አባ መፍቅሬ የደን ገበሬ

ኢትዮጵያ የብዙ ደማቆች ሀገር መሆንዋ የታወቀ ቢሆንም ታሪካቸው በአግባቡ በወረቀት ላይ ተፅፎ የተመዘገበው የጥቂቶቹ ብቻ ነው። በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎችና ባገኙአቸው ዕድሎች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ዕውቀት ለመቅሰምና የበለጠ ግንዛቤ ለማግኘት የቻሉ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ያገኙትን ዕውቀት ለወገኖቻቸው ለማድረስና አዳዲስ አሠራርንና አስተሳሰብን በሕዝባችን መካከል ለማስረጽ፣ አብዝተው የደከሙና ሕይወታቸውን አሳልፈው እስከ መሰጠት የደረሱ ፋና ወጊ ምሁራን እንደ ነበሩ ይታወቃል።

ሀገራቸውን ከውጭ ወራሪና ጠላት በመከላከል አኩሪ ታሪክ የሠሩ፣ የሕዝባቸውን ደህንነትና አንድነት እንዲጠበቅ ለማድረግ መሥዋዕትነት የከፈሉና አንፀባራቂ ታሪክ የሠሩ ጥቂቶች አልበሩም። በደራሲነት፣ በሙዚቃ፣ በሥዕል፣ በስፖርት፣ በታሪክ፣ በሳይንስና በእምነት አስተምሮ፣ የኪነ ጥበብና የምርምር ሥራዎችም ኢትዮጵያን በዓለም የበለጠ እንድትታወቅ ያደረጉ ትናንትናም ዛሬም ደምቀው የሚታዩ ደማቅ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ብዙዎች ናቸው።

እነዚህ የሀገር ባለውለታዎች ሕይወታቸው ቢያልፍም ደማቅ ታሪካቸው ግን ዘወትር ሲወሳ ይኖራል። ስማቸው ከመቃብር በላይ ሆኖ ተተኪ ትውልድ ይማርበታል፤ ታዳጊዎች ይታነጹበታል፤ ሀገር ተረካቢዎች ዳናቸውን ተከትለው የነገዋን ኢትዮጵያ ይገነቡበታል።

ኢትዮጵያ በየዘመናቱ በሁሉም ዘርፍ ጀግኖችን ስታፈራ ቆይታለች። የዛሬው ጀግና ደግሞ ለየት ያለ ስብዕና ባለቤት የሆኑና በተለይም ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ በእጅጉ አስፈላጊ የሆኑ ሰው ናቸው። የእኒህ ሰው የሕይወት ገጽታ እንዲህ ይነበባል።

የሁሉም አባት ናቸው። ሁሉም ልጆቻቸውም ናቸው ወጣት ፣ አዛውንት ፣ ህጻናት የክርስትና እምነት ተከታዮች ብቻም ሳይሆኑ የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ በአጠቃላይ የደሴ ከተማ ሕዝብ ስለእሳቸው አባትነትና መልካምነት፤ የሥራ ትጋታቸውን ሰላም ወዳድ መሆናቸውን የተፈጥሮ ወዳጅ መሆናቸውን በአንድ ድምጽ ይመሰክሩላቸዋል። እኚህ ታላቅ አባት የሚጠሩትም ሕዝቡ ባወጣላቸው ስም ነው። ማንም ሰው ወላጆቻቸው ያወጡላቸውን መጠሪያ ስማቸውን አያውቀውም እሳቸውም ስለራሳቸው ማውራት የሚወዱ አይደሉም።

ነገር ግን ያገኟቸው ሁሉ አባ መፍቅሬ ይላቸዋል፤ እሳቸውም ተቀብለውታል ። ሊቀ ትጉሃን አባ መፍቅሬ ሰብእ የእድሜያቸውን ከግማሽ በላይ ዛፎችን ሲተክሉ ደኖችን ሲያስጠብቁ አሳልፈዋል። በሥራዎቻቸው የሚደግፏቸውን ሰዎች በተፈጥሮ ላይ የሚያደርጉትን ጥቃት እና ጥፋት ምን ያህል ጉዳት ለው መሆኑን በማስተማር ሰዎች እንዲተባበሯቸው በማድረግ በቤተእምነት ቦታ እና በሌሎች በርካታ አካባቢዎች ዛፎችን ተክለዋል ደኖች እንዲጠበቁ አድርገዋል። እኚህ በደሴ ከተማ ሕዝብ ዘንድ እጅግ የሚወደዱት አባት በ96 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል። በዛሬው የሕይወት ገጽታ አምዳችን እኚህን አባት ሕይወት የሚዘክር ከሰጧቸው ቃለመጠይቆች ፣ ስለእሳቸው ከተጻፉ እና ከተነገሩ ጥታሪኮች ይህንን ጥንክር አዘጋጅተናል።

“ደሴን በአራቱ ማዕዘን ስታዩአት አረንጓዴ ብትሆንባችሁ አትገረሙ፤ እርሳቸው ከአርባ ዓመት በላይ የለፉበት ነው። ለእርሳቸው ዛፍ የሚቆርጥ ቀርቶ ቅጠል የሚበጥስም የማርያም ጠላት ነው። አይከፈላቸውም፣ አልተመደቡም፣ ደብዳቤ የሰጣቸው የለም፣ እርሳቸው ግን ‘የሀገሬ መራቆት የኔ መራቆት ነው’ ብለው ደን ሲተክሉና ሲንከባከቡ ይኖራሉ” በማለት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በአንድ ፅሁፉ ስለ ጉምቱው የወሎ አባት ተምሳሌታዊ ሥብዕና አድናቆቱን ሰንዝሯል።

‹‹አባ መፍቅሬ ሰብዕ በደሴ ከተማ ከልጅነታችን ጀምሮ ስማቸውን እየሰማን ያደግን የሃይማኖት አባት ናቸው። ደሴ ተወልዶ እና አድጎ እሳቸውን የማያውቅ ይኖራል ማለት አይቻልም።›› በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ኡስታዝ አቡበከር አህመድ በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት መልዕክት ነው።

አባ መፍቅሬ በጌምድር (ጎንደር) ክፍለሀገር ውስጥ በአገልግሎት በነበሩበት ጊዜ ደን ያለአግባብ ሲጨፈጨፍ በማየታቸው ከ 1943 ዓ.ም ጀምሮ ‘ደን መጠበቅ አለበት’ የሚል እሳቤ በመያዝ ዛፎችንም መትከል መጀመራቸውን ያስረዳሉ።

“የደን መጨፍጨፍ ለተለያዩ የተፈጥሮ ችግሮች ይዳርጋል። ዝናብ ይጠፋል፣ ድርቅ ይከሰታል፣ ሙቀት ይጨምራል። በመሆኑም ያለአግባብ ዛፍ የሚቆርጡትንና ደን የሚጨፈጭፉትን ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ በተለያየ ጊዜ ትምህርት እሰጣለሁ። ከዚህ አልፈው በእኩይ ተግባራቸው የሚቀጥሉትንም የእግዚአብሔርን ቃል በመጥቀስ እገዝታቸዋለሁ” በማለት ለተፈጥሮ ያላቸውን ስስት ይናገራሉ።

የስማቸው ትርጓሜ እንደሚያስረዳው “መፍቅሬ ሰብእ” ማለት ሰውን የሚወድ በሰዎችም ዘንድ ተወዳጅ የሆነ ማለት ሲሆን ስማቸውንም ከተግባራቸው ተነስቶ ሕዝብ አወጣላቸው፣ እርሳቸውም ተቀበሉት። “መፍቅሬ ሰብ ማለት ሰው የሚወደው ማለት ሲሆን ዋናው ስምም የክርስቶስ ስም ሲሆን (ሰው ወዳጅ እግዚአብሔር) የሚል ትርጓሜም ስላለው ስያሜውን ልቀበለው ችያለሁ” በማለት አባ መፍቅሬ ሰብእ ይናገራሉ። ከትውልድ ሀገራቸው መቄት ወረዳ ወደ ደሴ ከተማ ከመጡ ጀምሮ ከቆሎ ተማሪነት ጀምሮ በሃይማኖት ትምህርት አሳልፈው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተዘዋወሩ አገልግለዋል።

አባ መፍቅሬ ሰብእ ለእጽዋት የተለየ ፍቅር አላቸው፣ ለደን የተለየ ቦታ ይሰጣሉ። የእድሜያቸውን ከግማሽ በላይ የተለያዩ ዛፎችን በመትከል ፣በመንከባከብ እና በመጠበቅ ሌሎችም እንዲንከባከቧቸው በማድረግ ያስተምራሉ።

በአንድ ወቅት በፋና ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ-መጠይቅ የደን ማስከበር ሥራቸውን በ1943 ዓ.ም በበጌ ምድር እንደጀመሩት ተናግረዋል። ደን ለሰው ልጆች ብቻም ሳይሆን በሥፍራው የሚኖሩ የዱር አራዊቶችን ብርቅዬ ተብለው የሚጠሩ እንስሳት ቁጥር እንዳይመናመን እንደሚያደርግ በተለያዩ መድረኮች ያስተምራሉ።

ደን የሚጨፈጭፉ እና በተፈጥሮ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሰዎችን ተፈጥሮን ብታጠፉ ዝናብ አታገኙም እያሉ ይናገራሉ። በሥራቸው ቁጭ ብለው የተማሩ የሰንበት ትምህርት ቤት አገልጋይ ህጻናትን የተለያዩ መጫዎችን በመስጠት እና በማበረታታት የተከሏቸውን ችግኞች እንዲያጠጡላቸው ያደርጋሉ ወጣቶችም ቢሆኑ በዚህ ተግባር ላይ እንዲሠማሩ ያደርጋሉ።

በሃይማኖት አባትነታቸው ብቻ ሳይሆን ለተፈጥሮ ባላቸው ቦታ የሚታወቁት አባ መፍቅሬ ከሚታወቁባቸው ሥራዎቻቸው ውስጥ አንደኛው የግሸን ደብረከርቤ የእምነት ሥፍራ የእምነቱ ተከታዮች ከተለያዩ ቦታዎች መጥተው እንዲገለግሉበት ያደረጉበት መንገድ ነው።

ግሸን ደብረ ከርቤ እንደ ዛሬው መንገዱ ሳይሠራና ለተጓዦች ምቹ ሳይሆን ብዙዎች ቦታው ላይ ተገኝተው የነፍስ ርሃባቸውን ለማስታገስ በምኞት ብቻ በሚኖሩበት ጊዜ የሕዝብን ስሜት ተረድተውና የቦታውን ታላቅነት ዓለም እንዲመሰክር፣ ወደሥፍራው መሄድን የተመኙም ምኞታቸው እንዲሰምር በ1973 ዓ.ም በወቅቱ ለነበሩ ባለሥልጣናት አባ መፍቅሬ ሃሳብ አቀረቡ።

ያቀረቡት ምክረ ሃሳብ አመኔታ በማግኘቱ እንኳን ለሰው ለዝንጀሮም ያስቸግራል የሚባለውን 17 ኪሎ ሜትር ተራራ መንገድ እንዲሠራበት በማድረግ እልፎችን ከምኞታቸው ጋር ያገናኙ፣ ታሪክ በደማቁ ከወርቅ መዝገብ ላይ ያሰፈራቸው፣ የግማደ መስቀሉ ማረፊያ ግሸን ደብረ ከርቤ ክብረ በዓል በመጣ ቁጥር ስማቸው አብሮ የሚነሳ አባ ፍቅሬ ሰብእ ናቸው።

ህጻን ዘላሊበላ በላሊበላ የሚገኙ ካህናት ያወጡላቸው ስያም ነው ‹‹አባ መፍቅሬ ›› ደግሞ በሥራዎቻቸው በተግባራቸው የአካባቢው ማህበረሰብ ሕዝብ ያወጣላቸው ስያሜ ነው። በወሎ እና አካባቢዋ ከሚከበሩ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ክብረ በዓላት አባ መፍቅሬን እነኚህን አባት ለይቶ ማየት በፍጹም አይቻልም።

አባ መፍቅሬ ሰብን በደሴ ከተማ የማያውቃቸው ሰው በፍጹም የለም። በክርስትና እምነት ተከታዮች ብቻም ሳይሆን በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በአካባቢው ማህበረሰብ በደሴ ሕዝብ በእጅጉ የሚታወቁ እና የሚወደዱ የሃይማኖት አባት ብቻም ሳይሆን የሀገር ሽማግሌ አስታራቂ ፣ ልዩ የሀገር ፍቅር ያላቸው የተፈጥሮ ዘብ ናቸው። በዚህም ምክንያት አባ መፍቅሬ ሰብእ የሚል ስያሜ በጎንደር ከተማ ዙር አምባ ወጥቶላቸዋል።

የስማቸው ትርጓሜ እንደሚያስረዳው “መፍቅሬ ሰብእ” ማለት ሰውን የሚወድ በሰዎችም ዘንድ ተወዳጅ የሆነ ማለት ሲሆን ስማቸውንም ከተግባራቸው ተነስቶ ሕዝብ አወጣላቸው፣ እርሳቸውም ተቀበሉት። “መፍቅሬ ሰብ ማለት ሰው የሚወደው ማለት ሲሆን ዋናው ስምም የክርስቶስ ስም ሲሆን (ሰው ወዳጅ እግዚአብሔር) የሚል ትርጓሜም ስላለው ስያሜውን ልቀበለው ችያለሁ”።

በሀይቅ ገዳም በርካታ ዛፎችን ተክለዋል ። ልዩ የሚያደርጋቸውም የሚተክሏቸው የአየር ንብረት ለውጥ ላይ የራሳቸውን ተጽዕኖ ማሳረፍ ለውጥ ማምጣት የሚችሉ ተክሎችን እንዲሁም ሀገር በቀል እጽዋቶችን ነው።

ባህር ዛፍ ፣ ዋንዛ ፣ የሀበሻ ጽድ ፣ ዋርካ አባ መፍቅሬ ሰብእ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ላበረከቱት አስተዋጽኦ በክብር የሸለማቸው ሲሆን የሚተክሏቸውን እጽዋቶች ልጆቼ ብለው ጭምር ይጠሯቸዋል። ከተለያዩ ቦታዎች ሽልማት እና እውቅና የተበረከተላቸው ሲሆን ወሎ ዩኒቨርሲቲ ለአበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅና ሰጥቷቸዋል። በዚህም ‹‹አባ መፍቅሬ የደን ገበሬ››

የሚል ስያሜም አላቸው።

በደሴ ከተማ የሚገኘውን የደሴ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን በአካባቢው አጠጠራር ‹‹ዳግማዊ ላሊበላ›› እየተባለ የሚጠራ ሲሆን ህንጻ ሲሠራ ይህ ቤተክርስቲያን 18 ዓመታትን የፈጀ እና በብዙ አቅም ተሠርቶ እና ተገንብቶ ቀላል የማይባል ገንዘብን ከፈጀ በኋላ ባለመጠናቀቁ የህንጻ ቤተክርስቲያን አሠሪ ኮሚቴው የአቡነ አትናትዮስን እና የእሳቸውን አባ መፍቀሬ ሰብእ ፎቶ በጨረታ መልክ ለገበያ ቢያቀርቡት ከፍተኛ ገንዘብ ሊያገኙበት እንደሚችሉ በማሰብ ለአባ መፍቅሬ ሃሳብ ያቀርቡላቸዋል። አባ መፍቅሬ ይህንን ሃሳብ ሲሰሙ ለቤተክርስቲያ ከሆነ እንኳን ፎቶዬን እኔንም ሽጡኝ ብለው መናገራቸው የብዙዎች ትውስታ ነው።

አቶ ሰኢድ ሀሰን የደሴ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ አባ መፍቅሬ ሰብእን ከ30 ዓመት በላይ እንደሚያውቋቸው ገልጸው ስለ ማህበራዊ ተሳትፏቸው ምስክርነታቸውን ሲሰጡ “የአባ መፍቅሬ መገለጫ የሆነው ዋናው ባህሪያቸው ሰውን በሃይማኖቱና በማንነቱ ሳይመዝኑ በደስታውም ይሁን በኀዘኑ ጊዜ ፈጥነው ከጎኑ በመገኘት ‘አይዞህ’ የሚሉ አባት ናቸው። በሃይማኖቶችና በአማኙ መካከልም መተባበርና መከባበር እንዲኖር የሰሩት ተግባር ሁልጊዜም ከሰዎች ልብ ውስጥ እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል” ይላሉ።

ዛሬ ላይ ግሸን ደብረ ከርቤ በዓመታዊ የንግሥ በዓሉ ላይ ሚሊዮኖች የሚገኙበት ስፍራ በመሆኑ ከሃይማኖታዊ ስፍራነቱ በተጨማሪ ለአካባቢው ማህበረሰብና ለዞኑ የገቢ ምንጭ ሆኖም እያገለገለም ይገኛል። ዲያቆን ናሁሰናይ ወልደሚካኤል ስለ አባ መፍቅሬ ሰብእ ተፈጥሮንና ልማት ወዳድነታቸውን ሲገልጽ “ማንኛውም ሰው አካባቢውን እንዲያለማ፣ ዛፎችን በመትከል ተፈጥሮን መንከባከብ እንዳለበትና የሀገር ቅርሶችን መጠበቅ እንደሚገባው በአውደምህረት ላይ ሳይቀር ትምህርት የሚሰጡ ድንቅ አባት ናቸው” ይላል።

“ዛፎቼ እንደሰው የማወራቸው ልጆቼም ጭምር ናቸው። ከእነርሱ ጋር በምሆን ሰዓት ሳልበላ ሁሉ እጠግባለሁ” የሚለው ንግግራቸው አባ መፍቅሬ ከተፈጥሮ ጋር ያላቸውን ጥልቅ ቁርኝት ማሳያ ነው።

አባ መፍቅሬ የእድሜ ዘመናቸው ሙሉ ዛፍ በመትከል ተፈጥሮን መንከባከባቸውን፣ ለህብረተሰቡ ጠቃሚ የሆኑ በርካታ የልማት ሥራዎችን መሥራታቸውንም ለመዘከር “አባ መፍቀሬ፣ የደን ገበሬ/ አባ መፍቅሬ ሰብእ፣ የዛፎች ቤተሰብ” የሚል የአድናቆት መጠሪያ ስንኝ ማህበረሰቡ እስከማውጣት የደረሰ ሲሆን በተለያዩ ጊዜያትም በዞንና በክልል ደረጃ በርካታ የእውቅና ሽልማቶችን አግኝተዋል።

የደሴ ከተማ ማህበረሰብም ለአባ መፍቅሬ ሰብእ ያለውን ፍቅርና አክብሮት ለመግለጽ ባዋጣው ገንዘብ ወጪያቸውን ችሎ ሃይማኖታዊ ጸሎትና እንዲያደርሱና ጉብኝት እንዲያደርጉ ወደ ኢየሩሳሌምና ግብጽ ደርሰው እንዲመጡ አድርጓቸዋል።

የደሴ ከተማ በተለያየ ዘመን ካፈራቻቸው ታላላቅ ሰዎች መካከል ተፈጥሮን አብዝተው በመንከባከብ ችግኞችን በመትከል በርካታ ሰው ሰራሽ ደኖችን በመፍጠር የሚታወቁት ታላቁ አባት አባ መፍቅሬ ሰብእ አንዱ ናቸው።

አባ መፍቅሬ ሰብእ በማህበራዊ ኑሮ ላይ ያላቸው ንቁ ተሳትፎ በድፍን የደሴ ከተማ ሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ ካደረጓቸው ተግባራት አንዱ ነው። የታመመ በመጠየቅ፣ የሞተን በመቅበር፣ ኀዘን በመድረስ፣ በደስታ ጊዜ ሰርግ ላይ በመገኘት፣ በበዓላት “እንኳን አደረሳችሁ” ለማለት ሰዎች ቤት በመሄድ፣ በወሎና በአካባቢው በሚከበሩ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሕዝባዊ በዓላት ላይ በማስተባበርና በማስተማር የሚያደርጓቸው ተሳትፎዎች ለሌሎች የኃይማኖት አባቶች እንደ ምሳሌ የሚጠቀሱ ናቸው።

ይህ ዘገባ ሲዘጋጅ አባ መፍቅሬ ሰብእ እድሜያቸው 80ዎቹ አጋማሽ ላይ የደረሰ መሆኑን የሚገልፁት አባ፣ የእድሜያቸውን 60ውን ዓመታት ከኃይማኖት ትምህርት ጎን ለጎን ዛፍ በመትከልና ተፈጥሮን በመንከባከብ እንዳሳለፉ ይናገራሉ። “ዛፎችን መትከል የጀመርኩት በቤተክርስቲያን ቅጥር ጊቢ ውስጥ ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ ቤተክርስቲያን ውስጥ በሃይማኖታዊና በሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ምክንያት ሕዝብ የሚሰባሰብበት ስፍራ በመሆኑ ማረፊያ ጥላ እንዲሆን በማሰብ ነው” ይላሉ።

በደሴ ከተማ የሚገኙትን አብዛኞቹን አብያተ ክርስቲያናት ማለትም የቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል፣ ቁስቋም፣ አማኑኤል እና ኪዳነ ምህረት አብያተ ክርስትያናትን ካሳነጹት አባቶች መካከል አንዱ አባ መፍቅሬ ሰብ በመሆናቸው ምዕመኑ ሁልጊዜም ያስታውሳቸዋል። በሌላም ማህበረሰቡን በሚጠቅሙ የልማት ሥራዎች ላይ ነዋሪውን በማሳተፍና በማስተባበር ብዙ በጎ ተግባራትን ማከናወን የቻሉ አባት ናቸው።

መሪጌታ እዝራ በአምላኩ በልጅነት እድሜያቸው የቤተክህነት ትምህርት ለመከታተል በ1979 ዓ.ም ከትውልድ ሀገራቸው መቄት ወረዳ ወደ ደሴ ከተማ ከመጡ ጀምሮ ከቆሎ ተማሪነት ጊዜያቸው አንስቶ አባ መፍቅሬን የሚያውቋቸው ሲሆን ከእርሳቸው መለኮታዊ እውቀትን ከመማራቸው በተጨማሪ ችግኝ መትከልና የመንከባከብ ልምድ መውረሳቸውን ይናገራሉ።

“ልጅ ሆኜ የቆሎ ተማሪ እያለሁ እርሳቸው የሚተክሉትን ችግኝ ከወንዝ ውሃ እያመጣን በማጠጣት እናግዛቸው ነበር። ተግባሩን ልማድ አድርጌው አሁን ድረስ ችግኝ እተክላለሁ። አብዛኞቹን ደሴ ከተማ ውስጥ ያሉትን የቤተክርስቲያን አጸዶች ያሳመሩት እርሳቸው ሲሆኑ ለዚህም የቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል አንዱ ማሳያ ነው” ይላሉ መሪጌታ እዝራ።

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በአንድ ወቅት ስለአባ መፍቅሬ ሰብእ “የተሸጡት አባት” በሚል ርዕስ በአዲስ ጉዳይ መጽሄት ላይ ባሳተመው ጽሁፉ ስለ አባ መፍቅሬ ሰብእ የስብዕና ከፍታ እና የሕዝብ ፍቅር እንዲህ በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷል፤

“ለእርሳቸው ዘርና ሃይማኖት ሰውን ለመርዳት መመዘኛዎች አይደሉም። ሰውነት ብቻ ይበቃቸዋል። ይህ ርዳታቸው ከመከራ ያወጣቸው፣ ከችግር የታደጋቸውና ሕይወታቸውን ያቀናላቸው ሰዎች ስለ እኒህ አባት ሲያወሩ ከማያቋርጥ ዕንባ ጋር ነው። አንዳንዶች እንዲያውም ከንግግር ይልቅ እርሳቸውን እያሰቡ ዝም ብለው በማልቀስ ይገልጧቸዋል። መቼም ለአንዳንዱ አብዝቶ አይደል የሚሰጠው። እርሳቸው የአካባቢ ጥበቃ አርበኛም ናቸው።

ዳንኤል በፅሁፉ ስለ አባ መፍቅሬ ሰብዕ የረዥም ዓመታት የተፈጥሮ ጥበቃ ሥራ ውጤታማነትን ከመግለፁ ባሻገር የአባ መፍቅሬን የአካልና የመንፈስ ጥንካሬ በማድነቅ፤ በራስ ተነሳሽነት ለሀገር ስላደረጉት ትልቅ ተግባር እንዲህ ይላል፦

“በዚህ የእርጅና እድሜያቸው እንኳን መኮትኮቻና መቆፈሪያ፣ አካፋና ባሬላ ይዘው በደሴ ተራሮች ላይ ዛፍ ሲተክሉ ይውላሉ። ደሴን በአራቱ ማዕዘን ስታዩዋት አረንጓዴ ብትሆንባችሁ አትገረሙ፤ እርሳቸው ከአርባ ዓመት በላይ የለፉበት ነው። ለእርሳቸው ዛፍ የሚቆርጥ ቀርቶ ቅጠል የሚበጥስም የማርያም ጠላት ነው። አይከፈላቸውም፣ አልተመደቡም፣ ደብዳቤ የሰጣቸው የለም፣ እርሳቸው ግን ‘የሀገሬ መራቆት የኔ መራቆት ነው’ ብለው ደን ሲተክሉና ሲንከባከቡ ይኖራሉ።”

አባ መፍቅሬ ሰብእ ከተከሏቸው ደኖች መካከል ከደሴ ከተማ 35 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውና በዘጠነኛው ክፍለ ዘመን እንደተመሠረተ የሚነገርለት የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ቅጥር ጊቢ አይነተኛ ማሳያ ነው። ገዳሙ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ለሚመጡ ተማሪዎች ሃይማኖታዊ ትምህርት ይሰጥበት የነበረ ሲሆን አንዳንድ ምሁራንና አበው “የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ሥነ መለኮት ዩኒቨርሲቲ” በማለት ይገልፁታል። አባ መፍቅሬ ሰብእ የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ቅጥር ግቢን የተለያዩ ሀገር በቀል ዛፎችን በመትከል አካባቢውን ባላበሱት ግርማ ሞገስ፣ በጣም ማራኪ፣ የዓይን ማረፊያና የመንፈስ ምግብ ብሎም የቱሪስት መስህብ መሆኑ ለታላቅ ተግባራቸው ቋሚ ምስክር ሆኗል።

“የደሴ ከተማ ሕዝብ ከሕዝበ ክርስቲያኑ ባልተናነሰ ሙስሊሙ ማህበረሰብም ለኔ ያለውን ፍቅርና አክብሮት ይገልጽልኛል። ያገኙኝ ሁሉ ‘አላህ ረዥም እድሜ ያኑርህ’ እያሉ ይመርቁኛል” በማለት የከተማውን ነዋሪ ስለሚለግሳቸው ፍቅር እና አክብሮት ይናገራሉ።

በደሴ ከተማ ሕዝብ ዘንድ በእጅጉ የሚታወቁት እኚህ አባት ለብዙዎች ምሳሌ መሆን የሚችል ሥራን እስከ እርጅና እድሜቸው ድረስ ሠርተው አባ መፍቀሬ ሰብእ ባደረባቸው ህመም በ96 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል። ለሀገር የዋሉት ውለታ እና የአባትነት ፍቅራቸውም በቅርበት ለሚያቋቸው የማይጠገብ ተነግሮ የማያልቅ ሲሆን እንደሀገር ያላቸው እውቅና እና የተሰጣቸው ቦታ እምብዛም አልተጠቀምንባቸውም በሚል የሚያስቆጭ መሆኑን ይገልጻሉ።

በአጠቃላይ ሰውና ሸክላ ተሰባሪ ነው። ዋናው ነገር የማይሰበር ስም ትቶ ማለፍ ነው። አባ መፍቀሬ ይህንን ልዕልና ከተጎናጸፉ ጥቂት ሰዎች ውስጥ አንዱ ናቸው። በኖሩባቸው ዓመታት ሰውን በስውነቱ እንጂ በሃይማኖቱ እና ብሄሩ ሳይለዩ ማድረግ የሚገባቸውን ያደረጉ የታላቅ ስብዕና ባለቤት ናቸው።

አሁን እንደሀገር የተጠናወተንን በሽታ አራግፈው የጣሉና ለብዙዎችም በአርአያነት የሚጠቀሱ ስነበሩ። ለእኒህ የገዘፈ ሥብዕና ለነበራቸው አባታቸውን ነፍስሄር በማለት ሁላችንም የሳቸውን ሥብዕና የምንላበስበትን ጸጋ እና አቅም ይስጠኝ በማለት ጽሁፌን አጠቃልላለሁ።

 አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You