
ጥበብ ወዶ ፒያሳ፣ ትዝታ ነው በአራዳ። ትናንትና ነበር፤ ዛሬም ሊሆን ነው። ምክንያቱም በጣይቱ ነው። ጣይቱ የባህልና የትምህርት ማዕከል ከባህር ማዶ ተነስቶ አዲስ አበባ ላይ ከትሟል። ዳግም ኢትዮጵያን፣ ዳግም ጥበቧን ለማፍለቅና ከፈለቀው ለማጣጣት መቀነቱን ከወገቡ ሸብ አድርጎ ተነስቷል። የት? ካሉ መሃል አራዳ ላይ። በጥንት በጠዋቷ በአዲስ አበባ ሜልኮን።
ከአራዳ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ጉልላት ፊት ዓይን ላይን እየተያየና ጸሎቱን እያደረሰ 120 ዓመታትን ባስቆጠረው ታሪካዊ ቤት ውስጥ። ፈንጠር ብሎ በግርማ ሞገስ ከቆመው የምኒልክ ሐውልት ጋር እየተያየ ከሚነጋገረው ታሪካዊ ህንጻ ላይ። ስንቱን አስረጅቶ ወደ ሞት ከሸኘው አባሙላት ቤት። ከጥንቱ የቢትወደድ ኃ/ጊዮርጊስ ወልደ ሚካኤል መኖሪያ። ከእነዚህ ሁሉ ዓመታት አምልጦ፣ ዛሬ ቅርስ ሆኗል። ከዛሬ ጀምሮ ደግሞ የጥበብ ውርስ ሆኗል። ከብዙ አምልጦ ለጥበብ ተርፏል።
ከአምስት ዓመታት በፊት፣ በ2011ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይህንን ቤት ለአንዲት እውቅ አርቲስት በስጦታ አበረከተላት። የዕድሜ ዘመን ህይወቷን ዛሬም ድረስ ለሀገሯ በጥበብ ላበረከተችው አርቲስት ዓለም ፀሐይ ወዳጆ፣ በቅርስነት የተያዘውን ግዙፍ ቤት ለመኖሪያ እንድትገለገልበት ተሰጣት። እርሷ ግን ከራሷ ጥበብን፣ ከምቾቷ ሀገሯን አስቀድማ “ይህ ቤት፤ ይህ ግቢ ለመላው ኢትዮጵያውያን የጥበብ ማዕከል ነው” አለች።
ዓለም ፀሐይ ወዳጆ…በእርግጥም ከኢትዮጵያ የኪነት ሰማይ ስር ብቅ ብላ የጥበብን ዓለም በብርሃኗ ስታደምቅና ስታሞቅ የነበረች ውብ ፀሐይ ነበረች። ባላት ኪናዊ ሙያ የጥበብ ባልቴት ያስብላታል። ጸሀፊ ተውኔት፣ ገጣሚና ተዋናይ ናት። በጥቂቱ የሙዚቃ ግጥም ደራሲም ጭምር። ለዘመናት በሀገሯ ዞራ ዞራ ሳትደክምና ኪነ ብርሃኗ ሳይደበዝዝ፣ የሀገሯን ጥበብ ይዛ ባህር ማዶ ስትሻገር ለኢትዮጵያ የጥበብ አፍቃሪያን በሙሉ ትዝታ ነበረች። ለሀገሯ የማለዳዋን ፀሐይ እንደሆነችና እንዳበራች ባህር ማዶ ተሻግራ ሳትመለስ ዓመታትን ከዚያው ቀረች። ከ24 ዓመታት በኋላ የሀገሯን አፈር እንደረገጠች የጠበቃት ስጦታ፣ የአየር ማረፊያው እቅፍ አበባ ብቻ ሳይሆን 120 ዓመታትን ያስቆጠረው ታሪካዊ ቤትም ጭምር ነበር።
የባህር ማዶ ህይወቷ ለእንጀራ ሳይሆን ለሀገሯ ጥበብ መስዋዕት የተደረገ ነበር። የእርሷ እንጀራ ጥበብ ነበረች። የምታሰፋበት ምጣዷም “ጣይቱ የባህልና የትምህርት ማዕከል” ነበር። በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ እንዲሁም በአውስትራሊያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ከነወዳጆቻቸው እየቀረቡ ለ24 ዓመታት የጥበብን እንጀራ በልተው፣ ከወይኑ ተጎንጭተዋል። ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ታሪክ፣ ባህልና ቋንቋ እንዲያውቁ እንዳይረሱት ስትሠራ ነበር። በየጊዜያቱ በየሀገራቱ ጥልቅ የውይይት መድረኮችንና ስልጠናዎችን ታሰናዳለች። በጣይቱ ማዕከል ውስጥ በመደበኛነት በየወሩ ያለማቋረጥ የግጥም ሥራዎች ይሠራሉ። ተውኔቶች ይዘጋጃሉ። 60 ቲያትሮች ተሠርተው ለእይታ በቅተዋል።
የማዕከሉ መስራች የሆነችው አርቲስት ዓለም ፀሐይ ወዳጆም “በስደት የማይታመን የጥበብ ምርት ያውም በጥራት። አሜሪካን ሀገር ለ24 ዓመታት ስሠራ ባህልና ትምህርትን በማስተዋወቅ ቢያንስ በሀያ ሰባት ያህል ስቴቶች እየዞርን ነበር። የኢትዮጵያን የመጀመሪያውን ላይብረሪ ከፍተናል። በካናዳና በአውስትራሊያ ደግሞ መሰል ማህበራትን መሥርተናል” ትላለች።
በተለይ በአሜሪካን ሀገር ውስጥ ስለሀገሯ የሠራቻቸው ሥራዎች አንዳንዶቹ ይሆናሉ ብሎ ለመገመት እንኳን አዳጋች ናቸው። በአሜሪካ ግዛቶች ውስጥ አማርኛ የሥራ ቋንቋ የሆነባቸው ቦታቸው ሁሉ ይገኛሉ። “ዛሬ ቨርጂኒያ፣ ዲሲና ሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አማርኛ ክሬዲት የሚያሰጥ ቋንቋ ነው። በሕክምና በመንጃ ፈቃድ፣ በኢሚግሬሽን ተቋማት ውስጥ አንድ ኢትዮጵያዊ የአማርኛ አስተርጓሚ መጠየቅ መብቱ ነው። ያንን ሁሉ ያደረገ ነው የጣይቱ ማዕከል” ስትል በውጭ ሀገራት ውስጥ በማዕከሉ የተገኙትን የስኬት ፍሬዎች በማንሳት፤ እዚህ በተመሠረተው ተቋም ውስጥ ያላት ራዕይም እኚህንና መሰል ሌሎችንም የኪነት ሥራዎችን በሰፊው ማከናወን እንደሆነ ትገልጻለች።
ከዓመታት በፊት ዓለም ፀሐይ ወዳጆ ቤቱን ከከተማ አስተዳደሩ ተረክባ፣ ወደ ጣይቱ የባህልና ትምህርት ማዕከል መቀየሩን በይፋ ካበሰረችበት ጊዜ አንስቶ፣ ከሦስት ዓመታት በላይ የዘለቀው በሥራ ነበር። ሥራውም ይህን 120 ዓመታትን ያስቆጠረውን ባለ አንድ ፎቅ ህንጻ ማደስና ገጽታውን ወደ ዘመኑ ማምጣት ነበር። ምንም እንኳን ህንጻው ከዚህ ቀደም በፍርድ ቤትነት ሲያገለግል የነበረ ቢሆንም፤ የነበረበት ደረጃ ግን ስጋት የታጀበበት ነበር። ከ120 ዓመታት መካከል አብዛኛውን ያለ አገልግሎት ኦና ሆኖ የከረም ነው። ከዕድሜውም አንጻር እንደ ሰው ሁሉ እርጅናው ተጫጭኖታል። ከውስጥና ከውጭ ከጥቅም ውጭ የሆኑ ብዙ መሠረታዊ ነገሮችም ነበሩበት። እናም በነበረበት ሁኔታ እንኳንስ ይህን ያህል ግዙፍ እንቅስቃሴ ለመከወን፤ ከህንጻው ለመውጣት እንኳን የሚያሰጋ ነበር።
ዓለም ፀሐይ ወዳጆ ቤቱን ስትረከብና ወደ ለማዕከልነት ስታሰብው፣ ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቅና በእርሷ አቅም ይህን ለማድረግ እንደማትችልም ታውቅ ነበር። ነገር ግን፤ ‹ከራስ በላይ ነፋስ› ሳትል የራሷን ገጸ በረከት አሳልፋ በሰጠችበት መልካምነት ውስጥ ሌላ ደጋግ ልቦችን በመተማመን ብቻ ነበር። ያኔውኑ በእቴጌ ሆቴል አደራውን ለሚዲያው፣ አደራውን ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ሰጠች።
ከዚያን ጊዜ አንስቶም በዚህ ታሪካዊ ሥራ ውስጥ አሻራውን ለማኖር ከኪነ ጥበብ እስከ ኪነ ህንጻ ባለሙያዎች ድረስ በአለኝታነት ተረባርበውበታል። ከጡረታ አበላቸው ቆርሰው ለዚህ ያበረከቱ ደጋጎች ጥቂቶች አይደሉም። ያላቸውም ካላቸው ላይ እስከ ሚሊየን ብሮች ችሮታ አደረጉ። ከሥራው በፊት የተቋቋመው ቦርድም፣ በባለቤትነት እየተጋ ወደፊት ቀጠለ። በዚህ ቤት ላይ ያረፈው ኢትዮጵያዊ የኪነ ህንጻ ጥበብ ግን ቀላል አልነበረም። ህብለሠረሠሩ በየትኛውም ዓይነት የገንዘብ ኃይል ብቻ የሚደርስበትም አይደለም። በእርግጥ የዚህን ቤት ቀመር አግኝቶ እንደነበረው አድርጎ በአስተማማኝ ሠገነት ከመሥራት፣ ሌላ ዓይነት ዘመኑን የዋጀ ህንጻ ማቆሙ የሚቀል ነበር። ደፍሮ ይህን ለማድረግ የሚመጣ ብቻ ሳይሆን፣ ሠርቶ እውን ለማድረግ የሚችል የኪነ ህንጻ ባለሙያ ይገኝለት እንደሆነም እርግጠኛ ለመሆን የሚያዳግት ነበር። ግን…ኢትዮጵያ በልጆቿ፣ በየትኛውም ጥበብ ውስጥ መካን ሆና አታውቅም።
“ልክ የቦታውን መሰጠት ዜና እንደሰማሁ ወዲያው ያወራሁት አርክቴክት ፋሲልን ነበር። አገኘሁትናም እንዲህ ዓይነት ቦታ ተሰጥቶኝ ነበር እንዴት ልትረዳኝ ትችላለህ? አልኩት። ‹ኸረ አይመስለኝም። እሱን ቦታ ሊሰጡሽ አይችሉም። ብዙ እክል ያለበት ቦታ ነው› አለኝ። እውነት መሆኑን ሲያረጋግጥ ግን ከጎንሽ ነኝ በማለት በነጻ እንደሚሠራልኝ ነገረኝ” ስትል በጊዜው የገጠማትን የመጀመሪያውን በጎነት አስታውሳው ነበር። ከዚያ በኋላ ነበር በስሩ የነበሩ ባለሙያዎችን በማስከተል ታሪካዊውን ሥራ ለመሥራት መጀመሩ። ሀገር በታሪክና በጥበብ እንደ ጸደይ ወራት አበባ የምትፈካው እንዲህ ያሉ ኢትዮጵያዊ ደግነቶች ሲያብቡ ነው። ሁላችንም ባለን ነገር ያለችንን ይዘን ብንቀርብ እንኳንስ ይህቺንና የማንሠራው ምንም ነገር እንደሌለ ያለፈው ታሪካችን ገልጦ የሚናገረው ነው።
“ብዙ ውጣውረድ ነበረው፤ ያንን መናገር ግን አልፈልግም። ሁሉንም አልፈን እዚህ ደርሰናል” ትላለች ዓለም ፀሐይ ከበድ ያሉ ፈተናዎች እንደነበሩም ጭምር በማስታወስ። በእነዚያ አራት ዓመታት ውስጥ አንድ ጊዜ ባህር ማዶ፣ ሌላ ጊዜም ወደ ሀገር ውስጥ እየተመላለሰች፣ ለሥራው ስንቅ ሁሉንም አስተባብራ ዛሬ ሁሉም እውን ሆኗል። ለጣይቱ የባህልና የትምህርት ማዕከል በተቋቋመው ቦርድ ስር ሰብሳቢውን ጌታቸው ቅጣውን ጨምሮ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፣ ዳንኤል በቀለ፣ አርቲስት አዜብ ወርቁ እና ደራሲ ይታገሱ ጌትነት በተባበረ ክንድ ያሳረፉት አሻራም ቀላል አይደለም።
ከዚህ ሁሉ በኋላ ትልቁ ጥያቄ እዚህ ጋር ይነሳል። ከመሃል አራዳ ላይ የቆመው የጣይቱ ማዕከል፣ ከእንግዲህ ምንስ ስለመሥራት ያስባል? “በየወሩ በየዓመቱ ንድፍ ተነድፏል። ግጥምና ቲያትር ይካሄዳል። መሥራት ብቻ ሳይሆን በትወናና በድርሰት ባለሙያዎችን ማፍራትንም ይጨምራል። በእያንዳንዱ ክፍሎች ውስጥም ትምህርት ቤቶችን አስበናል። የትወና፣ የዝግጅት፣ የሲኒማቶግራፊ፣ የስነ ጽሁፍ፣ የብራና አጻጻፍ፣ የሸክላና የሽመና ሥራዎችንም ያካተተ ነው” ስትል አርቲስት ዓለም ፀሐይ ወዳጆ ገልጻለች። ከዚሁ ጋር በተያያዘ፤ በእኚህ ሁሉ ዘርፎች ወደ ትምህርት ቤቱ የሚመጡ ተማሪዎች በሁለት መንገድ የሚስተናገዱ ናቸው። አቅም ያላቸው ከፍለው እንዲማሩ፣ የሌላቸውም ደግሞ ትምህርቱን ከቀሰሙ በኋላ የሚጠበቅባቸው ሀላፊነቶች ይኖራሉ።
የማዕከሉ አገልግሎት ይህ ብቻም አይደለም፤ “በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አብዛኛዎቹ ደራሲያን፣ ሰዓሊያንና ሌሎችም ምንም የኔ የሚሉት ቦታ የላቸውም።” ስለዚህ? “ይሄ ግቢ የኔ ብለው የሚጠሩት፣ ገብተው በተመስጦ ለመጻፍ ቢፈልጉ፣ ቲያትራቸውን ስክሪፕታቸውን አስተካክለው ማጥናት ቢፈልጉ፣ ሰዓሊያን የራሳቸውን ሥራ የሚነድፉበት ቦታ ቢፈልጉ፣ ይህ ማዕከል ቤታቸው እንዲሆን ነው የምንፈልገው” ትላለች። ከቤቱ ጋር በተያያዘ ገና ብዙ ሀሳቦች እንዳሏትም ገልጻለች። ህንጻው ምንም እንኳን ግዙፍ ቢሆንም፤ ከታሰቡት ነገሮች አንጻር ግን በቂ ላይሆን እንደሚችል ሁሉ ግምቷን ታስቀምጣለች።
ዕሮብ ሚያዝያ 15 ቀን 2017ዓ.ም፣ የማዕከሉ መሥራች የሆነችው ዓለም ፀሐይ ወዳጆና የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው ቅጣው፣ ለሚዲያ አካላት ጥሪ በማድረግ መግለጫ ሰጥተውበት ነበር። በዚሁ ዕለት ዓለም ፀሐይ ወዳጆ ባደረገችው ንግግር ከዓመታት በፊት ስለነበራት ህልም ስታወሳ “…አንደኛ የእቴጌ ጣይቱን ሐውልት ማቆም። ሁለተኛው ደግሞ የባህልና የትምህርት ማዕከል መመሥረት ነበር ህልሜ። ለግሌ የተሰጠኝን ቤት ለማዕከሉ ያዋልኩበት ምክንያትም ለዚሁ ነው። …ላለፉት አራት ዓመታትም ክብሩን ታሪክነቱን፣ ቅርስነቱን በጠበቀ መልኩ ሠርተን ለሕዝብ አበርክተናል” አለች። አዎን…ለራሷና ለግል ጥቅሟ ሳይሆን ለአንዲት ሀገሯ፣ ለአንዲት ጥበብ፣ ለሀገሯ ልጆች ሁሉ ይህን ትልቅ ገጸ በረከት ከእቅፍ አበባ ጋር አበርክታላች።
በቤቱ ውስጥ አሻራቸውን ያኖሩ እጅግ በርካቶች ናቸው። በሀገረ አሜሪካ ከሚኖሩት ሎሬት ደስታ ሀጎስን ጨምሮ 22 ዕውቅ ሰዓሊያን ለዚሁ በማሰብ ያዘጋጇቸውን የስዕል ሥራዎቻቸውን በመላክ፣ የቤቱን ዙሪያ ላይና ታቹን አስጊጠውታል። በሌላ በኩል ደግሞ ህንጻው የቆመበትን የተንጣለለውን ግቢ በራሱ ወጪ ያሳመረው ራሱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ነው። “ሥራው ከተሠራ በኋላ ዓለም ፀሐይ ከንቲባዋን ጋብዛ ነበርና በተሠራው ሥራ ተገርመው ደስ በመሰኘታቸው አንቺ ይህን ያህል ከሠራሽ እኛ ደግሞ ግቢውን እንሠራዋለን” ሲሉ አቶ ጌታቸው ቅጣው በመግለጫው አንስተውት ነበር። “ገና የቲያትር አዳራሽ እንሠራለን። ‹ጥበብና ጥበበኛ› የሚል ሙዚየም እናስባለን። ያልተሠሩ ገና መዓት ሥራዎች አሉ” ስትል የአሁኑ ጅምር እንጂ መጨረሻ እንዳልሆነ ዓለም ፀሐይ ተናግራለች። እስካሁን በተሠራው ሥራ 17 ሚሊየን ብር ገደማ ወጪ የተደረገበት ሲሆን፣ ያላለቀ እዳ ግን ገና ብዙ እንደሆነም ጭምር አንስታለች።
የማዕከሉ ድንበርም በመሃል አራዳ በአዲስ አበባ ብቻ ከትሞ አይቆምም። ከወደ አርባምንጭ አንድ ብላ ነካክታዋለች። እናም በየክፍለሀገራቱ በተመሳሳይ መልኩ የማስፋፋት ትልቅ ዕቅድ አላት። “ያኔ እኔ በማውቃት ኢትዮጵያ የማህበረሰቦቿን አንድነትና ኢትዮጵያዊነት ስንተርክ ነበር የቆየነው። ያቺ ኢትዮጵያም ባደገችና በበለጸገች መልኩ እንድትመጣ ነው የምንሠራው። ባለፉት ዓመታት ያልተሰረጸ የተሳሳተ ትርክት ወጣቱንም የምንመልስበት ቤት ነው” የሚለው የዓለም ፀሐይ ንግግር፣ በጣይቱ ማዕከል ከፍ ብሎ የሚወልበለበው አርማዊ ግዙፍ ዓላማ ኢትዮጵያዊነት እንደሆነ ደጋግማ አስረግጣዋለች።
ከሦስት ቀናት በኋላ፤ ቅዳሜ ሚያዝያ 18 ቀን ጥበብ ከመሃሏ አራዳ ሠገነት ላይ ቁጭ ብላ ፈገግ ስትል ታየች። ከሌት ንጋት ተስፈንጥራ ማልዳ ብቅ ያለች ፀሐይ ከአራዳ ጊዮርጊስ አናት ታብረቀርቃለች። ‹እንደምን አደርሽ አራዳ? ኸረ እንዴት ነሽ ጥበብ?› ያለ የተመለከታት ሁሉ ገና በማለዳው ለአንዳች ሙሽርነት ሽር ብትን ስትል ስትኳኳል ስለመሆኗ የሚያጤነው ነበር። ከጥበብ ምኩራብ ውስጥ ጉንጉን አበባ ታቅፎ በግርማ ሞገስ የቆመው ታሪካዊ ህንጻ ዓይኖቹን ከሩቅ ወርውሮ እንግዶቹን በመጠበቅ ላይ ይመስላል። ጀርባውን ለአራት ኪሎ፣ ፊቱን ለመርካቶ፣ ጎኑን ለፒያሳና ውቤ በረሃ ሰጥቶ ሁሉንም ይጣራል።
ከቆሙበት ከሐውልታቸው ላይ ፊታቸውን መለስ አድርገው፣ ከዚያች ታሪካዊ ግቢ ውስጥ የሚሆነውን ለመመልከት አፄ ምኒልክም ሳይነሽጣቸው አልቀረም። ቄንጠኛው ፈረሳቸው አባ ዳኘው እንኳን የፊት እግሮቹን አየር ላይ እንዳንሳፈፋቸው ሲመለከቱት እየተወነጨፈ የሚያጅብ ነው የሚመስለው። ጌታው እምዬ ምኒልክ እንዲያ ቢሆኑ፣ የሆኑበት ትልቅ እውነት አላቸው። ነብሳቸውን ደስ የምታሰኝ ግብር ከሚያውቋት ስፍራ ላይ እንደ እጣን ሲጤስ ያለው፤ በሚወዷት ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ ብጡል ስም ከተሰየመበት ነውና። የቤቱ የምረቃ ሥነ ሥርዓት በእቴጌይቱ የልደት ቀን በነሐሴ 12 ታስቦ የነበረ ቢሆንም፤ ከንቲባዋ ቃል የገቡትን ጨምሮ ሌሎች የማስዋብ ሥራዎች እንደገና ተጀመሩ። ቀኑም ሌላ ብሩህ ቀን ወለደ።
በ120 ዓመታት ታሪካዊ ቅርስ፣ በአራት ዓመታት ውጣውረድ፣ ለዘለዓለማዊ ጥበብ መቀነት ሸብ አ`ርጎ ሁሉንም በምርቃቱ ተከወነ። መጋረጃውን በገለጠው የማርሽ ባንድ ኦርኬስትራዊ ህብረ ዝማሬ ጅምሩ ተበሰረና ማዕከሉም ጉዞውን ጀምሯል። በዕለቱ ለዚህ ታሪካዊ የባህልና የጥበብ ብሥራት ማንም ሳይቀር፣ የወደፊቱን የቤት ሥራ ተቀብሏል። ከነበረው ልዩ ልዩ የባህል ሙዚቃና ውዝዋዜ ጋር የጥንቷ አራዳ ትዝታ ተቀስቅሶባት እንደሆን ራሷ ትናገረው። ዳግም ገና ከጥበብ ጋር ልትውረገረግ ነውና የእኛም ምኞት ይሁንኑ መመልከት ነው። ጥበብ ከጣይቱ፣ ትዝታ ከአራዳ ይፍለቅለቅ።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 30 ቀን 2017 ዓ.ም