ወጣት ሰሎሞን ቀለሙ ይባላል። በራያ አካባቢ የዋጃ ነዋሪ ነው። በዋጃ ማዘጋጃ ቤት፤ በከተማው የመሬት ሪፎርም ሊቀመንበርነት እንዲሁም የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ በመሆን ሲያገለግል ቆይቷል። ሰለሞን እድሜው ለአቅመ አዳም ከደረሰበት ግዜ አንስቶ ባደገባቸው ራያ አላማጣ፤ ራያ ዋጃ፤ ራያ ኮረም ኦፍላና ሌሎች አካባቢዎች በሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ላይ ይደርስ የነበረውን ጭቆና፣ ግፍና የመብት ጥሰት በቅርበት ሲከታተለውና ሲቆጭበት ኖሯል። ሁኔታዎች ተመቻችተው አንዳች ነገር መስራት እንዳለበትም ለራሱ ሲነግር ነበር።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ ነበር የዛሬ ሶስት አመት አካባቢ የእርሱን አላማ ከሚደግፉ ሌሎች ባልንጀሮቹ ጋር በመሆን መላው የአካባቢው ነዋሪ ሲብሰለሰልበት የነበረውን ‹‹በቋንቋችን እንማር፤ በምንፈልገው እንተዳዳር፤ የተጫነብን ማንነት ይነሳልን›› ጥያቄ በማንሳት ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ የጀመሩት። እንቅስቃሴው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶም ይህን አላማ ለማሳካት ይንቀሳቀስ የነበረውን የራያ አላማጣ የወጣቶች ስብስብን ይመራ የነበረውም ራሱ ሰለሞን ነበር። እነ ሰለሞን ወቅታዊ ሁኔታዎችን እየተከታተሉ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ ከቆዩ በኋላ በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የድጋፍ ሰልፍ በሚደረግበት ወቅት ግን አዲስ ነገር ይፈጠራል።
እነ ሰለሞን በድጋፍ ሰልፉ ላይ ጠቅላይ ሚንስትሩ የጀመሩትን ጉዞ እንደሚደግፉ በመግለጽ ነገር ግን እነሱ አማራ በመሆናቸውና ያለ ፍላጎታቸው በትግራይ ክልል ስር መካተታቸው ስህተት በመሆኑ እንዲስተካከል ጥያቄ ያቀርባሉ። ትምህርታቸውንም በቋንቋቸው አማርኛ ሊማሩ እንደሚገባና አጠቃላይ የአካባቢው አከላለል ከሀያ ሰባት አመት በፊት ወደነበረበት ወሎ ክፍለ ሀገር እንዲመለስ ያሳስባሉ። በተጨማሪም ለሰላሳ አመት በአካባቢው ነዋሪ ላይ ሲደርስ የነበረውም ሁለንተናዊ ጭቆና መቆም እንደሚገባውና መቋጫውም ወቅቱ አሁን እንደሆነ የተለያዩ መፈክሮችን ይዘው በመውጣት በአደባባይ ይናገራሉ። ወትሮም ይህ እውነታ የማይዋጥላቸው የትህነግ ባለስልጣናት በሰልፉ ማግስት እነ ሰለሞንን ህገ ወጥ ሰልፍ በማካሄድና መንገድ በማዘጋት በሚል ክስ መስርተው የእስር ማዘዣ በማውጣት በይፋም በስውርም ያድኗቸው ይጀምራሉ።
ከዚህ ቀደም በተለያዩ ግዜያት በአካባቢው ተወላጆች በተመሳሳይ የማንነት ጥያቄ ሲያነሱ በነበሩ ሰዎች ላይ የተሰራውን ግፍ፣ ማሳደድና ግድያ እነ ሰለሞን ጠንቅቀው ያውቁታል። በተለይ ከአስር አመት ወዲህ ህብረተሰቡም ጥያቄውን እየደጋገመ በማንሳቱ በተደጋገሚ ከፊሉ ይታሰራል፤ አንዳንዱ ይገደላል፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሌሎች ይህን የሚያስቡ አርፈው እንዲቀመጡ በሚል የተገደሉ ሰዎችን ሬሳ ሳይቀር በየቦታው በመጣል በጅብ ሲያስበሉም ነበር። በመሆኑም እነሱም የቀደምት ወገኖቻቸው እጣ እንዳይደርስባቸው በማለት ነሐሴ 23 ቀን 2010 ዓ.ም ሊገድሏቸው እንደሚፈልጓቸው ከህብረተሰቡ በደረሳቸው መረጃ ሲያውቁ ያገኙትን አጋጣሚ ተጠቅመው ወደ ቆቦ ለመሻገር ይገደዳሉ።
ቆቦ ሲደርሱም አገሬው ተቀበላቸው። የአካባቢው አስተዳደሮችም ለትህነግ ባለ ስልጣናት እንዲያስረክቧቸው ቢጠየቁም ሳይስማሙ ይቀራሉ። ነገር ግን ችግሩ በወቅቱ ባለመፈታቱ ቀን ቀንን እየወለደ ይመጣና ለአመታት ተወልደው ካደጉበት ቀዬ በመፈናቀል 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ለመቀመጥ ይገደዳሉ። በዚህ ሁኔታ የትውልድ ቀያቸውን ለቅው ለሶስት አመት ያህል በቆቦ ከተማና አካባቢዋ ሲኖሩ የወሎ ህዝብና ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት በማምጣትና ሌሎች የተለያዩ ድጋፎችንም በማድረግ ሲንከባከባቸው ቆይቷል። በወቅቱ ከተለያዩ ቦታዎችም ‹‹ችግራችሁ ችግራችን ነው›› ያሉ ወገኖቻቸውም የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርጉላቸው ነበር።ሀሳባቸው ሁሉ የእለት ችግራቸውን ለመቅረፍ ሳይሆን የጠየቁትን የማንነት ጥያቄ ለማስመለስ ነበር።
በመጀመሪያ ሰላማዊ ሰልፉን ተከትሎ ከአካባቢያቸው በማሳደድ እንዲፈናቀሉ የተደረጉት 587 ወጣቶች ነበሩ። ነገር ግን ጊዜው እየረዘመ ሲሄድ ወጣቶቹ ‹‹የራሳችንን ህዝብ እያስቸገርን እስከ መቼ እንቆያለን›› በሚል 200ዎቹ ብቻ እስኪቀሩ ድረስ ቀስ በቀስ ሌሎቹ የሚመስላቸውን መወሰን ይጀምራሉ። ከፊሉ አዲስ አበባን ጨምሮ
ወደተለያዩ አካባቢዎች ሲሰደድ ቀሪዎቹ ደግሞ ባህር አቋርጦ ወደ ባእድ ሀገራት በመሻገር ህይወታቸውን ለመምራት መንቀሳቀስ ይጀምራሉ። ከእነዚህ መካከል ግን በባህር ሲጓዙም እዛው የቀሩ እንዳሉ እነ ሰለሞን መረጃው ደርሷቸዋል።
በዚህ ሁኔታ ወስጥ እያሉ አሸባሪው ትህነግ በሰሜን እዝ ላይ የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ መንግስት በጀመረው ህግ የማስከበር ስራ የነበረው ደመና መገፈፍ ይጀምራል። የተለያየ ቤተሰብ እየተገናኘ የታሰሩት እየተፈቱ ነገሮች ሁሉ እየተስተካከሉ መምጣት ይጀምራሉ። ከወራት በፊት ግን መንግስት ለአርሶ አደሩ ብሎ ያደረገው የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ውሳኔ ለእነ ሰለሞን ሁለተኛ ዙር የስደት በር የከፈተ ነበር። የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተከትሎ ትህነጎች በራያ በኩል በሰላማዊ ሰዎች ላይ ግድያ ዝርፊያና ማፈናቀል ሲጀምሩ እነ ሰለሞንም ቆቦ ወልድያ እያሉ ወደ ደሴ ለመምጣት ተገደዱ። እነ ሰለሞን እንደ ግለሰብ ከጓደኞቹ ጋር ወጣት እንደመሆናቸው የትም ሄደው ራሳቸውን ለመቀለብ የማይሰንፉ ቢሆንም ከራሳቸው ቤተሰብ ጀምሮ አብረዋቸው ያሉትን የመንከባከብ ሀላፊነት እንዳለባቸው ይገነዘቡ ነበር።
እናም እዚያው አብረዋቸው ከነበሩት አመራሮች ጋር በመተባባር ቡድን መስርተው የህግ ማስከበር ዘመቻውን ተከትሎ በአሸባሪው ትህነግ የተፈናቀለው ዜጋ ወደ ትውልድ ቀየው በመመለስ ሰላማዊ ኑሮውን እስኪጀምር ድረስ የሚያስፈልገውን ሁሉ ለመስራት ከስምምነት ይደርሳሉ። ሰለሞን ባለቤቱን ጨምሮ አስራ ሁለት ቤተሰቦቹን ይዞ የመጣ ሲሆን በአሁኑ ወቅት እየኖሩ ያሉት አንድ ክፍል ቤት ተከራይተው ነው። ነገር ግን የተከራዩዋት ቤት ለሁሉም የማትበቃ በመሆኗ እሱ ሌሊቱን የሚያሳልፈው በተለያዩ ዘመዶችና ወዳጆቹ ቤት ነው። ይህም ሆኖ ሰለሞንና ጓደኞቹ ዛሬም ቢሆን እንቅልፍ የሚነሳቸውና በነጋ በጠባ ክፉ ከመስማት ጠብቀን የሚያሰኛቸው ጉዳይ በአሸባሪው ትህነግ ስር ያሉ ወገኖቻቸው ጉዳይ ነው። የሰለሞንን ወላጅ አባት ጨምሮ በርካታ ዜጎች በትህነግ ቁጥጥር ስር ይገኛሉ። ስላሉበትም ሁኔታ የሚያውቁት ነገር የለም። በአካባቢው ውሃ፣ ስልክና ሌሎች ነገሮች የሉም። ዘረፋውና ግድያውም ተጠናክሮ ቀጥሏል። አንዳንድ ተወላጆችም በተለያዩ መንገዶች እያመለጡ ሲመጡ ያሉበትን አስከፊ ሁኔታ እየነገሯቸው ይገኛል።
‹‹በሰላሙ ግዜ ከአምስት መቶ በላይ ንጹሀን የራያተወላጆችን አፍነው ወስደዋቸው መከላከያ ወደ አካባቢው ሲገባ የተፈቱ አሉ። በቅርቡ በራያ የተፈጸመውንም የጅምላ ጭፍጨፋ እየሰማን ነው። በመሆኑም በአካባቢው ያሉት ዜጎች ጉዳይ ያሳስበናል። መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከመንግስት ጎን በመቆም ትህነግን ለማጥፋት እየተረባረበ እንደሆነ እናውቃለን። ነገር ግን ሁሉም ነገር በፍጥነት ካልተከናወነ ውሎ ባደረ ቁጥር የህዝባችንን ሞትና ስቃይ ይጨምራል። በመሆኑም መንግስት እኛን ጨምሮ በማሳተፍ በወቅቱ ትህነግን ደምስሶ እኛን ብቻ ሳይሆን መላው ሀገራችንንና ህዝቦቿን የሰላም አየር እንዲተነፍሱ ማድረግ ይጠበቅበታል። ለዚህም እኛም በአቅማችን በመናኝዋም መልኩ ከመንግስት ጎን በመቆም ህዝባችንን ለማገልገል ሀገራችንንም ለመታደግ ዝግጁ ነን›› ይላል። ሰለሞን እሱና መሰሎቹ ወራሪውንና አሸባሪውን ትህነግን ለመፋለም እንዲዘምቱ ጥያቄ አቅርበው ለጊዜው ባሉበት ህዝቡን በማስተባበር እንዲቆዩ እንደተነገራቸው በመግለጽ፣ መንግስት በማንኛውም ወቅት የሚያደርግላቸውን ጥሪ ካለማንገራገር ለመቀበልና የህግ ማስከበር ዘመቻውን ለመቀላቀል ዝግጁ መሆናቸውን ይናገራል።
ሌላው የእነ ሰለሞን ጭንቀትና ሀሳብ ነገ ከነገ ወዲያ ሁኔታዎች ሲስተካከሉ ህብረተሰቡን የስነ ልቦናውን ቀውስ ለማስተካከል የሚጠበቀው ነገር እንዳለ ሆኖ በቁሳቁስ አቅም ለመፍጠር በሚደረገው ዝግጅት የሚሰራው ስራ ነው። ሰለሞን ቆቦ በሚኖርበት ጊዜ ብዙ ነገሮችን ለመገንዘብና በቅርበት ለመከታተል እድሉን አግኘቷል። ምንም እንኳን የአካባቢው ህዝብ ራሱን ችሎ የሚኖሮ ጠንካራ ሰራተኛ ቢሆንም የደረሰበትና እየደረሰበት ያለው ግፍ ግን ነገን ተስፋ የሚያሰንቀው አይደለም። ተፈናቅሎ የመጣውም ሆነ እዛው ያለው የራያ ነዋሪ ሙሉ ጥሪቱ አንድም በወያኔ ተዘርፏል፤ አልያም ወድሟል። በመሆኑም ወደ ሀገሩ የሚመለሰው ባዶ እጁን ሆኖ ነው። አንዳንድ አረጋውያን ደግሞ ‹‹ይጦረኛል ይቀብረኛል›› ያሉትን ልጃቸውን አጥተዋል። እናትና አባታቸውን ያጡ ልጆችም አሉ።
ሰለሞን ከመፈናቀሉ በፊት ዋጃ ላይ በ2010 ዓ.ም መጀመሪያ 80 ሺ ብር በማውጣት የራሱን ቤት ሰርቷል። እንደማንኛውም ሰው ከሙሉ የቤት እቃ ጀምሮ ያፈራው ንብረትም ነበረው። በአሁኑ ወቅት ግን ከትዝታ ውጪ የእኔ የሚለው አንድም ነገር የለውም። ትህነጎች ገና ካገሩ ሲያፈናቅሉት ወንድሙንና የአጎቱን ልጅ ፖሊስ ጣቢያ አስረው ቤቱን በመውረስ ለራሳቸው ሰው ሰጥተውበታል፤ ንብረቱንም ዘርፈው ወስደውበታል። የዚህ አይነት ተመሳሳይ እጣ የደረሰባቸው ጥሪቴ ይሉት ነገር የሌላቸው የራያ ሰዎች እጅግ ብዙ ናቸው። በመሆኑም በሰለሞን እይታ ከመንግስትና ከበጎ አድራጊዎች ጎን በመቆም እነዚህን መደገፍ፣ ማጽናናትና አብሮ ይቺን ክፉ ቀን ማለፍ ይጠበቃል።
በዚህ ወቅት ከመንግስት ጎን በመቆም የሚሰራቸውን ነገሮች መደገፍ የራስን ሕዝብ መታደግ የሰቆቃ ጊዜውንም መቀነስ ነው የሚለው ሰለሞን፤ በአሁኑ ወቅት ሰለሞን በደሴ አራት ካምፕና ኮምቦልቻን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙትን ከ350ሺ ሀምሳ በላይ ለሚጠጉ ስደተኞች እየተደረገ ያለውን ድጋፍ ከሌሎች ጓደኞቹና የደሴ ወጣቶች ጋር በመሆን እያስተባበረ ይገኛል። ተፈናቃዮቹ ከአፋር ክልል፤ ከሰሜን ወሎ፣ ከደቡብ ወሎና ከዋግኽምራ ዞኖች እንዲሁም ከራያ የመጡ ናቸው። በመንግስት በኩል ብዙ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ቢሆንም ለአንድ ክፍል ቤት ኪራይ እስከ 3500 ብር የሚጠየቅ በመሆኑ ስደተኛው ሕይወት በእጅጉ ከብዶታል።
በተለይ በዘመዶቻቸው ቤት ከተጠጉት ውጪ በቤት ኪራይ ላሉት ክፍያው ብቻ ሳይሆን ሀሳቡም ሌላ ፈተና ሆኖባቸዋል። በሌላ በኩል ‹‹እየተቸገርንና እየሞትን እንኳን ተስፋ እንዳንቆርጥ የሚያደርገን የወገናችን ድጋፍ ነው›› የሚለው ሰለሞን፤ ‹‹ሊዘምቱ የሚመዘገቡትን ወጣቶች ስናይ ትልቅ ክብርና ኩራት ይሰማናል። በአሁኑ ወቅት በርካታ የደሴ ወጣቶች በየካምፑ እየመጡ የአቅማቸውን እያደረጉ፣ ለበአልም እኛንና ሌሎችንም እንኳን አደረሳችሁ እያሉን ነው። ወጣቶቹ ቤት ለቤት በመዞርም ተፈናቃይን ከመመዝገብ ጀምሮ በርካታ ድጋፎችን እያደረጉ ናቸው። የደሴ ህዝብ እያደረገው ያለው ድጋፍና ትብብር እስካሁን የከፋ ችግር እንዳይደርስ አድርጓል። መንግስትና የተለያዩ ክልሎች የሚያደርጉት ድጋፍም እኛን ከህዝባችን እንዳንለይ የሚያደርገን ነው›› ይላል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን መስከረም 14/2014