የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከመካሄዱ አስቀድሞ ከተማ አቀፍ ቅድመ ውድድር በማዘጋጀት ይታወቃል። ይኸው ተወዳጅና የሊጉ ተሳታፊ ክለቦችን የሚያወዳድረው የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ዘንድሮ ለ15ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን፤ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል።
ውድድሩ ክለቦች ወደ ውድድር ዓመቱ ከመግባታቸው አስቀድሞ ያሉበትን የጥንካሬ ደረጃ እና ድክመታቸውን የሚለዩበት፣ አዳዲስ ፈራሚ ተጫዋቾች ከክለባቸው ጋር የሚዋሃዱበት እንዲሁም ከወጣት ቡድኖች ያደጉ ተጫዋቾችም አቋማቸውን የሚያሳዩበት በመሆኑ ጠቀሜታው እጅግ የጎላ ነው።
ይህ ውድድር በዋናነት ከተማውን ወክለው በፕሪምየር ሊጉ ተሳታፊ የሚሆኑ ክለቦችን በቅድመ ውድድር ራሳቸውን እንዲገመግሙ ለማገዝ የሚካሄድ ነው። ይሁን እንጂ ከከተማዋ ክለቦች ባሻገር ሌሎች የሊግ ተሳታፊ ክለቦችም በተጋባዥነት በሚሳተፉበት በዚህ ውድድር ክለቦች ከፍተኛ ፉክክር የሚያደርጉበት ውድድር ነው። በአዲስ መልክ በታደሰው የአበበ ቢቂላ ስታዲየምም ከዛሬ ጀምሮ እስከ መስከረም 30 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ቀጥሎ ይደረጋል።
የመክፈቻው ጨዋታም ዛሬ 8 ሰዓት ላይ የሚጀመር ሲሆን፤ በምድብ አንድ ዘንድሮ በድጋሚ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ባደጉት የአዲስ አበባ ከተማ እና መከላከያ እግር ኳስ ቡድኖች መካከል የሚካሄዱ ይሆናል። ቀጣዩ ጨዋታ በ10 ሰዓት የሚካሄድ ሲሆን፤ ጅማ አባጅፋርን ከኢትዮጵያ ቡና ያገናኛል። ለመክፈቻው ጨዋታም 10ሺ የስታዲየም መግቢያ ቲኬቶች የተዘጋጁ መሆኑን የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
በዚህ ውድድር ላይ ሁለት የውጪ ሃገር ቡድኖችን ጨምሮ ስምንት ክለቦች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ ቢጠበቅም፤ የደቡብ ሱዳኑ እንዲሁም የኤርትራው ክለቦች በተለያየ ምክንያት በውድድሩ ተሳታፊ ሊሆኑ አልቻሉም። በመሆኑም ጅማ አባጅፋርን በመተካት በድጋሚ ቁጥሩን በማስተካከል ይቀጥላል። በዚህም መሰረት ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ አዲስ አበባ ከተማ፣ መከላከያ፣ አዳማ ከተማ፣ ፋሲል ከተማ፣ ጅማ አባጅፋር እና ባህር ዳር ከተማ ተሳታፊ ክለቦች መሆናቸው ታውቋል።
ኮከብ ተጫዋች ከየጨዋታው የሚመረጥ ሲሆን፤ ለዚህ ውድድር ሲባል ከጀርመን የመጣና ጥራቱን የጠበቀ ልዩ ዋንጫ ለተጫዋቾቹ የሚበረከት ይሆናል። ከዚህ ቀደም ከተለመደው ሽልማት የተሻለ ማበረታቻ መዘጋጀቱም ተጠቁሟል።
የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ፤ ውድድሩ ለክለቦች በብዙ መንገድ ጥቅም የሚያስገኝ መሆኑን አስታውቀዋል። በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ተመልካቾች በመገኘት የእግር ኳስ ፍቅራቸውን የሚወጡበት ውድድርም ይሆናል። ከስታዲየም ትኬት ሽያጭ የሚገኘው ገቢም በፐርሰንት ለተሳታፊ ክለቦች ገቢ ሲደረግ፤ በተጓዳኝ ለሃገር ክብር ሲል በጦርነት ውስጥ ለሚገኘው የሃገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ የሚደረግ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ መጠቆማቸውንም ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ከዚህ ቀደም በዓለም አቀፉ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ተመልካቾች ስታዲየምን ጨምሮ በስፖርታዊ ውድድሮች ላይ እንዳይገኙ መደረጉ የሚታወስ ነው። በዚህ ውድድር ግን ደጋፊዎች በስታዲየም ተገኝተው ጨዋታዎችን በመመልከት ከረጅም ጊዜ በኋላ በሚወዱት ስፖርት የሚታደሙበት እንዲሁም ለሃገርም ድጋፍ የሚሰጡበት ይሆናልም ተብሏል።
ከወረርሽኙ ስርጭት ጋር ተያይዞ ጥንቃቄ ለማድረግ ሲባልም ግማሽ ተመልካች ብቻ እንዲገኝ በማድረግ ከንክኪ ነጻ ለማድረግ ታቅዷል። ደጋፊዎች ወደ ስታዲየም ለመግባት የሚያስችላቸውን ትኬት በመቁረጥ ሂደት ንክኪ እንዳይፈጸምም ፌዴሬሽኑ ከዳሽን ባንክ አሞሌ ጋር በመተባበር ሁለት አማራ ጮችን ያስቀመጠ ሲሆን፤ በኢንተርኔት እንዲሁም ከባንኩ ቅርንጫፎች በመ ግዛት አገልግሎቱን እንዲ ያገኝ የሚደረግ መሆኑም ታውቋል።
ከ1998 ጀምሮ በየ ዓመቱ የሚካሄደው የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ፤ ለሁለት ጊዜያት ሳይካሄድ ቀርቷል። እነዚህም ጊዜያት በ2000 ዓ.ም እንዲሁም ያለፈው ዓመት 2013 ዓም በኮቪድ 19 ስርጭት ምክንያት ናቸው።
በዚህ ውድድር ላይ ለበርካታ ጊዜያት ዋንጫ በማንሳት ቀዳሚ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ለስድስት ጊዜያት አሸናፊ ሲሆን፤ ከ2002-2004 ዓ.ም ባሉት ሶስት ዓመታት ያለ ተቀናቃኝ ዋንጫውን የግሉ አድርጓል። ኢትዮጵያ ቡና ለአራት ጊዜያት ውድድሩን ሲያሸንፍ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ደግሞ ለሶስት ጊዜያት ዋንጫውን የግሉ ማድረግ ችሏል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 15/2014