ይህ ወቅት የጎዳና ላይ ሩጫዎች በስፋት የሚካሄድበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ያለፈው ዓመት በኮቪድ- 19 ወረርሽኝ ምክንያት የተሰረዙ ውድድሮች ዘንድሮ ሊካሄዱ ቀን ተቆርጦላቸዋል፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ትልቅ ስፍራ ከሚሰጣቸው ስድስት ዋና ዋና የጎዳና ላይ ውድድሮች መካከልም አምስት የሚሆኑት እስከ ቀጣዩ ወር አጋማሽ ድረስ የሚካሄዱ መሆኑ ታውቋል፡፡
ከስድስቱ ታላላቅ የጎዳና ላይ ውድድሮች መካከል አንዱ በሆነውና በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃ የተሰጠው የበርሊን ማራቶን ከነገ በስቲያ ይደረጋል፡፡ እአአ ከ1974 አንስቶ መካሄድ በጀመረው በዚህ ማራቶን እስካሁን ድረስ 11 የሚሆኑ የማራቶን ክብረወሰኖች በሁለቱም ጾታዎች የተሰበረበት ውድድር በመሆኑ በአትሌቲክስ ቤተሰቡ ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው፡፡ የወቅቱ የርቀቱ ክብረ ወሰን ባለቤት ኬንያዊው ኢሉድ ኪፕቾጌም በዚህ ውድድር ላይ ክብሩን በእጁ ማስገባቱ ይታወሳል፡፡ እአአ 2019 አትሌቱ 2:01:39 ሰዓት በማስመዝገብ የሰው ልጅ በርቀቱ ከ2ሰዓት በታች የመግባት አቅም እንዳለው ፍንጭ አሳይቷል፡፡
በዚህ ውድድር ላይም 25ሺ የሚሆኑ ሰዎች እንዲሁም በስፖርቱ ስመጥር የሆኑ አትሌቶች እንደሚሮጡም የውድድሩ አዘጋጆች አስታውቀዋል፡፡ በርቀቱ እጅግ ተጠባቂ በሆነው ሌላኛው አትሌት አዲስ ክብረወሰን ይመዘገባል በሚልም ይጠበቃል፡፡ የርቀቱ ሁለተኛው ባለ ፈጣን ሰዓት ኢትዮጵያዊው የረጅም ርቀት ንጉስ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ተሳታፊ እንደሚሆን የዓለም አትሌቲክስ በድረ ገጹ አረጋግጧል፡፡ ይህም በውድድሩ አዲስ ነገር ይታያል በሚል በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል፡፡ ቀነኒሳ በበርሊን ብቻም ሳይሆን በቀጣዩ ወር በሌላኛው ትልቁ የጎዳና ላይ ሩጫ በሆነው ኒውዮርክ ማራቶን እንደሚሮጥም አትሌቲክስ ዊክሊ የተሰኘው መጽሄት አስነብቧል፡፡
ቀነኒሳ ከኬንያዊው ኢሉድ ኪፕቼጌ ቀጥሎ ባለፈጣን ሰዓት አትሌት ሲሆን፤ እአአ በ2019 በዚሁ የበርሊን ማራቶን 2:01:41 የሆነ ሰዓት አስመዝገግቧል፡፡ በዚህ ወቅትም በርቀቱ የዓለም ክብረወሰንን የማሻሻል አቅም አለው በሚል በሰፊው የሚጠበቅ አትሌት ነው፤ ቀነኒሳ፡፡ በለንደን ማራቶን በጉዳት ምክንያት
ከውድድር ዝርዝሩ ውስጥ በመውጣቱ ምክንያት አድናቂዎቹ ቅር ቢሰኙም በቶኪዮው ኦሊምፒክ ማራቶን ኢትዮጵያን ወክሎ ዳግም በርቀቱ ይሮጣል የሚል ተስፋ ነበራቸው፡፡ ይሁን እንጂ አትሌቱ በኦሊምፒኩ ተሳታፊ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ቀነኒሳ ከሁለት ዓመት በኋላ በጀርመን ምድር ላይ ውድድር በማካሄድ በርቀቱ ምርጥ አትሌት መሆኑን የሚያስመሰክር እንደሚሆንበስፋት ይጠበቃል፡፡
ውድድሩን አስመልክቶም አትሌቱ ‹‹በጥሩ ጉልበትና መነሳሳት ወደ በርሊን ማራቶን ተመልሻለሁ፡፡ ከዚህ ቀደም በበርሊን የነበረኝ ሩጫ በእጅጉ አነሳስቶኛል፤ ስለዚህም የዓመቱን ዕቅዴን አሳካለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ›› ሲልም ስለውድድሩ ገልጿል፡፡
አትሌቱ ከማራቶኑ ባሻገር እአአ በ2009 በበርሊን በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በ5ሺ እና 10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት በመሆን አስደናቂ ድል መቀዳጀቱ የሚታወስ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ስፍራ ሌላ ክብርና ድል በሌላ ርቀት ሊያስመዘግብ እንደሚችል ይገመታል፡፡ ከቀነኒሳ ጋር በውድድሩ ተካፋይ የሚሆነው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ጉዬ አዶላ ሲሆን፤ አትሌቱ ከአራት ዓመታት በፊት ያስመዘገበው 2:03:46 የሆነ ፈጣን ሰዓት አለው፡፡
ኦሊቃ አዱኛ እና ታዱ አባቴም የውድድሩ አካል የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡ በተፎካካሪነት ደግሞ ኬንያዊው ኢሉድ ኪፕታኑይ፣ ፊሊሞን ካቼራን እና ፌስተስ ታላም ተካፋይነታቸውን ያረጋገጡ አትሌቶች ናቸው፡፡ እነዚህ አትሌቶች ከ2ሰዓት ከ07 ደቂቃ ያነሰ ፈጣን ሰዓት ያላቸው ቢሆኑም፤ አሸናፊ ይሆናሉ በሚል ቅድመ ግምት ካገኙት አትሌቶች ከሁለት ደቂቃ በላይ የዘገየ ሰዓት ባለቤቶች ናቸው፡፡
በሴቶች ምድብ በሚካሄደው ውድድርም በተመሳሳይ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች የማሸነፊያ ቅድመ ግምቱን አግኝተዋል፡፡ በተጠናቀቀው ዓመት በሚላን ማራቶን 2:19:35 የሆነ ሰዓት በማስመዝገብ አሸናፊ የሆነችው አትሌት ሂወት ገብረኪዳን ተጠባቂ ሆናለች፡፡ በማራቶን የምትታወቀውና በርቀቱ ስኬታማ የሆነችው የሃገሯ ልጅ ሹሬ ደምሴም የውድድሩ ተሳታፊ ናት፡፡ ኬንያዊያኑ ፋንሲ ቼሙታይ እና ፑሪቲ ሪዮሪፖ ደግሞ በውድድሩ ፈተና እንደሚሆኑ የሚጠበቁ አትሌቶች ናቸው፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 14/2014