ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ኃያል ሀገር የመሆን እድልን ከተቀዳጁት ሀገራት መካከል አንዷና ቀዳሚዋ አሜሪካ ነች። የአሜሪካ የመንግስት ባለሥልጣናት፣ ሴናተሮች፣ ምሁራን እና የፖለቲካ ተንታኞች በጋራ መክረው ያስቀመጧቸው አምስት ወሳኝ የአሜሪካ ብሄራዊ ፍላጎቶች (America’s National Interests) እንዳሉ መረጃዎች ያመላክታሉ።
ከእነዚህም ውስጥ የመጀመሪያው በዩናይትድ ስቴትስ ወይም የአጋር ሀገራት ወታደራዊ ኃይሎቹ ላይ የኑክሌር፣ የባዮሎጂ እና የኬሚካል የጦር መሣሪያ ጥቃቶችን መከላከል፣ ማገድ እና መቀነስ የመጀመሪያው ነው። ሁለተኛው አሜሪካ ማደግ የምትችልበትን ዓለም አቀፍ ስርዓት በመቅረፅ ሀገራት አጋር መሆናቸውንና ተባባሪነታቸውን ማረጋገጥ ነው። በሶስተኛ ደረጃ የተቀመጠው በዩናይትድ ስቴትስ ድንበሮች አካባቢ በጠላትነት የሚተያዩ ታላላቅ ኃይሎች እንዳይፈጠሩ መከላከል ሲሆን አራተኛው ደግሞ ዋና ዋና የአለም አቀፍ ስርዓቶችን (የንግድ፣ የገንዘብ ልውውጦችን፣ የኃይል አቅርቦት፣ እና የአካባቢ ጥበቃ) ተግባራዊነትና እና ዘላቂነትን ማረጋገጥ የሚለው ነው። በአምስተኛ ደረጃ ከአሜሪካ ብሔራዊ ፍላጎቶች ጋር ስትራቴጂካዊ ተቀናቃኝ ሊሆኑ ከሚችሉ አገሮች፣ ቻይና እና ሩሲያ ጋር ውጤታማ ግንኙነቶችን መመስረት የሚለውም እንደዚሁ የአሜሪካ ብሄራዊ ፍላጎት ሆኖ ተቀምጧል።
እነዚህ ብሄራዊ ፍላጎቶች በግልፅ ይቀመጡ እንጅ ብዙ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚስማሙበት የአሜሪካ ብሔራዊ ፍላጎት ውስብስብ ጥያቄዎችን ያካተተ ነው። ለምሳሌ አሜሪካውያን ብሔራዊ ፍላጎቶቻቸውን በተመለከተ ሊያስቡባቸው ከሚገቡት ጉዳዮች ቀዳሚው እንደ ቦስኒያ፣ ሩዋንዳና ሜክሲኮ ያሉ አገሮች ከሩሲያ፣ ቻይና ወይም ፋርስ ባሕረ ሰላጤ ጋር ሲወዳደሩ ምን ያህል ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ፤ ትኩረት በሚሹ አካባቢዎች ችግሩን በመፍታት ፍላጎታቸውን ለመጠቀም ምን ያህል ገንዘብ ማውጣት እንደሚኖርባቸው በሚስጥር የተያዘ ነው።
በመካከለኛው ምስራቅም እንደ የመን ባሉ ሀገሮች እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ሩዋንዳና ሶማሊያ ውስጥ የተከሰቱ የእርስ በርስ ጦርነቶች ሁሉ ከጀርባ ፈጣሪና አድራጊ በመሆን የምትታማው አሜሪካ እንደሆነች በግጭቶቹ ዙሪያ ይፋ የተደረጉ መረጃዎች ያመላክታሉ።
በኢትዮጵያም በአሸባሪው ህወሓት ሲመራ የነበረው መንግስት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ከስልጣን ከተወገደ በኋላ በርካታ ግጭቶች ተካሂደዋል። እንደ ህወሓት እና ሸኔ ያሉ ጽንፈኛ የሽብር ቡድኖች መፈጠርና ከኢትዮጵያ አልፎ የአካባቢውን ሰላም በማወክ፤ በሀገሪቷ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር የሚጥሩ ሃይሎችን ፋይናንስ በማድረግ የሚደረግ ጥረት እንደነበረም ይነገራል።
አሜሪካ በምስራቅ አፍሪካ ላይ የምታንፀባርቀው አቋም “ለጥቅሜ ስጋት” በሚል የሚገለፅ ሲሆን፤ ፈረንሳይና እንግሊዝም የቀይ ባህር ቀጠና ጂኦፖለቲካን ከሚዘውሩት ተርታ ይመደባሉ። የቀጠናው ዋነኞቹ ተዋናዮች ኢትዮጵያ፤ ኤርትራ፤ ሱዳን፤ ሱማሊያ እና ጅቡቲ በአንድ እንዳይሰባሰቡ፤ እርስ በርስ በጥርጣሬ እንዲተያዩና በጦርነት እንዲታመሱ በማድረግ ብሄራዊ ጥቅማቸውን የሚያስጠብቁት ሃያል ሀገራት የምስራቅ አፍሪካን የትርምስ ቀጠና ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ አለ ማለት አይቻልም። ይህ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአካባቢው እየተፈጠረ ያለው ጦርነትና የጂኦፖለቲካ ቀውስ ምንጩ ከየት እንደሆነ ከአጠቃላይ ሂደቱ መረዳት ይቻላል።
አሜሪካ ጥቅም አለኝ ወይም ጥቅም አገኝበታለሁ ብላ እስካሰበች ድረስ በሀገሮች ላይ ለሚደርሰው መመሰቃቀል ብሎም ለዜጎቻቸው ሞት፣ መፈናቀልና ስደት ደንታ እብደሌላት ከታሪኳ መረዳት ይቻላል። በ”ውጪ ጉዳይ ፖሊሲ”ው የሚመካው የአሜሪካ መንግስት የአገሪቱን ጥቅም የሚነካ ተፃራሪ ኃይል በማንኛውም ሁኔታ ሲያቆጠቁጥ በተለያዩ ማዕቀቦች እንዲሽመደመድ በማድረግ፣ በድህነት እንዲማቅቅ በማድረግ በእነሱ መዳፍ ውስጥ እንዲገባ ማድረግን እስከዛሬ ይዘውት የዘለቁት የፖለቲካ ሴራቸው ነው፡፡
አሜሪካ ይህን ሁሉ ስታደርግ ብሄራዊ ጥቅሜን እያጠኑ ያቀርቡልኛል የምትላቸውን ሎቢስቶች በመቅጠር ሲሆን የሎቢስቶቹ ሚና በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ አሁንም አከራካሪ ሆኖ የዘለቀ ነው።
በአሜሪካ የሚስተዋለው የፖለቲካ ሁኔታ እንደሚያሳየው በሀገራት ላይ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች፣ ኩባንያዎች፣ ለትርፍ ባልተቋቋሙ ድርጅቶች ውስጥ ሎቢስቶች እንዲቀጠሩ በማድረግ በተመረጡ የመንግስት ባለስልጣናት ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር እንዲሰሩ ይደረጋሉ። በሀገሪቱ በፌዴራል ደረጃ የተመዘገቡ 9ሺህ 500 ሎቢስቶች ያሉ ሲሆን፣ ለእያንዳንዱ የተወካዮች ምክር ቤት እና የአሜሪካ ሴኔት አባል 18 ሎቢስቶች አሉ ማለት ነው። ለዚሁ ስራ ማስኬጃም በየዓመቱ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ በጀት ይመደባል።
አሜሪካ በኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካ ጣልቃ በመግባት አንዴ በኢትየጵያ ያለው አለመረጋጋት ለብሄራዊ ጥቅሜ ያሳስበኛል ስትል ፤ በሌላ መልኩ የኢትዮጵያን ልኡላዊነት በመዳፈር በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ላይ የቪዛ፣ የኢኮኖሚና የፀጥታ ድጋፍ ማዕቀብ የመጣል ውሳኔ እስከማሳለፍ ስትደርስ ይስተዋላል።
ይህም ጫና እየበረታ የመጣው በሎቢስቶቹ አማካኝነት እነ አንቶንዮ ብሊንከን፤ ሳማንታ ፓወር፣ ሱሳን ራይዝ፣ ሱሊቫኒንና የመሳሰሉ የባይደን አስተዳደር አማካሪዎች እንደ አሸባሪው ህወሓት ካሉ አጋሮቻቸው ጥቅም አንፃር የተቃኘ፤ አደገኛና አድሏዊ ውሳኔ እንዲሰጥ በሚሸርቡት ሴራ እንደሆነ በተለያዩ ጊዜያት ከሰጧቸው ማብራሪያዎች መረዳት ይቻላል፡፡
የሽብር ቡድኑ ሀገር በታኝ የፖለቲካ አጀንዳ ቀርጸው የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት ሲወጉ፤ በማይካድራ፣ በጭቅና፣ በቆቦ ሰላማዊ ዜጎችን በጅምላ ሲጨፈጭፍ እያዩ እንዳላዩ ሆነው አልፈውታል፡፡ ማዕቀብ መጣል ቀርቶ ድርጊቱን ለማውገዝ እንኳን አንደበታቸው ሲፈታ አልታየም። ይህም የሆነው አሸባሪው ቡድን የውክልና ጦርነት ለማካሄድ የሚያግዛቸው ታማኝ ተላላኪያቸው በመሆኑ፤ እንዲሁም፣ በአፍሪካ ቀንድ የጂኦፖለቲካ አሰላለፍ ውስጥ የኢትጵያን ተፅዕኖ ፈጣሪነት ለማዳከም በማሰብ እንደሆነ ግልፅ ነው።
በአጠቃላይ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገው ይሉኝታቢስ ጣልቃ ገብነት ሀገር የማፍረስ ግብ ያለው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በኢራቅ፣ በሶማሊያ፣ በአፍጋኒስታን፣ በየመን፣ በሊቢያ ወዘተ የፈጸመችውን ማየቱ ብቻ በቂ ማሳያ ነው፡፡ በመሆኑም ወደ መፍትሄው ስንመጣ የኢትየጵያ አባት አርበኞች ከውጭ ወራሪ ጋር አፈሙዝ ለአፈሙዝ ተዋግተው የሀገር ሉዓላዊነትን አስጠብቀው እንዳቆዩልን ሁሉ በአሁኑ ወቅትም ይህ ትውልድ እንደ አሜሪካ ያሉ የአንድን ሀገር ሉዓላዊነት የሚዳፈሩ የውስጥና የውጭ ሃይሎችን በጋራ መታገል ይኖርበታል።
ዘላለም ግርማ
አዲስ ዘመን መስከረም 17 ቀን 2014 ዓ.ም