በአረጋዊያን አያያዝና እንክብካቤ የበለፀጉት ሀገሮች አይታሙም። ካላቸው የጎለበተ ኢኮኖሚ አንፃር የተሻለ ልምድ አላቸው። እንዲያውም በነዚህ ሀገሮች አረጋዊያን በልዩ ሁኔታ ነው የሚታዩት። የሚሰጧቸው ስያሜ በራሱ ‹‹የዕድሜ ባለፀጎች›› የሚል ክብርና ሞገስ አጎናፃፊ፤ እንዲሁም ለቀሪ ዘመናቸው ጉልበት የሚቸር ተስፋ ሰጪ መሆኑን የማህበራዊ ጉዳይ ጠበብቶች ይናገራሉ። እንደሚባለው ምዕራባዊያኑና አውሮፓውያኑ በእንክብካቤና አያያዝ በተቀራረበ ደረጃ ቢገኙም ሲውዲን በቀደምትነት ትጠቀሳለች። ከአህጉራችን አፍሪካም እነ ሌሴቶና ሞሪሸስ ላይ ያለው ልምድ በብርቱ ይሻላል። ከገቢም ሆነ ከሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶችና ከማህበራዊ ዋስትና አንፃር ለአረጋዊያን የተለየ እንክብካቤ ያደርጋሉ።
እንዲያውም የበለፀጉት ሀገሮች ‹‹ዲጂታል ኢኩዩቲ ፎር ኖውሎጅስ› በሚል በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ31ኛ ጊዜ የሚያከብሩበት መሪ ቃል ሲታይ ጭራሽ ምግብና መጠጡን እንዲሁም የመጠለያውን ጉዳይ ተሻግረው የነሱ አረጋዊያኖች የዲጂታላይዜሽን ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባቸው የሚጠይቅ ደረጃ ላይ ደርሰዋል።
በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአረጋዊያን ጉዳይ ማስተባበሪያ መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳምጠው ዓለሙ እንደገለጹልን እኛ አሁን ካለንበት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር የኛ ሀገር አረጋዊያን የዲጂታላይዜሽን ቴክኖሎጂ መጠቀም ጉዳይ አይደለም። እንኳን አረጋዊያኑ ወጣቱም ያለበት በዚህ ልክ ነው ማለት አያስችልም። የእኛ ሀገር የአረጋዊያን አንገብጋቢ ጉዳይ የማህበራዊ ጥበቃ አገልግሎት ስርዓት ተጠቃሚ የማድረግ ጉዳይ ነው። ለዚህም ነው ዘንድሮ በሀገራችን ለ30ኛ ጊዜ የሚከበረው የአረጋዊያን ቀን መሪ ቃል ‹‹ሁሉን አቀፍ ማህበራዊ ጥበቃ ለአረጋዊያን›› በሚል ያለንበትን ተጨባጭ ሁኔታ በማገናዘብ እንዲከበር የተወሰነው።
በእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ አረጋዊያን ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጡ ናቸው። አብዛኞቹ በደረሱበት ዕድሜ ደረጃ ማግኘት የሚገባቸውን እያገኙ አይደሉም። አረጋዊያን ካለባቸው መሰረታዊ ችግር አንዱ ሕብረተሰቡ ለአረጋዊያን ካለው አመለካከት ጋር ተያይዞ የሚደርስባቸው ነው። በንብረታቸው፣ በውሳኔ ሰጪነታቸው፣ በቤተሰብ ኃላፊነታቸውና በሌሎች ጉዳዮች ተጋፊ ሰው ይገጥማቸዋል። ዕድሜያቸው ሲገፋ ሥራ መሥራት የሚችሉ አይመስለውም። በተለይ በከተሞች አካባቢ መደበኛ በሆነው 60 ዓመት ያለፋቸው ሰዎች በጡረታ ይገለላሉ። ሆኖም በጡረታ ተገለሉ ማለት ሥራ የመሥራት አቅማቸው ሙሉ በሙሉ ተሟጦ አልቋል ማለት አይደለም። በጡረታ ወቅት የነበራቸውን ዕውቀትና ልምድ የሚያካፍሉበት ስርዓት ሊበጅላቸው ቢገባም ስለማይበጅላቸው ይገለላሉ። ይሄ ደግሞ ስነ ልቦናዊና አካላዊ ጫና ያደርስባቸዋል። አብዛኞቹ አረጋዊያን በእንደዚህ ዓይነት አስከፊ ችግር ውስጥ ለመገኘት የበቁት በዋናነት በገቢ ማነስ ወይም በቀሪ ሕይወታቸው አስተማማኝ የሆነ የገቢ ምንጭ በማጣታቸው ነው።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በሀገራችን ካሉት 6 ነጥብ 8 ሚሊዮን አረጋዊያን መካከል 23 በመቶው በእንዲህ ዓይነቱ እጅግ አስቸጋሪና አስከፊ በሆነ ማህበራዊና ኢኮኖሚያ ችግር ውስጥ የሚኖሩ ናቸው። 6 ነጥብ 8 ሚሊዮን አረጋዊያን ውስጥ የሴቶቹ ቁጥር ግማሽ እንደመሆኑ ሴቶቹ አረጋዊያን ከወንዶቹ በበለጠ ጫና እንዳለባቸው ጥናቶች ይጠቁማሉ። በታሪካችን እንዲህ ዓይነቱ የአረጋዊያን ችግር እንደ ችግር መታየት ከጀመረ 50 ዓመት ሆኖታል። ሆኖም አንድም ከዚህ በፊት የነበረው የቤተሰብ ተቋም በተቋጥሮ የነበረው ዝምድና ሳይቀር የላላ ሳይሆን ጠንካራ፤ ትውልዱም ለአረጋዊያን ተገቢውን ክብር የሚሰጥ ነበር። ሁለትም በዘመኑ አረጋዊያንም በሕብረተሰብ ውስጥ ያላቸውን ሚና እየተጫወቱ ቆይተውበታል። እንደ አቶ ዳምጠው በመሆኑ ከ50ው ዓመት በፊት የነበረው አረጋዊያን በከፋ ችግር የኖሩበት ነው ማለት አያስደፍርም። በሃምሳው ዓመታት ግን ለተለያዩ አስከፊ ችግሮች መጋለጣቸውን መረጃዎች ያወሳሉ።
ከዚህ በመነሳት መንግስት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አማካኝነት የተለያዩ አካላትን በማስተባበር ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እያደረገ ይገኛል። በተለይ በሦስቱ የለውጥ ዓመታት ውስጥ ወደ ተቋሙ የመጣው የለውጥ አመራር ለአረጋዊያን ትኩረት በመስጠት በርካታ ሥራዎች አከናውኗል። ቀዳሚው በተቋሙ ውስጥ ያለው አደረጃጀት ትኩረት እንዲሰጠው ማድረግ ሲሆን በሌላ ዳይሬክቶሬት ውስጥ እንደ ንኡስ ጉዳይ ተካቶ ሲሰራበት የነበረው የአረጋዊያን ጉዳይ ከመጋቢት ወር ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ራሱን ችሎ በዳይሬክቶሬት እንዲመራ ተደርጓል። ይሄ በተዋረድ ባሉም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አደረጃጀቶችም ተግባራዊ እንዲሆን እየተሰራነው። ሀገራዊ የልማት ዕቅድን መሰረት ባደረገው በዘርፉ የ10 ዓመት ልማት ዕቅድም የአረጋዊያን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ተብሎ ተካትቷል። ለኮቪድ 19 ተጋላጭ እንዳይሆኑና ከሆኑ በኋላም ሕይወታቸውን እንዳያጡ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።
የኮቪድ ተጋላጭ እንዳይሆኑ በማድረግ ረገድ ለአረጋዊያን ድጋፍ፣ ክትትልና ቁጥጥር የሚያደርጉ ማዕከላትና ተቋማትም አስተዋጽኦ አድርገዋል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች መኖሪያ ቤታቸውን የማደስ ተግባር ተንተርሶም የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰባት አቅመ ደካማ አረጋዊያን ቤቶችን ጠግኖ አስረክቧል። በሆሳዕናና በአርባ ምንጭ ከተሞች አዳዲስ የአረጋዊያን ገቢ ማስገኛ እና የገቢ ማዕከላት ለመገንባት የመሰረተ ድንጋይ ተጥሏል። ሚኒስቴሩ ለዚህ የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ አድርጓል። በተጨማሪም መንግስት በብሄራዊ ደረጃ የአረጋዊያንን ውለታ የሚያንፀባርቅ አርአያነት ያለው ሁለገብ ማዕከል ለመገንባት እየተንቀሳቀሰ ነው። ማዕከሉ የሚገነባው ሲ.ኤም.ሲ አካባቢ ፀሐይ ሪል ስቴት አካባቢ በ6ሺህ 814 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ነው።
የአረጋዊያንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ብሄራዊ ማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ ላይ የተቀመጡ አምስት የትኩረት መስኮች ሲኖሩ ሁሉም አረጋዊያንንም ይመለከታሉ። እነሱም የሴፍትኔት መርሐ ግብር፣ የሥራ ስምሪትና የተሻሻለ የኑሮ ሁኔታ መፍጠር ሲሆኑ የጤንነት ሁኔታቸው ካሉበት የዕድሜ ደረጃ አንፃር የተለየ እንክብካቤ የሚፈልግ ከመሆኑ ጋር ተሰናስሎ የሚያስፈልጋቸው ማህበራዊ መድህን ነው። ሌላው የጤናቸውን ሁኔታ የሚጨምረውና እንደ ትራንስፖርት፣ መጠለያ ቤትና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶችን ማግኘት የሚያስችላቸው፤ አምስተኛው ደግሞ በብዙ ተጋላጭ የሆኑበትን ጥቃትና በደልን መከላከል መሆኑን ዳይሬክተሩ ይናገራሉ። እነዚህ ለዘለቄታው ሲተገበሩ መሪ ቃሉ ግቡን ይመታል!
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን መስከረም 13/2014