እአአ መስከረም 21 ቀን 1999 ምሽት በእንግሊዟ ለንደን ከተማ አንድ የቦክስ ውድድር ተሰናድቷል።የወቅቱ የመካከለኛ ሚዛን ቻምፒዮናዎቹ ሚካኤል ዋትሰን እና ክሪስ ኡባንክ ለወሳኙ ፍልሚያ ከቦክስ ቀለበቱ ተገኝተዋል፤ በጉጉት የተሞሉ ተመልካቾችም በአዳራሹ ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል።12 ዙሮች ባሉት በዚህ ውድድር አሸናፊ ሆኖ የሚጨርሰው ቦክሰኛ የእንግሊዝ ምርጥ የቦክሰኝነት ክብርን እንዲሁም ሌሎች ሽልማቶችንም ይቀዳጃል፡፡
በመሆኑም ተፋላሚዎቹ የክብር ባለቤት ለመሆን የሚያስችላቸውን የአሸናፊነት መንፈስ ሰንቀዋል።ውድድሩ ከተጀመረ አንስቶም ሁለቱ ቦክሰኞች እየተፈራረቁ አንዱ ሌላኛውን በማጥቃት በአዳራሹ የተገኙትን ተመልካቾች ስሜትም ይዘውት ቆዩ።በጥቅሉ እስከ 11ኛው ዙር በነበረው ፍልሚያ ዋትሰን አሸናፊ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ያስገኘለትን ብቃት በተጋጣሚው ላይ አስመሰከረ።
ወሳኙና የመጨረሻው ዙር ፍልሚያ ከጥቂት እረፍት በኋላ ሲጀመር የታየው ግን ነገሩን የተገላቢጦሽ ያረገው ጀመር።የተሸናፊነት ዕድሉ የሰፋ ይሆናል በሚል የተጠበቀው ኡባንክ በተፋላሚው ላይ ሁለንተናዊ የበላይነትን ተላብሶ ታየ።ዋትሰን እንደቀድሞ ማጥቃት እስኪሳነው ድረስም የቡጢ ውርጅብኝ
ደረሰበት።በተደጋጋሚም የቦክስ ቀለበቱን አስደግፎ ተፋላሚው ላይ ጥቃት የሚሰነዝረውን ኡባንክ ዳኛው በተደጋጋሚ ያቋርጡት ነበር፤ ዋትሰን ግን ፊቱን በእጆቹ ከልሎ ራሱን ከመከላከል በቀር አማራጭ አልነበረውም።
በመጨረሻም የውድድሩ ማጠናቀቂያ ደወል ተሰማ፤ ዳኛውም የኡባንክን እጅ ወደላይ በማንሳት አሸናፊነቱን አበሰሩ።ደጋፊዎቹና አሰልጣኞቹም አንገቱ ላይ እየተጠመጠሙ ደስታቸውን ይጋሩት ያዙ።ከግርግሩ ሌላኛው ማዕዘን ግን አሳዛኙ ተሸናፊ ዋትሰን ራሱን ስቶ ተዘርሯል።አሁን የሁሉም ሰው ትኩረት ምክንያቱ ሳይታወቅ አቅሉን የሳተው ቦክሰኛ ላይ ሲሆን፤ እንደተጠበቀው በቀላሉ ሊነቃ አለመቻሉ ደግሞ በበርካቶች ዘንድ ስጋትን አሳደረ።ይበልጥ ሁኔታውን አስከፊ ያደረገው ደግሞ በአካባቢው ተጎጂውን ወደ ህክምና ስፍራ ሊያደርስ የሚችል አምቡላንስም ሆነ የህክምና ባለሙያ አለመኖሩ ነው፡፡
በዚህ ሁኔታ 8 ደቂቃዎች ከተቆጠሩ በኋላም የህክምና ባለሙያዎች የእራት ልብሳቸውን እንደለበሱ ከስፍራው ተገኙ።ሆስፒታል ከደረሰም በኋላ በዚያ ሁኔታ ውስጥ ለ28 ደቂቃዎች ቆይቶ የአእምሮ ህክምና ባለሙያ ቢታይም፣ ዋትሰን ራሱን ሳያውቅ ለ40 ቀናት ያህል ቆየ፤ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥም ጭንቅላቱ ውስጥ በተፈጠረው የደም መርጋት ምክንያት ለ6 ጊዜያት ቀዶ ጥገና ተደርጎለታል።ከገባበት ሰመመን ሲነቃም ለአንድ ዓመት ያህል በራሱ ነገሮችን ማከናወን የሚችል ባለመሆኑ በከፍተኛ የህክምና ክትትል ስር ሊቆይ የግድ ሆነ።የጤናው ሁኔታ መሻሻል ካሳየ በኋላም ለ6 ዓመታት በተንቀሳቃሽ ወንበር ላይ በመሆን ነበር ህይወቱ የቀጠለው።
ይህ ክስተት በወቅቱ አስደንጋጭ እንዲሁም በብዙዎች ዘንድ ቁጣን የቀሰቀሰም ነበር።ቦክሰኛው ዋትሰን ህክምና በቶሎ ባለማግኘቱ ምክንያት ህይወቱ አደጋ ላይ በመውደቁና ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት በመሆኑም ጭምር የእንግሊዝ ቦክስ ቦርድ የአንድ ሚሊዮን ፓውንድ ካሳ እንዲሰጠው በፍርድ ቤት ተወሰነበት።የቦክስ ውድድር በሚካሄድባቸው ስፍራዎችም ኦክስጂን፣ የህክምና ባለሙያዎች እንዲሁም አምቡላንስ እንዲኖርም አስገዳጅ ህግ ወጣ።ህይወቱን ከማጣት ለጥቂት በተረፈው ዋትሰን ላይ በተሰራው በዚህ ስህተት ምክንያትም ስፖርቱን የሚቀይር ውሳኔ ላይ ተደርሷል።
ዋትሰን ከደረሰበት ጉዳት በኋላ ዓመታትን በፈጀ ሂደት ሊያገግም ችሏል፤ ጤናውን ለመመለስ እንዲረዳው ጠዋትና ማታ ለሁለት ሰዓታት እርምጃ በማዘውተሩ የለንደንን ማራቶን እስከማጠናቀቅ ደርሷል።ከአደጋው በኋላ ለአካል ጉዳተኞች ስፖርት ባከናወነው ስራም በእንግሊዝ የክብር ሽልማት የሆነውን ኒሻን ከእንግሊዝ ንግስት ኤልሳቤት ሁለተኛ እጅም ሊበረከትለት ችሏል።
ተጋጣሚው ኡባንክ እንዲሁም ህክምናውን ሲከታተሉ የቆዩት የአእምሮ ሃኪሙም እስካሁንም ድረስ ከጎኑ ያልተለዩ የህይወት አጋሮቹ ሆነዋል።ኡባንክ በወቅቱ ስለጉዳዩ በመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በተጠየቀበት ወቅት በእንባ እየታጠበ ‹‹በእኔ ምክንያት ይሁን ወይም በሌላ አላቅም›› ሲል ይቅርታውንና ጸጸቱን ገልጾ ነበር።ከዓመታት በኋላም ሁለቱም የልብ ጓደኞች አብረው ተቀምጠው ስለሁኔታው እየሳቁ ለማውሳት በቅተዋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 16/2014