ባለፈው ዓመት ሰኔ 14 ቀን ሀገርን አሸናፊ ያደረገ ምርጫ ተካሄዷል። ምርጫው በሀገሪቱ ታሪክ ከፍ ያለ ቁጥር ያለው መራጭ ህዝብ የተሳተፈበት፤ ይወክሉኛል ብሎ ያመነባቸውን ወኪሎቹን በነጻነት መምረጥ የቻለበት ታሪካዊ ምርጫ እንደነበር ይታወሳል።
በምርጫው በስልጣን ላይ ያለው ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ ለሰላማዊ ትግል እራሳቸውን ያዘጋጁ እና አዲስ የፖለቲካ ባህል ለመገንባት ተስፋ የሰነቁ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፈውበታል። በምርጫው ሀገርን አሸናፊ ለማድረግ ከፍ ባለ ቁርጠኝነት ተንቀሳቅሰዋል ።
ከመጣንበት የምርጫ ታሪክና ከዚሁ ከሚመ ነጨው የተዛባ አስተሳሰብ አንጻር በምርጫው አንዳ ንድ ችግሮች ቢያጋጥሙም ፤ ምርጫው የአዲስ ታሪክ አዲስ ጅማሮ በመሆን ሀገርና ህዝብን አሸናፊ ባደረገ መልኩ ተጠናቋል። በወቅቱ የታየው የተፎካካሪ ፓርቲዎች ስክነትም የአዲሱ ታሪክ አካል ሆኖ ተመዝግቧል።
በእርግጥ ምርጫው እንዳይካሄድ በሀገር ውስጥ የሚገኙ ለምርጫ ፖለቲካ እራሳቸውን ያላዘጋጁ ሀይሎችን ጨምሮ በሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት የሚፈልጉ የውጪ ሀይሎች የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል። ህዝባችን ለምርጫው ከነበረው ቁርጠኝነት የተነሳ በነዚህ ሀይሎች ተፈጥሮበት የነበረውን ተግዳሮት በመሻገር ምርጫውን አካሂዷል።
ሀገር እንደ ሀገር በብዙ ፈተናዎች ውስጥ በነበረችበት ወቅት የተካሄደው ይህ ምርጫ የሀገርን እጣ ፈንታ ከመቀየር ባለፈ እየተፈታተኑን ላሉት ወቅታዊ ሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ያመጣል የሚለው የህዝባችን እምነት ለምርጫው ስኬት ከፍ ያለ አቅም መፍጠሩም ይታመናል።
ከዚህ በመነጨም በምርጫው የህዝብ ይሁንታን በማትረፍ መንግስት የመመስረት አቅም የተጎናጸፈው የብልጽግና ፓርቲ በድሉ ማግስት በምርጫው የሀገርን አሸናፊነት ከፍ ወዳለ ደረጃ ማሳደግ ያስቻለ የመንግስት ምስረታ እውን እንደሚያደርግ አስታውቋል። ከካ ቢኔ ጀምሮ በየደረጃው ባሉ የመንግስት መዋቅሮች የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮችን ለማሳተፍ መወሰኑን አብስሯል።
ይህ በመጣንበት የፖለቲካ ባህል ያልተለመደ፤ ከአሸናፊነትና ከተሸናፊነት ትርክት የወጣ ሐገርን እንደ ሀገር አሸናፊ ያደረገ፤ ከዛም በላይ ለቀጣዩ ሀገራዊ የፖለቲካ ተሀድሶ መንገድ ጠራጊ የሆነ ውሳኔ የመላውን ህዝባችን ትናንቶች መካስ የሚያስችል እንደሆነም ይታመናል።
የፓርቲው ውሳኔ አንድም በመንግስት አሰራር ዙሪያ ግልጽነት ማስፈን የሚያስችል፤ ከዚህም በላይ በምርጫው ሀገር አሸናፊ መሆኑዋን በአደባባይ የሚያጸና፤ በሀገሪቱ አዲስ የፖለቲካ ባህል እያቆጠቆጠ መሆኑን በተጨባጭ ያሳየ ነው።
ይህ እውነታ በመጪው መስከረም 24 ተጨባጭ የታሪካችን አካል ይሆናል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ለጀመርነው ለውጥ ከፍ ያለ አቅም በመሆን የፖለቲካ ተሀድሷችን ትርጉም ወዳለው ታሪካዊ ምእራፍ መሻገሩን ያበስራል።
አዲስ ዘመን መስከረም 15 ቀን 2014 ዓ.ም