አያት ቅድመ አያቶቻችን በጥበባቸው ፊደል ቀርጸዋል። እነሆ በዚህ ጥበባቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ የራሷ ፊደል ያላት ብቸኛ አገር እንድትባል አብቅተዋል። ‹‹የራሷ ፊደል ያላት›› እየተባለም በዓለም አደባባይ ይነገርላታል። በዚህ ላይም ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘጋቢ ፊልም ሰርተውላታል።
አያት ቅድመ አያቶች የቀረጹትን ይህን ፊደል ደግሞ ቀጣዩ ትውልድ በማስተዋወቅ፣ እንዲማሩበት በማድረግ፣ ለህጻናት ዜማ በመፍጠር ቅደም ተከተሉን በማስጠናት፣ የፊደል ገበታ የመቅረጽ ሥራ ሰርቷል።
በእዚህ በኩል ተጠቃሽ ተግባር ያከናወኑ አንድ የጥበብ አርበኛን ለዛሬ ይዘን ቀርበናል። ወቅቱ ትምህርት ቤቶች የሚከፈቱበት፤ በተለይም ወደ አንደኛ ክፍል እና በከተማ አካባቢ ደግሞ መዋለ ሕጻናት የሚጀመርበት ነውና ይዘን የቀረብነው ስራ የአንድ ታዋቂ የአማርኛ ፊደል የጥበብ አርበኛን የሚመለከት ነው።
እኚህ ታላቅ ሰው ‹‹የፊደል ገበታው ጌታ፤ የእውቀት አባት›› የሚሉ ቅጽል መጠሪያዎች አሏቸው። ኢትዮጵያ የራሷ የዘመን አቆጣጠር እና የራሷ የፊደል ገበታ አላት ብለን በኩራት እንድንናገር ካደረጉን ሊቃውንት አንዱ ናቸው። ቀኛዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ!
የአዲስ ዓመት የመጀመሪያ ወር ላይ ሆነን ታሪካችንን እና ቋንቋችንን ስናስብ፤ የፊደል አባት የሚባሉት ቀኛዝማች ተስፋገብረሥላሴን ለማስታወስ የምንገደደውም ለዚህ ነው። ትምህርት ቤቶች እየተከፈቱ ነው። አዳዲስ ሕጻናት ወደ ትምህርት ቤት ገብተው ‹‹ሀ ሁ›› ሊሉ ነው። መንግስት እድሜው ለትምህርት የደረሰ አንድም ህጻን እቤት መዋል የለበትም፤ ትምህርት ቤት መግባት ይኖርበታል እያለ በሚገኝበት ወቅት ላይ እንገኛለን። እናም በእዚህ ወቅት እኚህ ታላቅ ሰው ሊታወሱ ይገባል ብለን ተነሳን። እኝህ የፊደል ገበታ አባት የሚባሉት ቀኛዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ የፊደል ገበታን ቀርጸው ‹‹እውቀት ይስፋ ድንቁርና ይጥፋ!›› ብለው ብዙ የሰሩ ናቸው።
ጋዜጠኛና የታሪክ ጸሐፊው ፍጹም ወልደማርያም ‹‹ያልተዘመረላቸው›› በተሰኘው መጽሐፉ ላይ ደግሞ ይህን ንግግራቸውን እናገኛለን።
‹‹ማንኛውም ሰው እናት አገሩ ባስገኘችለት፤ ሊቃውንት አባቶች አዘጋጅተው ባቆዩለት ፊደል ተምሮ፤ ማንበብና መጻፍ ተቀዳሚ ተግባሩ ይሆናል። መምህራንም የፊደላትን ስነ ባህሪ ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል። ይህም በየጊዜው ለሚነሳው ብሄራዊ ትውልድ፤ ራሱን ክዶ ሌላውን ሆኖ እንዳይገኝ ያደርገዋል፤ ወይም ‹መነሻውን አያውቅ፤ መድረሻውን ይናፍቅ› ከመሰኘት ነጻ ያደርገዋል››
ይህ የቀኛዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ ምክረ ሀሳብ በተለይ በዚህ ወቅት ለመምህራን አስፈላጊ መልዕክት ነው። አባቶች ቀርጸው የሰጡንን የፊደል ገበታ የማሳወቅ ኃላፊነት አለባቸው። ከአማርኛ የፊደል ገበታ ይልቅ ለእንግሊዘኛ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል የሚባለው ወቀሳ ተደጋግሞ ሲነሳ ይሰማል። ‹‹መነሻውን አያውቅ መድረሻውን ይናፍቅ›› ያሉት ጥበበኛው ቀኛዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ የፈሩት እንዳይደርስ መምህራን ትኩረት መስጠት አለባቸው።
ጋዜጠኛና የታሪክ ፀሐፊው የቀኛዝማች ተስፋገብረሥላሴን ታሪክ ይቀጥላል። ከእፅዋት ቀለም አንጥረው፣ ከሸምበቆ ብዕር ቀርፀው፣ የፍየል ቆዳ ፍቀውና አለስልሰው በመጻፍ ‹‹ሀ ሁ… ዕውቀት ይስፋ፣ ድንቁርና ይጥፋ! ይህ ነው የኢትዮጵያ ተስፋ›› የሚል መፈክር ተጠቅመው ወደ ማህበረሰቡ ገብተዋል። ይህን ሲያደርጉም በተደላደለ ኑሮ አይደለም። አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ሰርተው ራሳቸውን ለመቻል በእንጨት ፈለጣ፣ ውሃ በመቅዳት፣ ጉድጓድ በመቆፈር፣ በጎዳና ንግድ እና መሰል ትናንሽ ስራዎች ላይ ተሰማርተዋል። ወደ አዲስ አበባ የመጡትም በ1909 ዓ.ም ገና የ15 ዓመት ልጅ ሆነው ነበር።
ቀኛዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ የተወለዱት በሰሜን ሸዋ ዞን በቡልጋና በረኸት ተድላማርያም ወረዳ ክትብ ወይራ አክርሚት በሚባል ቀበሌ ውስጥ ነው። ከአባታቸው ከመምህር ገብረሥላሴ ቢልልኝ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ሥዕለሚካኤል ወልደአብ ታህሳስ 24 ቀን 1895 ዓ.ም ተወለዱ። ገና የአራት ዓመት ሕጻን እያሉ ነበር አባታቸው መምህር ገብረሥላሴ ፊደል ያስቆጠሯቸው።
በአካባቢው ማህበራዊ አኗኗር ተፅዕኖም ፈርጠም ማለት ሲጀምሩ እረኝነትና የግብርና ሥራ እንዲሰሩ ተደረገ። ቀለም ገብ መሆናቸውን ያስተዋሉት አያታቸው መምሬ ቢልልኝ ግን ይህን እያዩ ዝም ማለት አልቻሉም። ከወላጆቻቸው ነጥቀው መምህር ገብረአብ ለሚባሉ ሰው ሰጧቸው። መምህር ገብረአብም ቃላቸውን ጠብቀው በማስተማር ለቁም ነገር አበቋቸው።
ቀኛዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ ከአባታቸውና ከመምህሮቻቸው በቀሰሙት እውቀት ብራና እየፋቁና ቀለም እየበጠበጡ በመጻፍ ወደ ማህበረሰቡ መግባት ጀመሩ። በዚህ ጅማሮ ላይ እያሉ ግን አንድ ፈተና ገጠማቸው። አባታቸው አረፉ፤ የቤተሰቡ ጫና እርሳቸው ላይ ሆነ። በግብርና ሥራ ሊሰማሩም የግድ ሆነ። ገና 15 ዓመት ሳይሞላቸው በዚህ ኃላፊነት ላይ የነበሩት ብላቴና በ15 ዓመታቸው ግን ወደ አዲስ አበባ መጡ። አዲስ አበባ መጥተው ግን ያደረጉት ይህን ነበር።
ከተለያዩ እፅዋት ቀለም እየበጠበጡ የመቃ ብዕር (ከቀጭን ሸንበቆ የሚዘጋጅ) አዘጋጅተው የአማርኛ ሆሄያትን መጻፍ ጀመሩ። የጻፉትን ጽሑፍ ይዘውም በአዲስ አበባ ከተማ መዞር ጀመሩ። በኋላም የመርሐ ጥበብ ማተሚያ ቤት ሲቋቋም የፊደል ገበታውን አሳትመው በመላው ኢትዮጵያ ማሰራጨት ጀመሩ። ገጠራማው የአገሪቱ ክፍልም ፊደላትን ማየት ጀመረ፤ ይህ የሆነው እንግዲህ ከዛሬ 104 ዓመታት በፊት ነው።
እሳቸው ግን አሁንም ፈተና አላጣቸውም። የፋሽስት ጣሊያን ወራሪ ድርጊታቸው አላማረውም። ማህበረሰቡን ማንቃታቸውን አልወደደውም። በዚህም ብዙ ችግር ደርሶባቸዋል። እርሳቸው ግን ጥበበኛ ነበሩና ሊበገሩ አልቻሉም፤ አሁንም ግን ትግላቸው በብዕር ነው። ጥበበኛው ብላቴና የፊደል ገበታን መቅረጽና ማስፋፋት ብቻ ሳይሆን ግጥም መጻፍም ጀመሩ። የወቅቱን የፋሽስት ጣሊያን ድርጊት እንዲህ ሲሉ በግጥም ስሜታቸውን ተናግረዋል።
ከባህር እየወጣ መጣልን አሳው፣
በሰይፍ እየመተርን፣ በአረር እየቆላን ፈጥነን እንብላው።
ጥንት አባቶቻቻን ምግባቸው ይህ ነው፣
ምነው ያሁን ልጆች ዝምታው ምንድነው፣
የባህሩ አሳ ወጥቶ ከጎሬው፣
አጥማጁ አንቆ ሥጋውን ይብላው እያሉ በመጻፍ ሕዝቡን ለነፃነት ጦርነት አነሳስተዋል።
በጣሊያን ወረራ ጊዜም የዳግማዊ አጼ ምኒልክ ፎቶ ያለበትን አርማ በማድረግ የተለያዩ ጽሑፎችን አሰራጭተዋል። በወቅቱ አንድ ጽሑፍ ሳንሱር ሳይደረግ አይታተምም ነበርና ቀኛዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ ለእስር ተዳርገዋል። ያሰራጩት ጽሑፍ ሁሉ ከመላ አገሪቱ እንዲሰበሰብ ተደርጓል፤ ይዞ የተገኘም ታስሯል። ቤተሰቦቻቸውም ታስረዋል፤ መኖሪያ ቤታቸውም ታሽጓል። ተከሰውም በንጉሡ ፊት ቀርበው ነበር።
ንጉሡም ‹‹በመላ ኢትዮጵያ ያሰራጨኸውን ጽሑፍ የት ነበር ያሳተምከው?›› ሲሉ ጠየቋቸው። እሳቸውም ‹‹በሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቂርሎስ ግቢ ባለው ማተሚያ ቤት›› ሲሉ መለሱ። ጳጳሱም ‹‹እንዴት በብጹዕነትዎ ግቢ ወንጀል ይሰራል?›› በሚል ተጠየቁ። ጳጳሱም ‹‹ንጉሥ ሆይ! አገራችሁን አትካዱ፤ ከጠላት ጉቦ አትቀበሉ፤ ብሎ መስራት ወንጀል ነውን?›› ሲሉ በጥያቄ መልክ መለሱ።
ነገሩ ይጣራ ተብሎ ለስድስት ወራት ያህል በማረፊያ ቤት እያሉ ከጣሊያን ጋር ያለው ጦርነት ተፋፋመ። እነ ቀኛዝማች ተስፋ ገብረሥላሴም ተፈቱ። ከጣሊያን ወረራ ጊዜ ጀምሮም በአርበኝነት ከፍተኛ ሚና ተወጥተዋል። በጣሊያን ወረራ ጊዜም እንዲህ ብለው ግጥም ጽፈዋል።
የተረገመ ነው አገሩን የካዳ፣
ክብሩን ነፃነቱን አበሻን የጐዳ።
ከኢትዮጵያ ከሐበሻ ጠላት ጉቦ የበላችሁ፣
የትነው የምትበሉት አገር ሳይኖራችሁ።
ደራሲና ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ስለፊደል ገበታ አባት ቀኛዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ እንዲህ ብሎ ነበር። ‹‹አንድ ህፃን ልክ አራት አመት ሲሞላው ከፊደል ገበታ ጋር መተያየት ይጀምራል። ‹‹ሀ›› በል፣ ‹‹ሁ›› በል እየተባለ ይረዳል። የዓለምን ምስጢር፣ ውጣ ውረድ በፊደሎች መቁጠር ይጀምራል። እነዚያ ፊደሎች እየሰፉ እየተገጣጠሙ ሲመጡ ቃል ሆነው ሀሳብ ያስተላልፋሉ። ሀሣብ ደግሞ ብዙ አይነት እውነታዎችን በውስጡ የያዘ ነው። የህይወት ጉዞ እንግዲህ ይጀመራል። በሀገራችን ኢትዮጵያ በየቤታችን ውስጥ ‹‹ሀ ሁ›› ያስቆጠሩን ማናቸው ብንባል ብዙ ሚሊዮኖች አንድ ላይ ‹‹ተስፋ ገብረሥላሴ እንላለን››
ቀኛዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ በኪነጥበቡ ዘርፍም በብዙ ሥራዎች ተጠቃሽ ናቸው። ከሀገር ፍቅር ቴአትር መስራቾች አንዱ ነበሩ።
በ1933 ዓ.ም በውጭም ሆነ በውስጥ ያሉ የኢትዮጵያ አርበኞች ጣሊያንን ከወረራው አጨናግፈው አገራቸውን ተረከቡ። በሰው ጉልበት ይሰራ የነበረው የቀኛዝማች ተስፋ የፅህፈት መሣሪያ በጣሊያኖች ተወርሶ ለሌላ ማተሚያ ቤት ተሰጥቶ ነበር። እርሳቸውም ተስፋ ባለመቁረጥ በአዲስና በጋለ መንፈስ ተነሳስተው ‹‹ድንቁርና ይጥፋ ዕውቀት ይስፋ፣ ይህ ነው የኢትዮጵያ ተስፋ›› በማለት በሌላ ማተሚያ ቤት እያሳተሙ የወገናቸውን እውቀት ለማጐልበት እንደገና ሰርተዋል። የህትመት መሳሪያ ከውጭ በማስመጣትም እንዲያውም የበለጠ ሰርተዋል። የማተሚያ ባለሙያ እንደነበሩም ይነገርላቸዋል። ይጠግኑና ይገጣጥሙ እንደነበር ታሪካቸው ይናገራል።
ከቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ መንግስት የቀኝ አዝማችነት ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል። የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ደጋግሞ አመስግኗቸዋል። በ2008 ዓ.ም ደግሞ የበጎ ሰው ሽልማት ልዩ ተሸላሚ ነበሩ። በዕለቱም ስለእርሳቸው የተሰሩ ሥራዎችና ታሪኮች ቀርበዋል። ድምጻዊ ፀሐዬ ዮሐንስ ‹‹ማንበብና መጻፍ፤ ዋናው ቁም ነገር›› በሚለው ዘፈኑ ፡-
ፊደሉን ሳየው መልሰው ያዩኛል
ሌላው ሲያነባቸው እኔን ይጨንቀኛል
የዘመድ ሰላምታ ሲመጣ ደብዳቤ
መርዶ እየመሰለኝ ሲደነግጥ ልቤ ሲል ስለ አዚሟል።
እኝህ ‹‹የፊደል ገበታ አባት›› እየተባሉ የሚጠሩና የእውቀት ብርሃን በአገሪቱ እንዲስፋፋ ሲጥሩ የነበሩ ታላቅ ሰው ግንቦት 26 ቀን 1992 ዓ.ም በ97 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ህያው ሥራቸውን ግን ታሪክና ሕዝብ ሲዘክረው ይኖራል። ስለ ቀኛዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ በብዙ ጋዜጦችና መጽሔቶች ብዙ ተብሏል፤ በሬዲዮ ጣቢያዎች ብዙ ተተርኳል። ከዚህ አለፍ ሲልም በስማቸው መድረኮች እየተዘጋጁ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በመግቢያችን እንዳነሳነው ይህ የመስከረም ወር ነው የእርሳቸው የትምህርት አርበኝነትና የጥበብ አባትነት ታሪክ እንድናነሳ ያረገን። በአሁኑ ወቅት በገጠር አካባቢ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ከመምህራን እና ከአካባቢው የአስተዳደር አካላት ጋር ግብ ግብ ይገጥማል። መምህራንና የትምህርት አስተዳደር ባለሙያዎች የእነ ቀኛዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ የጥበበኝነት እና ትውልድ ቀራጺነት በመማር ልጆች የትምህርት ቤትን ደጅ እንዲረግጡ በማድረግ እንዲማሩ፣ የጥበብ መንገድ እንዲያያዙ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን መስከረም 13/2014