ኢትዮጵያውያን በሀገርና በርስት ለመጣ ባዕድ ጠላት ምንም አይነት ምህረት እንደሌለን በርካታ የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ። በዓድዋ ፣ በአንባላጌ፣ በካራማራና በኡጋዴን የታየው ይኸው ነው፤ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ያስቀደመ የተጋድሎ ታሪክ ነው። ዛሬም የሀገራችን መነሳት የማይፈልጉ ሀይሎች እየፈጠሩ ያለውን ችግር ለመቀልበስ መላው ህዝባችን ያሳየው ተነሳሽነት የዚሁ ታሪካዊ እውነታ ቀጣይ ምእራፍ ነው።
እነዚህ ሀይሎች ከሀዲውንና የምንጊዜም የኢትዮጵያ ጠላት የሆነውን አሸባሪው ህወሓት በመደገፍና ሽፋን በመስጠት የሀገርን ሉዓላዊነትና የህዝባችንን አንድነት ስጋት ውስጥ በሚከት የሴራቸው መንገድ ላይ ይገኛሉ። በስውር እና በግልጽም በሚታይ ደባ ከከሀዲውና ከነፍስ በላው ህወሓት ጋር አብረው ኢትዮጵያን ለማጥፋት እየተንቀሳቀሱ ነው። በተለይም የባይደን አስተዳደር ግልጽ በሆነ ወገንተኝነት ለአሸባሪው ህወሓት ህይወት ለመስጠት የተለያዩ ጫናዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል።
የባይደን አስተዳደር ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ለመጡባቸው ቀልድ እንደማያውቁ። ለሀገራቸውና ለክብራቸው አንገታቸውን ለሰይፍ የሚሰጡ ጀግኖች ማፍሪያ እንደሆነች። ይሄም ትውልድ በአባቶቹ እውነት ላይ የቆመ፤ ኢትዮጵያን ከጁንታው አገዛዝ ነጻ ለማውጣት ነፍሱን የሰጠ ትውልድ መሆኑን በአግባቡ የተረዱ፤ የጫናዎች ብዛት ይህን ሀገራዊ መንፈስ ሊሰብር እንደማይችል፤ የጀመርነው የለውጥ ጉዞ ከዚህ መንፈስ የተቀዳ እንደሆነም የተረዳው አይመስልም።
ይህንን እውነታ አስተዳደሩ በአግባቡ እንዲረዳውም ‹ነጩ ፖስታ ለነጩ ቤተመንግስት› በሚል የጋራ ሀሳብ ሁሉን አቀፍ ንቅናቄ እየተካሄደ ይገኛል። የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ እያደረሰ ያለውን ያልተገባ ጫና እንዲመረምር የሚጠይቁ በርካታ የህዝብ ድምጾች ከዚህም ከዛም እየተሰሙ ነው። እንዲህ እንደ አሁኑ አይነት ያልተገባ ነገር ሲፈጠር በጋራ መጮህ መፍትሄ አለው። በተለይም በባይደን አስተዳደር በኩል የሚታየው ያልተገባ ወገንተኝነት ለመቀልበስ ትልቅ አቅም እንደሚሆን ይታመናል።
የባይደን አስተዳደር በተሳሳቱ መረጃዎች ላይ በመመስረት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በሚገዳደሩ ተግባራት ላይ ይገኛል። በሽብርተኝነት የተፈረጀ አሸባሪ ቡድን ወደ ስልጣን ካልመጣ በሚል በመንግስት ላይ ጫና ለማሳደር እየሰራ ይገኛል። ከዚህ በተጻራሪ ደግሞ ቡድኑ ንጹሐንን ሲገድልና ንብረት ሲያወድም፣ ብዙዎችን ከቤት ንብረታቸው ሲያፈናቅል በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ኢ- ሰብአዊ ድርጊት ሲፈጽም ድምጹን ለማሰማት ተግባሩን ለማውገዝ ፈቃደኛ አይደለም።
አሸባሪው ህወሓት በአደባባይ በአፋርና በአማራ ክልል ያደረሰው ዘግናኝ እልቂት ዙሪያ የባይደን አስተዳደር ምንም ለማለት ፈቃደኛ አይደለም ። በርካታ ትምህርት ቤቶችን፣ በርካታ ጤና ጣቢያዎችንና ሆስፒታሎችን እንዲሁም የግልና የመንግስት ድርጅቶችንና ባንክ ቤቶችን ሲያወድምና ሲዘርፍ ዝምታም መርጧል። ህጻናትን በአደንዛዥ እጽ አደንዝዞ በጦርነት ሲማግድ፣ የዘር ማጥፋት ወንጀሎችን ሲፈጽም ድርጊቱን ከማውገዝ ዝምታን መርጧል ።
በቅርቡ እንኳን የሰብአዊ እርዳታ ጭነው ወደ ክልሉ ከገቡ የጭነት መኪናዎች ውስጥ አራት መቶ ሃያ ስምንት የሚሆኑት እስካሁን አለመመለሳቸው አስመልክቶም አሜሪካ ያለችው አንድም ነገር የለም።
ከዚህ በተቃራኒ በኢትዮጵያውያን የጋራ ክንድ አሸባሪው ህወሓት ሲመታ.. ሽንፈትን ሲከናነብ፤ ወደ ኋላ ሲሸሽና እየተሸነፈ መሆኑን ስታውቅ የባይደን አስተዳደር ድምጽዋን ከፍ አድርጎ ከመጮህ ባለፈ ያልተገቡ ጫናዎቹን ለማሳደር ሲተጋ ይስተዋላል።
አሸባሪው ህወሓት በስልጣን ዘመኑ ከአሜሪካ መንግስት አንዳንድ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ከነበረው መርህ አልባ ግንኙነት የተነሳ የነበረው እውነታ አሜሪካ ለጁንታው ጁንታው ለአሜሪካ ምን ማለት እንደሆኑ ተጨባጭ ምስክሮቻቸው ናቸው። አሸባሪው ህወሓት በስልጣን ዘመኑ ከተላላኪነት ባለፈ ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም የሰራው ይህ ነው የሚባል ስራ የለም። ሀገርንና ህዝብን ከመከፋፈል፤ የህዝብን ሀብት ከመዝረፍና ከማሸሽ ከዛም አልፎ የሀገርን አንድነት አደጋ ውስጥ የሚከቱ ተግባራትን ከመፈጸም ያለፈ አይደለም።
በነጩ ፖስታ በምናሰማው ድምጻችን የቡድኑን ማንነት ከፍ አድርገን በማሰማት፣ ቡድኑን ለመታደግ የሚደረገውን ጥረት መቀልበስ ይጠበቅብናል። ልክ እንደ ሰሞኑ ከነጩ ቤተመንግስት ሹማምንት ዘንድ ኢትዮጵያውያንን የሚያስቆጣ ወሬ ልንሰማ እንችላለን። ይህ ግን ሊገርመንና ሊደንቀን አይገባም፤ ከእኛ የሚጠበቀው ግን በአንድ አላማ ወደፊት መጓዝ ብቻ ነው።
የአሜሪካ ማዕቀብና ክልከላ ለእኛ አዲስ ነገር አይደለም፤ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጀምሮ ስንሰማውና ስንፈተንበት ያለፍነው ፈተና ነው። ፈተና ለኢትዮጵያውያን ብርቃችን አይደለም። በእሳት ውስጥ ተፈትነን እንደ ወርቅ ያበራንበት ጊዜ ብዙ ነው። ይሄም ጊዜ ያበረታናል እንጂ አያላላንም። ያደምቀናል እንጂ አያደበዝዘንም።
አንድ አሸባሪ ቡድንን ወደ ስልጣን ካልመጣ ብሎ እርዳታ መከልከልና ማዕቀብ መጣል ምን ማለት እንደሆነ ለሁላችንም ግልጽ ነው። ከሀገርና ህዝብ ጥቅም በላይ የጥቂት ግለሰቦችን ፍላጎት አስቀድሞ እንዲህ ካልሆነ እንዲህ አደርጋለሁ ማለት ከአንድ ስልጡን ነኝ ከምትል ሀገር የሚጠበቅ አይደለም። የሆነው ሆኖ ግን እኛ የአባቶቻችን መልኮች ነን። ለባዕድ ተንበርክከን አናውቅም። በእውነት ስናሸንፍ እንጂ በውሸት ስንሸነፍ አንታወቅም። እውነትና ፍትህ በልባችን ስላለ ሁሌም እናሸንፋለን። በዚህም ሁሉን አልፈን በድል የምንደምቅበት ቀን ሩቅ አይሆንም ።
ሀገራችን በአዲሱ የለውጥ መንግስት ብርሀን ለማየት በምታደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ምን ያክል እንደሆነ የሚታወቅ ነው። አሜሪካ በኢትዮጵያ የተጀመረውን የለውጥ መንገድ ለማደናቀፍ እየሄደችበት ባለው ያልተገባ መንገድ ተሸንፈን እንጂ አልሰጠንም፤ ወደፊትም አንሰጥም።
ከዚህ በኋላ በሚኖረው ጊዜ ጫናዎች እየበረከቱ ቢሄዱ እንኳን የያዝነው እውነት ከፍ ያለ ስለሆነ በጽናት ታግለን እንደምናሸንፍ የትናንት ታሪካችን የሚያረጋግጠው ነው ለዚህም ባላቸው እውቀትና አቅም እየተንቀሳቀሱ ላሉ ዜጎች ሁሉ ከበሪታና ምስጋና ይገባቸዋል። እያጋጠሙን ባሉ ችግሮች ዙሪያ በጋራ መቆማችን የሀራችንን ሉዓላዊነትና የለውጥ ጉዞ አስቀጥሎ ለመሄድ ወሳኝ አቅም ነው። አሸባሪውን ህወሓትን ለመጣል እንደታገልነው ሁሉ የውጪ ሐይሎችን ተጽእኖ ለመቀልበስ መታገል ይኖርብናል።
ነጩ ፖስታ እኔና እናንተ ነን። ነጩ ፖስታ የኢትዮጵያ እንባ ነው። ነጩ ፖስታ የመቶ ሃያ ሚሊዮን ህዝብ እውነት ነው። ኢትዮጵያን የማዳን ተልዕኮ ነው። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሚጮሁ የጋራ ድምጾች የፈጠሩት ድምጽ ነው።
አሁን ላለችውም ነገ ለምትፈጠረው ሀገራችን የጋራ ድምጽ ያስፈልገናል። የኢትዮጵያን መነሳት በማይፈልጉ በጥቂት ራስ ወዳድ ሀገራት ክብራችንን ማጣት የለብንም። የአባቶቻችን እውነት አንድነት ነው። የአባቶቻችን የአደራ ቃል ኢትዮጵያዊነት ነው። የአባቶቻችን የተጋድሎ አላማ አንድ ሀገርና አንድ ህዝብ ነው። ከዓድዋ ያገኘነውን ነጻነት ለውጪ ሀይሎች ተጽእኖ አሳልፈን መስጠት የለብንም። የአባቶቻችን ልጆች ሆነን መቀጠል ይኖርብናል።
የአሸባሪው ህወሓትን ምኞት ከንቱ በማድረግ፣ የውጪ ሀይሎችን ሴራ በድል በመወጣት ትንሳኤችንን የምናበስርበት ቀን ሩቅ አይሆንም። የምንፈልጋት ኢትዮጵያ በድምጻችን ውስጥ ነች። ስለ ሀገራችን ዝም አንልም። ጁንታውን ለመጣል በጋራ እንደዘመትን ሁሉ የውጪ ሀይሎችን ልሳን ለመዝጋትም በጋራ መጮህ ይኖርብናል።
ኢትዮጵያውያን የባይደን አስተዳደር በሀገራችን የውስጥ ጉዳይ ገብቶ እንዳሻው እንዲሆን አይፈቅዱም። ይህንን እድል ሊፈጥርለት የሚችለው አሸባሪው ህወሓት ብቻ ነው። ይህን የሚያደርገው ልብ ውስጥ ሀገርና ህዝብ ስለሌለ ነው። በፍጥረቱ ሆድ እንጂ ራስ ፤ አካል እንጂ ነፍስና አእምሮ ስለሌለው ነው።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን መስከረም 13 ቀን 2014 ዓ.ም