የክርስትና እምነት ድርሳናት እንደሚያሳዩት አይሁድ በሮማውያን ላይ እስከ አመጹበት እና እየሩሳሌም ከክርስትና በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ እስከጠፋችበት እስከ 70 ዓ.ም ድረስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል በክርስቲያኖች እጅ እንደ ነበር ይታመናል።በኋላ ግን ክርስቲያኖቹ የሮማውያንን እና የአይሁድን ጦርነት በመሸሽ ከእየሩሳሌም ወጥተው ወደ ሌሎች ሀገሮች ሲሰደዱ፤ በኋላም እየሩሳሌም ፈጽማ በሮማውያን ስትደመሰስ የመስቀሉ እና የሌሎችም ክርስቲያናዊ ንዋያት እና ቅርሶች ነገር በዚያው ተረስቶ ቀረ።
ቀጣዮቹ 300 ዓመታትም ለክርስቲያኖች የመከራ ጊዜያት እንደነበሩ ይነገራል።እነዚህ ዓመታት የሮም ቄሳሮች ክርስቲያኖችን የሚያሳድዱባቸው ዓመታት በመሆናቸው መስቀሉን የመፈለግ /ፈልጎ የማግኘት መሻት/ ጉዳይ በልቦና እንጂ በተግባር ሊታሰብ የሚችል አልነበረም።ዓመታት እያለፉ ሲሄዱም እየሩሳሌም እየተዘበራረቀች እና የጥንት መልኳ እየተቀየረ በመሄዱ ነገሮችን የበለጠ አስቸጋሪ አደረገው ።
ነገር ግን የንግስት ዕሌኒ ወደ እየሩሳሌም መሄድ እውነታውን የቀየረ ታላቅ ታሪካዊ ክስተት ሆኗል። በደመራ አማካኝነት የክርስቶስን መስቀል ማግኘቷም ለክርስቲያኖች ትልቅ የብስራት ዜና ይዞ መጥቷል። በዛሬው እለት የምናከብረው የደመራ በዓል የዚሁ ታሪካዊ እውነታ አካል ነው።የመፈለግ መሻት በማግኘት ብስራት ፍጻሚው እንደሚያምር አመላካች ነው።የዓለም ታሪክም በአብዛኛው ከዚሁ እውነታ የሚቀዳ ነው ፡፡
ለምሳሌ ቻይናዊያን አሁን ወደ ደረሱበት መሻት ለመድረስ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል ። እንደ ህዝብ በርካታ ፈተናዎችን ተጋፍጠዋል፤ የሚበሉትን አጥተው ቅጠል ከመብላት ጀምሮ ብዙ መከራዎችን ተቀብለዋል።የኮርያና ሌሎች የበለፀጉ ሃገራት የማደግ መሻት ዝም ብሎ በአንድ ምሽት የበቀለ ሳይሆን በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፎ የተገኘ ነው።አንዳንዶችም ስለ ብልጽግና ያላቸውን መሻት ያህል ከፍ ባለ ድህነትና ኋላቀርነት ተፈጥትነዋል።
እኛ ኢትዮጵያውንም አሁን የምንገኘው በዚህ አይነት የታሪክ ምእራፍ ውስጥ ነው። ከመሻታችን በወጡ ፈተናዎች እየተናጥን ነው።በአንድ በኩል መሻታችንን በሚፈታተን ጦርነት በርካታ ዜጎቻችን ዋጋ እየከፈሉ ነው ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ጦርነት በሚያስከትላቸው ተመጋጋቢ ችግሮች ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል ውስጥ ገብተናል ።
ዛሬ በአሸባሪው ህወሓት እና በተባባሪዎቹ የውጭ ጠላቶቻችን የደረሰብን ከባድ ፈተና ወገብን የሚያጎብጥና ትዕግስትን የሚፈታተን ነው። ልክ እንደ ደመራው የመሻት ስኬት ብስራት ተስፋ ሳንቆርጥ መሻታችንን ለመጨበጥ በቁርጠኝነት ከሰራን የደስታ ቀናችን ሩቅ አይሆንም።
ንግሥት ዕሌኒ መስቀሉን ለማውጣት ስትነሣ ብዙዎቹ በአካባቢው ስለነበረው የቆሻሻ ክምር እንጂ ከክምሩ በታች ስለተቀበረው መሻቷ ተስፋ አድርጎ የነገራት አልነበረም።
መስቀሉ የት እንደተቀበረ እንደማይታወቅ፤ ከተቀበረ ብዙ ዘመናትን እንዳስቆጠረ፤ ለማውጣት አስቸጋሪ እንደሆነ፤ ሁኔታዎች ሁሉ ተስፋ አስቆራጭ እንደሆኑ ነበር የሚተርኩላት። እርሷ ግን እንደተቀበረ ብቻ ሳይሆን እንደሚወጣም ታምን ነበር። እንደጠፋ ብቻ ሳይሆን ሊገኝ እንደሚችልም እንዲሁ።
‹ፈተና› ደካማና ተሸናፊዎችን ሲሰብራቸው በተቃራኒው ለአሸናፊዎች የትምህርት ዕድል ነው። አሸናፊዎች ከፈተናው ትምህርት ወስደው ይለወጡበታል፤ እንደ ብረት ጠንክረው ይወጡበታል። ወደ መሻታቸው መገስገስ የሚያስችል አቅም ይሆናቸዋል።
እኛ ለኢትዮጵያውያን ስለ ትልቁ መሻታችን /ብልጽግናችንን እውን ማድረግ/ አሁን ያጋጠመን ፈተና በብዙ መንገድ ቢያንገዳግደንም ፈጽሞ የሚጥለን አይደለም።ለዘመናት በድህነትና ኋላቀርነት፣ በርሃብና በቸነፈር፣ በልዩ ልዩ ችግሮች ተፈትነናል። በዚህ ሁሉ እንደሀገር ባለተስፋ መሆናችን ከልባችን አልተሰወረም።
ዛሬም አዲስ በሆነችው በዝች ቀን ይህ የመሆን መሻታችን፤ የቃል ተስፋችንን ለመውረስ በተሻለ መነቃቃት ላይ ብንገኝም፤ ብዙዎች አሁንም የሚነግሩን እንደ ንግስት ዕሌኒ ተስፋችን ረጅም ዘመን ስለማስቆጠሩ፤ ስለ መጣንባቸው ውጣ ውረዶች እና እነሱ ስለፈጠሩት መዛል ነው።
ከቃልም ባለፈ እየደረሰብን ያለው ጫናና ማስፈራሪያ ሁሉ ለዘመናት ከኛ ጋር የኖረውንና አሁን አደባባይ የሞላውን የመሆን መሻታችንን ለማዳፈንና በሱ ውስጥ የነበረውንና አሁንም ሕያው የሆነውን የትውልዶች ተስፋ ለማክሰም ነው ።
እኛ ኢትዮጵውያን አሁን ከደረስንበት መንቃት ከመድረሳችን በፊትም አበቃላቸው የተባሉ ብዙ ታሪካዊ ክስተቶችን በጽናት ተሻግረናል።በተደጋጋሚ ከውጭ ሃይሎች ከጫና ባለፈ የደረሱብንን ጥቃቶች መክተን ሉኣላዊነታችንን አስከብረናል፤ በዚህ ዘመንም ቢሆን ከውጭ ሃይሎች የደረሰብንን ጫና ተቋቁመን ለብዙ ድሎች በቅተናል።
ለዚህ ደግሞ በተለይ በ2013 ዓ.ም የታላቁ ህዳሴ ግድብን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት እንዳናከናውን ከሱዳንና ግብጽም አልፎ እስከ ጸጥታው ምክር ቤት ድረስ የደረሱብንን ጫናዎች ተቋቁመን ያለፍንበትና ሃይል ለማመንጨት ከጫፍ የደረስንበት ስራችን አንዱ ስኬታችን ነው፡፡
ከዚህም ባሻገር ምርጫ እንዳናካሂድ ሲደረግብን የነበረው ጫና ከብዙዎቻችን ልብ ውስጥ የማይጠፋ ትልቅ ተግዳሮት እንደነበር የምናስታውሰው ነው።ነገር ግን ይህንንም ጫና ችለን ምዕራባውያን ከሚመኩበት ምርጫ የተሻለ ምርጫ በማካሄድ መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ሂደት ላይ መድረሳችን ሌላው ስኬታችን ነው፡፡
የሃገር መከላከያ ሰራዊታችንም ከጀርባው የተፈፀመበትን ጥቃትና ከውጭ ሃይሎች እየደረሰበት ያለውን ጫና ተቋቁሞ የሃገሩን ሰላም ለማረጋገጥ እየሄደ ያለበት መንገድና ወቅታዊ ቁመናው ተጨማሪ ስኬታችን ነው።ከዚህ ጎን ለጎንም ደጀን የሆነው መላው የሃገራችን ህዝብ ነገ የተሻለ ቀን እንደሚመጣ ተስፋ በማድረግ በአንድ ልብ ከሃገር መከላከያ ሰራዊት ጎን በመሰለፍ እያደረገ ያለው አስተዋፅኦ ታሪክ የማይዘነጋው ጀግንነት ነው፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በተሻለ መሻታችንን በስኬት ለመውረስ በሚያስችል የታሪክ ምዕራፍ ላይ ነን። ለዚህም በአንድነትና በፍቅር እጅ ለእጅ ተያይዘን በጀመርነው የብልጽግና መንገድ በመጓዝ፤ ወደከፍታ ማማ መሻገር ይጠበቅብናል።ፈተናዎቻችን ወደ መሻታችን /ተስፋችን/ የሚያሻግሩን ድልድዮቻችን መሆናቸውን አምነን በጽናትና በቁርጠኝነት ልንጋፈጣቸው ይገባል ! ።
አዲስ ዘመን መስከረም 16 ቀን 2014 ዓ.ም