የተዘነጉት የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቅኝቶች

ኢትዮጵያ የራሷ ማንነት አላት ብለን ለመናገር ከምንጠቅሳቸው ነገሮች አንዱ ሙዚቃ ነው። ሀገር በቀል የሙዚቃ መሳሪያዎችና ሀገር በቀል የዜማ አይነቶች አሉን። መጠሪያቸውም ሀገር በቀል ነው። ስለዚህ እነዚህን የራሳችን የሆኑ ነገሮችን ማስተዋወቅ አለብን።

ከጥንቱ የሙዚቃ ታሪካችን ተነስተን አሁን ያለው ዘመናዊ የሙዚቃ መተግበሪያ ላይ ደርሰናል። በዚህ ሁሉ የሙዚቃ ሂደት ውስጥ ግን አንድ ልብ የማንለው ነገር አለ። ይሄውም ረቂቅ የሆነው የቅኝት አይነቶች ነው። ምናልባትም የሙዚቃ ባለሙያ ካልሆነ በስተቀር ተራው ዜጋ ልብ ላይለው ይችላል። አንድን ዘፈን አሰምተን ‹‹ምን የሚባል ቅኝት ነው?›› ተብሎ ቢጠየቅ ምናልባትም ትዝታ ብቻ ይመስለኛል ብዙ መላሽ የሚያገኘው።

ከአራት ይሁን አምስት ዓመት በፊት በቴሌቭዥን ከሰማሁት አንድ ትዝብት ልነሳና ወደ ዋናው ጉዳይ ልሂድ።

በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እሁድ መዝናኛ ፕሮግራም ላይ ጋዜጠኛው ወጣቶችን እያስቆመ ይጠይቃል። ጥያቄውም ‹‹አራቱ የሙዚቃ ቅኝቶች›› የሚባሉትን እንዲነግሩት ነበር። ወጣቶቹ እንኳን የቅኝቶችን ስም ‹‹አራቱ የሙዚቃ ቅኝቶች›› የሚባሉ መኖራቸውንም የሚያውቁ አይመስሉም። ትንሽ ሞከሩ የተባሉት ደግሞ የእስክስታ ስሞችን ነው የተናገሩት።

አራቱን የሙዚቃ ቅኝቶች ‹‹አናውቃቸውም!›› ያሉት ወጣቶች ናቸው። ወጣቶች ማለት ደግሞ ለሙዚቃ ያላቸው ፍቅር ግልጽ ነው። ግልጽ የሚሆነው ግን ለሮክ፣ ብሉስ፣ ቻቻቻ፣ ባቻቻ… ለሚባሉት የውጭ ሙዚቃዎች ነው። በታክሲ ውስጥም ይሁን በሥራ ቦታ አብዛኛው ወጣት በጆሮ ማዳመጫ ጆሮውን ደፍኖ ነው የምናየው። ኤፍ ኤም ሬዲዮ እየሰሙ አይደለም። ‹‹እንዴት አወቅክ›› አይባልም። የአንዳንዶቹ እኮ በጆሮ ማዳመጫ ይሁን እንጂ እንኳን ከአጠገባቸው ላለ ሰው አልፎም እስከሚሰማ ነው የሚጮኸው። እነዚህ ወጣቶች ‹‹አራቱን የሙዚቃ ቅኝቶች ‹‹አናውቃቸውም›› ብለዋል። ጠንቀቀው የሚያውቁ ቢኖሩም እያወራን ያለነው ስለማያውቁት ነው።

በወጣቶቹ አራቱን የሙዚቃ ቅኝቶች ‹‹አናውቃቸውም›› ማለት የተገረመ ካለ ሌላ የባሰ አስገራሚ ነገር ይጨመርለታል። በአንድ የሙዚቃ ውይይት ላይ እንደሰማሁት፤ በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት (ልብ በሉ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ነው) በትልቅ ኃላፊነት ላይ የሚገኙትን አንድ ጋዜጠኛ ስለ አራቱ የሙዚቃ ቅኝቶች ይጠይቃቸዋል። ሰውየው ‹‹የሙዚቃ ቅኝቶች በጣም ብዙ ናቸው›› አሉ። ጋዜጠኛው ከአራቱ የሙዚቃ ቅኝቶች ውጭ ሰምቶ ስለማያውቅ አዲስ ሆኖበት ብዛታቸውን ደጋግሞ ጠየቀ። ሰውየው ለካ አያውቋቸውም። በተደጋጋሚ ‹‹በጣም ብዙ ናቸው›› እያሉ መለሱ። እንግዲህ እርሳቸው የመሰላቸው በአገሪቱ ውስጥ ከሰማንያ ምናምን በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ስላሉ የሙዚቃ ቅኝቶችንም ከሰማንያ በላይ ይሆናሉ ብለው የገመቱ ይመስላል።

እርግጥ ነው ከአራቱ የሙዚቃ ቅኝቶች ውጭ አሉ የሚሉ አዳዲስ ሀሳቦች እየመጡ ነው። ‹‹ፊላና ሌሎች ሙዚቃዊ ጥበባት በጋርዱላ ዲራሼ›› የተሰኘ በ2012 ዓ.ም የታተመ የፍሬው ተስፋዬ መጽሐፍ በደቡብ ኢትዮጵያ ስለሚገኙ ሙዚቃዎች ይነግረናል። በጥናት አዳዲስ ነገሮችን ማግኘት የተለመደ ነው። ዳሩ ግን የነበሩትን እንኳን አለማወቅ ደግሞ ሀገርን አለማወቅ ነው።

እንግዲህ የአንድ አንጋፋ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ኃላፊ እንዲህ ካሉ በሌሎች መፍረድ አይቻልም ማለት ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናቶች ሲሠሩ፣ የመገናኛ ብዙኃን ፕሮግራም ሲሠሩበት እምብዛም አይስተዋልም። ሙዚቃ ቀላል ነገር ሆኖ ነው እንዳይባል በውጭው ዓለምም ሆነ በሀገር ውስጥ ሰዎች ለሙዚቃ ምን እንደሚሆኑ በግልጽ እየታየ ነው። የሙዚቃ ኢንዱስትሪም ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ነው። ይህ የሆነው ግን በውጭው ዓለም እንጂ በኢትዮጵያ ውስጥ አይደለም። ለዓለም ምሳሌ መሆን የሚችሉ ሀገር በቀል የሙዚቃ ቅኝቶች እያላት ከወጣት እስከ አዋቂ የውጭውን አድናቂ ሆኗል።

ለመሆኑ አራቱ የሙዚቃ ቅኝቶች እነማን ናቸው? ከአራቱ ውጭ ሌሎች የሀገራችን የሙዚቃ ቅኝቶች እንዳሉ ከዚህ በፊት በዚሁ ጋዜጣ አስነብበናል። ዛሬ ስለ አራቱ የሙዚቃ ቅኝቶች ነው። በእነዚህ ላይ ጥናትስ ተሰርቶ ያውቅ ይሆን? እስኪ ለዛሬ በምሁራን የተሠሩ ሁለት ጥናቶችን ዋቢ አድርገን ስለ አራቱ የሙዚቃ ቅኝቶች እናውራ።

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የባኅልና ኪነ ጥበብ ዳይሬክተር ጽህፈት ቤት የወሎ ዩኒቨርሲቲ የሙዚቃና ኪሮግራፊ አስተባባሪ አቶ ፋሲል መንግሥቱ ‹‹የአራቱ ቅኝቶች አሰያየም እና ከቦታው ጋር ያላቸው ተዛምዶ›› በሚል ርዕስ ጥናት ሰርተዋል። በጥናታቸውም ስለ አራቱ የሙዚቃ ቅኝቶች ዳሰሳ አድርገዋል።

‹‹ቅኝት ምንድነው?›› ከሚለው እንጀምር። ቅኝት የሚለው ቃል የተገኘው ‹‹ቀነየ›› ከሚለው የግዕዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙም አጀበ ማለት ነው። የሙዚቃ ባለሙያዎች እና ተመራማሪዎች ቅኝትን (በእንግሊዘኛው Scale ይባላል) የሙዚቃ ድምጽ ቃና አወቃቀር በሚለው ይስማማሉ። ከነዚህም ውስጥ ለምሳሌ ያህል የተወሰኑትን የሙዚቃ ባለሙያዎች የሰጡትን ትርጉም እንመልከት፣

የሙዚቃ ደራሲ እና ተመራማሪ ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ከዓለማዊ ሙዚቃ መሳሪያዎች የአቀኛኝት ሥርአት እና ከዘፈኖች ድምጽ አወቃቀር አንጻር የሰጡት ትርጉም።

ቅኝት ድምጾች ባላቸው የድምጽ ቃና ስብስብ (ሬንጅ) እና ርቀት (ከአንደኛው ድምጽ እስከ ሁለተኛው ድምጽ ያለው ርቀት) ይመደባሉ።

በተከታዩ ምሳሌ እንመልከት።

ዲያቶኒክ ———- 8 የድምጽ ቃና ስብስቦች የያዘ

ሄፐታቶኒክ ———- 7 የድምጽ ቃና ስብስቦች የያዘ

ሄክሳቶኒክ ———– 6 የድምጽቃና ስብስቦች የያዘ

ፔንታቶኒክ ———– 5 የድምጽቃና ስብስቦች የያዘ

ትራ ቶኒክ ———— 4 የድምጽቃና ስብስቦች የያዘ

ትሪቶኒክ ———– 3 የድምጽቃና ስብስቦች የያዙ ናቸው።

እዚህ ላይ አንድ ግልጽ መሆን ያለበት ነገር አለ፤ ይሄውም የምት እና የዜማ አይነቶችን በጽሑፍ ማስረዳት ከባድ ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን ሙዚቃ ስንሰማው ቀላል ይመስለናል እንጂ በውስጡ ብዙ ቀመራዊ ስሌቶች አሉት። በብዛት አጥኝዎችም የውጭ ስለሆኑ ቃሉ ራሱ የተለመደ ቃል ላይሆን ይችላል። ለማንኛውም አራቱን የሙዚቃ ቅኝቶች እንያቸው።

ትዝታ

ባባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር አስቴር ሙሉ በ2006 ዓ.ም በሰሩት ጥናት ስለ ትዝታ ቅኝት የሚከተለውን ይሉናል።

‹‹የትዝታ ቅኝት በሌላ ስሙ ወሎ ቅኝት ይባላል። ቅኝቱ ስያሜውን ያገኘው ከሚያነሳው ጉዳይ አንጻር ነው። በትዝታ ቅኝት የትናንትን (ያለፈን) ሕይወት የሚያነሱ ግጥሞች ይቀርቡበታል። ያለፈ ሕይወት ምን ይመስል እንደነበር፣ ትናንት ከዛሬ ጥሩ እንደነበር፣ ትናንት በማለፉ የተሰማን ፀፀት የሚገልጹ ግጥሞች ይቀርቡበታል››

ይህ የትዝታ ቅኝት ሌሎች ዜማዎችን በውስጡ ይይዛል። ለምሳሌ መዲና፣ ዘለሰኛ እና ሙኔ የሚባሉ ዜማዎች የሚገኙት በዚህ ቅኝት ሥር ነው። መዲና እና ዘለሰኛ ለአምላክ ምስጋና የሚቀርብባቸው ዜማዎች ናቸው። ይህ የሆነው ደግሞ ከመሰንቆ አመጣጥ ጋር ተያይዞ ነው። ዛሬ ላይ ሁኔታው ቢቀየርም የመሰንቆ አፈጣጠር አምላክን ለማመስገን ነበር።

በትዝታ ቅኝት ውስጥ የሚገኘው ሌላኛው የዜማ አይነት ሙኔ ነው። ሙኔ በትዝታ ቅኝት ውስጥ ይሁን እንጂ ፈጣንና ለውዝዋዜ የሚጋብዝ ዜማ ነው። በዚህ ዜማ የፍቅር ዘፈን ይቀርባል፣ ገጣሚው ለወደዳት ፍቅሩን ይገልጽበታል። የዜማው ዓይነት ሰቆጣ ተብሎ በሚጠራው የወሎ አካባቢ የሚዘፈኑ ዘፈኖችን ምት የያዘ ነው።

መዲና እና ዘለሰኛ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ግጥሞች የሚቀርቡበት ሲሆን ልዩነቱ በዘለሰኛ ዜማ ውስጥ ‹‹ና ምነው ወዳጄ›› የሚለው አዝማች ይገባል።

ውለታው ብዙ የአግዚአብሔር

አመስጋኝማ ሰው ቢኖር

ወልድ በራስህ ኮርተህ

ከሰማያት ወርደህ

ከድንግል ማርያም ተወልደህ

አብ አይበልጥም ወይ አባትህ

ተለማኝ እናትህ

በዘለሰኛ ዜማ ውስጥ ደግሞ ‹‹እህ ና ምነው ና ምነው›› የሚለው ይገኝበታል።

አምላክ ግብር አርጎ ያበላል ይላሉ

አንድ ቀሪ የለም ሁሉም ይጠራሉ

አምላኬ ግብርህን እንዳታሳንሰው

እምቢ ብሎ አይቀርም አንተ የጠራኸው ሰው

እመቤቴ ማርያም ኧረ ተይ ኧረ ተይ

ኧረ ተይ ኧረ ተይ ልጅሽን ተቆጭው

አንቺ እንደምን አዘንሽ አንድ ቀን ብታጭው

በአቶ ፋሲል ጥናት ውስጥ ደግሞ ሁለት አይነት የትዝታ ቅኝቶች እንዳሉ እናገኛለን። እነዚህንም ዓብይ (ሜጀር) ትዝታ እና ንዑስ (ማይነር) ትዝታ ይሏቸዋል። የኢትዮጵያ ቅኝቶች የራሳቸው ወጥ ባህርይ ያላቸው ቢሆንም፣ በቀላሉ ለመግባባበት ግን ባለ ሰባት ድምጽን እንደ መነሻ በመውሰድ እና በመገንባት በቀላሉ መግባባት ይቻላል። የዚህም ቅኝት የድምጽ ቃና አወቃቀር በ ‹‹C (do) middle C›› እንደ መነሻ በመውሰድ እንመልከት።

ከዓብይ ቅኝት ላይ አራተኛውን ድምጽ እና ሰባተኛውን ድምጽ ሳንጠቀም የምንጫወትበት የቅኝት አይነት ነው።

C ን እንደመነሻ በመውሰድ በ C ዓብይ ዲያቶኒክ ስኬል የምንጠቀምባቸው ድምጾች

C D E F G A B C

1 2 3 4 5 6 7 8

ፔንታቶኔክ ስኬል በመላው ዓለም በተለያየ ቅርጽ በጥንታዊ፣ በባህላዊ በሬንታል ሙዚቃ ውስጥ የሚገኝ ነው። ፔንታቶኔክ ስኬል በአብዛኛው መሰረቱ አንድ ሲሆን ነገርግን የተለያየ ቅርጽ አሉት።

ባቲ

የባቲ ቅኝት ስያሜውን ያገኘው ወሎ ውስጥ ከሚገኙ አካባቢዎች በአንዱ ነው። ይህ ቅኝት ራሱን ባቲንና ሌሎች የወሎ አካባቢዎችን የሚጠቅስ ነው።

እንደ አቶ ፋሲል ጥናት ባቲ ቅኝት ባቲ የሚለውን ስያሜ ያገኝበት ሁለት ምክንያቶች አሉ። በጣም ታዋቂ ከሆነው ባሕላዊ ዘፈን ባቲ የሚል ስያሜ እንዳገኘ እና ይህን ቅኝት በአብዛኛው የሚጠቀሙት ባቲ አካባቢ ወይም ወሎ አካባቢ ያሉ አዝማሪዎች ስለሆነ ነው። ለባቲ ቅኝት እነዚህ ዘፈኖች ምሳሌ ይሆኑናል።

ኸረ ባቲ ባቲ ባቲ ገንደ ሊዩ

ሀድራው የሚሞቀው ደራርበው ሲተኙ

ተይ ድማማ እየ ተይ ድማማ

ተይ ድማማ እየተይ ድማማ

የማትበላ ወፍ ተይዛ በጪራ

ልቤን አደማችው ቦጭራ ቦጫጭራ

አምባሰል

በወሎ ውስጥ ከሚገኙ ግዛቶች የተሰየመ ነው። በአስቴር (ዶ/ር) ጥናት ላይ እንዳገኘነው አምባሰል ‹‹አምባ›› እና ‹‹ሰል›› ከሚሉት ሁለት ቃላት የተመሰረተ ሲሆን አምባ ማለት ተራራ ሰል ማለት ደግሞ ማር ማለት ነው። እንዲህ ከሆነ የማር ተራራ ብለን ልንጠራው እንችላለን። አካባቢው ማር የሚመረትበት መሆኑ ደግሞ አፋችንን ሞልተን እንድንናገር ያደርገናል። አንዲያውም በአምባሰል ወረዳ ውስጥ ‹‹ማርዬ›› የምትባል ቀበሌ አለች። ቀበሌዋ አብዛኛው ገበሬ ማር የሚያመርትባት ናት።

ወደቅኝታችን እንመለስ። የአምባሰል ቅኝት በቦታው የተሰየመ ስለሆነ በዚህ ቅኝት ውስጥ የሚዘፈኑ ዘፈኖች የአምባሳል ተራራንና ታሪካዊ ሁነቶች የሚገልጹ ናቸው። የአምባሰል መልክዓ ምድር ተራራማና ገደል የበዛበት ነው። በታሪካዊነት ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ግማሽ አካል (ግማደ መስቀል) የሚገኝበት የግሸን ደብረ ከርቤ ቤተክርስቲያን የሚገኝበት ነው። ከአምባሰል ቅኝት ዘፈኖች ውስጥ ምሳሌ እንውሰድ።

አምባሰል ለገደል ምን ያሽማጥጡታል

ፈረሰ ባያስጋልብ ሰው ይወጣበታል

ግማደ መስቀሉ ተቀምጦበታል

ንጉሥና ጳጳስ ይወለድበታል።

የአምባሰል ማር ቆራጭ ይወርዳል በገመድ

አደራ ቢሰጡት ይበላል ወይ ዘመድ?

አንቺ ሆየ

ለዚህ የሙዚቃ ቅኝት አንድ አፈታሪክ አለ። አንቺ ሆየ በአንድ ወታደር አማካኝነት እንደተፈጠረ ይነገራል። በአንድ ወቅት በተደረገ ዘመቻ ከሚሴ ውስጥ ርቄ በምትባል ቦታ ወታደር ሰፍሮ ነበር። ከሰፈሩት ወታደሮች አንዱ በአካባቢው ካለች አንድ ሴት ፍቅር ይይዘዋል። በልጅቷ ፍቅር ተይዞ ሳለ ጦሩ እንድነሳ ታዘዘ። ይህን ጊዜ ወታደሩ በጣም ተጨንቆ ፍቅሩን ለመግለጽ ‹‹መገን አንቺ ሆየ›› ብሎ አንጎራጎረ። ከዚያ በኋላ ሰዎች ፍቅራቸውን ለመግለጽ ተጠቀሙት። አንቺ ሆየ የሚለውም ቅኝት ሆነ።

‹‹አንቺ ሆየ ቅኝት ከሌሎች ቅኝቶች ለየት ያለ ፀባይ አለው። በጀመረበት የማይጨርስ፣ በጨረሰበት የማይጀምር አወናባጅ ቅኝት ነው›› ይሉታል አስቴር (ዶ/ር) በጥናታቸው። ሌሎች ቅኝቶች በጀመሩበት የሚጨርሱ፣ በጨረሱበት የሚጀምሩ ናቸው። በአንቺ ሆየ ቅኝት እነዚህ ዘፈኖች ይዘፈናሉ።

አንች ሆየ ለኔ የሚሏት ዘፈን

ታጫውተኛለች ብቻየን ስሆን

አምና በሬ ገዛች ዘንድሮ ወይፈን።

እኔ ጠላ ወዳጅ እሷ ጠላ ወዳጅ

የዚህ ጠላ ነገር እኔስ ጠፋኝ ቅጡ

እናቲቱ ገብተው እየበጠበጡ።

ስለ አራቱ የሙዚቃ ቅኝቶች ምንነት አይተናል። አንድ ነገር ግን እወቁልን። በእያንዳንዱ ቅኝት ውስጥ ብዙ ሒሳባዊ የሆኑ አሠራሮች አሉ። እንኳን ሒሳባዊ አሠራሮችን የቅኝቶችን ስም እንኳን ለማስታወስ በተቸገርንበት ጊዜ ቀመሮችን ማስቀመጥ የኒኩሌር ፊዚክስ ሊሆንብን ነው ማለት ነው። እንዲህ አይነት ሀገራዊ ፍልስፍና እያለን ነው እንግዲህ የሙዚቃ ትምህርት ቤቶቻችን ሳይቀር በውጭው የተቃኙት። የዘርፉ ሰዎች በዚህ ላይ ሊሠሩበት ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን እስከነ ስማቸውም ቢረሱ አይደንቅም !

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You