ብዙዎቻችን ‹‹የስራ ትንሽ የለውም›› የሚለውን አባባል ከንድፈ ሀሳባዊ ፍችው በዘለለ አናውቀውም። አንድ የሆነ ስራ እንድንሰራ ምክር ሲሰጠን አይመጥነንም በሚል እጃችንን አጣጥፈን የተቀመጥነውን ቤቱ ይቁጠረን። ኑሯቸውን ለማሸነፍ የሚጥሩ ሰዎች ግን ስራ አይመርጡም፤ ‹‹የስራ ትንሽ የለውም›› የሚለውን አባባል በተጨባጭ ይተረጉማሉ። ሁልጊዜ በጥረት፤ ሁልጊዜ በስራ ላይ ናቸው። የዛሬዋ እግዳችንም ከነዚህ አንዷ ነች። የልጅነት ህልሟ ሞዴል መሆን ነበር። ፋሺኖችን እና ዘመናዊ አኗኗርን መከተል ፍላጎቷ ነበር። ህልሟን ለማሳካት የሚያስችል የኢኮኖሚ አቅም ግን አልነበራትም። ያሰበችው የህይውት መንገድ ሳይሳካላት ሲቀር በምኞት ከፍ ብላ መኖሯን ትታ ዝቅ ብላ እየሰራች መኖር ጀምራለች። ሽቅርቅሯ ወጣት እየሰራች ያለችው ስራ ህይወቷን የሚቀይር ባይሆንም ለስራ ያላትን ክብር ያየንበት በመሆኑ እንግዳችን ልናደርጋት ወደናል።
እምወድሽ ዳባ ትባላለች። ትውልዷና እድገቷ በአዲስ አበባ ልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ቀበሌ 50 ነው። እድሜዋ ለትምህርት ሲደርስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በአቅራቢያዋ በሚገኘው ጆን ኤፍ ኬኔዲ፤ ከዚያም የሁለተኛ ደረጃ ትምርቷን በድላችን ትምህርት ቤት ተምራለች። ገና የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ እያለች አብሮ አደጎቿና የትምህር ቤት ጓደኞቿ ሞዴል ለመሆን የሚያስችል ተክለ ሰውነት እንዳላት ይነግሯት ስለነበር በሰዎች ተጽእኖ ሞዴል ኢዱስትሪውን የመቀላቀል ፍላጎት እያደረባት መምጣቱን ትናገራለች።
ህልሟን እውን ለማድረግ ስለ ሞዴሎች እና ሞዴልነት መረጃዎችን እያሰባሰበች እራስዋን ለማብቃት የተቻላትን ጥረት ማድረጓን ትቀጥላለች። ነገር ግን እገዛ የሚያደርግላት ሰው በማጣቷና በዘርፉ ከተሰማሩ ሙያተኞች ጋር የሚያስተዋውቃት መድረክ ባለማግኘቷ ያሰበችውን እውን ማድረግ ይከብዳታል። ቤተሰቦቿ በአነስተኛ ገቢ በርካታ ልጆችን እደሚያስተዳድሩ የምትናገረው ወጣቷ በወቅቱ የእርሷን ፍላጎት አሟልተው ያሰበችውን እድታሳካ የሚያስችል አቅም እንዳልነበራቸው ትገልጻለች።
ያም ሆኖ ከትንሽ ተነስቶ ትልቅ መሆን እደሚቻል በማመንና ላሰበችው ሙያ መንደርደሪያ እዲሆናት በማሰብ የውበት ወይም የቁንጅና ስልጠና ወስዳ በሴቶች የውበት ሳሎን ውስጥ ተቀጥራ መስራት ትጀምራለች። ምወድሽ በሴቶች የውበት ሳሎን ለዓመታት ተቀጥራ በሰራችበት ጊዜ እንዳሰበችውም የሞዴሊንግ ፍላጎቷ እንደጨመረ ትናገራለች። ተቀጥራ በምትሰራበት ቤት የሚሰጣት ክፍያ በየወቅቱ እየናረ ከመጣው የኑሮ ውድነት ጋር አልመጣጠን ሲል ስራዋን ለቃ በግሏ መንቀሳቀስ ትጀምራለች። ለሴቶች ቁንጅና ሳሎን የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን አሟልታ ወደ ስራ መግባት የሚያስችል አቅም ባይኖራትም ሹሩባ በመስራትና የጥፍር ቀለም በመቀባት የምታገኘውን ገንዘብ እያጠራቀመች እራሷን ለማደራጀት ትጥር ጀመር። ነገር ግን የምታገኘው ገንዘብ ከፍጆታዋ አልፎ እቃ ለመግዛት የሚያስችል ሳይሆን ይቀራል።
ታዲያ የምወድሽን ሰርቶ የመኖር ፍላጎት የተረዱት ጓደኞችዋ ለጥቂት ዓመታት ወደ አረብ ሀገር ሄዳ ብትሰራ መቋቋሚያ የሚሆናትን ገንዘብ ይዛ ልትመጣ እንደምትችል ሀሳብ ይሰጧት ጀመር። እርሷግን ከልጅነቷ ጀምሮ በሀገሯ ሰርቶ የመኖር ፍላጎት ስለነበራት አይኖቿ ሌሎች ስራዎች ላይ ከማማተር ውጭ የአረብር ሀገር መንገድን ዞር ብሎ ማየት አልፈለጉም። አረብ ሀገር ለስራ የሚሄዱ ሰዎች የተለያዩ እንግልትና መከራ እንደሚደርስባቸው የምትናገረው ምወድሽ ስራን ሳይንቁ መስራት ከተቻለ ሀገር ውስጥ ሰርቶ ሞኖር እንደሚቻል ከአጭር ጊዜ ተሞክሮዋ እንዳረጋገጠች ትናገራለች።
እምወድሽ የሞዴልነቱ ህልሟ እንደማይሳካ በተረዳች ጊዜ አዲስ የህይወት ምእራፍን ትጀምራለች። ዛሬ አብሯት ከሚኖረው ባለቤቷ ጋር ተዋውቃ ትዳር ትመሰርታለች። በትዳር ቆይታዋም ልጆችን ወልዳ ማሳደግ ትጀምራለች። ባለቤቷ ሞት ባይኖር ብርሃኑ ይባላል። የጦር ጉዳተኛ ሲሆን በሚከፈለው አነስተኛ የጡረታ ብር የሚተዳዳር ነው። ከምወድሽ ጋር ትዳር ከመሰረተ በኋላ ግን ተጨማሪ ስራ እየሰራ ቤተሱን ለማስተዳደር የሚጥር መሆኑን ትናገራለች። ያም ሆኖ በየጊዜው እየናረ በሚሄደው የኑሮ ውድነት ምክንያት ህይወታቸው ፈተና ውስጥ መውደቁ አልቀረም። ምወድሽና ቤተሰቧ ባለቤቷ በጦር ጉዳተኝነት ምክንያት በተሰጠችው ጠባብ ቤት ውስጥ ተጨናንቀው ይኖራሉ።
እምወድሽ ሁለቱን ልጆቿን ከወለደች በኋላ የተለያዩ ችግሮችን እንዳሳለፈች ትናገራለች። በባለቤቷ ደመወዝ የቤት አስቤዛ የትምህርት ቤት ክፍያና የተለያዩ ወጪዎችን እየሸፈነች በአስቸጋሪ የህይወት ፈተና ውስጥ አልፋለች። ታታሪዋ ወጣት ልጆቿ ራሳቸውን ባልቻሉበት ወቅት እንኳ ባገኘቸው አጋጣሚ ሁሉ የድሮ ደንበኞቿን ሹሩባ እየሠራች ኑሮዋን ለመደጎም ትጥር እንደነበር ትናገራለች። ልጆቿ እራሳቸውን መቻል ከጀመሩ ወዲህ ደግሞ ማንኛውንም አይነት ስራ እየሰራች ባለቤቷን ለማገዝ ወስናለች። በውሳኔዋ መሰረት አደባባይ ከወጣች ሰንበትበት ብላለች።
ስራ ወዳዷ ወጣት ሞዴል የመሆን የልጅነት ሀሳቧን እውን ማድረግ ባትችልም በጎዳና ጽዳት ላይ ተሰማርታ ዝቅ ብላ እየሰራች ለአካባቢው ማህበረሰብ ምሳሌ መሆን ችላለች። ምወድሽ ዛሬ በልደታ ከፍለ ከተማ ወረዳ 8 ቀበሌ 50 የሚገኙ አውራ ጎዳናዎችን በማጽዳት ኑሮዋን ለማሻሻል በመጣር ላይ ትገኛለች። ወደ ስራ የገባችበትን ሁኔታ እንዲህ ታስረዳለች።
‹‹ አንድ ቀን ቀበሌው በር ላይ የጎዳና ጽዳት ሰራተኛ ለመቅጠር የወጣ ማስታወቂያ አነበብኩና ተመዝግቤ ወደ ቤቴ ሄድኩኝ። ከዚያም ማታ ባለቤቴ ከስራ ሲመጣ ሁኔታውን ነገርኩት። በጣም ገረመው፤ ሞዴል ለመሆን ስትመኚ የነበርሽ ልጅ እንዴት እንዲህ ዓይነት ስራ ለመስራት ወኔ አገኘሽ አለኝ። ባለቤቴ ውሳኔዬ እየገረመውም ቢሆን አበረታታኝ። ውድድሩን አልፌ ስራ እስክጀምር ድረስ አላመነም ነበር። እኔ ግን ውስጤን አሳምኜዋለሁ። አረብ ሀገርም ተሂዶ የሚሰራው አንዱ ስራ ጽዳት ነው።
እንኳንም ተከፍሎኝ ይቅርና ሳይከፈለኝም ቢሆን የምኖርበትን አካባቢ ማጽዳት ጥቅሙ ለራሴ ጭምር እንደሆነ ተረድቻለሁ። ሰው ትልቅ ደረጃ ላይ የሚደርሰው ከትንሽ ተነስቶ ነው። እንደነገርኩህ ሞዴል የመሆን ህልሜ አልተሳካም ብዬ እጅ እግሬን አጣጥፌ መቀመጥ የለብኝም። ሞዴልነት በአለባበስና በአቋም ብቻ አይደለም። አሁንም በምሰራው ስራ ለአብሯደግ ጓደኞቼና ለአካባቢዬ ሰዎች ሞዴል እንደሆንኩ ይሰማኛል። አንዳንድ የአካባቢው ሰዎች በጎዳና ጽዳት ላይ ተሰማርቼ ሲያዩኙ ይገርማቸዋል። አንዳዶችም ያበረታቱኛል። ›› ትላለች እምወድሽ።
እምወድሽ የጎዳና ጽዳት በጀመረች ሰሞን የገጠሟት አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንደነበሩ ትናገራለች። ከሁሉም በላይ ከሌሊቱ አስር ሰዓት እየተነሳች ወደ ስራ መሄዱ ፈተና ሆኖባት ነበር። የምትኖርበት ሰፈር ከዋናው አውራ ጎዳና ወደ ውስጥ ስለሚገባ እስክትለምደው ድረስ ባለቤቷ ይሸኛት ነበር። አንድ ቀን ብቻዋን ተነስታ ስትሄድ የገጠማትን ሁኔታ እንዲህ ታስረዳለች።
‹‹ መኖሪያ ቤቴ ከልደታ ቤተክርስቲያን ጀርባ ነው። አንድቀን ባለቤቴን ላለማስቸገር በማሰብ ልክ ከሌሊቱ አስር ሰዓት ሲሆን ብቻዬን ወደስራ መጓዝ ጀመርኩ። በየበረንዳው ጥጋጥግ የጎዳና ተዳዳሪዎች ተኝተዋል። በአካባቢው የሚኖሩ አብዛኛዎቹ የጎዳና ተዳዳሪዎች ጎዳና ሳጸዳ ያውቁኛል። እንደውም ዘራፊ ቢገጥመኝ እንኳ ቀድመው የሚደርሱልኝ እነርሱ ናቸው ብዬ እመካባቸዋለሁ። በዚያን እለት የገጠመኝ ምን መሰለህ ? ልክ የውስጥ ለውስጡን መንገድ ጨርሼ አስፋልቱ ጋር ልደርስ ትንሽ ሲቀረኝ በርካታ ውሾች ከፊት ከኋላዬ ከበውኝ ይጮሁ ጀመር። እንዲህ አይነት ነገር ገጥሞኝ ስለማያውቅ በጣም ደንግጬ ጩኸቴን አቀለጥኩት። የሚደርስልኝ ሰው ጠፋ። ውሾቹ ጭራሽ ከበውኝ መፈናፈኛ አሳጡኝ።
አንዳዶቹ እንደውም የለበስኩትን ቱታ ሳይቀር ይጎትቱት ጀመር። በኋላ በጥበቃ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ደርሰውልኝ አስጣሉኝ። ውሾቹ ለካስ እንደዚያ ከበውኝ የጮሁት የለበስኩትን የስራ ልብስ አይተው ነበር። ውሻ ዘባተሎ ልብስ የለበሰ ሰው ላይ ለምሳሌ:- የኔ ቢጤዎች፤ ቆራሊዬ ሰራተኞች ላይ እንደሚጮህባቸው ትዝያለኝ ከዚያ በኋላ ነው። ከዚያ ጊዜ ወዲህ የስራ ልብሴን በፌስታል ይዤ በመሄድ ስራ ቦታ ስደርስ ነው የምለብሰው። ይህ የማልረሳው ገጠመኜ ነው። በስራው ሂደት የሚያጋጥሙኝን ቆሻሻዎች ሳልጠየፍ አጸዳለሁ። አንዳንድ ጊዜ እንደ ሰገራ፣ በደም የተለወሰ ጨርቅ ፣ የሞቱ እንሰሳት ምናምን ሊያጋጥመኝ ይችላል። ጓንት ስለማደርግ ሳልጠየፍ አነሳለሁ ።
አልፎ አልፎ ቀን ቀን ስንሰራ የሚገጥሙን ሰዎች ባህሪ ግን ያማርራል። አስፋልቱን አጽድተን አንድ ርምጃ ወደፊት ሳንሄድ መልሰው ቆሻሻ ይጥሉበታል። እንዴት እንደዚህ ታደርጋላችሁ ስንላቸው ደግሞ ስድብ ይቃጣቸዋል። ቆሻሻዎችን በቆሻሻ ማስወገጃ ቦታዎች የመጣል ልምድ የለንም።
እንዲህ አይነት ልምድ ብናዳብር በጽዳት ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎችን እናግዛለን። እንደምታየኝ እኔ ወጣት ነኝ። በዚህ ስራ ላይ የተሰማሩ በርካታ እናቶች አሉ። ሁሉም ሰው እናቱን በሚያከብርበት ልክ እነዚህን ሰዎች ማክበር ይኖርበታል። አንዳድ ሰዎች አስፋልት ለሚጠርጉ ሰዎች የሚሰጡት ግምት አናሳ መሆኑ ያሳዝነኛል። ማበረታታትና ማገዝ ሲገባቸው የሚያመነጫጭቁና የሚያንቋሽሹ አሉ። ለምን አቧራ ታቦኑብናላችሁ የሚሉም አሉ›› ትላለች እምወድሽ።
በጎዳና ጽዳት ከተሰማራች ዘጠኝ ወር ሆኗታል። ብርድ፣ ዝናብና ጸሀይን እየተቋቋመች ስራዋን ቀጥላለች። የሚከፈላት ገንዘብ ከምትሰራው ስራ አንጻር ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ትናገራለች። ግን ወጥታ መግባቷ ያስደስታታል። ከሁሉም በላይ ደግሞ በጽዳት ስራ ላይ ተሰማርታ ለከተማዋ እድገት የበኩሏን አስተዋጽኦ ማድረጓ ያኮራታል። ለነገ ህይወቷ የስራ ልምድ፣ ሞራልና አቅም ማግኘቷም እንዲሁ።
ዝቅ ብለው መስራትን እንደውርደት እየቆጠሩ ያለስራ የሚቀመጡ በርካቶች ናቸው የምትለው ምወድሽ ትንሹን ካላከበሩ ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ አይቻልም ትላለች። ምወድሽ ባለቤቷን ለማገዝ በስራ ላይ ብትሰማራም ዛሬም ኑሮዋ ከእጅ ወደ አፍ ከመሆን አልዘለለም። ለዚህም ትልቅ ምክንያት አድርጋ የምትጠቅሰው የኑሮ ውድነቱ እየተባባሰ መምጣቱ ነው። ለዚህም መንግስት እጁን በማስገባት ገበያውን እንዲያረጋጋ ትፈልጋለች።
ኑሮዬን ደረስኩበት ስል እልፍ ይልብኛል፤ ጨበጥኩት ስል ሹልክ ይልብኛል የምትለው እምወድሽ ጠንክራ በመስራት የፈተና ዘመኗን ለመሻገር እየጣረች መሆኗን ትናገራለች። የኑሮ ውድነቱ ግን ድካሟን ሁሉ መና እንዳስቀረው ትገልጻለች። መንግስት የኑሮ ውድነቱን አንድ ነገር እንደሚገባ ደጋግማ ታሳስባለች። ወጣቶች ከእምወድሽ የስራ ፍቅርና ታታሪነት ልምድ ቀምሰው እራሳቸው አሸንፈው ለመኖር ጥረት እንዲደርጉ ምክራችን ነው። ሳምንት በሌላ ባለታሪክ እስከምንገናኝ ቸር አንሰንብት።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን መስከረም 15/2014