የኢትዮጵያ ህዝብ ከመጣባት ውጣ ውረድ የተሞላበት መንገድ አንጻር ለውጥ ፈላጊነቱ ለማንም ሊሰወር የሚችል እውነት አይደለም። ለለውጥ ሲልም ብዙ ዋጋ መክፈሉ እንዲሁ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ይህም ሆኖ ግን ያሰበው ተሳክቶለት የስኬቱን ፍሬ ለመብላት ሳይታደል ረጅም መንገድ ለመጓዝ የተገደደ ህዝብ ነው።
አንድም የለውጡን መንፈስ ለህዝብ ሁለንተናዊ ጥቅምና ልእልና ማጋራት የሚችል የለውጥ ሀይል አለመፈጠሩ፤ ከዚህም በላይ ታሪካዊ የሚባሉ ጠላቶቻችንና የአፍሪካ ቀንድ ጂኦ ፖለቲካ በፈጠሩት ተግዳሮት እንደሀገርና ህዝብ የለውጥ መሻታችን የሚጨበጥ ተስፋ ሳይሆን ቆይቷል።
በተለይም በ1960ዎቹ የተጀመረው የለውጥ ንቅናቄ መላውን ህዝብ ማሳተፉ፤ በወቅቱ የነበረውን የተማረ ሀይል ከፍ ባለ መነሳሳት ከዳር እስከዳር ማንቀሳቀሱ በብዙ መልኩ ሀገርና ህዝብን ያሻግራል የሚል ተስፋ የተጣለበት ቢሆንም፤ የለውጡን መንፈስ ለግልና ለቡድን ጥቅም በሸቀጡ ሀይሎች ምክንያት መክኖ ቀርቷል።
ከፍ ያለው የህዝባችን የለውጥ ፈላጊነት መሻትም ከውስጥ እና ከውጪ ባጋጠመው ተግዳሮት የተነሳ የተከፈለለትን መስዋእትነት ባልመጠነ እንዲያውም የተከፈሉ መስዋእትነቶችን ትርጉም አልባ ባደረገ መልኩ ተቋጭቷል። ይህም በቁጭት የተሞላው የቅርብ ጊዜ ሀገራዊ ትዝታችን ነው።
የተለያዩ የፖለቲካ ሀይሎች ከህዝባችን መንፈሳዊ፣ ባህላዊና ማህበራዊ አሴቶች ያፈነገጡ የአስተሳሰብ መሰረት ያለው ሪዮተ አለም በህዝቡ ውስጥ ለማስረጽ ያደረጉት ጥረት፤ ከዛም ባለይ አንዳንድ የፖለቲካ ሀይሎች የያዙት የአክራሪ ብሄርተኝነት አስተሳሰብ ሀገራዊ የለውጥ መንፈሱን ከማቀዝቀዝ በዘለለ ለሀገራዊ አንድነቱ አዲስ ተግዳሮት ሆኗል።
በተለይም አሸባሪው ሕወሓት በኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ግንባታ ውስጥ ከፍያለ ስፍራ ያለውን የትግራይን ህዝብ እወክላለሁ በሚል የጀመረው የትጥቅ ትግል ገና ከጅምሩ ሀገረ መንግስቱን የማዳከምና የማፍረስ ግልጽና ስውር ተልእኮ የተሸከመ በመሆኑ፤ ቡድኑ ወደ ስልጣን መንበሩ ሲመጣ ሁሉም ነገር እንዳበቃ ከፍ ያለ መልእክት ያስተላለፈ ነበር።
በርግጥም ቡድኑ ወደ ስልጣን ከመጣ ማግስት ጀምሮ በህገመንግስት የተደገፈ ሀገረ መንግስትን የማዳከም ስራዎችን በተጠና መንገድ በስፋት ሲያካሂድ ቆይቷል። በዚህም በሀገሪቱ ያሉ ብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች እርስ በርስ ወደ አለመተማመንና በጥርጣሬ ወደ መተያየት እንዲያመሩ አድርጓል።
ህዝብን የመከፋፈል ተልእኮ ያላቸው ትርክቶችን በመፍጠርም ለዘመናት አብረው በኖሩ የሀገሪቱ ብሄር ፣ብሄረሰቦች እና ህዝቦች መካከል ግጭቶች እንዲበራከቱ አድርጓል ። ዜጎች በገዛ ሀገራቸው ሁለተኛ ዜግነት እንዲሰማቸው ፣ከዛም አልፈው የደህንነት መንፈስ እንዳይሰማቸው አድርጓል። ብዙዎች በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት ለከፋ ስቃይ፣ መከራና ስደት ዳርጓል። ለስነ ልቦና ቀውስ ሰለባ የዳረጋቸው ዜጎችም ቁጥር ቀላል እንደማይሆን ይገመታል።
ቡድኑ ከተዋቀረበት ሀገር እና ህዝብ ጠል የስነ ልቦና መዋቅር አንጻር ከውልደቱ ጀምሮ በሀገርና በህዝብ ላይ ያደረሰውን ሁለንተናዊ ስቃይና በደል ዘርዝሮ መጨረስ የሚሞከር አይደለም። ቡድኑ በህዝባዊ ትግል ከስልጣን ከተወገደ ማግስት ጀምሮም ከቀደመው አስተሳሰቡ በመነጨ በህዝብና በሀገር ላይ ከፍ ያለ ወንጀል ፈጽመሟል፤ እየፈጸመም ይገኛል።
በአለም አቀፍ የወንጀል ህግ የሚያስጠይቁ የጦር ወንጀሎችን ጨምሮ ኪኢትዮጵያዊ የስነ ልቦና ውቅር ያፈነገጡ ፀያፍና ዘግናኝ ግፎችንና ወንጀሎችን በአደባባይ እየፈፀመ በዚህም እየተኩራራ ይገኛል። ከዚህም ባለፈ ሀገር የማፍረስ የውክልና ተልእኮውን ለመፈፀም በአደባባይ እየፎከረ ነው። ሀገርን ለማፍረስ እስከ ሲኦል ለመውረድ ያለውን ዝግጁነት እንደ ገድል እየተረከ ይገኛል።
ይህ ከፍጥረቱ ጀምሮ ሀገርና ህዝብ ጠል በሆኑ በከፋ እራስ ወዳድነት በሰከሩ ግለሰቦች የተመሰረተ ቡድን እንደ ሀገር የኢትዮጵያን ህዝብ ከፍ ያለ ዋጋ ማስከፈሉ የአደባባይ ሚስጥር ነው። እወክለዋለሁ የሚለውን የትግራይ ህዝብ የፖለቲካ መቆመሪያ በማድረግ ያስከፈለውም ዋጋ ህዝብ ጠል ለመሆኑ ዋንኛ ማሳያ ነው።
ቡድኑ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ለውጡን ለመቀልበስ የሄደበት እርቀት ሀገርና ህዝብን ብዙ ዋጋ ያስከፈለው ቢሆንም ከባህሪው የሚቀዳው የቡድኑ ጸረ-ህዝብና ሀገር – ጠል ተግባሩ ሞቱን ብቻ ሳይሆን ግብአተ መሬቱን እያፈጠነው ይገኛል። ለዚህም መላው ህዝባችን ሆ ብሎ ከተነሳ ውሎ አድሯል።
እንደ ሀገርና ህዝብ ለጀመርነው ለውጥ ስኬታማነት አሸባሪውን የሕወሓት ቡድን እስከ አስተሳሰቡ ማስወገድ ለነገ የማንለው የቤት ስራችን ነው። ይህም መላው ህዝባችን በአግባቡ የተረዳውና በቁርጠኝነት የተሰለፈበት ወቅታዊ አጀንዳችን ነው።
አዲስ ዘመን መስከረም 14 ቀን 2014 ዓ.ም