ከጥንት ጀምሮ በሀገራችን ጡት መጣባት በመባል የሚታወቅ ባህል አለ፡፡ በጡት መጣባት ባህል ሁለቱ ተጣቢዎች ጡት ከተጣቡ በኋላ የአባት እና የልጅነት ዝምድና በመሀከላቸው ይፈጥራል፡፡ በጡት መጣባት ሂደት ውስጥ ጡት የሚጠባው አካል ለአጠቢው የጡት ልጅ ይሆናል፡፡ ጡት አጠቢው ደግሞ የጡት አባት ሆኖ በሚያስፈልገው ጉዳይ ሁሉ ከጡት ልጁ ጎን የሚቆም ይሆናል፡፡ በሀዘን ሆነ በደስታው ሁሉም ከአጠገቡ አይለይም፤ አለሁልህ በርታ ብሎ ያበረታታዋል፡፡
ዛሬ ስለ ጡት መጣባት ባህል ላወሳችሁ ሳይሆን እኛ በመልካም ጎኑ የምናውቀው ጡት መጣባት ባህል በተቃራኒ በመጥፎ መልኩ ለጥፋት ተግባራዊ መሆኑ ቢያገርመኝ ነው፡፡ ስር የሰደደ ግንኙነት ያላቸው መሆኑ የሚታወቀው አሸባሪ ህወሓትና የአሜሪካ መንግሥት በጡት መጣባት የተመሠረተው ዝምድናቸው ቁልጭ ብሎ ገሃድ ከወጣ ውሎ አድሯል፡፡ ቡድኑ ጡት ከተጣባቸው መካከል ደግሞ የአሜሪካ መንግሥት ያህል የታመነ ያለ አይመስልም፡፡
እንደሚታወቀው የጡት ተጣቢዎች ግንኙነት በጡት አባት ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የጡት ልጅ ፈጻሚ ነው፤ እንዲፈጸም የተፈለገው ሁሉ በተፈለገው ጊዜና ሰዓት ውስጥ መፈጸም እንጂ ሌላ ምንም አይነት ምርጫ የለውም፡፡ ቀድሞኑ ግንኙነት የተመሠረተው ሲጠሩት አቤት፤ ሲልኩት ወዴት በሚለው መርህ ላይ ነው፡፡
የታዛዡ እንቅስቃሴው ሁሉ በአዛዦቹ ፈቃድ የሚፈጸም እንጂ ከዚያ ውጭ ሆኖ አያውቅም፡፡ ለዚህም ነው አሸባሪው ህወሓት ካጋተው የአሜሪካ ጡት ለሚያገኛው ጠብታ ጥቅም በሀገሩ እና በወገኖቹን እጣ ፈንታ ላይ ደንዳና ሆኖ በጠላትነት እየሰራ የሚገኘው፡፡
የአሜሪካ መንግስት ቡድኑ ወደ አራት ኪሎ እንዲገባ በማድረግ እንደፈለገው አሻንጉሊት አድርጎ ሲጠቀምበት መቆየቱ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ተላላኪና ታዛዥ መንግሥት የሚፈልገው የአሜሪካ መንግሥት በቡድኑ እግር የተተካው የሀገሪቱ መንግስት በለመደው መልኩ የመስተናገድ እድል እንደማይሰጠው በአግባቡ እንደተረዳ ይታመናል፡፡
አሁን ያለው የለውጥ መንግሥት በሀገሩና በህዝቡ ጉዳይ ፈጽሞ የማይደራደር እንደሆነ በግልጽ ያስታወቀ መሆኑና በአደባባይም ደጋግሞ መናገሩ የአሜሪካ አስተዳደር ዓላማውን ሲያስፈጽምለት ወደ ቆየው አሸባሪው ህወሓት ፊቱን በማዞር ቡድኑን ከሞት በመታደግ ህይወት እንዲያገኝ እየሰራ ነው፡፡
አሸባሪው ከውልደቱ ጀምሮ ሀገራዊ መንፈስ የሌለውም፡፡ ሀገሪቱን ለማፍረስ ከውስጥና ከውጭ ሀይሎች ጋር ሆኖ ያልፈነቀለው ድንጋይ፤ ያልቆፈረው ጉድጓድ የለም፡፡ ይህንኑ ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል ስትራቴጂ ነድፎ ሲንቀሳቀሱ መቆየቱም የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ የቡድኑ አፈቀላጤ ጌታቸው ረዳም ሀገር ለማፍረስ ሲኦል መውረድ ካለብን እንወርዳለን በማለት ሀገርን የማፍረስ ያላቸውን ጽኑ አቋም ሲገልጽ እንደነበር ይታወሳል፡፡ የአመጣጥ ታሪኩም ቢሆን የሚያሳየው ይህንኑ ነው፡፡
ቡድኑ የደርግ መንግስትን ለመጣል በተደረገው ትግል የአሜሪካ መንግሥት ከጎኑ ሆነ ሲያገዘው እንደነበር ይታወሳል፡፡ የሰብዓዊ እርዳታ የሚውሉ ድጋፎች ዘርፎ የጦር መሳሪያ እንዲገዛበት እስከማገዝ የደረሱ ተግባር መፈጸሙም የሚረሳ አይደለም፡፡
ከዚህ ሁሉ በኋላ ዛሬ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት አሸባሪ ብሎ ያወገዘውን ይህን ቡድን የአሜሪካ መንግስት ባልተገባ መንገድ ከመደገፍ አልፎ፣ ለቡድኑ እድሜ ለመስጠት እየሄደበት ያለው መንገድ አጠቃላይ የኢትዮጵያን ህዝብ ያሳነሰና ከፍ ያለ ነውር ጭምር ነው፡፡
የአሜሪካ መንግስት አሸባሪው ህወሓት ሀገር ለማፍረስ በሀገርና በህዝብ ላይ የሚፈጸመውን ግፋና በደል እያወቀ ድርጊቱን ከማውገዝ ይልቅ ዝምታ መርጧል። መንግሥት በአሸባሪው ላይ እርምጃ ሲውስድ ደግሞ የተለመደውን የማስፈራሪያና ዛቻ አዘል ንግግር ያሰማል፡፡ ከራሱም አልፎ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት ሳይቀር በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ እንዲጥል ለማድረግ ያልተገቡ ትረቶችን ያደርጋል ፡፡
ሌላው ቀርቶ የሰሞኑን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በኢትዮጵያ ውስጥ ጉዳይ በመግባት ያስተላለፉት የውሳኔ ሀሳብ ይህንኑ እውነታ በተጨባጭ የሚያጠናክር ነው፡፡ የአሸባሪውን እስትንፋስ በመመለስ ከሞት እንዲያንሰራራ ለማድረግ የማታደርገው ጥረት አንዱ ማሳያ ነው፡፡
ምንም እንኳን የአሁኑ የጆ ባይደን ተጨማሪ ማዕቀብ ለትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ እንዳይቀርብ ያስተጓጎሉ እና የተኩስ አቁም ስምምነት እንዳይደረግ እንቅፋት የሆኑ አካላት ላይ የሚጣል መሆኑን ቢገለጽ ቅሉ በመሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ እንዲሉት አይነት ነው፡፡
አሸባሪው ህወሓት የሚፈጸመውን እኩይ ተግባር ከማውገዝ በዝምታ ማለፍ የሚመርጡት የጆ ባይደን አስተዳደር ከፍተኛ ሀላፊዎች የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አድርጎ ከትግራይ ክልል ሲወጣ ለድርጊቱ እውቅና ለመስጠት እንኳን ፈቃደኛ አልነበሩም። በተቃራኒው የአሸባሪው ቡድን በጠበጫሪነቱን ቀጥሎ በአማራና በአፋር ክልል ጥቃት ሲያደርስ ምንም አይነት ነገር ለመናገር አልወደዱም፣ ዝምታን መርጠዋል፡፡
አሜሪካ ጨምሮ ምዕራብያውያኑ ሀገራት አሸባሪው ህወሓት በማይካድራ፣ በጋሊኮማ እና በጭና በንጹሃን ላይ የደረሰውን የጅምላ ጭፍጨፋ ለማውገዝ ተግባሩን ለመኮነን አልወደዱም፡፡ ለሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ወደ ክልሉ የገቡ 466 መኪናዎች ውስጥ 428ቱ በቡድኑ ታግተው ላልተገባ ተግባር እየዋሉ ባለበት ሁኔታም ዝምታን መርጠዋል። ይህ ሁሉ እየሆነ ባለበት ሁኔታ በመንግስት ላይ ጫና ለማሳደር እየሄዱበት ያለው መንገድ ጤነኛ አይደለም።
በታሪክ ተመዝግቦ እንደምናገኘው እስካሁን በኢትዮጵያ ታሪክ ከህወሓት በስተቀር በሀገሩ ጉዳይ ፈጽሞ ተደራድሮ የሚያውቅ መንግሥት የለም፡፡ ኖሮም አያውቅም፡፡ ከፍጥረቱ ጀምሮ ሀገራዊ መንፈስና ስሜት የሌለው ይህ ቡድን እድሜ ባገኘ ቁጥር ሀገር በማፍረስ ሴራው የሚቀጣም፤ መቼም ከዚህ እኩይ ተግባሩ የሚመለስ አይደለም። ይህ ለመላው ኢትዮጵያዊ ያልተሰወረ እውነት ነው። ለዚህም ነው ቡድኑን እስከ አስተሳሰቡ ለማጥፋት ሆ ብሎ የተነሳው።
የአሸባሪው ወዳጆች የቱንም ያህል ቢጮሁ ኢትዮጵያውያን ያሰቡትን ያለሙትን ከግብ ለማድረስ የሚቦዝን ስብእና የላቸውም፡፡ በሀገራቸው ጉዳይ ለመደራደር የሚያስችል የሞራል ውድቀት የለባ ቸውም። ምንም አይነት ማዕቀብ እና ጫና ይህንን ማንነታቸው አይለውጠውም፡፡ ከዚህ ይልቅ አሜሪካም ሆነች አንዳንድ ምዕራባውያን ከተሳሳተው መንገዳቸው ሊመለሱ ይገባል፡፡
አሸባሪውን ህወሓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ግብዓተ መሬቱን ለመፈጸም ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከዳር ሆ ብለው በአንድነት ተነስተዋል። የቡድኑን ግብአተ በመሬት እንዳይፈጽሙ ለአፍታ የሚያዘናጋቸው አንድም እውነት፤ ሀይል የለም። ኢትዮጵያ እንደሀገር አሸነፈች ትወጣለች፡፡ በቅርብ የድል ብስራት እንሰማለን፡፡ ያኔ የጡት አባትና የጡት ልጅ ጉዳይ ፍጻሜ ያገኛል! ቸር እንሰንብት።
ትንሳኤ አበራ
አዲስ ዘመን መስከረም 15 ቀን 2014 ዓ.ም