በቅሎ፣ ፈረስ፣ ሰረገላ በልጓም ከመስገር፣ ሽምጥ ከመጋለብ እንደሚገታ እንደሚቆም ሁሉ የመኪና፣ የባቡርና እና የአውሮፕላን ልጓም ቴክኒኩ ይለያይ እንጂ ያው ፍሬን ነው።ፍጥነቱ ይገታል።ይቆማል።መርከብ ደግሞ በመልሕቅ ይቆማል።በተለይ ለውጡ ከባ’ተ ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ ደግፈን አደባባይ በወጣንለት ለውጥ መፅናት፣ መተማመን፣ መቆም፣ ተስፋ ማድረግ ይኖርብናል።ምንም እንኳ በኃይለኛ ማዕበል እንደሚናወጥ መርከብ ከወዲህ ወዲያ እየተላጋን፣ እየዋዠቅን፣ እየወላወልን አረፋ እየደፈቅን ቢሆንም።አሁን አሁንማ በተለያዩ ችግሮች ነፍስ ግቢ ነፍስ ውጪ ቢሆንም ጸንተናል።የተሳፈርንለትን መዳረሻ በመመልከት በርትተናል ።የሰነቅነውን ተስፋ ለማየት ጥርሳችን ነክሰናል ።ትልቁን ሀገራዊ ስዕል፣ ሕልም አይተን በቆምንበት ጸንተናል።ተስፈኛ ሆነናል።
ከኃይለኛ ማዕበል ፣ መናወጥ ለመዳን ወይም መዳረሻ ወደብ ላይ ሲደረስ መርከበ መልሕቁን እንደሚጥል ሁሉ እኛም ውሽንፍሩን፣ ማዕበሉን ፣ መናወጡን ለማለፍ የሀሳብ መልሕቃችንን ጥለናል ። ተረጋግተናል። በአቋማችን ጸንተናል ። ነገን ተስፋ በማድረግ ጉልበታችን እንዳይዝል አበርትተናል ። በነፈሰ፣ ማዕበል በተነሳ ቁጥር መረበሽ፣ ማወላወል፣ ተስፋ መቁረጥ የዕለት ተዕለት ግብራችን መሆኑ ቀርቷል።ለዚህ ነው በአዲሱ አመትም የተስፋ፣ የፅናት ተምሳሌት የሆነውን መልሕቅ እንደገና እንጣል የምለው።ለመሆኑ የመልሕቅ ተምሳሌታዊ ስረወ _ ሀሳብ እንዴት ተፀነሰ ?
በሮማን አገዛዝ ዘመን ክርስቲያኖች በእምነታቸው ይሳደዱ ፣ ይዋከቡ ፣ ይጋዙ ፣ ይገረፉ ፣ ይሰቀሉ ስለነበር ዕምነታቸውን በሚስጥር ለመያዝ ይገደዱ ነበር። በአደባባይ ማምለክ ፣ መመስከር ፣ በዕምነት መመላለስ ስለማይችሉ ህቡዕ ገብተው ነበር። እርስ በእርሳቸው የሚተዋወቁትም በያዙት ፣ አንገታቸው ላይ ባሰሩት የመልሕቅ ምልክት ነበር ።ይህ ምልክት ያለበት ቤትም መማፀኛ ለሚፈልጉ ክርስቲያኖች አስተማማኝ መሸሸጊያ ሆኖ ያገለግል ነበር።
መልሕቁን በመለያነት የመረጡት መርከቡ በኃይለኛ ማዕበል ሲናወጥ ፀንቶ ለመቆም እንደሚያስችል ሁሉ በዕምነታቸው የተነሳ የሚደርስባቸውን ግፍ ፣ መከራ ፣ መሳደድ በፅናት ፣ በተስፋና በጥንካሬ እንደሚያልፉት ለማሳየት ነው ።የክርስትናስ አስተምህሮ ይሄው ተስፋ እና ፅናት አይደል ! መልሕቅ ሚዛናዊ እና በመስቀል ላይ የተቀመጠ ነው ።በመስቀሉ ወደ ጎን የተጋደመው መስመር መንፈስን ከላይ ወደ ታች የተሰመረው ደግሞ አካልን ይወክላል።
መስቀሉ በአንድነት የመንፈስና የአካልን አንድነት ያሳያል ። የሰውን ስጋ ለባሽነትንም ያመለክታል ።ከፍ ሲልም በመልሕቁ ያለው መስቀል ተባዕታይ ጾታን ግማሿ ጨረቃ ደግሞ አነስታይ ጾታን ፣ መሀፀንን ይመሰጥራል። መርከቡ ከቆመበት ወደብ ተነስቶ አዲሱን ጉዞውን ፣ ጀብድ adventure የሚጀምረው የጣለውን መልሕቅ በማንሳት ስለሆነ ተስፋን ይወክላል ።ለአመታት ሕይወት በአንድም በሌላ መልክ ከረጋበት ፣ ከቆመበት በአዲስ ወኔ መንፈስ መልሕቃችንን አንስተን አዲስ መንገድ ስንጀምር ሰንቀነው የምንነሳ ተስፋንም ይገልጻል።
መርከብ መቅዘፍ ሲጀምር ወደ አዳዲስ ውኆች ሲንቀሳቀስ መልሕቁን እንደሚያነሳ ሁሉ እኛም በህይወት መርከብ መቅዘፍ ስንጀምር ሊመጣ ያለውን በተነቃቃ ስሜት ፣ ተስፋና ጉጉት እንጠብቃለን። አዲሱን ህልም ከሩቅ እየተመለከትን ለመድረስ በድፍረት፣ በፅናት እንቀዝፋለን ።ፅናታችን ውሳኔ የመስጠት ብቃታችን ተምሳሌታዊ ወኪል ከመሆኑ ባሻገር የምንወስደውን አቋምም ሆነ የምንመራበትን መርህ ያሳያል።
መርከብ መልሕቁን ከጣላ በኋላ እንደማይንቀሳቀስ ሁሉ እኛም ስለ እውነት ፣ ተስፋ ስለምናደርገው ነገር በመተማመን ስለ መጠበቅ አቋም ከወሰድን ከወሰን በኋላ ዳር እስኪደርስ እውን እስኪሆን እንፀናለን እንጅ አናወላውልም ።ምንም አይነት ቀውስ ፣ ምስቅልቅል ፣ ትርምስ ፣ ፍርሀት ፣ ችግር ፣ መከራ ፣ ፈተና ዙሪያችንን ቢከበን ብርክ ቢይዘን ሁኔታዎች ሁሉ ምንም ያህል ቢያጠራጥሩን የህይወትን መልሕቅ መጣል በፅናት መቆም ይገባል ።ይህ የተረጋጋ ሰብዕና መገለጫም ነው ።በሚያምኑበት ነገር ፅኑ አቋም ያላቸው ሰዎች ለማህበረሰባዊም ሆነ ለግል እሴቶች ከፍ ያለ ዋጋ ያላቸው መሆኑንም ያሳያል ተብሎ ይታመናል።
እንደኛ በብዙ ውጣ ውረድና መከራ ላለፈ ሕዝብ ፅናት ፣ ተስፋ የአሸናፊነት ሚስጥር ነው ።ይህ ፅናት ፣ ይህ ተስፋ ነገ የተሻለ ቀን እንደሚመጣ ያለንን ህልም ፣ ራዕይ ያመለክታል ።በታላቁ መፅሐፍ ወደ ዕብራውያን 6 ÷ 19 ላይ በፈተና ፣ በአጠራጣሪ ወቅት በዕምነት ፀንቶ በተስፋ ስለ መጠበቅ እና ተስፋን እንደ ነፍስ መልሕቅ አድርጎ በሚያሳየው ጥቅስ ሀሳቤን ልቋጥር፤” ይህም ተስፋ እንደ ነፍስ መልሕቅ አለን እርሱም እርግጥና ጽኑ የሆነ ወደ መጋረጃውም ውስጥ የገባ ነው “፡፡
እስካሁን መልሕቅን ስለመጣል ፣ ስለ ፅናት ፣ ስለ ተስፋ ፣ ስለ አለማወላወል ፣ ስለ አለመናወጥ ፣ ወዘተ . ስሰብክ ፣ ስደሰኩር ማዕበሉን ፣ ወጀቡን ፣ ፈተናውን እረስቸው ፣ ችላ ብየው አይደለም ።በግሌ ባለፉት ሶስት አመታት መልሕቄን ጥዬ ያለፍኋቸውን ከበባድ ውሽንፍሮች ፣ ማዕበሎች እናንተንም የፈተኑ ዛሬም እየፈተኑ ያሉ ስለሆኑ ዋና ዋናዎች ላነሳሳ እና እንዴት እንዳለፍኋቸው ደግሞ መጨረሻ ላይ አጋራችኋለሁ።
በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የሚመራው የለውጥ ኃይል ወደ ኃላፊነት እንደመጣ ይወስዳቸዋል ብዬ እጠብቃቸው የነበሩ ማሻሻያዎች በአሸባሪው ህወሓት ደባና በሴራ በምፈልገው ልክ ፣ ጥልቀት ፣ ጥራትና ፍጥነት አለመፈፀማቸው ለእኔ እንደ ኃይለኛ ማዕበል ሆነው ፈትነውኛል ። ይህ ፈተና ግን እኔ ብቻ ያለፍሁበት ሳይሆን ዜጋም ፣ ሀገርም የተፈተኑበት ናቸው ።ሆኖም ፈተናዎች ፣ አደጋዎች ተከስተው ባለቡት፣ በነበሩበት ወቅት የነበራቸው አስፈሪ ፣ አስጨናቂ ፅልመት በአምላክ ጥበቃ እንደ ደመና ሲያልፉ የጠራ ሰማይ እንመለከትና እንደገና ተስፋ እናደርጋለን። እስኪ ያለፉትን ጥቁር ደመናዎች “ በተስፋ “ እና ዛሬም ያልተገፉ ደመናዎችን “ በማዕበልነት “ እንመልከት።
1 . የተገፈፉ ፣ እየተገፈፉ ያሉ ደመናዎች
1 . 1 ከለውጡ በፊት በነበሩ ሶስት አመታት መጀመሪያ በኦሮሚያ በመቀጠል በአማራና በሌሎች ክልሎች ተቀጣጥሎ የነበረው በወጣቱ ፊታውራሪነት ይመራ የነበረው ሕዝባዊ አመፅ መቋጫው ምን ሊሆን እንደሚችል ማናችንም እርግጠኛ መሆን አለመቻላችን በሀገሪቱ ሰማያ እስካዛሬ አዣንበው ከነበሩ የጥፋት ደመናዎች ሁሉ አስፈሪው ነበር ።ቀደም ላሉት 24 አመታት በልዩነት ላይ ተመስርቶ ይቀነቀን የነበረው በጥላቻ፣ በማንነት ላይ ተመስርቶ የነበረው አገዛዝ መውጫ አልባ ዙሪያው ገደል ነበር። ዛሬ ምስጋና አይግባውና ይሄው የሽብር ኃይል መከላከያን በማጥቃቱ ሀገራችንን ለማፍረስ ሲኦልም እወርዳለሁ በማለቱ ኢትዮጵያውያን ዳር እስከዳር በአንድነት እንዲቆሙ በማድረግ”ክሶናል”።
1 . 2 የሀገራችንን ሰማይ የስጋት ፣ የፍርሀት ቡልኮ አልብሷት የነበረው ሌላ ደመና ገዥው ፓርቲ ህወሓት በወቅቱ ከነባራዊ ሁኔታ ተናጥቦ ስልጣንን የሙጥኝ ብሎ ለውጥን ላለመቀበል ከማንገራገር አልፎ የሕዝብን ጥያቄ በነፍጥ ለማፈን የሄደበት እርቀት የመጀመሪያው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ለውጡን በግማሽ ልብ ከተቀበለ በኋላም ስልጣኑን ለለውጥ ኃይሉ ለማስረከብ ያሳየው መንፈራገጥ ነው።በወቅቱ ቲም ለማ የሚባለው የለውጥ ኃይል አሸናፊ ሆኖ ባይወጣ በተለይ ዐቢይ አህመድ (ፒ ኤች ዲ ) የዛን ጊዜው ኢህአዴግ ሊቀ መንበር ሆኖ ባይመረጥ ኖሮ ሊከሰት የሚችለውን ቀውስ ባሰብሁ ቁጥር ያቃዠኛል፤ ያባባኛል።
1 . 3 ከሁሉም የከፋው እና በሀገሪቱ ፣ በሕዝቡ፣ በለውጥ ኃይሉ ላይ በሰኔ 16 ቀን 2010 ዓም ተቃጥቶ የነበረው አደጋ ማለትም በመስቀል አደባባይ በተዘጋጀ የድጋፍና የዕውቅና ትዕይነት ሕዝብ ላይ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ ተቃጥቶ የነበረው ግድያ ነው ።በሰዎች ተመስሎ በአምላክ ጥበቃ በጥቂቶች መስዋዕትነት የግድያ ሙከራው ባይከሽፍ ኖሮ ሊከስት የሚችለውን ዕልቂት ለማሰብ እሞክርና ድፍረት አጣለሁ ።ዛሬ አቃቂር የምናወጣለት በሴራ ፖለቲካ እና በፈጠራ ወሬ የምናጠለሸውን ለውጥ እንኳ ልንነጠቅና ልናጣው እንችል ነበር ።ወደ ቀደመው እፉኝት አገዛዝም እንመለስ ነበር።
1 . 4 መፈናቀል እና ግጭት
የለውጥ ኃይሉ ከመምጣቱ በፊት እዚህም እዚያም ይቀሰቀሱ በነበሩ ግጭቶች የተነሳ ከቀዬው ተፈናቅሎ በነበረው 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ላይ በለውጡ ማግስት ደግሞ ለውጡን ለመቀልበስ ሌት ተቀን በሚያሴሩ አኩራፊዎች ጠንሳሽነት ሀገሪቱን የእርስ በእርስ ግጭት አውድማ ለማድረግ በማህበራዊ ሚዲያ በታወጀው መሰረት ወደ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ተፈናቅለው ነበር።በዚህ መዓበል ፣ ወጀብ ሽንቁር ለውጡን በማየት፣ በመመዘን ስንቶች አፈገፈጉ መልሕቃቸውን አነሱ !?
እነዚህን ወጀቦች ፣ ማዕበሎች ዛሬ ላይ መለስ ብለን ስናስባቸው ግን ቢያንስ እንደ አጀማመራቸው አስጨናቂና አስፈሪ አይደሉም ።ሆኖም በማዕበሎቹ የተናወጠው በለውጡ ተስፋ የቆረጠውን ቤቱ ይቁጠረው። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በበዓለ ሲመታቸው “ ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ እንሆናለን !!! “ ሲሉ በእንባ የተራጨው በመስቀል አደባባይ ባንዲራውን ለብሶ ለድጋፍ ከወጣው ስንቱ በፅናት ዘለቀ !? የዛሬውን የተስፋ ቀን ስንቱ በእምነት በተስፋ ጠበቀ !? ስንቱ መልሕቁን በመጣል በቁርጠኝነት ቀጠለ !? መልሱን ለእያንዳንዳችን ትቸዋለሁ።
2 . ዛሬም ከሀገራችን ሰማይ ገና ያልተገፈፉ ደመናዎች ከእነዚህ ደመናዎች ውስጥ መጣሁ መጣሁ የሚል መከራ ፣ ዝናብ ያረገዙትን ሁለት ደመናዎችን ብቻ በአብነት አነሳለሁ ።
2 . 1 ኢኮኖሚያዊ ጥቋቁር ደመናዎች
የለውጥ ኃይሉ ቀድሞ የመከላከል ከተከሰተ በኋላ በፍጥነት የማስወገድ ስራ ባለመስራቱና ስግብግብ ነጋዴና ወሮ በላ ደላላ ተጨምሮበት የኑሮ ውድነቱ ጣራ ነክቷል ።የዋጋ ግሽበቱ በብርሀን ፍጥነት እየጨመረ ነው።የምግብ ፣ የቤት ኪራይ ዋጋ ከዜጋው አቅም በላይ መሆኑ ምሬት ፣ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ከመክተት አልፎ ለውጡን በውልውል እንዲያየው እያደረገ ነው።የስራ አጡ ወጣት ቁጥር ከወር ወር ማሻቀብ ሌላው በለውጡ ፊት የተጋረጠ ፈተና ነው ።የሚፈጠረው ስራም ጥራት የሌለውና የተቀጣሪውን ህይወት መቀየር ይቅርና በልቶ የማያሳድር መሆኑ ፈተናውን አክብዶታል ።የለውጥ ኃይሉ በኢኮኖሚው ላይ መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት ላይ ዳተኛ መሆኑ ተስፋን ፣ ፅናትን በመፈተን ላይ ያለ ገና ያላለፍነው ማዕበል፣ ወጀብ ነው።
2 . 2 የሕግ የበላይነት
ባለፉት 27 አመታት በዜጎች ላይ ግፍና ስቃይ ሲፈፅሙ ሲገድሉ አካል ሲያጎድሎ ሲዘርፉ የነበሩ ተጠርጣሪዎች ዛሬ ድረስ ሙሉ በሙሉ ለሕግ አለመቅረባቸው በለውጡ ማግስት ዜጎችን ያፈናቀሉ፣ የገደሉ ፣ የሀገርን የሕዝብ ሀብት የዘረፉም በወቅቱ በሚጠበቀው ልክ ለሕግ እንዲቀርቡ አለማድረጉ ከጅምሩ ለውጡን ይጠራጠር ለነበረው ኃይል “ ተናግረን ነበር “ እያለ ጮቤ ሲያስረግጠው ለውጡን ተስፋ አድርጎ በፅናት ለሚጠባበቀውም ሳይቀር ፈተና መሆኑ አልቀረም። ለውጥ ያለ ተግዳሮት ፣ ያለ ዋጋ እንደማይመጣ ቢታወቅም ።የለውጥ ኃይሉ ከዚህ በበለጠ ማስተዋልና ጥበብ በተሞላበት እንዲሁም በጊዜ የለም ስሜት እነዚህን የስጋት ደመናዎች ሳይውል ሳያድር ከሕዝቡ ጋር በመቀናጀት መፍታት ይጠበቅበታል ።እንደ ትላንቱ በተስፋ፣ በፅናት ለሚጠብቁ መልሕቃቸውን ለጣሉ ተስፈኛ ፣ ቅን ወግኖች እነዚህ የስጋት ዳመናዎች እንደሚገፈፉ ያምናሉ ብዬ ባምንም ደመናዎቹ ከዚህ በላይ በሀገራቸው ሰማይ እንዲቆዩ ግን አይፈቅዱም። እንደ መልሕቅ
የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ያደረገውን ትንቅንቅ በድል የተወጣው ዛሬ ከደረሰበት የስልጣኔ ፣ የእድገት፣ የብልፅግና ፣ የአሸናፊነት ፣ የድል አድራጊነት ማማ ላይ ሊቆናጠጥ የቻለው በፅናት ፣ በዕምነት ፣ በተስፋ መልሕቁን በመጣሉ ነው ።የአሜሪካም ሆነ የአውሮፓ ስልጣኔና ብልፅግና የእነ ቻይና ፣ ደቡብ ኮሪያ ፣ ሲንጋፖር፣ ማሌዥያ ፣ ቬትናም ፣ ወዘተ . ትንግርታዊ ሽግግርን እውን ሊያደርጉ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ከድህነት አረንቋ ሊታደጉ የቻሉት በፅናት ፣ በተስፋ መስራት በመቻላቸው ነው።
ዛሬ “ የተስፋይቱ ምድር “ እያልን የፂዎንን ፣ የእየሩሳሌምን ስም በሞክሸነት ጀባ ያልናት ፣ ለዲቪ ሎተሪ ወገባችን እስኪንቀጠቀጥ የምንሰለፍላት ፣ ለቪዛዋ ለ44ቱ የምንሳልላት አሜሪካ መስራች አባቶች ከሶስትና አራት መቶ አመታት በፊት በፅናት ፣ በዕምነትና በተስፋ ባይታትሩላት ኖሮ ዛሬ ላይ ባልደረሰች ።አያት ቅድመ አያቶቻችን በፅናት በተስፋ ባይዋደቁላት ኖሮ ሉዓላዊነቷ የተከበረ ታሪካዊ የሆነችውን የዛሬይቷን ኢትዮጵያ ባልተረከብን ።እነ አጼ ምንልክ ንኩሩማህ ፣ ኪኒያታ፣ ሙጋቤ ፣ ወዘተ . በዕምነትና በፅናት የፀረ ቅኝ ግዛት ተጋድሎ ባያካሂዱ ኖሮ ዛሬ ነፃ አፍሪካን ባላገኘን ።እነ ማንዴላ በፅናት በተስፋ ባይታገሉ ኖሮ አፓርታይድ ዛሬም በዙፋኑ ይገኝ ነበር ።የሳይንስ ፣ የቴክኖሎጂ፣ የህዋ ምርምሮች በፅናት ፣ በዕምነት ባይከወኑ ኖሮ ለመኖር ቀላል የሆነችውን አለም ባላገኘናት።
ያለ ዕምነት ፣ ያለ ፅናት ፣ ያለ ተስፋ መንግስተ ሰማያት እንደማይወረሰው ሁሉ አለምም አትወረስም።እግራችን ስር አትወድቅም ።መዳፋችን ላይ አትገኝም ።የሀገራችን ለውጥ እንዲሳካ መልሕቃችንን ጥለን ፀንተን በተስፋ ፣ በዕምነት ካልቆምን የምናልማትን ሀገር እውን ማድረግ አንችልም።
ስለሆነም በደራሽ ፣ በድንገተኛ ማዕበል እንዳንናወጥ የተስፋ ፣ የፅናት ተምሳሌት የሆነውን መልሕቅ በአዲሱ አመት እንጣል።
መልካም አዲስ አመት !!!
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
አዲስ ዘመን መስከረም 16 ቀን 2014 ዓ.ም