ባንዳነት በሀገርና በህዝብ ላይ የሚደረግ የክህደት ተግባርና ከፍ ያለ መንጀልም ነው። ከራስ ወዳድነት እና ገደብ አልባ ከሆነ የስግብግብነት ፍላጎት የሚመነጭ፣ በህዝብና በሀገር ጥቅም የሚወራረድ ከፍ ያለ ክህደት ነው፡፡ በታሪክም ብዙ ሀገራትን ዋጋ ያስከፈለ እስከዛሬም እያስከፈለ ያለ ማህበራዊ እርግማን ነው።
ለግልና ለቡድን ጥቅም ሲባል ሕዝብንና ሀገርን ዋጋ የሚያስከፍለው ይህ ማህበራዊ ርግማን በኛም ሀገር በተለያዩ ወቅቶች ተከስቶ ሀገርን እንደ ሀገር ዋጋ ያስከፈለንና ዛሬም በዚህም ትውልድ ውስጥ ተከስቶ ዋጋ እያስከፈለን የሚገኝ ነቀርሳ የሆነ ያልተሻገርነው ሀገራዊ ችግር ነው።
ባንዳነት በመሰረቱ ከአስተሳሰብ ስንኩልነት የሚመነጭ፤ ከፍ ካለ ራስ ወዳድነት የሚቀዳ፤ ከተዛባ አስተዳደግ የሚወረስ እና ማንነት የሚሆን፣ ጤነኛ አእምሮን ማበላሸት የሚያስችል አቅም ያለው ማህበረሰባዊ ችግር ነው። አንዴ የችግሩ ሰለባ የሆነን አዕምሮን መመለስም ቀላል አይደለም።
ከቅርቡ ታሪካችን ብንጀምር እንኳን አባቶቻችን ከፋሽስቶች ጋር ስለ ነጻነት ባደረጉት መራራ ትግል ወቅት በብዙ የተፈተኑትና ከፍ ያለ ዋጋ እንዲከፍሉ ያስገደዳቸው የባንዳዎች የባንዳነት ተልዕኮና ተልዕኮው የፈጠረው ተግዳሮት እንደሆነ የታሪክ ማህደራት ይመሰክራሉ።
ስለ ሀገር እና ነጻነት ግድ የሌላቸው ባንዳዎች ለጠላት ኃይል የወገንን መረጃ ከመስጠት ጀምሮ ፣ ለጠላት መንገድ መሪ በመሆን ፣ ከዚህም በላይ በየአውደ ግንባሮች መሳሪያ ታጥቀው የወገንን ሀይል በመውጋት ታሪክ የማይዘነጋው ክህደት ፈጽመዋል። የሕዝብን የነጻነት መሻት ስነ ልቦና ለመስበር የሄዱበትም ርቀት የቱን ያህል ህሊና አልባ እንደነበሩ አመላክቶ አልፏል።
ገደብ ከሌለው ራስ ወዳድነት የሚመነጨው ይህ ሀገራዊ ችግር ዛሬም እንደ ሀገር ክፍ ያሉ ሀገራዊ ራዕዮችን ሰንቀን በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ በምንገኝበትም ወቅት ዋናው የመንገዳችን ተግዳሮት ሆኖ ከፊታችን ቆሟል። ወደ ከፍታ ለምናደርገው ጉዞም ከትናንቱ በከፋ መንገድ የመንገድ ላይ እንቅፋት ሆኗል።
እንደ ሀገር የጀመርነው ሀገርን የማበልጸግ ራዕይ ከግለሰብ ሆነ ከቡድኖች መሻት ከፍ ያለ የትውልዶችን ዕጣ ፈንታ የሚቀይር፣ ትውልዶች በዘመናት መካከል ሲያስቡትና ሲመኙት የቆዩ፣ አንድ ቀን ይከናወናል በሚል ተስፋ አሻግረው እያዩት የተሰናበቱት እውነታ ነው።
ከጅምሩ አንስቶ ይህ ሀገርን የማበልጸግ፤ ከፍ ባለ ማማ ላይ የማስቀመጥ የመነሳሳት ራዕያችን ከማንም በላይ በዘመናት መካከል ይህ ተስፋችን እውን እንዳይሆን በግልጽና በስውር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሀይሎችን በከፍተኛ ደረጃ እንዳስደነገጣችው ይታመናል። ድንጋጤው ነፍስ ዘርቶም ግልጽ ወደ ሆነ ጠላትነት እንዳሸጋገራቸው የአደባባይ ሚስጥር ከሆነ ሰንብቷል።
እነዚህ ኃይሎች በአንድ በኩል በራሳቸው አቅም የተጀመረውን ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞ ማሰናከል የሚያስችሉ አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ሴራዎችን በመሸረብ ወደ ተግባር ገብተዋል። በተለይም ግብጽ በሀገሪቱ የሚታየውን የመልማት እና የመበልጸግ መነቃቃት ለማቀዛቀዝ ከተቻለም ለመግደል ሰፊ ዘመቻ ውስጥ ከገባች ውላ አድራለች።
ሀገሪቱ በተፈጥሮ ሀብቷ የመጠቀም፤በሀብቷ የመልማት ተፈጥሯዊ መብቷን እንዳትጠቀም ለማድረግ ፤በተለይም የዓባይ ውሀ ላይ አለኝ የምትለውን ኢፍትሀዊ የመጠቀም መብት ለማስቀጠል ሁሉንም አማራጮች እየሞከረች ትገኛለች። ዓለም አቀፍ እና አካባባዊ ተቋማትን ከጎኗ ከማሰለፍ አንስቶ ሀገራትን በጉዳዩ ጣልቃ ለማስገባት ተኝታ ያደረችበት ቀን የለም።
ከዚህ ጎን ለጎንም ሀገራዊ ለውጡን በበጎ ጎኑ ማየት ያልፈለጉ፤ ለውጡ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ጥቅማችንን ይጎዳዋል ከሚሉ ሀገራትና ዓለም አቀፍ የቢዝነስ ተቋማት ጋር ሕብረት በመፍጠር ለውጡን ለመቀልበስ የተቀናጀ የሴራ ተግባራትን አከናውናለች፤ እያከናወነችም ትገኛለች።
ከዚህ በከፋ መልኩም በሀገር ውስጥ በአንድም ይሁን በሌላ ከማዕከላዊ መንግስት ያፈነገጡ ሀይሎችን በባንዳነት በማሰለፍ አጠቃላይ የሆነውን የመልማትና መበልጸግ መነሳሳት ለመግደል ሌላ የጦርነት ግንባር ፈጥራ እየሰራች ነው። በባንዳነትም አሻባሪው ህውሓትንና ሸኔን ጨምሮ ሌሎች ኃይሎችን አሰልፋለች።
እነዚህ ኃይሎች የሀገርን እና የቀጣይ ትውልዶችን እጣ ፈንታ አደጋ ውስጥ የሚከት፣ ብዙ ትውልዶች አይተውት በተስፋ የተሳናበቱትን የብልጽግና ጉዞ ከቡድን ጥቅም በማሳነስ እንደቀደሙት ዘመናት የዘመኑ ባንዳ በመሆን ሀገርን እስከማፍረስ የሚደርሰውን የጠላቶቻችንን ፍላጎት ለማሳካት እንወክለዋለን በሚሉት ህዝብ ስም እየተንሳቀሱ ነው ።
እነዚህ የዘመኑ ባንዳዎች ከቀደሙት ባንዳዎች የሚለዩት ፣ የቀደሙት ባንዳዎች በሀገር ነጻነት ሲቆምሩ ፤እነዚህ ደግሞ እንደ ሀገር በሀገር ላይ የሚቆምሩ ፤ለፍላጎታቸው መሳካት ሀገርን መስዋዕት እድርገው እስከመሄድ የደረሱና ምንም አይነት የሞራል ስብዕና የሌላቸው መሆናቸው ነው ። ይህ ያደገ የባንዳነት ታሪክ ድንገት የተፈጠረ ሳይሆን በስብዕና ደረጃ ያደገና ማንነት ሆነ የተገለጠ ስለመሆኑ ብዙ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም። የትኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም መልኩ አስቸጋሪና ማንነቱን የሚፈታተን ሁኔታዎች ቢያጋጥሙትም ሀገርን ለማፍረስ የሚማማልበት ስብዕናና የስነ ልቦና መሰረት ግን በፍጹም አይኖረውም።
የትኛውም ኢትዮጵያዊ ካደገበት ሃይማኖታዊ ፣ ባህላዊ እና ማህበረሰባዊ እሴቶች አንጻር በሀገር እንዲቆምር ፣ በህዝብ ተስፋ እንዲነግድ ድፍረት የሚሰጠው ነገር አይኖርም፤ ከዚያ ይልቅ እነዚህን ተግባራት እንዲጠየፋቸው ፣ እንዲዋጋቸውና ራሱን ለሀገርና ለህዝብ የተሻለ ዕድል ፋንታ አሳልፎ እንዲሰጥ የሚያነሳሱና በተግባርም የሚገልጹት ናቸው።
ዛሬ ያጋጠመን ያደረ ባንዳነት በብዙ መልኩ የመጣንበትን መንገድ በአግባቡ እንድንመረምር የሚያስገድደን ነው። ከዚህም በላይ ባንዳነት የቱን ያህል የተስፋችን ጸር እንደሆነ በአግባቡ ተረድተን ባንዳነትን በጽናት ለመታገልና ወደ መጪው ትውልድ እንዳይሻገር አበክረን የምንታገልበት ወቅት ጭምር ነው!
አዲስ ዘመን መስከረም 17 ቀን 2014 ዓ.ም