የጥርስ ህመም ከካንሰር ቀጥሎ ከባድ የሚባል የህመም ዓይነት ነው። ብዙ ጊዜም ታካሚዎች ከህመሙ ለመዳን ሲሉ ጥርሳቸው እንዲነቀል ሀኪሙን ሊያስገድዱ ይችላሉ። እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎች ቢኖሩም ታማሚው ጥርሱ በመነቀሉ ሊያጣቸው የሚችሉ ነገሮችን በማስረዳትና ጥርሱን ከመንቀል በሌላ ህክምና ማዳን ያስፈልጋል።
የጥርስ መቦርቦር፣ የድድ በሽታ፣ የአፍ ካንሰር፣ የአፍ ውስጥ ኢንፌክሽኖችና የመሳሰሉት በብዛት የሚከሰቱ የጥርስ በሽታዎች ናቸው። እነዚህ የጥርስ በሽታዎች በርካቶችን ለስቃይ እየዳረጉ ይገኛሉ። ከ60 እስከ 70 የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ 30 በመቶ የሚሆኑ አዋቂዎች የተፈጥሮ ጥርስ እንዳይኖራቸው ማድረጉን የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ያሳያል። የህመም ስሜት የማይሰማቸው ነገር ግን ጥርሳቸው ተፈጥሯዊ ይዘቱን የለቀቀ፣ የጠቆረ፣ የተቦረቦረ እና ሌላ የጥርስ ችግር ያለባቸውን ማየት የተለመደ ሆኗል።
የጥርስ ሕመም መንስኤዎች
ጤናማ ያልሆነ የአመጋገብ ሥርዓት፤ ሲጋራ ማጨስ፤ ከባድ አልኮሎችን መጠጣት፤ የአፍ ንፅህና አጠባበቅ ችግርና ሌሎችም ለችግሩ መንስዔ ናቸው። በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለችግሩ ያላቸው ተጋላጭነት ከፍተኛ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ። በአፍ ውስጥ የተለያዩ ባክቴሪያዎች ይገኛሉ እነዚህ ባክቴሪያዎች ምግብ ሲያገኙ አሲድ በማምረት ጥርስ እንዲቦረቦር ያደርጋሉ፤ የጨጓራ ህመምና አብዝቶ ማስመለስም ሌሎቹ የጥርስ በሽታ መንስኤዎች ናቸው። ጥርስ ማንኛውንም ምግብ አድቅቆ ወደ ጉሮሮ ከመላክ ባለፈ ሰዎች የተስተካከለ የፊት ቅርፅ እንዲኖራቸውም ወሳኝ ነው። የፈገግታ ማድመቂያ ጌጥም ነው።
የሕክምና መፍትሄዎች
የጥርስ ንፅህና አጠባበቅ የሚጀምረው ልጆች ጥርስ ማብቀል ከጀመሩበት ከስድስት ወር ጀምሮ ነው። ጥርስ ከመብቀሉ በፊትም ቢሆን የሕፃናት ድድ በንፁህ ጨርቅ ሊፀዳ ይገባዋል። ጠዋትና ማታ ጥርስን በአግባቡ ማፅዳትም ለጥርስ ጤና ወሳኝ ነው። ጥርሳችን በጥንቃቄ ከያዝነው በዕድሜ ዘመናችን ሁሉ እንዲያገለግለን ሆኖ የተዘጋጀ ነው። ከሰውነት ክፍላችን ሁሉ ጠንካራው የጥርሳችን የውጭው ክፍል ኢናሜል ነው። ጥርሳችንን በጥንቃቄ መያዝ ከቻልን በቀላሉ የሚጎዳ አይደለም በማለት ጥርስ የሚጎዳው በጥንቃቄ ሳይያዝ ሲቀር የሚፈጠሩ ጥቃቅን ቀዳዳዎች ስለሚሰፋ እንደሆነ ይናገራሉ።
ጥርስ ተቦርቡሮ ነገር ግን ምንም ዓይነት ስሜት ገና ካልተፈጠረ በቀላሉ በመሙላት ማከም ይቻላል። በቀላሉ የሚቆም የህመም ስሜት ተፈጥሮም የተቦረቦረን ጥርስ በመሙላት ማከም ይቻላል። ነገር ግን ብዙዎች ወደ ህክምና መስጫ የሚሄዱት ዴንቲን የሚባው ሁለተኛው የጥርስ ክፍል ከተነካ በኋላ ነው። እንዲያም ሆኖ ጥርስን መንቀል ብቸኛ አማራጭ አይሆንም።
ታማሚው ከባድ ህመም ላይ ቢደረስ እንኳ የጥርስ ህክምና በማድረግ ጥርሱን ከመንቀል ማዳን ይቻላል። ጥርስ መንቀል እጅግ በጣም የመጨረሻው አማራጭ ነው። ይሁንና ብዙዎች መንቀልን እንደ አንድ አማራጭ እንደሆነም አድርገው ይጠቀሙታል።
መከላከያ መንገዶች
በትንሹ ከሁለት እስከ አምስት ደቂቃ ድረስ ሁሉንም ጥርሶቹን በተገቢው መጠን ሊያፀዳ ይገባል። የጥርስን ጤና ለማስጠበቅ ተገቢውን የአቦራረሽ ቴክኒክና ሰዓት ተጠቅሞ ማፅዳት የግድ ያስፈልጋል። የጥርስ ህመም ለልብ፣ ለስኳርና ለሳንባ በሽታዎች ያጋልጣል። በስትሮክ የመሞት ዕድልን በእጥፍ ይጨምራል። አብዛኛዎቹ የታሸጉ ውሃዎች የፍሎራይድ እጥረት አለባቸው።
ምንጭ፡- ከሀኪም ቤት ዶት ኮም
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን መስከረም 15/2014