አንድን ሀገር እንደ ሀገር በዓለም የፖለቲካ መድረክ ላይ የተሻለ ተፎካካሪና ውጤታማ ከሚያደርጉት ጉዳዮች አንዱና ዋንኛው ለዓለም አቀፍ ህግጋቶችና መርሆዎች ያለው ተገዥነት እንደሆነ ይታመናል። ከዚህ የተነሳም ሀገራት በውጪ ፖሊሲዎቻቸው ለእነዚህ ጉዳዮች ከፍ ያለ ትኩረት ይሰጣሉ።
የሀገራት የውጪ ጉዳይ ፖሊሲዎች እንደየሀገራቱ ፍላጎትና የዕድገት ደረጃ የተለያየ ቢሆንም በመርህ ደረጃ ግን ሁሉም ሀገራት ለዓለም አቀፍ ህግጋቶችና መርሆዎች የተገዙ መሆናቸው ያመሳስላቸዋል። ለነዚህ ዓለም አቀፍ ህግጋቶችና መርሆዎች የመገዛቱ እውነታም ከህግም በላይ የሞራል እና የሰብአዊነት ጉዳይም ተደርጎ ይወሰዳል።
እነዚሀ ዓለም አቀፍ ህግጋቶችና መርሆዎች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል ሀገራት እንደ ሀገር እኩል ናቸው ከሚል የአስተሳሰብ መሰረት ላይ የተዋቀረ፤ ሁሉንም በእኩልነት የማስተናግድ ለዓለም አቀፍ ሰላምና መረጋጋት ከዛም በላይ አጠቃላይ ለሆነው የሰው ልጆች ሕልውና ከፍ ያለ አቅም ተደርጎ ይወሰዳል።
ይህን ዓለማቀፋዊ እውነታ በየዘመኑ የሚፈታተኑት የተለያዩ ተግዳሮቶች ቢያጋጥሙትም እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ በተለይም ፍትህን የሚሹ የዓለም ሕዝቦች ለእነዚህ ዓለም አቀፍ ህግጋቶችና መርሆዎች ተገዥ ከመሆን ባሻገር ያልተገቡ ተግባራትንም ለመግራት እንደሚረዳ ብቸኛ አማራጭ አድርገው ይወስዱታል።
ይህ እውነታ በሂደት ሀገራት በኢኮኖሚ ፣ በወታደራዊና በፖለቲካው መስክ እያጎለበቱት ካለው አቅም አንጻር፤ ከዚህም በላይ ዓለም አቀፍ ህግጋቶችና መርሆዎች ለማስፈጸም የተደራጁ ዓለም አቀፍ ተቋማትና በኢኮኖሚ፣ በወታደራዊና ፖለቲካ የፈረጠሙ ሀገራት ጉዳይ አስፈፃሚ ወደ መሆን እየሄዱ ያሉበት መንገድ ዓለም አቀፍ ፍትህን ሩቅ እያደረገው መጥቷል ።
በተለይም የአሜሪካ አስተዳደር ራሱን የዓለም ፖሊስ አድርጎ ከሚያይበት የተሳሳተ አመለካከት በመነጨ፤ ከዛም በላይ ያለውን ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ አቅም ታሳቢ በማድረግ በዓለም አቀፍ ህግ የሀገራት የውስጥ ጉዳይ በሆኑ ጉዳዮች ሳይቀር ጣልቃ በመግባት ብዙ ሀገራትን ለውድቀት ህዝቦቻቸውን ለስደትና ለከፋ ህይወት ዳርጓል።
ዓለም አቀፍ ህግጋቶችና መርሆዎች ከጉልበተኛች በታች የሆኑ እስኪመስል ድረስ የአሜሪካ አስተዳደር ለዓለም አቀፍ ህጎቹና መርሆቹ ደንታ ቢስ በመሆን፤ የሀገርን ጥቅም ማስከበር በሚል ትርክት ዓለሙ ሁሉ ለአሜሪካ ጥቅም ገበያ የወጣ ሸቀጥ እስኪመስል ድረስ ዓለሙን አሳንሶ የማየት አባዜ ውስጥ ወድቋል።
ዓለም አቀፍ ህጎችና መርህዎች ከፍ ካሉ ሰብአዊ እሴቶች የመነጨ መሆኑን፤ ለነዚህ ህጎችና መርህዎች መገዛት ከሁሉም በላይ ለሰው ክብር መስጠት መሆኑን እየዘነጋ የሄደው የአሜሪካ አስተዳደር፤ ሁሉንም የሀገር ጥቅም በሚል የራስ ወዳድነት ትርክት ውስጥ በማስገባት የቀደሙት የአሜሪካ መስራች አባቶች ለዓለም ያበረከቷቸውን ታላላቅ ሰብአዊ እሴቶች በማጥፋት ሂደት ውስጥ ተጠምዷል።
በዚህም እለት እለት አሜሪካ በዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ያላትን ተአማኒነትና ተቀባይነት አደጋ ውስጥ እየወደቀ ነው። በተለይም የእራሳቸውን እጣ ፈንታ በራሳቸው ለመወሰን በሚተጉ ድሆችና በማደግ ላይ ያሉ ህዝቦች ዘንድ ከአጋርነት ይልቅ የጠላትነት መንፈስ እየፈጠረች ነው። ይህ ደግሞ በቀጣይ በአሜሪካ ዕጣ ፈንታ ላይ ምን ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ለመገመት የሚከብድ አይደለም።
ለዚህም እንደ ትልቅ ማሳያ የሚታየው በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል ያለው አሁነኛ የግንኙነት እውነታ ነው። በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከመቶ ዓመት የተሻገረ ቢሆንም በአሜሪካ በኩል የሚታየው እውነታ ይህንን ታሳቢ ያደረገ አይደለም። እንዲያውም ዓለም አቀፍ ህግጋቶችና መርሆዎች የጣሰና ምን ታመጣላችሁ ለሚል መንፈስ የተገዛ የሚመስል ነው።
ይህ በብዙ መልኩ የቀደመን የጉርብትና መንፈስ ከማጎልበት ይልቅ የጠላትነት መንፈስ የሚፈጥር የፖለቲካ አካሄድ ለሁለቱም ሀገራት ህዝቦች የሚጠቅም አይደለም። በተለይም የአሜሪካ አስተዳደር በኢትዮጵያ ውስጥ የለውጥ አስተሳሰቦች ነፍስን ዘርተው አካል ለመልበስ በሚያደርጉት ሂደት ውስጥ በየዘመኑ ተግዳሮት ሆነ የመገለጡ እውነታ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ የልብ ስብራት እየሆነ ነው።
በዚህም ዘመን ከብዙ መራራ ትግልና የህይወት መስዋእትነት በኋላ ኢትዮጵያውያን ዋጋ ከፍለው ያመጡትን ለውጥ እንደ ቅርብ ወዳጅ ከመደገፍ ይልቅ የአሜሪካ አስተዳደር የለውጡ ተግዳሮት ሆኖ ተሰልፏል፤ ከሁሉም በላይ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት አድርጎ ከፈረጀውና በእርግጥም ጠላቱ ለሆነው አሸባሪው ህወሓት ህይወት ለመስጠት እያደረገው ያለው ጥረት በታሪክ እንደ አንድ የወዳጅ ክህደት ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
ከሚሰራቸው የሽብር ተግባራት በመነሳት የተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ብሎ ከሰየመውና ራሱ የአሜሪካ መንግስት ከ40 ዓመታት በፊት አሸባሪ ብሎ ከሰየመው ቡድን ጋር ተደራደሩ የሚለው ሀሳብ ከወዳጅ ቀርቶ ከለየለት ጠላት የሚጠበቅ አይደለም ።
ይህ ለቡድኑ ነፍስ ለመዝራት የሚደረግ ጥረት፤ በተዘዋዋሪ ሀገሪቱ የጀመረችውን ለውጥ በግልጽ ለማደናቀፍ የሚደረግ ጥረት እንደሆነ ለመላው ህዝባችን የተሰወረ አይደለም። ይህ ለውጥ ከተከፈለለት ከፍ ያለ ዋጋ አንጻር ለውጡን ለማደናቀፍ መሞከር በህዝባችን ተስፋ የተሞላ እጣ ፈንታ ላይ የመዝመት ያህል ይቆጠራል።
ከዚህም በላይ በቀጣይ የራሳቸውን እጣ ፈንታ በራሳቸው ለመወሰን ተስፋ አድርገው የሚንቀሳቀሱ ህዝቦች ከአሜሪካ ያልተገባ መንገድ ተጨባጭ ትምህርት የሚወስዱበት ከመሆኑም በላይ አሜሪካንን በአጋርነት ከጎናቸው ለማሰለፍ ከመወሰናቸው በፊት ቆም ብለው በብዙ እንዲያስቡ የሚያስገድዳቸው ይሆናል!
አዲስ ዘመን መስከረም 13 ቀን 2014 ዓ.ም