በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር የነበሩት ህንድና ፓኪስታን እኤአ በ1947 ትግላቸው ፍሬ አፍርቶ ነፃነታቸውን ማጣጣም ከጀመሩ አንስቶ ላለፉት ሰባት አስርት ዓመታት አንዱ አንዱን ሲተነኩስ ዘልቀዋል። ሁለቱ የደቡብ እስያ አገራት በተለይም የኔ ናት በሚሏት ካሽሚር ከመነታረክ ባለፈ ለሶስት ጊዜያት ያህልም ጦር ተማዘዋል። ጡንቻ ተለካክተዋል።
ምንም እንኳን እኤአ 1998 የኒውከሌር ጦር ባለቤት ስለመሆናቸው በይፋ ካሳወቁ በኋላ አንፃራዊ ሰላም ማውረድን ቢችሉም፣ እኤአ በ2003 በተፈፀመ የተኩስ ማቆም ስምምነትም ጃሙና ካሽሚር በተባለ ስፍራ ላይ እንዲወሰኑ የተደረገውን ወታደራዊ የድንበር መስመር ቢቀበሉም፣ በሂማሊያ ቀጠና በካሽሚር የይገባኛል እሰጥ አገባቸውን ግን ለአፍታም ዘንግተውት አያውቁም። አንዳቸውን አንዳቸው በአይነ ቁራኛ ከመጠበቅም አይቦዝኑም።
እንዲያም ሆኖ ግን በካሽሚር ቀጠና ያልተጠበቀ አደጋ መድረሱ አይቀርም። ከቀናት በፊትም በአካባቢው ፑልዋማ በተባለ ቦታ ከባድ የሽብር ጥቃት ተፈፅሟል። ይህም ወትሮም ትንሽ የሚበቃውን የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደ ከረረ ፍጥጫ አስገብቶታል።
ከአርባ በላይ የሚሆኑ የህንድ ወታደሮችን ህይወት የቀጠፈውና እኤአ በ1989 ከተከሰተውም የከበደ መሆኑ ለታመነበት የሽብር ጥቃት መቀመጫውን በፓኪስታን ያደረገውና ጃይሽ ኢ ማህመድ የተባለው ቡድንም ሃላፊነቱን መውሰዱም ኒው ዴህሊን ይበልጥ አብግኖ ቁጡ አድርጓታል።
ኒው ዴህሊ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል፤ ፓኪስታን ዓለም ዓቀፉን አቅጣጫ ከማሳት ይልቅ ጃይሽ መሃመድ የተባለው የሽብር ቡድን መሪው ማሱድ አዝሃር በአገሪቱ መከተሙ የአደባባይ ሃቅ መሆኑን አስታውቃለች፤ ኢስላማባድ አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ እንዳለባት አሳስባለች።
የህንድ በካሽሚር ግዛት መታየትን ፈፅሞ የሚቃመውን ይህን ቡድን ፓኪስታን አይዞህ እንደምትለው ብታስብም፤ ኢስላማባድ በሌላ በኩል ቡድኑን ከ 2002 ጀምሮ አይንህን ለአፈር ማለቷን በማስረገጥ ከኒው ዴህሊ የሚቀርብባትን ወቀሳ አጣጥላለች።
ፓኪስታን በሌላ ጎን ህንድ ለምታቀርበው ወቀሳ ማስረጃ ብቻ ትስጠኝ በሚል አቋሟ ፀንታለች። የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ከሃንም ህንድ ካለ ምንም ማስረጃ አግባብ ያልሆነ ወቀሳ እያቀረበች ነው ሲሉ ተደምጠዋል።አስፈላጊውን መረጃ ማቅረብ ከቻለም ውጫዊ ጫናን በመፍራት ሳይሆን አሸባሪዎቹ የፓኪስታን ህዝብን ስላም ነሺዎች በመሆናቸው ብቻ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነችም ብለዋል።
«ጦርነት መጀመር ቀላል ቢሆንም ማቆም ግን ከባድ ነው»ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ከሃን፤ ይህ ስለሆነም ፍጥጫውን ለማርገብ አማራጭ መሆኑን አስምረውብታል። ይህ የፓኪስታን መሪ ምላሽ ታዲያ በበርካታ ወገኖች ዘንድ ተጨብጭቦለታል። እጁን ለትብብር ይዘረጋ፣ ለመነጋጋር በሩን የከፈተ ተብሏል።
ፓኪስታን በዚህም ሳታበቃ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት አቤት ብላለች።ተቋሙ በጉዳዩ ላይ ጣልቃ እንዲገባም ጠይቃለች።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ሃላፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝም አገራቱ እሰጣ ገባቸው ጋብ በማድረግ በአፋጣኝ ወደ ሰላም እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህ ግን ዜጎቿን በተነጠቀችው ህንድ ዘንድ ተቀባይነትን አላገኘም። እናም አሸባሪዎቹን የመደምሰስ አፀፋ ለመስጠትም ወታደራዊ ተልዕኮ እስከመፈፀም ተሻግራለች። የህንድ መንግስት በዚህ ሳያበቃ ከፓኪስታን ጋር ያለውን የንግድና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት የሚያቀዘቅዝ ውሳኔ አሳልፏል። በህንድ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ የፓኪስታን ዜጎችን በአስችኳይ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አሳስቧል። ከዚሁ ሁሉ ደግሞ የሁለቱ አገራት አምባሳደሮቻቸውን መጥራት ግንኙነታቸውን ከድጡ ወደ ማጡ የሚወስዱ ምልክቶች እንዲታዩ አስገድዷል።
መጪው ያስፈራቸውና በደቡባዊው ኤሲያ ሰላማዊ አየር እንዲነፍስ ፍላጎት ያላቸው አገራትም የየበኩላቸውን አቋምና ተግባር እንዲያሳዩ ምክንያት ሆኗቸዋል።የህንድ አጋር እንደሆነች የምትታመነው አሜሪካ አሁንም አጋርነቷን አረጋግጣለች፡፡ የፓኪስታን ወዳጅ የሆነችው ቻይና በአንፃሩ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይዋ በኩል አገራቱ ጉዳዩን በሰከነ መንገድ እንዲመለከቱት ጠይቃለች። የሁለቱ አገራት ፍጥጫ መቋጫውን እንዲያገኝ ለማድረግ በመጣር ረገድ ግን በተለይ የሳውዲ አረቢያን ያህል የተራመደ አልታየም።
በእርግጥ ከህንድ ይልቅ ፓኪስታን ልባዊ የሳውዲ ወዳጅ ናት።ሳውዲ አርቢያ በጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ ግድያ ሰበብ ምዕራባውያን ፊታቸውን ሲያጠቁሩባቸውና አገሪቱ ባሰናዳቸው ታላቅ የንግድ ጉባኤ ላይ አንሳተፍም ብለው ሲቀሩ አለሁልሽ ያለችው ፓኪስታን ናት። ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ሳውዲ ተገኝተው ይህን በተግባር አስመስክረዋል።
ሳውዲም ብትሆን በፓኪስታን ላይ የሚጨክን አንጀት የላትም።ይሁንና ልዑል አልጋ ወራሹ ከቀናት በፊት ደቡባዊ እሲያንና ቻይናን ለመጎብኘት ሲወስኑ መዳረሻቸውን ፓኪስታንን ብቻ አላደረጉም። በእርግጥ ጉብኝታቸውን የጀመሩት ከፓኪስታን ነው። የኢስላማባድ መንግስት ታይቶ የማይታወቅ አቀባበል በማድረግ የአገሪቱን ከፍተኛ የክብር ሽልማትም ሰጥቷቸዋል።
አልጋ ወራሹ ኢስላማበድ ደርሰው ግን አልተመለሱም። ወደ ህንድም አቅንተዋል። በኒው ደህሊም የኢስላማባድን ያህል ባይሆንም ልዩ መስተንግዶ ተደርጎላቸዋል ።ጠቅላይ ሚኒስትር ናራዲ ሞዲም ከመንግስታዊ አቀባባል ፕሮቶኮል በተለየ መልኩ መሃማድ ቢን ሰልማንን ከኤርፖርት ጀምረው ተቀብለዋቸዋል።
በሁለቱ ተፋላሚ አገራት ቆይታቸው የሞቀ አቀባባል የተደረገላቸው የሳውዲው ዘዋሪውም በቆይታቸው ቢሊየን ዶላሮችን ለግሰው ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ለማካሄድና በመካከላቸው የተቀሰቀሰውን ውጥረት ለማርገብ አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ቃል ገብተዋል ።
አልጋ ወራሹ ይህን ቃል ከገቡ ውለው ሳያድሩ ግን ሁለቱ አገራት ፍጥጫቸውን ይበልጥ አክርረውት ታይተዋል። አንዳቸው አንዳቸውን መተንኮስ የቀጠሉ ሲሆን፤ ከሁሉም በላይ የህንዱ የትራንስፖርትና የውሃ ሃብት ሚኒስትር ኒቲን ጋዳክሪ ፓኪስታን ከፀብ አጫሪነቷ የማትቆጠብ ከሆነ ወደ ግዛቷ የሚፈሱ ወንዞችን በሙሉ እንደምትገድብና ሀገሪቱን በውሃ ጥም አደብ እንደምታስገዛት ዝተዋል፡፡ ይህን ዛቻቸው አስቂኝና አስገራሚ ከተባሉ ማስፈራሪያዎች አንዱ መሆኑን አልጀዚራ አስነብቧል።
ታሪክን ወደ ኋላ ተመልሶ ለተመለከተ ግን ይህ ቀልድ የማይሆንበትን ምክንያት ይረዳል። ምንም እንኳን በዙም ጊዜ ባይቆይም እኤአ 1948 ህንድ ወደ ፓኪስታን በሚፈሱ ወንዞቿ ላይ መሰናክል አርጋ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። እገዳው መፍትሄ እንዲያገምኝ .የዓለም ባንክ ጣልቃ መግባትን የጠየቀ ሲሆን፤ ለዘጠኝ ዓመታት ከተደረገ ድርድር በኋላ ሁለቱ አገራት የውሃ ሃብቱን በጋራ መጠቀም የሚያስችላቸውን ስምምነት እኤአ 1960 ፈርመዋል።
ስምምነቱም በወቅቱ የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩት ጃዋሃረላ ኔይሩ እና የፓኪስታኑ አቻቸው አያብ ከሃን ፊርማ ነው የታሰረው። አሁን ህንድ ይህን ስምምነት ለማፍረስ ፍንጭ መስጠቷ ታዲያ መጪው ጊዜ ለፓኪስታን ከባድ እንደሚሆን አመላክቷል።
ጠቅላይ ሚንስትር ኢምራን ከሃን የአገራቸው ወታደራዊ ጦር ሃይል ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ሁሉንም እንቅስቃሴ በንቃት እንዲጠብቅና ከህንድ በኩል ማናቸውንም አይነት ጥቃት የሚሰነዘር ከሆነም አፅፋውን ለመመለስ እንዳያመነታ ትዕዛዝ መስጠታቸውም ፍጥጫው ይበልጥ ስለመጋጋሉ በቂ ማሳያ ሆኖ መገኘቱን የዘጋርዲያን ዘገባ አመላክቷል።
በአሜሪካ መሪነት ለዓመታት የዘለቀውን የአፍጋኒስታንን ጦርነት ለመቋጨት በፓኪስታን ምድር ከታሊባን ጋር የስላም ድርድር ለማካሄድ አንዳንድ ተግባራት በተጀመሩበት በዚህ ወቅት፤በጎረቤታሞቹ አገራት መካከል የተከሰተው ፍጥጫ በስላም ውይይቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳረፉም ተጠቁሟል።በካቡል የኢስላማባድ አምባሳደር የሆኑት ዛሂድ ናስሩላህም ፍጥጫው በአሜሪካ መራሹ የአፍጋንኒስታን ስላም ድርድር ላይ ቀዝቃዛ ውሃ የሚቸልስ መሆኑን አመልክተዋል።
ከሁሉም በላይ እሰጣ አገባው ከሚያስከትላቸው ጥፋቶች አስከፊነት ባሻገር አገራቱ ጦርነት ከገጠሙ ፍልሚያቸውም በኒውክሌር የሚታጃብ መሆኑ ስጋቶችን ይበልጥ አክብዷቸዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 19/2011
በታምራት ተስፋዬ