ሰው ከተፈጥሮ፣ ከቤተሰቡ፣ ከአካባቢው ማህበረሰብ፣ ከትምህርት፣ ከባህላዊና ሃይማታዊ እሴቶች ወዘተ በሚያገኘው እውቀት እና ግንዛቤ ስብዕናው ይቀረጻል።በመልካም ስብዕና የተቀረጸ ሰው ቀናውን መንገድ ይከተላል፤ ጨለማውን በብርሃን ይለውጣል፤ ጎባጣውን ያቃናል።እንደዚያውም ክፉ ነገሮችን ይጠየፋል።
ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶች አርቆ አሳቢና መልካም ሰዎችን የመፍጠር አቅማቸው ከፍያለ ነው።ኢትዮጵያ አንድነታቸው የተጠናከረ ፍቅርና መተሳሰብ ያላቸው ህዝቦች ባለቤት ሆና ለዘመናት የቆየችውም በነዚህ እሴቶች የተገነቡ ህዝቦች ባለቤት በመሆኗ ነው። ኢትዮጵያውያን ፈጣሪያቸውን የሚፈሩ፣ ሳይድርሱባቸው የማይደርሱ፤ ፍትህና ርትዕን የሚያውቁ፤ ቁጭ ብለው በመነጋጋር ችግሮቻቸውን የሚፈቱ፣ የሚደማመጡ ፤ የሚከባበሩ ፣ የተበደለን የሚክስ ፤ የበደለን የሚቀጣና የሚገስጽ ወግና ባህል ያላቸው ህዝቦች ናቸው።በእነዚህ እሴቶቻቸው ተገንብተው ጠንካራ ማህበራዊ መስተጋብር በመፍጠር ዘመናትን አሳልፈዋል።
መስቀል፣ ኢሬቻ መውሊድ የመሳሰሉት ሃይማታዊና ባህላዊ ክብረ በዓሎቻችንን በጋራ በማክበር ፍቅርንና ደስታን የምንቋደስባቸው፤ መተዛዘንና መረዳዳትን፤ መስጠትና መቀበልን የምንለማመድባቸው በረከቶቻችን ናቸው።
የሰው ልጅ በተለይም ለሃይማኖታዊ ጉዳዮች ስሜቱ ስስ ስለሆነ ለዕምነቱ አስተምሮ ተገዢ ለመሆን ልቡ ይፈቅዳል፤ ከፈጣሪው ጋር ላለመጣላት ሲል በሚፈጽማቸው መልካም ነገሮች ማህበራዊ መስተጋብሩን ያሳምረዋል፤ ያጣፍጠዋልም።ይህ ታዲያ የሃይማኖት አባቶች የሰው ልጅ ሰማያዊውን ጸጋ እንዲያገኝ በምድር ላይ ሲኖር ደግ ደጉን ሰርቶ እንዲያልፍ በመምከራቸውና በማስተማራቸው የሚመጣም ነው።ሃይማኖታዊ እሴቶች ለጠንካራ ማህበራዊ መስተጋብር የሚያበረክቱት ትሩፋት አለ የምንለውም ለዚህ ነው።
ይህን ስንል ግን ሃይማኖት ካልገራቸው በስተቀር ቅን ተፈጥሮ ያላቸው ሰዎች የሉም ማለታችን አይደለም። ጠለቅ ያለ የሃይማኖት እውቀት ሳይኖራቸው ቅን የሚያስቡ፣ መልካም ነገርን የሚያደርጉ በርካቶች ናቸው። ካላቸው አካፍለው የሚበሉ ፣ የበጎአድራጎት ስራዎችን የሚሰሩ ስለሀገራቸውና ህዝባቸው የሚቆረቆሩ አርቆ አሳቢዎች አሉ።
በእርግጥ ሰው ከተሰጠው ጸጋ ሁሉ ትልቁ ሃብቱ ጭንቅላቱ ነው።ክፉና ደጉን ፤ እርባና ያለውንና እርባና ቢሱን መለየት የሚችለው በአስተሳሰቡ ምጥቀት ነው።የተሰጠውን ተፈጥሯዊ ጸጋ ማበልጸግ ወይም ያለማበልጸግ ግን ለባለቤቱ የተተወ ጉዳይ ነው።አዕምሮን በማበልጸግ ወይም በመግራት ረገድ እሴቶቻችን የሚጫወቱት ሚና ላቅ ያለ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡
ሃይማኖታዊ እሴቶች የፍቅርን ታላቅነት፤ የነዋይን ከንቱነት ይናገራሉ።በዚህ ምድር ላይ ያለው ነገር ሁሉ አላፊ ጠፊ እንደሆነና ሰው ፈጣሪውን ማክበርና ሰውን መውደድ ገንዘቡ እንዲያደርግ ይመክራሉ፤ ነፍስ ማጥፋት ፣ መስረቅ፣ መዋሸት፣ ማመንዘር ሰውን ከክብሩ ዝቅ እንደሚያደርጉ ያስረዳሉ።እነዚህ ሃይማኖታዊ አስተምሮዎች የሰዎችን አእምሮ በመሞረድ መልካምነትን ያላብሳሉ።
ሃይማኖቶች በሚከተሏቸው እውነታዎችና አስተምሮዎች ሊለያዩ ቢችሉም በርካታ የጋራ እሴቶች አሏቸው።ሁሉም ሃይማኖቶች ክፉ ድርጊቶችን ያወግዛሉ።የየእምነቱ ተከታዮች ፈጣሪያቸውን በመፍራት እንዲኖሩና እና ህግጋትን እንዲያከብሩ በሃይማኖት አባቶቻቸው ይመከራሉ።ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን ፣ ከመገፋፋት ይልቅ መደጋገፍን ፣ ከቂም በቀል ይልቅ እርቅን ፤ ከሀሰት ይልቅ እውነትን ይሰብካሉ፡፡
ለነገሩ ሰው ለሃይማኖቱ አደረም አላደረም ከመጥፎ ድርጊቱ ጸጸትን ካልሆ በስተቀር የሚያተርፈው እንዳችም ነገር የለም።ይህን በመረዳት ይመስላል እውቁ የሀገራችን ደራሲ ክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል ‹‹ ጽድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም፤ ከክፋት ደግነት ሳይሻል አየርቀርም ›› ያሉት።አባባሉ ጥልቅ መልእክት የሚያስተላልፍ ነው።
ሰው ከምድራዊውም ከሰማያዊውም ህግ በላይ የህሊናው ተገዢ መሆኑን የሚያስረዳ ነው።ለሆዳችን ምግብ እንደሚያስፈልገን ሁሉ ለህሊናችንም መልካም ስራ ምግቡ ነው።ህሊናችን ምግብ ሲያጣ ምሉዕነት አይሰማንም ፤ እንረበሻለን፤ እንታወካለን፤ በሰራነው መጥፎ ስራም እንጸጸታለን።
እኛ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊም ፣ ክርስቲያንም እንሁን ዋቀፌታ ተሳስቦ ተፈቃቅሮና ተዛዝኖ መኖርን በትውልድ ቅብብሎሽ እየወረስን እዚህ ድረስ የመጣነው በሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻችን የተገነባን /የተቀረጽን/ ስለሆንን ነው።
ከመስቀልም ከኢሬቻም ሆነ ከአረፋ ስብእናችንን የሚገነቡ ቁምነገሮችን እናገኛለን።ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ሀጥያት ለመደምሰስ ተሰቅሎ በከፈለው ዋጋ የፍቅርን ሃያልነት ተምረንበታል። ንግስት እሌኒ ይህ ዋጋ የተከፈለበት መስቀል እንደ አልባሌ ነገር ተቀብሮ ቆሻሻ ሊጣልበት አይገባም በሚል ከብዙ ዓመት በኋላ ከተቀበረበት አስወጥታ በክብር ማስቀመጧ ለተከፈለላት ዋጋ እውቅና መስጠቷን እንገነዘባለን።
መስቀሉ የፍቅር ፣ የይቅርታ ፣ የጽናት፣ የመዳን ተምሳሌት ሆኖ ይታወሳል።የመስቀል በዓለም በዚህ መንፈስ ይከበራል።በዓሉ ሲከበር ሰዎች ተሰብስበው ደስታቸውን ይገልጸሉ። እንኳን ለብርሀነ መስቀሉ አደረሰህ አደረሳችሁ በመባባል ሀሴት እያደረጉ ሃይማኖታዊ ስርዓቶችን ሲፈጽሙ በሀይማኖታዊ እሴቶቻቸው ማህበራዊ መስተጋብራቸውን ያጠናክራሉ።
የምስጋና የፍቅርና የአንድነት መገለጫ የሆነው የኢሬቻ በዓልም ማህበራዊ ቀረቤታና ትስስርን ከመፍጠር አንጻር ሚናው የላቀ ነው።በዓሉ ሲከበር ሰዎች ከቂምና ከጥላቻ ነጽተው በፍቅርና በወንድማማችነት መንፈስ እጅ ለእጅ ተያይዘው ለፈጣሪያቸው ምስጋና የሚያቀርቡበት ስርዓት ነው።ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ እንሰሳትም በተከለከሉት የግጦሽ ሳር ላይ ተሰማርተው ጠግበው እንዲቦርቁ የሚደረግበት እለት ነው።ይህ ትልቅ መልእክት ያለው ነው።
በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድም ምስኪኖችን መርዳትና ከሌላቸው ጋር ተካፍሎ መብላት ሃይማታዊ ግዴታ ነው።ሃይማኖታዊ እሴቶቹ መተዛዘን፤ መፈቃቀር፣ መተማመን በሰዎች አዕምሮ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዲኖራቸው ያስገድዳሉ።ኢትዮጵያውያን በጋራ ስንኖር በየብሄረሰቡና እና በየሃይማኖቱ ውስጥ የሚገኙ ቅን አመለካከቶችንና አስተሳሰቦችን እየተወራረስን እንድንመጣ አድርጎናል። ኢትዮጵያ ጠንካራ ማህበራዊ ትስስር እና አንድንት ያላት ሀገር እንድትሆን ያስቻሏትም እንዲህ አይነቶቹ እሴቶቻችን ናቸው።
አሁን አሁን ከባህላዊና ሃይማታዊ እሴቶቻቸን ያፈነገጡና የሀገራችንን ገጽታ የሚያበላሹ አስተሳሰቦችና አድራጎቶችን መታየታቸው ያሳፍራል።በተለይም የክርስትናም ይሁን የእስልምና ሃይማቶችን ለኢትዮጵያ ህዝብ ያስፋፋነው እኛነን ከሚሉ ወጎች ፍጹም የማይታመኑ ዘግናኝ ግፎች በሰው ልጆች ላይ ሲፈጸሙ ማየት ሃይማኖታዊ እሴታችንን አደጋ ላይ እንደወደቁ የሚያሳይ ነው። ሃይማኖታዊ እሴቶቻችን ለሰውም ይሁን ለሀገር በጎ ነገር እንዲሆን የሚመኙ ስለሆኑ ልንጠብቃቸው ይገባል።
ሀገርን ከወራሪ ጠላት መጠበቅ እንዱ ሃይማኖታዊ አስተምሮ ነው።ኢትዮጵያ የመጡባትን ወራሪ ጠላቶች እያሳፈረች ስትመለስ ኖራለች።ዛሬም የውጭና የውስጥ ጠላቶቿ ተመሳጥረው ሊያፈራርሷት በተነሱ ጊዜ ህዝቦቿ እንድ ሆነው ከዳር እስከዳር መንቀሳቀሳቸው እሴቶቻቸው ያጎናጸፏቸውን ጠንካራ አንድነት የሚያሳይ ነው። እንዲህ አይነት ስብዕና እንድንላበስ የረዱንን እሴቶቻችንን ጠብቆ ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ የሃይማት አባቶች ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ሃላፊነት ነው።መልካም የመስቀል በዓል።
ሜላት ኢያሱ
አዲስ ዘመን መስከረም 16 ቀን 2014 ዓ.ም