ሀገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሟን ከምታስጠራባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ስፖርት ነው። ኢትዮጵያም ኦሊምፒክን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ስሟን የሚያስጠሩላት በርካታ ስፖርተኞችን በየዘመኑ አፍርታለች። ከጀግናው አበበ ቢቂላ አንስቶ እስከ አሁኑ ትውልድ ድረስም የሃገርን ባንዲራ በአለም አቀፍ መድረክ ጭምር በማውለብለብ የሃገራቸውን መልካም ገጽታ መገንባት ችለዋል።
ከዚህ ባለፈም የስፖርቱ ዘርፍ ተዋንያን ሃገራቸው በምትፈልጋቸው የትኛውም ጉዳይ አጋርነታቸውን በማሳየትም በቀዳሚነታቸው ጸንተዋል። ዘርፉ በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ ይታወቃል።
ሀገር አደጋ ላይ ባለችበት ወቅትም የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽንን ጨምሮ የክልል ስፖርት ኮሚሽኖች እንዲሁም ተጠሪ ተቋማቱ በጋራና በተናጠል የሚጠበቅባቸውን ሚና በመወጣት ረገድ ቀዳሚ ተሰላፊ ከሆኑት መካከል ተጠቃሽ ሆነዋል። በተለያየ መልኩ የገንዘብ እና የዓይነት ድጋፍ ከማድረግ አንስቶ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮችን በማሰናዳት እንዲሁም ደም በመለገስ ለወገናቸው ያላቸውን አጋርነት በተግባር በማሳየት ላይ ይገኛሉ።
የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ደጀን መሆኑን ለማረጋገጥ ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ህብረተሰቡ በመውረድ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እና የገቢ መሰብሰቢያ መርሃ ግብሮችን ከነሃሴ ወር ጀምሮ በማካሄድ ላይ ይገኛል። በዚህም በሰባት ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በተደረገውእንቅስቃሴም በአጠቃላይ 479ሺ596 ብር ለማሰባሰብ ተችሏል። ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍልም ከ13ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሁም 7ሺ648 ዩኒት ደም መለገሱንም ኮሚሽኑ አስታውቋል።
ስፖርት ህብረተሰቡን አንድ ለማድረግ፣ ሰላምን ለማስፈን፣ ልማትን ለማስቀጠል እና ግጭትን ለመፍታት ትልቅ አቅም እንዳለውም ምክትል ኮሚሽነር ዱቤ ጂሎ ገልጸዋል። በዚሁ መሠረትም እንደ ስፖርት ሴክተር ለመከላከያ ሠራዊት ያለውን አጋርነት በማረጋገፅ ለመደገፍ የስፖርት ቤተሰቡ በከፍተኛ አመራሩ እየተመራ በተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛል። ከመደበኛ የስፖርት ልማት ስራዎች ጎን ለጎንም የሀገር መከላከያን ለመደገፍ የተጀመሩ የህብረተሰብ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ተጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በኮሚሽኑ አዘጋጅነት የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝምሚኒስትር መስሪያ ቤቶች፣ ተጠሪ ተቋማትና የስፖርት ማህበራት የተካፈሉበት የሩጫና የእግር ጉዞ ተካሂዷል። ‹‹የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት›› በሚል መሪ ሃሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው ንቅናቄ በኢፊዲሪ ስፖርት ኮሚሽን አስተባባሪነት የስፖርት ቤተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ከሁለት ሳምንታት በፊት በይፋ ተጀምሯል። በወቅቱም መርሃ ግብሩን ያስጀመሩት የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽነር አቶ ኤሊያስ ሽኩር ‹‹ መንግስታችን እና ሀገራችን የምታደርገውን የህልውና እና የህግ ማስከበር ዘመቻ እውነታ ለመላው ዓለም፣ ለምዕራባዊያን መንግስታት በተለይም ለአሜሪካ በማሳወቅና በማስረዳት የተሳሳተውን የዓለም ሀገራት ግንዛቤ ለማስተካከል ዘመቻውን መደገፍ አስፈላጊ በመሆኑ የስፖርት ቤተሰቡ ተቀላቅሏል›› ብለዋል።
በዚህም በተለያዩ ስፖርቶች ታዋቂና ውጤታማ የሆኑ እንዲሁም ጀግንነታቸውን ዓለም የመሰከረላቸውኢትዮጵያዊያን አትሌቶችም ተሳትፈዋል። ክልሎችም ይህንኑ መርሃ ግብር የተቀላቀሉ ሲሆን፤ የደቡብ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ‹‹የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት›› እንዲሁም ‹‹100 ብር ለወገኔ›› የሚል ንቅናቄ መጀመሩን ኮሚሽኑ በድረገጹ አስነብቧል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽንም በተመሳሳይ የተለያዩ መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት ድጋፉን በማሳየት ላይ ይገኛል። ከመርሃ ግብሮቹ መካከል አንዱ የአዲስ አበባ ቦክስ ፌዴሬሽን ‹‹አንድ ሆነን ጠንካራ ክንድ እንሰነዝራለን›› በሚል መሪ ሃሳብ የቦክስ ውድድር ተካሂዷል። ይህ ዓላማውን ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ህዝባዊ ድጋፍ ማሳየትን ያደረገው ውድድሩ፤ ለሰራዊቱ የደም ልገሳ በማድረግም ተጠናቋል።
በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማም በመጪው እሁድ መስከረም 16 ቀን 2014 ዓ.ም ‹‹እኔም ለኢትዮጵያ ወታደር ነኝ›› በሚል መሪ ሃሳብ የ5ኪሎ ሜትር ሩጫ ይካሄዳል። ታዋቂ አትሌቶችን እንዲሁም የከተማዋን ነዋሪዎች በማሳተፍ በሚካሄደው በዚህ ውድድርም ከቲሸርት ሽያጭ የሚገኘው ገንዘብ ለሃገር መካላከያ ሰራዊት ድጋፍ እንዲውልም ታስቧል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም የሃገር መከላከያ ሰራዊትን በመደገፍ የራሱን መርሃ ግብር ያዘጋጀ ሲሆን፤ ስፖርታዊ ውድድሮችን እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል። ‹‹እግር ኳሳችን ለሰላማችን›› በሚል በተካሄደው መርሃ ግብር ከ16 የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የተሰበሰበ በአጠቃላይ ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን ገንዘብ ለመከላከያ ሰራዊት በማበርከት ምስጋናቸውን ገልጸዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 13/2014