‹‹ንቅሳትን ለማስታወሻነት›› ስልዎ አዎ ንቅሳት ከማስታወሻነት በዘለለ ሌላ ምን አይነት ጥቅም ሊኖረው ይችላል? ይሉኝ ይሆናል፡፡ እውነትዎን ነው፤ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ሰውነታቸው ላይ ይነቀሳሉ፡፡ የሚነቀሱትም ለውበት፣ ለጤና መጠበቂያነት ሊሆን ይችላል፡፡ የሚወዱትን አልያም በሞት የተለያቸውን ሰው ለማስታወስ ሲሉ የሚነቀሱም አሉ፡፡
ንቅሳት ከእነዚህ ተግባሮች ውጪ ምንም አይነት ጥቅም ሊኖረው አይችልም ብለውም ሊከራከሩ ይችላሉ፡፡ ይልቅ ክርክሩን ትተው ይህችን መረጃ በጥሞና ያንቧትማ!! ንቅሳት ለውበት ወይም ሰዎችን ለማስታወስ ከሚሰጠው ጥቅም በዘለለ ሌላም ያልታየ ጥቅም እንዳለው ኦዲቲ ሴንትራል የተሰኘው ድረገፅ ከሰሞኑ ከወደቬትናም ዘግቧል፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ አንድ ወጣት በክንዱ ላይ የተነቀሰውን የራሱን መታወቂያ የሚያሳይ ፎቶ በማህበራዊ ድረገፆች ይለቃል፡፡ ይህንኑ የንቅሳት ፎቶ በማህበራዊ ድረገፅ የለቀቀው ወጣት ተግባር ግን ብዙዎችን አስገርሟል፡፡
ወጣቱና ጓደኞቹ ለካ የምሽት ክለቦችን አብዝተው ይጎበኙ ኖሮ ወደነዚህ የምሽት ክለቦች ሲሄዱ በተለይ እርሱ ብዙ ጊዜ መታወቂያውን ረስቶ ስለሚመጣ የምሽት ክለቦቹ እንዲገባ በጄ አይሉትም፡፡ በዚህ ክልከላ የተማረረው ይኽው ጠጪ ወጣት ታዲያ በስካር አእምሮው ይሁን ጤነኛ ሆኖ አንድ ሃሳብ ይመጣለታል፡፡
ያመጣው አዲስ ሃሳብ መታወቂያ የመርሳት አባዜውን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚፈታለትም ያምናል፡፡ ይኽውም መታወቂያውን በክንዱ ላይ መነቀስ ነበር፡፡ ይህንንም አደረገው፡፡ በክንዱ ላይ የተነቀሰውን መታወቂያ ንቅሳት በማህበራዊ ድረ ገፆች አሰራጨው፡፡ ይህንንም ተከትሎ በርካታ ሰዎች የንቅሳት ፎቶውን በማህበራዊ ድረገፅ ተቀባበሉት፡፡
የንቅሳቱ ምስል በማህበራዊ ድረገፅ ከተለቀቀ ወዲያ ግን የአብዛኛው ሰው ምላሽ ቀና አልነበረም፡፡ ገሚሶቹ ንቅሳቱን ያልተለመደና የእብድ ሃሳብ ነው በማለት ሲያብጠለጥለው ሌላው ደግሞ አስቀያሚና ደካማ የንቅሳት ስራ ሲል አጣጥሎታል፡፡
‹‹መጀመሪያ ላይ የንቅሳቱን ፎቶ ስመለከት ውሸት መስሎኝ ነበር፡፡ መጠነኛ ጥናት ካደረኩ በኋላ ንቅሳቱን የነቀሰውን ሰው የሚጠቅስ ፅሁፍ በማህበራዊ ድረገፅ ሳይ ግን እርግጠኛ ሆንኩ፡፡ በርግጥ የንቅሳት ባለሙያው ረጅም ጊዜ ንቅሳት ሲሰራ የቆየ ቢሆንም መታወቂያ በክንዴ ላይ ንቀስልኝ ተብሎ ሲጠየቅ ይህ የመጀመሪያው ሳይሆን አይቀርም›› ሲል አንዱ የማህበራዊ ድረገፅ ተጠቃሚ ተናግሯል፡፡
የንቅሳት ባለሙያው በበኩሉ በቀረበለት የንቅሳት ጥያቄ መጀመሪያ ላይ የተገረመ መሆኑን የገለፀ ሲሆን እንደውም ደንበኛው ውሳኔውን ዳግም እንዲያጤንበት ጠይቆት እንደነበረም ተናግሯል፡፡ ይሁን እንጂ ደንበኛው ሃሳቡን ባለመቀየሩ መታወቂያውን በክንዱ ላይ እንደነቀሰለት አብራርቷል፡፡ ንቅሳቱን ነቅሶ ለመጨረስም አንድ ሰአት እንደ ፈጀበት ገልፀዋል፡፡
በርካታ የማህበራዊ ድረገፅ ተጠቃሚዎች በንቅሳት ባለሙያው ደካማ ስራ ያሾፉ ሲሆን፣ ባለሙያውም እስካሁን ከሰራቸው ንቅሳቶች ሁሉ ይኽኛው ደካማ እንደሆነ አምኗል፡፡ ስራው ደካማ የሆነውም መስመር ሳይጠብቅ ዝምብሎ በእጁ ነፃ ሆኖ ስለሳለው እንደሆነም ተናግሯል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 19/2011
በአስናቀ ፀጋዬ