደ መስራት የምንሸጋገርበት የድርሻችንን የምንወጣበት ምቹ ጊዜ ላይ ነን፡፡
ልጆቻችን የአያቶቻቸውን ሳይሆን የእኛን የአባቶቻቸውን ታሪክ መስማት ይፈልጋሉ፡፡ እኛ በአባቶቻችን እንደኮራን ሁሉ ልጆቻችንም በእኛ የሚኩሩበትን ታላቅ እና ደማቅ ህዝባዊ ታሪክ መጻፍ አለብን፡፡ ታሪካችን ደግሞ ከአሁን የሚጀምር ነው፡፡ ታሪካችን ደግሞ በስራ፣ በተግባር የሚገለጽ ነው፡፡ ታሪክ ለመጻፍ ጦርና መሳሪያ መታጠቅ አይጠበቅብንም፡፡ ታሪክ ለመስራት ስልጣንና አለቅነት ግድ አይለንም፡፡ ታሪክ ለመጻፍ ጦር ሜዳ ዘምተን ከጠላት ጋር ተዋግተን መሞትና መግደል አይኖርብንም፡፡
ታሪክ በብዙ መንገድ ይሰራል፡፡ ተማሪ የሆነ በትምህርቱ ጥሩ ውጤት በማምጣት ሀገርና ህዝቡን በታማኝነት በማገልገል ታሪክ መስራት ይችላል፡፡ መምህሩ ሀገር ተረካቢ የሆኑ ታማኝና አስፈላጊ ተማሪዎችን በማውጣት የድርሻውን መወጣት ይችላል፡፡ ታሪክ ለመስራት ጊዜ አንጠብቅ፡፡ ለራሳችን ሆነ ለሀገራችሁ ታሪክ ለመስራት ትክክለኛ ጊዜ ላይ ነን፡፡ ባለንበት ሁኔታ፣ በምንኖርበት ቦታ ላይ ሆነን ለሀገራችን መልካሙን በማድረግ፣ መልካሙን በማሰብ የዜግነት ግዴታችንን በመወጣት ታሪክ መጻፍ እንችላለን፡፡
ሀላፊነት እንደሚሰማው ዜጋ ለሀገራችን ምርጡን የማድረግ ግዴታ አለብን፡፡ ከፊታችን ብርሃንና ጨለማ የቀላቀለ ድንግዝግዘ መልክ አለ፡፡ ከፊታችን እየበራ የሚከስም እየከሰመ የሚበራ ቅይጥ ብርሃን አለ፡፡ በእኔና በእናንተ የተሳለ ጉራማይሌ መልክም ከፊታችን አለ፡፡ ሁሉም የሚጠራው ሁሉም የሚስተካከለው በእኛ ነው፡፡
ምርጧ ኢትዮጵያ በምርጥ ሀሳባችን ውስጥ ናት፡፡ ምርጧን ኢትዮጵያ በምርጥ ሀሳባችን እንፍጠር፡፡ ብዙዎቻችን ጥሩ ነገርን ከሌላ የምንጠብቅ ነን፡፡ ጥሩ ሀገር ስልጡን ማህበረሰብ እንዲኖረን እንሻለን፡፡ ሰላሟ የበዛ በሁሉ ነገሯ የተረጋጋች ሀገር እንድትኖረን እንፈልጋለን፡፡ ከድህነት የወጣ በቀን ሶስቴ የሚበላ ህዝብ እንዲኖረን ምኞታችን ነው፡፡ ግን አንሰራም፣ ግን ለምንፈልገው ነገር ስንለፋ አንታይም፡፡ የምንፈልገውን ጥሩ ነገር ሁሉ ከሌሎች የምንጠብቅ ነን፡፡
ሳንሰራ ለውጥ የምንፈልግ፡፡ ሳንደክም ሳንለፋ ህልማችንን የምንጠብቅ ነን፡፡ ይሄ ሞኝነት ነው፡፡ ለዛሬ መጠሪያ የሆነችው የአባቶቻችን ኢትዮጵያ በድካማቸው እንደተፈጠረች ሁሉ የእኛም ኢትዮጵያ በእኛ ድካም የምትፈጠር ናት፡፡ ጥሩ ነገራችንን ድካማችን ውስጥ እንፈልግ፡፡ ለምንም ነገር አቅም ያለን ህዝቦች
ነን፡፡ ድህነት ኋላ ቀርነት ምን ማለት እንደሆነ በደንብ እናውቃለን፡፡ ችግርና ማጣትን እናውቀዋለን፡፡ ከዚህ በኋላ ግን በዚህ ክብረ ነክ ህይወት ውስጥ መኖር አይኖርብንም፡፡ የተሻለ ህይወትን ፍለጋ መስራት ማሰብ ይኖርብናል፡፡ በአባቶቻችን እውነት ላይ መራመድ ግድ ይለናል፡፡ በአንድነት በመቆም ጠላቶቻችንን ማሳፈር እንድትፈጠር ለምንፈልጋት ኢትዮጵያ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው፡፡
ሁላችንም የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ ለመሳል ብዕራችንን እናንሳ ፡፡ እውቀታችንን እንጠቀም፡፡ በሀሳብ የበላይነት እንመን፡፡ የአባቶቻችንን ታላቋን ዳግማዊ ምድር ለመፍጠር ከዝምታ ወጥታችሁ መናገር መቻል አለባችሁ፡፡ የበይ ተመልካች ከመሆን አልፈን እኔም ያገባኛል ስንል ለውይይት ለንግግር በራችንን ክፍት እናድርግ፡፡ እመኑኝ ይሄን ካደረግን ታላቋ ኢትዮጵያ ትፈጠራለች፡፡
ቆሞ ከማየትና ያልሆነ ወሬ እያወሩ ህዝብ ከማደናገር የድርሻችንን አንድ እንጨት በማዋጣት ኢትዮጵያን መስራት እንችላለን፡፡ ብዙዎች በተገነባ ሀገር እየኖሩ የእኛን ሀገር ለማፍረስ ቀን ከሌት የሚለፉ ናቸው፡፡ የእኛን ተለያይቶ መቆም የእኛን መነካከስ የሚፈልጉ እዛም እዚህም አሉ፡፡ እኚህን ሀገራት እኚህን ግለሰቦች የምናሸንፈው ለአንድ አላማ በአንድ ስንቆም ብቻ ነው፡፡
ወደሚጠቅመን መሄዱ ያዋጣናል፡፡ የሚጠቅመን ልዩነታችንን ትተን አንድ ሀገርና አንድ ህዝብ መፍጠር ነው፡፡ የሚጠቅመን ያለ ልዩነት የኖሩትን አባቶቻችንን መምሰል ነው፡፡ የሚጠቅመን ከጥላቻና ከመለያየት ወጥቶ ወደሚደነቅ ሀገራዊ ልማት መሄድ ነው፡፡ ከማንም በፊት ህዝብ ነበርን፡፡ ከማንም በፊት ሀገር ነበርን፡፡ ከማንም በፊት ስልጡን ማህበረሰብ ነበርን፡፡ ከማንም በፊት የስልጣንና የጀግንነት መሰረቶች ነበርን፡፡ ይህም ትልቅ እንድንሆን አስችሎን ነበርን፡፡ አሁን ደግሞ ከምንምነት ተነስተን ትልቅ የምንሆንበት ሌላ ዘመን ላይ ነን፡፡
እመኑኝ ትልቅ እንሆናለን፡፡ ትልቅ የምንሆነው ግን ውስጣችን የተዘራውን፣ ተዘርቶም የበቀለውን፣ በቅሎም መቶና ስልሳ ያፈራውን እኩይ የጥላቻና የመለያየት የሞት በለስ ነቅለን ስንጥል ነው፡፡ ባላየንውና ባልሰማንው በማናውቀውም ታሪክ መባላት ትተን በሰለጠነ አእምሮ ሀገር የሚጠቅሙ የጋራ እውነቶችን ስንገነባ ነው፡፡ የአባቶቻችን ኢትዮጵያ የተገነባችው በአንድነት ላይ ነው፡፡
የአባቶቻችን ታሪክና ስልጣኔ ዘመን የተሻገረው በአንድ አላማ በቆሙ ልቦች ነው፡፡ የእኛም ኢትዮጵያ ከዚህ ውስጥ የምትወጣ ናት፡፡ ኢትዮጵያችንን በንጹህ ልባችን፣ በንጹህ ነፍሳችን እና በንጹህ ሀሳባችን ውስጥ ዳግም ታፈራለች፡፡ ይሄ ትውልድ በአንድነት ከተነሳ የአባቶቹን እውነት መድገም የሚችል ነው፡፡ በአንድነት ከቆመ ዳግማዊ ዓድዋን የሚፈጥር ነው፡፡ ኢትዮጵያን ለመስራት ጊዜው የእኛ ነው፡፡ ለነጋችን ዋስትና የሚሆን መልካም ነገር እንስራ እንጂ የሚጸጽተንና የሚያስቆጨንን አንስራ ፡፡
በዙሪያዬ ያሉ ልክ እንዲሆኑ እኔ ልክ መሆን አለብኝ፡፡ የእኔ ልክ ሆኖ መቆም ለአዲሷ ኢትዮጵያ ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ የእያንዳንዳችን ወቅታዊ ሁኔታ አዲስ ለምንፈጥረው ሀገርና ህዝብ የላቀ ዋጋ አለው። ከጥፋትና ከስህተት ርቀን ራሳችንን ልክ በሆነ ቦታ ላይ እናቁም፡፡ ያኔ የሁላችን ኢትዮጵያ በሁላችን ልክነት ውስጥ ትፈጠራለች፡፡ ያኔ እንደ አባቶቻችን ትልቅ እንሆናለን፡፡ ያኔ የብርሃን ዘመን ይሆንልናል፡፡ አበቃሁ ቸር ሰንብቱ፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 17 ቀን 2014 ዓ.ም