ከተመሰረተ አስራ ሁለት ዓመታትን አስቆጥሯል። ስራውን የጀመረውም በአንዲት ሲቲ ስካን ማሽንና በስምንት ሰራተኞች ነው። በበርካቶች ዘንድ የሚታወቀውም ‹‹ ጳጉሜን ለጤና›› በሚል መሪ ቃል የመክፈል አቅም ላነሳቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በየዓመቱ የነፃ “ሲቲ ስካንና የኤም አር አይ” ምርመራ አገልግሎት በመስጠት ነው። በአገሪቱ ዲጂታል የኤክስሬይ ምርመራ ከሚያካሂዱ ጥቂት ማእከላት ውስጥም በግምባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።
በአንድ ሲቲ ስካን ማሽንና በስምንት ሰራተኞች ስራውን ጀምሮ ትልቅ ራእይ በመሰነቅ ራእዩንም ለማሳካት ተልእኮ በማስቀመጥ ላለፉት አስራ ሁለት ዓመታት የዲጂታል ኤክስሬ ምርመራ ሲያካሄድ ቆይቷል። በዚህ ሁሉ ሂደትም የበርካታ “ዲጂታል ኤክስሬይና” ሌሎች መመርመሪያ ማሽኖች ባለቤት ለመሆንና በርካቶችንም በስሩ ቀጥሮ ለማሰራት በቅቷል።
በአሁኑ ጊዜም በሌሎች የቢዝነስ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ እህት ኩባንያዎችን ከማቋቋም በዘለለ ወደ “መልቲ ስፔሽያሊቲ” ማእከል ለመሸጋገር የሚያስችለውን ግዙፍ የህንፃ ግንባታ እያከናወነ ይገኛል። ተቋማዊ ማህበራዊ ሃላፊነቱን ይበልጥ ለማስፋትም አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ነው- ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማእከል።
አቶ ዳዊት ሃይሉ የውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማእከል ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናቸው።‹‹ ውዳሴ›› በሚል ከዛሬ አስራ ሁለት ዓመት በፊት በባለቤታቸው ስም ነው ማእከልን የመሰረቱት። ይሁንና ዛሬ ላይ ማእከሉ በእህት ኩባንያዎቹ የሚሰሩትን ጨምሮ ሰባት መቶ ለሚሆኑ ሰራተኞች የስራ እድል ፈጥሯል። ከአንድ የሲቲ ስካን ማሽን ተነስቶ የሶስት ሲቲ ስካን ማሽን ባለቤት ለመሆንም ችሏል።ኤም አር አይ፣ አልታራሳውንድ፣ ኤክስሬ፣ አምቡላንሶችና ሌሎች የጂ አይ ዩኒት፣ ኢንዶስኮፒና ኮሎኖስኮፒን ጨምሮ የተለያዩ ለህክምና ምርመራ ትልቅ ጠቀሜታ ያላቸው መሳሪያዎችም አሉት።
ማእከሉ እምብዛም ባልተስፋፋውና አገልግሎቱም ውድ በሆነው የዲጂታል ኤክስሬ ምርመራ አገልግሎት ዘርፍ በመግባት በርካቶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል።ብዙዎችም ይህንኑ አገልግሎት ፈልገው ወደ ውጪ ሀገር ሄደው የውጪ ምንዛሬ እንዳያወጡ ታድጓል። እድሉን ላላገኙና የመክፈል አቅም ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችም ነፃ የምርመራ አገልግሎት እንዲያገኙ አመቻ ችቷል።
በተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ትርፍ ለማግኘት የየራሳቸውን ስትራቴጂ ነድፈው ይንቀሳቀሳሉ።አንዳንዶች የተለመደውን የቢዝነስ አካሄድ ተከትለው ብዙ ሳይራመዱ ከመንገድ ይቆማሉ።ሌሎቹ ደግሞ አዲስና ጊዜውን የዋጀ የቢዝነስ ስትራቴጂ ይዘው ብቅ ቢሉም የተነሱበትን አላማ ስተው እዚም እዛም ሲዳክሩ ለውደቀት ይዳረጋሉ።ጥቂቶች ግን በትክክል አቅደው ፤ እቅዳቸውንም ተግብረውና አፈፃፀማቸውን በተከታታይ ገምግምው በስኬት ላይ ስኬት ይደርባሉ። ከትውልድ ትውልድ ሲሻገሩ ይታያሉ።ውዳሴ ዲያጎኖስቲክ ማእከልም የጥቂቶችን የጥንካሬ መንገድ በመከተል ተሳክቶልኛል ሲል ይናገራል።
የማዕከሉ ባለቤት አቶ ዳዊት እንደሚሉት፤ ማእከሉ በአስራ ሁለት ዓመታት ሂደት ውስጥ ስራዎችን ሲሰራ የቆየው ተልእኮው ላይ አተኩሮ ነው።የማእከሉ ራእይም ይህንኑ ተልእኮ ያነገበ ነው።ወዴት መሄድ እንደሚፈልግም ራእይ አስቀምጧል።
ራእይ የሚፈጠርና የሚሰራ ነገር በመሆኑ ማንም ሰው የራእይ ችግር አለበት ተብሎ አይታሰብም።በሀገሪቱ የሚታየውና የአብዛኛው ሰውና የቢዝነስ ድርጅቶች መሰረታዊ ችግር ግን ተልእኮ ያለመኖር ነው።ተልእኮን ማወቅ ደግሞ ትልቅ ነገር ነው።ሰው ተልእኮውን ሲያወቅ ፤ የመጣበትንና የተቋቋመበትን አላማ ሲረዳ ራእይን መሰነቅ በጣም ቀላል ይሆንለታል።‹‹ውዳሴም ለአስራ ሁለት ዓመታት በአገልግሎት የዘለቀው ተልእኮውን በትክክል በማወቁና ራእዩን በመሰነቁ ነው›› ይላሉ ።
እንደ እሳቸው ገለፃ ስኬት ራእይን ማሳካት ወይም አንድን ነገር አስቦ ሃሳቡን እውን ማድረግ ነው።ይሁንና ስኬት አንድ ሰው ካስቀመጠው ራእይ ጋር የሚመጣጠን መሆን ይኖርበታል።ከራዕይ በኋላም ግብን በአግባቡ ማስቀመጥ የግድ ይላል።ራእይና ግብ ካለም ስልታዊ በሆነ መንገድ ድርጅትን መምራት ይቻላል።
በ21ኛው ክፍለ ዘመን ቢዝነስ (ንግድ) በራሱ ዘመናዊ ጦርነት በመሆኑና የተለየ ጥበብ የሚጠይቅ ከመሆኑ አኳያ ከራዕይና ግብ በኋላ ስልት (ስትራቴጂ) ማስቀመጥ ያስፈልጋል። ይህም ከተፎካካሪ የቢዝነስ ተቋማት፣ ከገበያውና ከአገር ኢኮኖሚ ጋር የሚደርገውን ጦርነት በአሸናፊነት ለመደምደም ያግዛል፡፡
ያለ ስልት አንድ እርምጃ መራመድ የውድቀት መሰረት ይሆናል። ከስልት በተጨማሪ እርሱን ለመጠቀም የሚያስችሉ “ታክቲኮች” ከሌሉም እድገት ቢኖርም እድገቱ አዝጋሚ ይሆናል።የስኬት ቁልፉም ስልታዊ እቅድ ነው። ይህን የሚሰሩ ድርጅቶች ስኬታቸው ፈጣን ይሆናል።
አቶ ዳዊት ‹‹በኢትዮጵያ በርካታ የቢዝነስ ድርጅቶች በየግዜው የሚከፈቱ ቢሆንም አብዛኛዎቹ ስልታዊ ስትራቴጂ ስለሌላቸው ለመሞት ቅርብ ናቸው›› ይላሉ። ከዚህ አኳያ ስልታዊ እቅድና ስልታዊ ትግበራ እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ። ማቀድ አንድ ነገር ሆኖ ሳለ የታቀደውን ደግሞ መተግበር የግድ እንደሚልም ያሳስባሉ። መተግበርን ለማወቅ ደግሞ የተከናወኑ ስራዎችን ቆም ብሎ መከለስ እንደሚገባ ያመለክታሉ።ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማእከል በአስራ ሁለት ዓመታት ቆይታው ፈጣን እድገት ማምጣት የቻለውም ይህንኑ ስልታዊ መንገድ በመከተሉ ነው ባይ ናቸው ።
እንደ አቶ ዳዊት ማብራሪያ ማእከሉ ስልታዊ እቅድ ያወጣል፤ እቅዱን ይተገብራል እንደገና ደግሞ ክንውኖቹን መለስ ብሎ ይገመግማል።ክፍተቶቹን በማየትም ያሻሽላል። እታች ድረስ ካሉ ሰራተኞች ጋር መግባባት ፈጥሮ ይሰራል።ከዚህ አኳያ ይህን ተሞክሮ ሌሎችም ቢጠቀሙበት የተሻለ ውጤት ማምጣት ይችላሉ።
‹‹እቅድ በአማካሪዎች ሊሰራ ቢችልም ትግበራውን የሚያከናውነው ማኔጅመንቱ ነው›› የሚሉት አቶ ዳዊት ይህን መተግበር የሚችል የሰው ሀይል አለ ወይ? የሚለውም ከግምት ውስጥ መግባት እንዳለበት ይጠቁማሉ ። አንድ የቢዝነስ ድርጅት ጥሩ ስልታዊ እቅድ ኖሮት ደካማ ስልታዊ ትግበራ ወይም አፈፃፀም ካለው የአመራር ችግር እንዳለበት ያሳያል ሲሉ ይናገራሉ።
የአመራር ችግር ባይኖርበት እንኳን በቂ በጀት ወይም የግብዓት ችግር ሊኖርበት እንደሚችልም ይጠቅሳሉ። ከዚህ አኳያ ድርጅቱ ቆም ብሎ አመራሩን መፈተሸና መቀየር አልያም ደግሞ ያለበትን የበጀት ወይም የግብአት ችግር ማስተካከል እንደሚጠበቅበት ይመክራሉ።
ከዚህ በተገላቢጦሽ ደግሞ አንዳንድ የቢዝነስ ድርጅቶች ደካማ እቅድ ኖሯቸው እጅግ በጣም ጥሩ አፈፃፀም ያላቸው ከሆኑ ደግሞ አካሄዳቸው ጤናማ ባለመሆኑና እቅዳቸው ላይ ችግር በመኖሩ ለአፍታ ቆም ብለው ራሳቸውን በመፈተሽ እቅዳቸውንና አካሄዳቸውን ማስተካከል እንደሚገባቸው ያሳስባሉ።በሌላ በኩል ደግሞ እቅዳቸውም፤ አፈፃፀማቸውም ደካማ ከሆነ ወደ መዘጋት የሚያደርስ በመሆኑ ሁለቱንም ሙሉ በሙሉ ማስተካከልእንደሚኖርባቸው ይጠቁማሉ።
ከዚህ አንፃር ‹‹እቅድ የሚታይ፣ የሚገመገምና የሚከለስ መሆን ይኖርበታል›› ይላሉ አቶ ዳዊት። በተመሳሳይም እቅድን ሊተገብር የሚችል ጥሩ ማኔጅመንት ይዞ መሄድ እንደሚያስፈልግም ይገልፃሉ። ለዚህም ተከታታይነት ያለውና የማያቋርጥ ክለሳ ማድረግ እንደሚገባ ይመክራሉ። ይህንንም በማድረጉ ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማእከል ውጤታማና ስኬታማ ስለመሆኑ ይመሰክራሉ።
አቶ ዳዊት እንደሚሉት ከማእከሉ ስኬት ማሳያዎች ውስጥ አንዱና የመጀመሪያው ፈጣን እድገቱ ሲሆን ከራሱ አልፎ ሌሎች እህት ኩባንያዎችን መፍጠር ችሏል። በስሩ ‹‹ጆርጎ አካዳሚ›› የተሰኘ ትምህርት ቤት ከፍቷል።‹ ‹አኮ ኮፊ›› የሚል ቡናና ሬስቶራንትም አቋቁሟል።‹‹ፍቱን›› ቴክኖሎጂ ሶሊዩሽን እንዲሁም “ኤልስሜድ ሄልዝ ኬር ሶሊዩሽን” የተሰኘ የህክምና መሳሪያዎችን ከውጪ ሀገር የሚያስመጣ ተቋምም መስርቷል።
በሌላ በኩል ደግሞ አሁን በደረሰበት ደረጃ በአገሪቱ ትልቅ የተባለ የራሱን “የመልቲ ስፔሻሊቲ ማእከል” ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ አስቀምጧል።በቅርቡም ግንባታ ጀምሯል።ይህም እ.ኤ.አ በ2017 ለመገንባት አቅዶት የነበረውና እ.ኤ.አ በ2021 ላይ ወደ ተግባር የገባበትና እ.ኤ.አ በ2023 ላይ ተጠናቆ ስራ የሚጀምረው ፕሮጀክት ሲሆን እንደ ሁለተኛ የማእከሉ ስኬት ማሳያ ሆኖ ይቆጠራል።
በሌላ በኩል ማእከሉ የሃምሳ ዓመት እቅድ ያወጣ ሲሆን ከአምስት አስርት ዓመታት በኋላ ምን ደረጃ ላይ እንደሚደርስ አስቀድሞ ያውቀዋል።በተመሳሳይ ከመቶ ዓመት በኋላም ውዳሴ ምን ደረጃ ላይ እንደሚደርስ እቅድ አውጥቷል።ለዚህም ሳይንገራገጩ መቶ እና ሀምሳ ዓመታትን የዘለቁ ብሎም ከነዚህ ዓመታት በኋላ የከሰሙ የቢዝነስ ድርጅቶችን መረጃና ተሞክሮ በግብአትነት ወስዷል።ማእከሉ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር የዛሬን ብቻ ሳይሆን የቀጣዩንም ያቅዳል።
ከዚህ በኋላም ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማእከል በዘንድሮው በጀት ዓመት የጀመረውን ባለ20 ወለል ህንፃ “የመልቲ ስፔሽያሊቲ ማእከል” ግንባታን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ ይዟል።ይህንኑ ግንባታም በአጭር ግዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ በሙሉ ዝግጅት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።ግንባታውን ካጠናቀቀ በኋላም ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማእከል ወደ መልቲ ስፔሺያሊቲ ሴንተር ይቀየራል ተብሎ ይጠበቃል።
ተቋማዊ ማህበራዊ ሃላፊነቱን በመወጣት ረገድም ማዕከሉ የታወቀ ሲሆን ከተመሰረተበት ግዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ይህንኑ ተግባር አጠናክሮ ቀጥሎበታል።ተቋማዊ ማህበራዊ ሃላፊነትን መወጣትም የተልዕኮው አንዱ አካል አድርጎታል።እንደ አንዱ የማእከሉ ስልታዊ እቅድም ተካቷል።ከሚያገኘው ገቢም ሃያ ከመቶውን መልሶ ለማህበረሰቡ ለመስጠት እቅድ ይዟል።ይህንንም ከእቅዱ በላይ እያከናወነው ይገኛል።ይህም ማእከሉን ከማህበረሰቡ ጋር ያገናኘውና ዜጎችም ለማእከሉ ቀና አመለካከት እንዲኖራቸው አስችሏል።
እስካሁን ባለው ሂደትም ማእከሉ ‹‹ጳጉሜን ለጤና›› በሚል መሪ ቃል ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ በአቅም ምክንያት ምርመራ ማድረግ ላልቻሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ነፃ የሲቲ ስካን፣ ኤም አር አይ፣ አልትራሳውንድ፣ ኢኮ፣ራጅና ጂ አይ (ኢንዶስኮፒና ኮሎኖስኮፒ) ምርመራ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል።
እስካሁን በተካሄደው የበጎ አድራጎት ስራ ብቻ 17 ሺ ያህል ሰዎች የነፃ ምርመራ አገልግሎቱ ተጠቃሚ ሲሆኑ ማእከሉ ከተመሰረተበት ግዜ አንስቶ ባሉት አስራ ሁለት ዓመታት ሙሉ 47 ሺ አቅም የሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በተመሳሳይ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን ችለዋል።
በኢትዮጵያ “የጤናው ዘርፍ” ገና እያደገ ያለ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ዳዊት ዘርፉን ለማሳደግ በመንግስትና በግል መካከል አብሮ የመስራት ሁኔታ በተግባር የታየበት እና የተሻለ ውጤት የተገኘበት መሆኑን ይጠቁማሉ። ማእከሉ የመልቲ ስፔሻሊቲ ማእከል ግንባታ እያከናወነ የሚገኘውም መንግስት በሰጠው ቦታ ላይ በመሆኑ በዚህ አጋጣሚ የከተማ አስተዳደሩንና የጤና ሚኒስቴርን ከፍ ያለ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን መስከረም 15/2014