“ታሪክ ራሱን ደግሞ ይከሰታል ወይንስ አይሞክረውም?”፤ የሩቅ ዘመን ክርክር ያቆረፈደውን ይህንን ጥያቄ ዳግም ቀስቅሰን ለመሸናነፍ “በጉንጭ አልፋ” አታካራ “ንሳ በል ጃል!” እያልን መሟገቱ እጅግም ፋይዳ የለውም።ይሁን እንጂ የአንዳንድ ዘመናት ክስተቶች፣ ድርጊቶችና ታሪኮች በርካታ ዓመታትን ተሻግረውም ቢሆን በሚታወቁበት መለያቸው የዓይነትም ሆነ የባህርይ ልዩነትና ለውጥ ሳያሳዩ ሲከሰቱ ማስተዋላችን እንግዳ አይደለም።ይህን መሰሉ ክስተት የተደጋገመ ባይሆንም አልፎ አልፎ ግዘፍ ነስቶና ዳግም ነፍስ ዘርቶ ስናስተውል መገረም ብቻ ሳይሆን ለተለየ ምርምርም ሊጋብዝ፡፡
ዘመን የራሱ ዐውድ፣ የራሱ መገለጫ እንዳለው የታወቀ ነው። እርግጥ ነው ባህል፣ ቋንቋ፣ ወግና የእምነት ቀኖናን የመሳሰሉ የማሕበረሰብ ጠንካራ እሴቶች ከዘመን ጉዞ ጋር ፈጥነው እንደማይለወጡ ቢታሰብም መጠነኛ መሻሻልና እጅግም ባልጎሉ ለውጦች ከትውልድ ትውልድ መተላለፋቸው በሌላ ገጽታው የሚፈተሽ ስለሆነ ከታሪክ ጉዳይ ጋር አይጎዳኝም፡፡
ከቅርጽና ከይዘት አንጻር ታሪክ እንደነበረ ራሱን ደግሞ ማስተዋል ብዙ ጊዜ የሚከሰት እውነታ አይደለም።“ይደገማል እንጂ!” የሚል መከራከሪያ የሚቀርብ ከሆነ አንድም የታሪክ ፈጻሚዎቹ ቀደምቶ ቻቸው በተጓዙበት መንገድ ተቸክለው በመቆም ሳይነቃነቁ ከዘመን ጋር ተኳርፈዋል ወይንም ታሪክ ራሱን በራሱ ደግሞ ሻምፒዮና በመሆን ሊሳለቅባቸው ፈልጎም ሊሆን ስለሚችል በዚሁ አኳያ መረዳቱ ይበጃል።ይህንን የጠነነ ፍልስፍና ከራሳችን ታሪክና ወቅታዊ ሁኔታ አኳያ የታሪክ ሰነዶችን እየፈተሽን ለማየት እንሞክር፡፡
የምሥረታው ምክንያት እንደሚባለው በሀገራችን ሰፍኖ የነበረውን ፊውዳላዊ ሥርዓት በመቃወምም ይሁን ወይንም ሌላ ዓላማ ይኑረው ብቻ ዋናው ጉዳይ እርሱ ስላይደለ ዝርዝሩን ትተን ዋና ዋና አንኳር ሃሳቦችን በመጠቃቀስ ስለ “የትግራይ ሕዝብ ቀዳማይ ወያነ” አመሠራረትና ስለፈጸማቸው ድርጊቶች ከዛሬው አሸባሪና ግፈኛ ልጁ “ከዳግማዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ” ጋር በማነጻጸር እንደምን ታሪክ ራሱን እንደደገመ በጥቂቱ ለመቃኘት እንሞክራለን፡፡
ቀዳማይ ወያነ ትግራይ በ1934 ዓ.ም በዋጀራት አካባቢ ተጠንስሶና የእንደርታ ሕዝብ ቀኝ እጁን ሰጥቶት የተወለደው በ1935 ዓ.ም መሆኑን በበርካታ የታሪክ ድርሳናት ውስጥ ተጠቅሶ እናገኛለን። የመቋቋሙ ዋነኛ ተልዕኮ “የትግራይ ሕዝብ ማንነት እንዳይረገጥና እንዳይጠፋ የተደረገ ትግል ሲሆን የአንድ የተወሰነ አካባቢ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ቀስቅሶ የትግራይን ሕዝብ ብሔራዊ አንድነት ለማረጋገጥ የተነሳና…የፀረ አማራ ገዢ ሥርዓትን የተቃወመ የተጋድሎ አንቅስቃሴ ነው። (የህወሓት ሕዝባዊ ትግል ከ1967 – 1992፤ ገጽ 21) ይለናል ዋቢ ያቆምነው ሰነድ። በዚህ እንቅስቃሴ ወቅት ከተፈጸሙት እጅግ ዘግናኝ የግፍ ድርጊቶች መካከል ከፊሎቹን ብቻ በመረጃ አጣቅሰን እንዘክራቸው፡፡
“የቀዳማይ ወያነ የጎበዝ አለቆች የአገሬውን ጦር እየመሩ ኩሕያ ከተባለው ቦታ ላይ ሠፍሮ በሰላም ከተቀመጠው የጦር ሠራዊት ላይ አደጋ ጥለው ብዙ የጦር ሠራዊት ገደሉ። የጦሩ አዛዥ የነበሩትን ሻለቃ/በኋላ ጄኔራል ኢሳይያስ ገብረ ሥላሴን ማረኩ…።ቀጥሎም መቀሌ ከተማ መስከረም 9 ቀን 1936 ዓ.ም ገብተው የሕዝቡን ሀብትና ንብረት ዘረፉ።ዕቃ ተደብቆበት ይሆናል በማለትም የቤት ኮርኒስ ሳይቀር አፈረሱ፡፡”
“መቀሌን እጅ ካደረጉ በኋላ የትግሬን ጠቅላይ ግዛት አጠቃለው በእጃቸው ሳያስገቡ የወሎን ጠቅላይ ግዛት በእጃችን ካደረግን በኋላ መንግሥት እናቋቁማለን ለማለት ይመስላል፤ ለመንግሥትነት ያጯቸውን የልዑል ራስ ጉግሣን ልጅ “ልጅ በኩረ ጽዮን” የተባሉትን ይዘው ወደ ወሎ ጉዞ እንደጀመሩ…ከመንግሥት ጦር ጋር በጥቅምት ወር 1936 ዓ.ም አምባላጌ ላይ ጦርነት ገጥመው ወያነ ተቸነፈ፡፡…ምንም የማያውቀው ተንኮልና ክፋት የሌለውን አርሶ የሚበላውን ገበሬ አነሳስተው የኩሕያንና የመቀሌን ከተማ ሕዝብ ሀብትና ንብረት እንዲዘረፍ፤ እነርሱን ተከትሎ የወጣው ባላገር ብዙ ጉዳት እንዲደርስበት ከአደረጉ በኋላ ሕዝቡን ጥለው ሸሽተው ጠፉ፡፡” [የዓፄ ኃይለ ሥላሴ ታሪክ፤ በሪሁን ከበደ፤ ገጽ 700-701።የደም ዕንባ፤ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ፤ ገጽ 141።ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ፤ ገብሩ አሥራት፤ ገጽ 22-23]፡፡
ይህ የቀዳማይ ወያነ ታሪክ ከዛሬው አሸባሪ “ዳግማዊ” ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት ወይንም ትህነግ) በምን ሊለይ ይችላል? አንባቢው ግጥምጥሞሹን በማሰላሰል የራሱን ብያኔ ቢሰጥበት የተሻለ ይሆናል።ለማሰላሰያነት ይረዳን ዘንድ ከስምንት ዐሥርት ዓመታት በፊት የተፈጸመውን ይህንን ታሪክ ከዛሬው የአሸባሪው ቡድን ተልዕኮ ጋር እያነጻጸርን አንዳንድ እውነታዎችን እንምዘዝ፡፡
የቀዳማይ ወያነ አስኳል ዓላማ “የፈረደበት አማራ” ላይ ማነጻጸሩን ልብ እንበል።ለመሆኑ በፊውዳሉ ሥርዓተ መንግሥት የአገዛዙን ማሽነሪ ሲዘውሩ የነበሩት “የአማራ ገዢዎች” ብቻ ነበሩን? የተጎዳውና ማንነቱ የተረገጠውስ በውኑ በተለየ ሁኔታ የትግራይ ሕዝብ ብቻ ነበርን? የምሥራቁ፣ የደቡቡና የምዕራቡ ሕዝባችን ከጭቆና ነፃ ነበርን? በንጹህ ህሊና ሊመለሱ የሚገባቸው ቀዳሚ ጥያቄዎች ናቸው፡፡
የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ካከተመ ገና ሙት ዓመቱ ሳይዘከርና ከዐውደ ግንባር በተመለሰበት ማግሥት እድል ቀናን ብሎ ቁስሉና ሥነልቦናው ያልጠገገውን፤እንደዚያም አንኳን ሆኖ የሉዓላዊነት ዘብ ሆኖ ከቀበሮ ጉድጓድ ገና ያልወጣውን የጦር ሠራዊት ልክ እንደ ወራሪው ፋሽስት መጨፍጨፍ በውኑ “የነፃነት ፍለጋ ተጋድሎ ነው” ወይንስ የተደበቀ የታሪክ በቀል ቢኖር? ምንስ ቢሆን ህሊና ያለው ፍጡር ገና ባልተረጋጋ የጋራ ሀገራዊ መንግሥት ላይ ልክ እንደ ወራሪ ጠላት ጦር ሰብቆ ይዘመታል? የሠራዊቱን አዛዥስ እንደ ፋሽስት ወራሪ መማረክን ምን ይሉታል? የራሳቸውን ከተማ መቀሌን ወሮ የእኔ የሚሉትን ሕዝብ ሀብትና ንብረት ማውደምንስ ምን አመጣው? ምንስ የተደበቀ ዓላማ ቢኖራቸው? የታሪክ ባለሙያዎች ይህንን የታሪክ አሻሮ “ከጎታ ውስጥ” አውጥተው ዳግም ሊያነፍሱትና ሊያበጠሩት ይገባል።
የያኔውን “የወሎ ጠቅላይ ግዛት” በእጅ ለማስገባት መሞከርስ ምን ምክንያት ይሰጥበታል? “ፈረስ ቢጠፋባት ቡሃቃ ውስጥ ፈለገች”ን ተረት አያስተርትም? መቼም በምኞት የሰከረ ጭንቅላት ያመዛዝናል ባይባልም “ማዕከላዊውን መንግሥት ከተቆጣጠሩ በኋላስ” ሀገሪቱን ሊመሩ አስበው የነበረው በምን ዓይነት ርዕዮተ ዓለም ነበር? ለዙፋን አጭተዋቸው የነበሩት ግለሰብስ በርግጡ “ኢትዮጵያን እንዲመሩ” ወይንስ ሌላ የማፍረስ ተልዕኮ ቢኖራቸው? ለመሆኑ እንደዚያ እንዲያስቡ ያስገደዳቸው የሥልጣን ርሃብ እጃቸው ገብቶ ቢያጠግባቸው ኖሮ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ምን መልክ ይኖራት ነበር? ምስኪኑን የትግራይ አርሶ በሌ እንደ እሳት እራት ማግደው እነርሱ ወደ ኋላ ማፈግፈጋቸውስ ምን ስያሜ ሊሰጠው ይችላል?
እነዚህ ዝርዝር ጥያቄዎች የሚያጭሩብን እውነታዎች የዛሬው አሸባሪ “ዳግማዊ ወያኔ” የተፈጠረበትን ዓላማ ፍንትው አድርጎ ስለሚያሳየን “የማን ዘር ጎመን ዘር”ን ብሂል እያስታወስን ፍተሻችንን እንቀጥል።ይህ ህወሓት ይሉት አሸባሪና ጨካኝ ጁንታ የአባቶቹን ዓላማ አንድም ሳያዛንፍ ለመተግበር የሚፍጨረጨረው ሥረ መሠረቱ የታነጸው በቀዳሚው ወያኔ ቅዠት ላይ ስለመሆኑ ቅንጣት ያህል ልዩነት የሌላቸውን የቅርቦቹን የግፍ ድርጊቶች እየዘረዘርን መመልከት ይቻላል፡፡
አሸባሪው ህወሓት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጀግናውን የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊታችንን ክህደት ፈጽሞበት ከጀርባና ፊት ለፊት የወጋው የአባቶቹን የ1935 ዓ.ም የጭካኔ ታሪክ ደግሞ የቅዠት ህልማቸውን እውን ሊያደርግ ስለመሆኑ የሚያከራክር አይደለም።ወቅቱንም ስናይ ሀገሪቱ ከኢህአዴግ የባርነት ቀንበር የተላቀቀችበት የሽግግርና የመቋቋሚያዋ ዋዜማ ስለነበር ከዚህ የተሻለ ጊዜ አይኖርም ብሎ በማሰብ ያደረገው እንደነበር ለክርክር የሚቀርብ አይደለም።ልክ ቀዳማይ ወያነ በፋሽስት ወረራ የድል ማግሥት የኢትዮጵያ መንግሥት ተዳክሟል፣ ፈራርሷል ስለዚህም አስተዳደሩ አቅም የለውም ብሎ እንዳሰበው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
ይህ አሸባሪ የትህነግ ቡድን ዛሬ እየፈጸማቸው ያሉትን የግፍና የእልቂነት ተግባራትን የሚከውነው የአባቶቹ የሙት መንፈስ (ኤኬራ) “በል! በል!” እያለው መንፈሱን ስለተቆጣጠረው እንደሆነ ብዙ ማሳያዎችን መዘርዘር ይቻላል።ጉዳዩ “ያዳቆነ ሠይጣን ሳያቀስ አይቀርም” ሆኖበት እንጂ ለምን የአማራን ክልል ሊወር ፈለገ? ለምንስ ሰላማዊውን የአፋር ክብር ተዳፈረ? ከጎንደር ጋር ምን ጉዳይ አለው? በተለየ ሁኔታ ወሎን ለማጥፋትስ ለምን ጥርሱን ነክሶ ያንን ሁሉ ዕልቂት ሊፈጽም ፈለገ? “ኮርኒስ ውስጥ የተደበቀ ነገር ይኖር ይሆናል” በማለት አባቶቹ የራሳቸውን ሕዝብ እንዳስጨነቁት ሁሉ ዛሬም የጣዕረ ሞት መንፈሱ የተጋባባቸው ልጆቹ የደሃውን ቤት እየበዘበዙ፣ የበሉትን በልተው የተረፈውን እያቃጠሉና እንስሳትም ሳይቀሩ እየጨፈጨፉ የግፍ ዋንጫ መጎንጨት ምን ይሉት በላዔ ሰብነት ነው?
ለአቅመ እውቀት ያልደረሱ ሕጻናትንና አርሶ አደሮችን አሰልፎ የባሩድ ማብረጃ ማድረጋቸውስ በርግጥም “ለአርነታቸው” ሲሉ የሚያደርጉት ነው ወይንስ በደም የተጨማለቀው እጃቸውና ህሊናቸው እያቅበዘበዛቸው? ምስኪኑ ሕዝብ እንደ እሳት እራት በጦርነት ወላፈን ሲለበለብ ዋነኞቹ ስምሪት ሰጭዎች የት ናቸው? ከዚህ በላይ ታሪክ ራሱን ስለመድገሙስ ምን ማስረጃ ማቅረብ ያስፈልጋል?
ሃሳቤን ለመጠቅለል የሚያግዘኝን አንድ በሳይንሳዊ የምርምር ውጤት ይፋ የሆነ የማጣቀሻ ወሽመጥ አስታውሼ ርዕሰ ጉዳዬን ልሸምልል።በቅርቡ ኒውስ ዊክ የተባለው ዝነኛ የአሜሪካኖች ሳምንታዊ ዓለም አቀፍ መጽሔት ዘመንን ከዘመን የሚያቆራኝ አንድ የምርምር ውጤት አስነብቦ ነበር።የምርምሩ ዋነኛ ትኩረት ባለፉት ሺህ ዓመታት ውስጥ የሰው ልጆች ዘረ-መል (deoxyribonucleic acid, DNA) እንዴት ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ ሲወራረስ እንደኖረ በዝርዝር የሚያስረዳ የጥናት ውጤት ነው፡፡
በግል መረዳቴ የቀዳማይ ወያነ “ዘረ-መል” የዛሬውን አሸባሪ የህወሓት ቡድን መፍጠሩ ብቻ ሳይሆን በቀጣይነትም መሰል አሸባሪ የጥፋት ቡድኖች እንዳይፈለፈሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማያዳግም ሁኔታ ይህ የትግራይና የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት ከሥሩ ተነቅሎ ሊወገድ ይገባል፡፡
የአሸባሪው ቡድን እስትንፋሶችና አቀንቃኞች ያልተረዱት ትልቁ ምሥጢር ወረራው የትዬለሌ የሆኑ ሀገራዊ፣ ሰብዓዊ፣ ቁሳዊና ኢኮኖሚያዊ መስዋዕትነት እያስከፈለ ቢሆንም ከመርገምቱ ውስጥ ባዕዳኑ ብሂለኞች “A blessing in disguise” እንዲሉ በረከቶች እየተገኙ መሆኑን ነው።ይህንን የአሸባሪውን የትህነግ ወረራ ተከትሎ የብዙ የአፍሪካ ሀገራት አርአያ ሰብ ዜጎች የፓን አፍሪካኒዝምን መንፈስ አጋግለው እያነቃቁ ይገኛሉ።ይህ አንዱ ትሩፋት ነው።አሜሪካና አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት በኢትዮጵያ ጉዳይ እጃቸውን እየዘረጉ መፈትፈታቸው ገሃድ እየወጣ በመሄዱ “የአፍሪካ ጉዳይ በአፍሪካዊያን ብቻ ሊፈታ ይገባል” የሚለው መርህ ተጠናክሮ እንዲስተጋባ ምክንያት ሆኗል።“ነፃና ገለልተኛ” ሲባሉ የኖሩት በርካታ የዓለማችን የመገናኛ ብዙኃንና በተራድኦ ስም ሲንቀሳቀሱ የኖሩ ድርጅቶችም እስከ ዛሬ ደብቀው ያኖሩት ሴራቸው ይፋ እየተገለጠ እርቃናቸውን እንዲታዩ ሀገራዊ ችግራችን የማይናቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል፡፡
ከሁሉም በላይ ግን በዚህ አሸባሪ ቡድን ወረራ ምክንያት በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ጥቃቱን ለመመከት ልብ ለልብ ተናበውና እጅ ለእጅ ተያይዘው “እምቢኝ ለወራሪው አሸባሪ ቡድን!” እያሉ ሲፎክሩና ቃላቸውን በተግባር ሲያረጋግጡ መመልከት እንደምን አያስደስት! እንደምንስ አያኮራ! የወያኔ ግባ መሬት በቅርቡ መፈጸሙ እንደተጠበቀ ሆኖ ይህ ሕዝባዊ ድል ለወደፊቱም መሰል ቡድኖች በመሰል ቅዠት ተነሳስተው እንዳይንፈራገጡ ትልቅ ትምህርት የሰጠ ስለሆነ “ልብ ያለው ልብ ይበል!” መልእክታችን ነው።ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ መስዋዕትነትና በፈጣሪዋ ተራዳዒነት በክብር ለዘላለም ፀንታ ትኖራለች።ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን መስከረም 15/2014