የአለማቀፍ ጉዳዮች ሊቅ ፣ ጋዜጠኛ ፣ ደራሲ፣ አንሰላሳይ ተናጋሪ የCNN ቴሌቪዥን GLOBAL PUBLIC SQUARE/GPS/ አዘጋጅና የዋሽንግተን ፖስት አምደኛ ፋሪድ ዘካሪያ፤ አምና በዚህ ሰሞን ዋሽንግተን ፖስት ላይ ባስነበበን መጣጥፉ 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲው የሚመራው በስሜት በአፈተት በጥድፊያ በግዴለሽነትና በእንዝህላልነት እንጂ መሬት በረገጠ አበክሮ ተጠንቶ በተቀመረ ፖሊሲ አይደለም ሲል አምርሮ ተችቶ ነበር። ” America’s excessive reliance on sanctions will come back to haunt it “ በሚል ርዕስ ባስነበበን ማለፊያ አስተያየቱ፤ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በአንድ አመት ብቻ የቀደሙት ሁለት ፕሬዚዳንቶች ከጣሏቸው ማዕቀቦች በሁለት እጥፍ የሚበልጥ ማዕቀብ ጥሏል። በ2018 እኤአ ብቻ 700 ማዕቀቦችን ኢራን ላይ ጥሏል። ትላንት እሁድ ደግሞ በዚሁ ጋዜጣ”Is Biden normalizing Trump’s foreign policy?” በሚል ርዕስ ባስነበበን መጣጥፍ የፕሬዚዳንት ጆ ባይደንን አስተዳደር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የትራምፕ ቅጥያ በመሆኑ ክፉኛ አብጠልጥሎታል። መረጃና ማስረጃ ቆጥሮ ተችቶታል።
የባይደን አስተዳደር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለስምንት ወራት በቅርብ በአንክሮ የገመገሙና ያጠኑ ጉምቱ ልሒቃን ያልጠበቁት ነገር ገጥሟቸዋል ይላል ፋሪድ። የባይደን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የዶናልድ ትራምፕን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እግር በእግር የሚያጸና በአንጻሩ የባራክ ኦባማን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አሻራ የሚጠርግና የሚክድ ሆኖ ስላገኙት ተደንቀዋል። ወግ አጥባቂው ካቶሊክና እንደ መነኩሴ መቁጠሪያ ከኪሳቸው የማይለዩት የወቅቱ ፕሬዚዳንት ባይደን ቃላቸውን አጥፈው ሲገኙ ለምን አያስገርም ያስገርማል እንጂ። እኤአ 2016 ዓም ላይ ዴሞክራቶችን ወክለው ለፓርቲያቸው እጩነት ሒላሪን ሊፎካከሩ ሲዘጋጁ የመወዳደሪያ አጀንዳቸው የኦባማን አሻራ ማስቀጠል ነበር። የልጃቸው ቦው በካንሰር መሞት ከፉክክሩ በጊዜ ቢያስወጣቸውም። ከአራት አመት በኋላ አወዛጋቢውን ትራምፕ አሸንፈው 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ኋይታወስ ሲገቡ የባራክ ኦባማን ፖሊሲ ዳር ያደርሳሉ ተብሎ ሲጠበቅ የትራምፕ አስቀጣይ ሆነው ሲያርፉት ለምን አያስገርሙ ያስገርማሉ እንጂ።
ትራምፕ በፕሬዚደንታዊ ውሳኔ የሻሯቸውን የባራካ ኦባማ ስኬት ተደርገው የሚታዩ የኢራንና የኪውባን ስምምነቶች ባይደን ይቀለብሷቸዋል ተብሎ ሲጠበቅ ማራዘማቸውና የማዕቀቡን መሠረት ማስፋታቸው በአለማቀፍ ግንኙነትና በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሊቃውንት ዘንድ መነጋገሪያ መሆኑን ፋሪድ ያትታል። የሚገርመው ትራምፕ አሜሪካንን ከኢራኑ የኒውክሌር ስምምነት ሲያስወጧት ቀድመው ጠንከር ባለ ቋንቋ ያወገዙት ባይደን ነበሩ። ወደ ስልጣን ሲመጡ ግን ኢራን ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ መጣላቸው ሳያንስ ወደ ድርድር ለመመለስ እግራቸውን ሲጎትቱ ተስተውሏል። ለዚህ ነው ብዙዎች የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተገማችና ዕምነት የሚጣልበት ካለመሆኑ ባሻገር ቅጥ አንባሩ ጠፍቶታል ሲሉ የሚደመጡት።ከ20 ዓመት በፊት በአሜሪካው የወቅቱ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ ፊትአውራሪነትና በእንግሊዙ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌየር አዝማችነት፤ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳንን/ኔቶ/፤ ሌሎች አጋርና ወዳጅ ሀገራትን እና የአሜሪካን ጦር ይዘው አፍጋኒስታን ዘምተው ለ20 አመታት በአንድ የዕዝ ጠገግና ምሽግ ከታሊባን ከአልቃይዳና ከአይሲስ ጋር ሲፋለሙ እንዳልኖሩ፣ በዚያ ሰሞን አሜሪካ ለአጋሮቿ ሳታሳውቅ ድንገት ከአፍጋኒስታን ነቅላ መውጣቷ አጋሮቿን ከማስደንገጡ ባሻገር ወዳጅነታቸውን መልሰው እንዲያጤኑ አስገድዷቸዋል።
ሰሞኑን ዩናይትድ ኪንግደም አውስትራሊያና አሜሪካ የተፈራረሙት የሶስትዮሽ የባህር ሰርጓጅ የኒዩክሌር ትጥቅ ለብዙዎቹ ምዕራባውያን ሚስጥር የነበር ከመሆኑ በላይ ፈረንሳይ በ65 ቢሊዮን ዶላር ለአውስትራሊያ ተመሳሳይ ኒውክሌር የታጠቀ ባህር ሰርጓጅ ለማቅረብ አስራው የነበረ ውል ላይ ቀዝቃዛ ውሃ በመቸለሱ ተቆጥታ የየሀገራቱ አምባሳደሮችን እስከመጥራት ከመድረሷ ባሻገር በአሜሪካና በእንግሊዝ ከጀርባ ተወግቻለሁ በማለት ከንፈሯን እየነከሰች ነው። በዚህ የፈረንሳይ እርምጃ የተደናገጡት ባይደን የልባቸውን ከሰሩና ከጀርባ ከወጉ በኋላ ለኢማኑየል ማክሮን የእንነጋገር ጥሪ እያቀረቡ ነው።
ብዙዎች የባይደን አስተዳደር የቆረጣ የሶስትዮሽ ስምምነት በአፍጋኒስታን የፈጸመውን ታላቅ ክህደትና ስህተት ለማጣፋትና ትኩረት ለማስቀየር የተደረገ አድርገው ወስደውታል። በአውሮፓ ሕብረትና በአንግሎ ሳክሰን መካከል ያለውን የኢኮኖሚና የደህንነት ስምምነት እንዳይጎዳውም ተሰግቷል። ፈረሳይ ሰሞኑን በደህንነት ዙሪያ ልታደርገው የነበረውን ውይይት ሰርዛለች። እንደ ፈረንሳይ ሁሉ ካናዳ አውሮፓ በተለይ ጀርመን በባይደን አስተዳደር እየቀጠለ ያለው የትራምፕ ፖሊሲ ነው በሚል ግንኙነታቸው ንፋስ እየገባው ነው። ከ70 አመት በላይ የቆየው ትብብራቸው ቁዘማ ላይ ወድቋል።
በውድቀት ቁልቁለት እየተንደረደረ ያለው የውጭ ፖሊሲዋ አይነተኛ መገለጫ ወደ ሆነው ፍርደ ገምድል የአሜሪካ ማዕቀብ ስንመጣ፤ ኪውባውያን ከ60 ኢራናውያን ከ40 ኤርትራውያን ከ20 አመታት በላይ ቬኒዞላ ሶሪያ የመን ራሽያ ቻይና በርማና ሌሎች ወደ 30 የሚጠጉ ሀገራት ሕዝቦች በተለያዩ የአሜሪካ ማዕቀቦች እየማቀቁ ነው። የቀድሞዋ የቺሊ ፕሬዝዳንት የአሁኗ የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ሚሼል ባችሌት እንደ ኢራንና ቬኒዞላ ባሉ ሀገራት የተጣሉ ማዕቀቦች የየሀገራቱን ዜጎች ጤና አደጋ ላይ ከመጣላቸው ባሻገር የሚሊዮኖችን የዕለት ተዕለት ህይወት ጎስቋላ አድርገውታል። ኮሚሽነሯ ለዚህ ነው በአገዛዞች ላይ የሚጣል ማዕቀብ ዳፋ ለዜጎች እየተረፈ ነው በሚል የማዕቀብን ውጤታማነት የሚሞግቱት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሰሞኑን ለጆ ባይደን በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ፤የተለያዩ የአሜሪካ መንግሥታት ያልተጠኑ ቅፅበታዊ ውሳኔዎችን በማሳለፍ በሌሎች አገሮች የውስጥ ጉዳይ ላይ ያደረጉት ጣልቃ ገብነት መፍትሔ ከማምጣት ይልቅ፣ ሕዝቦችን ለባሰ ቀውስ ሲዳርግ እንደነበር በመጥቀስ የኮምሽነሯን ሀሳብ ይጋራሉ። ኢትዮጵያ ግን እንዲህ ባለው ፍርደ ገምድልነት እንደማትንበረከክም አስገንዝበዋል። ፕሬዚዳንት ባይደን ወደስልጣን ከመጡ በኋላ ከ100 ሊበልጡ የሚችሉ ፕሬዚዳንታዊ ውሳኔዎችን EXECUTIVE BORDER አሳልፈዋል። ባለፈው አርብ ፕሬዚዳንቱ በታሪክና በትውልድ ሲያስወቅሳቸው የሚኖርን ሌላ ታላቅ ስህተት ፈጽመዋል።
የአሜሪካ ሕዝብ ወዳጅና አጋር ከሆነችው እና በአሸባሪው ሕወሓት እየተጠቃች የምትገኘውን ኢትዮጵያ ጎን ከመቆም ይልቅ፤ ራሷ አሜሪካ ሳትቀር አሸባሪ ብላ ከፈረጀችው፤ በኢትዮጵያ ህልውናዋ ከፍ ሲልም በቀጣናው ላይ አደጋ ከደቀነው፤ ሕዝብን በማንነቱ ከሚጨፈጭፈው፤ የጦር ወንጀለኛ ከሆነው፤ በሰብዓዊ ፍጡር ላይ በተፈጸመ ወንጀል ከሚከሰሰው፤ የጎሳ ማጽዳት ወንጀል ከፈጸመው፤ ከ20 አመታት በላይ ሲሞትለት ሲያርስለት ከቀለቡ ቀንሶ ሲያጎርሰው በኖረ በገዛ ሰራዊት ላይ ትውልድም ሀገርም የማይረሱት ክህደትና ጭፍጨፋ ከፈጸመው፤ለ27 አመታት ኢትዮጵያውያንን ሲገድል ሲያሰቃይ ሲያጉር ሲያሳድድ ሲያግዝ ከኖረ፤ ኢትዮጵያ ላይ እንደመዥገር ተጣብቆ ደሟን ሲመጥ ከኖረ፤ ኢትዮጵያውያን ያለ ልዩነት አንቅረው ከተፉት አሸባሪ ጋር መሳ ለመሳ ማዕቀብ እንዲጣል ወስነዋል።
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ማዕቀብ እንዲጣል ባዘዙ በሰዓታት ልዩነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለፕሬዚዳንቱ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ፤ “የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በግለሰብ ፖሊሲ አውጭዎች ተፅዕኖ ሥር ወድቆ መቀጠሉንና እንደ ሕወሓት ባሉ’አሸባሪ’ ቡድኖች ጭምር ተፅዕኖ የሚያርፍበት መሆኑን” በማንሳት፤ እነ ፋሪድ ዘካሪያ”በዋሽንግተን በከተሙ ልዩ የፖለቲካ የኢኮኖሚ ፍላጎትና ጥቅም አሳዳጆች ውትወታና ጫና በሀገራት ላይ በሚጣሉ ማዕቀቦች ሕዝብ እየማቀቀ ነው።”በሚል የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሀሳብ አጽንቶታል።
እንደ መውጫ ፕሬዚዳንት ባይደን በኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ባዘዙ በሰዓታት ልዩነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለፕሬዚዳንቱ የጻፉት ታሪካዊ ደብዳቤ አፄ ቴዎድሮስ ለእንግሊዟ ንግስት ከጻፉት ደብዳቤ ጋር እየተነጻጸረ ይገኛል። እኔም ከዚህ ደብዳቤ ባገኘኋቸው ጥቅሶች ልውጣ።
“ኢትዮጵያ ለውጭ ተፅዕኖ አትንበረከክም ! ከብዙኃን ደኅንነት ይልቅ ሥልጣንን ያስቀደሙ ግለሰቦች ባቀናበሩት ሴራ ለመጣው የውጭ ግፊት ኢትዮጵያ አትንበረከክም !ኢትዮጵያዊ ማንነታችንና አፍሪካዊ ማንነታችን ይህ እንዲሆን አይፈቅድም ! ቀደምት የአፍሪካ መንግሥታት ላይ የደረሰው በደልና ግፍ በአሁኑ ወቅት በዚህች ምድር ላይ አይደገምም ! የአረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀለም ምድር የሆነች ነፃ አገር ሌሎች በርካቶች በትግላቸው ነፃነታቸውን እንዲቀዳጁ ተምሳሌት የሆነች አገር ናት !የአሜሪካ መንግሥት ከቀደመው በግለሰብ ተፅዕኖ ሥር ከወደቀ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲው ይላቀቃል የሚል ተስፋ ነበረን። ነገር ግን በተቃራኒው የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በግለሰብ ፖሊሲ አውጭዎች ተፅዕኖ ሥር ወድቆ መቀጠሉንና እንደ ሕወሓት ባሉ’አሸባሪ’ ቡድኖች ጭምር ተፅዕኖ የሚያርፍበት ሆኗል።”
አዲሱ አመት የሰላም ፣ የጤና፣ ብልፅግና እና የአንድነት ይሁን !!!
አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን መስከረም 13/2014