እራሱን ከህግ የበላይነት በላይ አድርጎ ያስቀመጠው አሸባራ ሕወሓት ከመንበሩ ወርዶ መቀሌ ከከተመበት ጊዜ ጀምሮ ከዛው፣ ከእራሱ ያልተሰማ የቋንቋ አይነት፣ የውርጅብኝ መአት የለም፤ ከቀድሞው ሴኩቱሬ ጌታቸው እስከ አሁኑ ጌታቸው ረዳ ድረስ እነሆ ቃላት እየተዥጎደጎዱ ይገኛሉ።
ሁለቱም፣ በተለይ ጌች ያሉትን የፕሮፓጋንዳ አይነቶች ሁሉ፤ ካሉት የወሬ ቋቶች ሁሉ አራግፎ (በሚያስገርሙ የቃላት ምርጫዎቹ አማካኝነት) ያወራበትን የሚዲያ አይነት ከመፈለግ ያላወራበትን መጥራቱ ይቀላል እስከሚባል ድረስ ከአማርኛ እስከ ትግሪኛ፣ ከዛም አልፎ እንግሊዝኛ፤ አሁን ደግሞ እንግሊዝኛና አረቢኛ ጋብቻ የፈፀሙበት ፕሮግራም ላይ ተገኝቷል።
በእነዚህ ሁሉ ግን አጥብቆ የያዛቸው ሁለት ጉዳዮች ናቸው። አንደኛው ኢትዮጵያን ማፍረስ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ስም ማላመጥ ነው። በቃ የፈለገ ሰው ጌታቸው ረዳን ሲያዳምጥ ቢውል ከእነዚህ ውጪ ሌላ ከአንደበቱ ጠብ የሚል ፍሬ ነገር አያገኝም።
ጎሞራው፤
ከጥንት ጀምሮ እኛ እንደምናውቀው
ሲነድ ሲቃጠል የሚስቅ እሳት ነው።
እንዳለው (እና ድምፃዊያንም እንዳስተጋቡት) ጌታቸው ረዳ ከላይም ከታችም እሳት እየነደደበትም ቢሆን ከላይ ያልናቸውን ሁለት ጉዳዮች (ባላንጣዎቹ ሁሉ እስኪመስሉ ድረስ) ሳያነሳ ውሎ አያድርም። ከፖለቲካ ባለፈ በተለይ ከዶ/ር ዐቢይ ጋር የግል ፀብ ያላቸው እስኪመስል ድረስ ነው ጌች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስም ሲያኝክ የሚውለው።
ጌች አንድ አባባልን አበጥሮ ማወቅና አጥብቆ መያዝ ነበረበት – እሳት ቢያንቀላፋ ገለባ ጎበኘው – የሚለውን። ሴኩ ይህ እውቀት ስላልነበረው ተበላ። ጌችም ይህ ስለጎደለው ነው ዛሬ እየተቃጠለ የሚስቀው፤ እየነደደ ….።
ጌታቸው ረዳና ኩባንያው ከመከላያ ጋር ሲገጥሙ – እሳት ቢያንቀላፋ ገለባ ጎበኘው – የሚለውን ባለማወቃቸው፣ አውቀውም ከሆነ ገና ለገና የውስጥ አርበኞች አሉኝ በሚል ህልማቸው ዘው ብለው እሳት ውስጥ ገብተዋል። እሱ ብቻም አይደለም የማይገኝ እድል ማለትም ለህዝብ (በተለይም ለትግራይ ህዝብ) ሰብአዊ መብትና ጥቅም ሲባል የተወሰደውን የተኩስ አቁም ርምጃ እንደ አንድ መልካም አጋጣሚ በመቁጠር መጠቀም ሲገባቸው ጭራሽ ወደየአጎራባች ክልሎች በመሄድ የንፁሀንን ደም ከማፍሰስ እስከ ተራ የኩሽና ውስጥ መንደፋደፍ ድረስ የዘለቀ ሀጢያትን ፈፀሙ።
ይህን ሁሉ ሲያደርሱ መንግስት ከዛሬ ነገ በማለት ዝም አላቸው። አልጠግብ ባይ ሆኑና ጭራሽ ቀጠሉበት፤ ከኋላቸው አንድም ሀይ የሚላቸው ጠፋ። አንድ አዛውንት በማህበራዊ ሚዲያ ጌች ለአረቡ ቴቪ የሰጠውን ኢትዮጵያን የማፍረስ እቅድ ማብራሪያ አስመልክተው በሰጡት አስተያየት “አሁንስ የትግራይ ህዝብ ምን ይላል!? እንዴት አንድ ሽማግሌ እንኳን ይጠፋል ? ብለዋል።
የአሸባሪው ሕወሓት ቃል አቀባይና ልዩ አማካሪ ጌታቸው ረዳ በሴኮንድ ስንተኛ ጊዜ “ኢትዮጵያ ፈረሰች” ወይም “ትፈርሳለች”፤ “ዐቢይ አህመድ አይቀጥልም”፤ “ጦርነቱን እስከ ቢሾፍቱ ድረስ እንቀጥላለን” ወዘተረፈ — የግብፅ ባለስልጣናትን ያስደሰተ መስሎት እንጂ ሊሆን እንደማይችል (መቸም እሱም አበሻ ነውና) ልቡናው ያውቀዋል።
ኢትዮጵያ ብትፈርስ ኖሮ ዛሬ ሳይሆን ድሮ ሕወሓት ዜጎችን “ሁልህም በየ ብሄርህ” ብሎ ያወጀ እለት እንደነበር ለጌችና ኩባንያው የተሰወረ አይደለም። ጉዳዩ ካፈርኩ አይመልሰኝ እንደ ተባለው፤ አንዴ ገብቼበታለሁና በዛው አቋሜ ልፅና ከሚል መደንዘዝ የመጣ ውሳኔ ነው።
ብዙ ግዜ ብቻ ሳይሆን ሁል ጊዜ ጌታቸው ረዳ ማይክ ወደ አፉ ጠጋ ባለ ቁጥር ሲናገር ለነገ ብሎ አያውቅም። አለም እያዳመጠው መሆኑን ሁሉ ይረሳዋል። በመሆኑም በህልሙም በቁሙም ኢትዮጵያን በማፍረስ ስራ ላይ በመጠመዱ ምክንያት ከሰላም ወዳዱ የአለም ህዝብ ጋር ሁሉ እየተጣላና የነበሩትን ወዳጆች እየቀነሰ፤ አይንህ ላፈር የሚሉ ጠላቶችን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መጥቷል። በመሆኑም ዛሬ ተቃውሞው ከእዛው ከመቀሌ ሳይቀር እየጀመረለት ነው።
እዚህ ላይ አንድ ጠጠር ያለ ጥያቄን ማንሳት ይቻላል፤ “ለመሆኑ ጌታቸው ረዳን እንዲህ የሚያደርገው፤ ከማንኛውም – ከፖለቲካም፣ ከብሄርም፣ ከጦርነት ስነምግባርም ባፈነገጠ መልኩ የሚያስቀባጥረውና አገርና ህዝብን (ለዛውም የራሱን አገር – ኢትዮጵያን) ካላፈረስኩ ወይም ካልፈረሰች ሞቼ እገኛለሁ የሚያስብለው ጉዳይ ምንድን ነው?” የሚል ነው ። መልሱም ብዙ ከባድ አይደለም ።
ከላይ ያቀረብነው ጥያቄ መልስ ቀላል የሚሆንበት ዋና ምክንያት ጌታቸው ግልፅ የሆነ የስነ ልቦና ቀውስ ውስጥ መግባቱና ተስፋ በቆረጠ ስሜት ውስጥ ሆኖ የሚያደርገውን ያሳጣው መሆኑ ነው። የሚሰጣቸው አስተያየቶች በሙሉ ነገን ያገናዘቡ አይደሉም። የቃላት ምርጫዎቹ ሁሉ ህዝብንና ትውልድን እስከወዲያኛውም የዘነጉ ናቸው። ሁል ጊዜ ንዴት ነው። ሁል ጊዜ ብስጭት ነው፤ ሁል ጊዜ ውሸት ነው። ይህ ደግሞ “እኔ ከሞትኩ ….” እንዳለችው እንስሳ ሲሆን ምድቡም ከአሳማ ፖለቲካ የባሰ ከአህያ ፖለቲካ ነው።
ባጠቃላይ አሸባሪው ሕወሓት እስካሁን ከሽብር ተግባሩ አልወጣም። ጌታቸውና ኩባንያውም እዛው ድርቅ ያለ ለዛቢስ ፕሮፓጋንዳቸውን እየፈጩና እያስፈጩ ነው ያሉት። ከላይ በመግቢያችን፤
ከጥንት ጀምሮ እኛ እንደምናውቀዉ፣
ሲነድ ሲቃጠል የሚስቅ እሳት ነው።
እንዳልነው እየነደዱ፣ እየተቃጠሉ በመሳቅ ላይ ነው ያሉት። በዚህ መሀል የትግራይ ህፃናትን እያስጨረሱ፣ የትግራይ እናቶችን እያስለቀሱ፣ የአገሪቷን ኢኮኖሚ (ልክ እንደ ዶሮዋ) ጭረው እየደፉ፣ በአጠቃላይ የንፁሀንን ደም እያፈሰሱና ህይወት እየቀጠፉ መሆናቸውን እንኳን ለአፍታ አምነው ሊቀበሉ አይደለም ፤የመቀበል አዝማሚያ እንኳን እስካሁን አልታየባቸውም።
ባጠቃላይ፣ መቸም ስንትና ስንት ልጆች ያሏት ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ብሎ መጠበቅ፣ የበሬ …. ምን ይወድቅልኛል ብላ ስትከተል ውላ እቤቱ አድርሳው እንደተመለሰችው ቀበሮ መሆን ነው። ምን እያልኩ ነው፣ ኢትዮጵያ አትፈፈርስም!!! ጌታቸውም እስከዚያችው ቀን ድረስ ከ”ኢትዮጵያን እናፈርሳለን” ትርክቱ አይወጣም። ስለዚህ ያቺ ቀን ደርሳ እስክትገላግለን ድረስ ጌች ገና ከዲያቢሎስ ጋር ቃለ መጠይቅ ሊያደርግ ይችላልና እዳው ገብስ ነው።
MኣR
አዲስ ዘመን መስከረም 14 ቀን 2014 ዓ.ም