በጤናውም ሆነ በሌላው ዘርፍ ብዙውን ጊዜ የመረጃ አያያዝና አደረጃጀት ችግር በአዳጊ ሃገራት ውስጥ ስር ሰደው የሚታዩ ችግሮች ናቸው። በተለይ በጤናው ዘርፍ ከመረጃ እና አገልግሎት ጋር ተያይዞ ውስብስብ ችግሮች ይታዩበታል። በተቃራኒው ደግሞ የሕክምና መሠረተ ልማታቸው በተስፋፋባቸውና በበለጸጉት ሃገራት፤ ይህ አይነቱን ችግር ከተሻገሩት ዘመናት ተቆጥረዋል። ሃገራቱ ዲጂታል የጤና መረጃ ስርዓት ቴክኖሎጂን ከችግሩ መውጫ ቁልፍ አድርገውታል። ለመረጃ/ኢንፎርሜሽን አደረጃጀት ትልቅ ስፍራ የሚሰጡት በመሆኑ፤ በጤናው ዘርፍ ከአገልግሎት እና መረጃ አያያዝ ጋር የሚታየውን ክፍተት በቴክኖሎጂ በመታገዝ መሻገር ችለዋል።
በሃገራቱ ወደ ሃኪም ቤት የሚሄዱ ህሙማን ስማቸውን ገልፀው በዕለቱ የተሰማቸውን የህመም ስሜት ከመግለፅ ባለፈ በየጊዜው ዝርዝር የጤና ይዞታቸውን መግለጽ አይጠበቅባቸውም። ቴክኒዎሎጂው የታካሚዎችን የምርመራ ሒደት፣ የሕክምና ክትትል ሥርዓት መዝግቦ የሚይዝ ሲሆን፣ የታካሚዎችን የሕክምና ታሪክ ጊዜ ሳይፈጅ ያለ ውጣ ውረድ ለማግኘት ያስችላል። እንዲህ ያለው ዘመናዊ የሕክምና መረጃ አያያዝ የታካሚዎችን እንግልት ከማስቀረቱም በላይ፣ የሐኪሞችን ድካምም እንደሚቀንስ ይታመናል። በዚህም የሕክምና ሒደቱን የሚያቀልል ቀልጣፋ አሰራር ነው። በሃገራችን ዲጅታል ሥርዓትን ያካተተው የሕክምና አገልግሎት ቴክኖሎጂን በስፋት መጠቀም ቢቻል፤ የማኅበረሰቡን የተቀላጠፈ የሕክምና አገልግሎት የማግኘት ችግርን መቅረፍ ይቻላል።
የጤና ሚኒስቴር ከጤና መረጃ አያያዝ ጋር የሚስተዋለውን የአሰራር ችግር ለመቅረፍ፣ በየጤና ተቋማቱ የሚታየውን የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ችግርን ለማሻሻል ቴክኖሎጂውን መጠቀም አማራጭ አድርጎ መንቀሳቀስ ጀምሯል። በሃገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም ጤና ተቋማት የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መረጃ ስርዓትን ዲጂታላይዝ ለማድረግ እየተሰራ ሲሆን፤ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ሁሉም ጤና ተቋማት የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መረጃ ስርዓት ወደ ዲጂታል እንዲቀየር የሚደረግ መሆኑን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የጤና ሚኒስቴር ባዘጋጀው የዲጂታል ጤና ኮንፈረንስና ኤግዚቢሽን መክፈቻ ፕሮግራም ላይ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ እንደተናገሩት፤ የዲጂታል የጤና መረጃ ስርዓት ቴክኖሎጂ የጤናውን ዘርፍ በማሳደግ ፍትሃዊነትንና ጥራትን በማረጋገጥ ረገድ ጉልህ ሚና እንዳላቸው ይታወቃል። በጤናው ዘርፍ ዲጂታል የጤና መረጃ ስርዓት መዘርጋቱ ለህብረተሰቡ የአገልግሎት አሰጣጡን ከማቀላጠፉ በተጨማሪ ውጣ ውረድና እንግልቱን ለመቀነስ ያስችላል፡፡
በሃገራችንም የቴክኖሎጂውን አስፈላጊነት መሰረት በማድረግ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ያመላከቱት ዶ/ር ሊያ፤ በጤና ሚኒስቴር አስተባባሪነት ቀደም ብሎ የተጀመረውና ከትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎች አንዱ የሆነው የመረጃ አብዮት አተገባበር እንደሆነ ጠቅሰው፤ በዚህም የመረጃ አያያዝን ከጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች እስከ ሆስፒታሎች ድረስ በተዘረጋ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማዘመን መቻሉን ይናገራሉ። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አባወራና እማውራዎችን ሁኔታ በመረጃ ቋት በማደራጀት ጤናቸውን በቀላሉ ለመከታተል ማስቻሉ ለቀጣዩ ስራ ተስፋ ሰጪእንደሆነም ጭምር ያብራራሉ።
በሃገሪቱ በአሁኑ ወቅት የጤና ስርዓቱን በቴክኖሎጂ ለማዘመን የሚያስችሉ ስራዎችን በመለየት እየተሰራ መሆኑንም ያመላከቱት ዶ/ር ሊያ፤ በጤና ሚኒስቴር የዲጂታል የጤና መረጃ ስርዓቱ የሚመራበት የዲጂታል የጤና ፍኖተ ካርታ እና መመሪያም መዘጋጀቱን አስታውቀዋል። ይህም የህክምና አገልግሎቱን ቀልጣፋና ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ ይረዳል። የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ከማሳለጡም በላይ የታካሚዎችን ደህንነት ለማረጋገጥ አስተዋፅኦ የሚኖረው መሆኑን ነው ያስታወቁት ።
” አሁን ላይ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ያልተዳረሰበት የዓለም ጫፍ፣ ተጽእኖ ያልፈጠረበት የስራ መስክም ሆነ የህይወት ዘይቤ የለም ሲሉ ንግግራቸውን የጀመሩት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ዓለምፀሀይ ጳውሎስ፤ በዲጂታል አሰራር ለውጥ እያመጡ ካሉ ግንባር ቀደም ዘርፎች መካከል የጤናው ሴክተር ተጠቃሽ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ዲጂታል የጤና መረጃ ስርዓት መረጃን በፍጥነት ተደራሽ ለማድረግ እንግልትን ለመቀነስ ቶሎ ውሳኔ ለመስጠት ወረርሽኝን ለመግታት እና ለመሳሰሉት አስፈላጊ መሆኑንም ያመላከቱት ወ/ሮ ዓለምፀሀይ፤ “የጤና ሚኒስቴር በመጀመሪያውም ሆነ በሁለተኛው የጤናው ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን እቅድ ለጤና መረጃ አብዮት ትኩረት በመስጠት የዲጂታል የጤና ስርአትን ለማስፋፋትና አሰራሮችን በቴክኖሎጂ ለማዘመን ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል “ነው ያሉት።
የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው ደግሞ ፤ የጤና ስርዓቱን ወደ ዲጂታል ማሸጋገሩ ለዘርፉ እድገት ከፍተኛ እንደሆነ ይናገራሉ። የዲጂታል ቴክኖሎጂው በተለይም ሊከሰቱ የሚችሉ ወረርሽኞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አይነተኛ ሚና እንደሚኖረውም ያስታወቁት ዋና ዳይሬክተሩ፤” ይሁን እንጂ የጤና ዘርፉ ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ በመሆኑ ስርዓቱ ገቢራዊ ሲደረግ የሳይበር ደህንነት ስጋትን ለመቀነስ በሚያስችል መልኩ መተግበር ይኖርበታል “ሲሉ በጤናው ዘርፍ ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ያለውን ስራ ተገቢ መሆኑን ያስታወቁት።
በዚህ ዘመን በሁሉም ዘርፍ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የደረሰባቸውን ምጥቀቶች በመጠቀም ካለው ማህበራዊ ቀውስ መውጣት ይገባናል ያሉት ደግሞ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ናቸው። በዚህ ረገድ የጤና ሚኒስቴር መተግበር የጀመረው የጤና መረጃ ስርዓት የሚበረታታ መሆኑን ያመላከቱት ዶክተር አብርሃም፤ የዲጂታል ቴክኖሎጂው ዘመኑን የዋጀ የጤና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን ነው ያመላከቱት። የጤና መረጃ ስርዓቱ እንዲሻሻል በማድረግ አገሪቱ በዘርፉ ያላትን ደረጃ ማሻሻል የሚያስችል በመሆኑ፤ የዲጂታል የጤና መረጃ ስርዓቱን በአገሪቷ ሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ መስራትም እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።
በአጠቃላይ በሃገራችን ባለፉት ዓመታት ሲተገበር የነበረው የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መረጃ ውጤት መገኘቱን መልካም ነው። የዲጂታል መረጃ ስርዓት መተግበሩ የጤና ተቋማትን አሰራር ወደ ዘመናዊነት የማሻገሩ ትግበራን ለማሳለጥ በርካታ ሙያተኞች ከማሰልጠን ባሻገር፤ ከ30 ሺህ በላይ ታብሌቶችን ለጤና ተቋማት በማከፋፈል ስራውን ለመደገፍ የተደረገው ሙከራ ጥረቱን አበረታችች ያደርገዋል። ስለዚህ የመረጃ ስርዓቱ ፍትሀዊና ጥራት ያለው ጤና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ድርሻ ስላለው ለተግባራዊነቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ባይ ነን፡፡
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን መስከረም 15/2014