በቀጣዩ ዓመት (እአአ 2022) በሚካሄደው የኳታር ዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ለመሆን የሀገሮች ብሄራዊ ቡድኖች የማጣሪያ ጨዋታዎችን ማካሄዳቸው ቀጥሏል። በማጣሪያ ጨዋታው ላይ በመሳተፍ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሄራዊ ቡድንም (ዋሊያዎቹ) ከደቡብ አፍሪካ አቻው ጋር በቅርቡ ለሚያካሂደው ጨዋታ ቡድኑ እንዲሰባሰብ ጥሪ ተደርጎለታል።
በተወዳጁ የእግር ኳስ ስፖርት ታላቁና አጓጊው ውድድር የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ በቀጣዩ ዓመት በኳታር እንደሚካሄድ ይታወቃል። ኳታርም በዚህ ውድድር አስተናጋጅነት የመጀመሪያዋ የአረብ ሃገር በእስያ አህጉር ደግሞ ሁለተኛዋ ሃገር ለመሆን ችላለች።
ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በተግባር ላይ ያዋለችው ኳታር ዝግጅቷን በማጠናቀቅ ላይም ትገኛለች። ሃገራት በየአራት ዓመቱ በጉጉት ለሚያገኙት ውድድር ተሳታፊ የሚሆኑበትን ዕድል ለማግኘትም በየአህጉሩ በሚካሄዱት የማጣሪያ ጨዋታዎች እየተፎካከሩ ይገኛሉ። በዓለም ዋንጫው አምስት ሃገራትን የምታሳትፈው አህጉረ አፍሪካም ብሄራዊ ቡድኖችን በአስር ምድብ በመከፋፈል የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያካሄደች ትገኛለች።
ኢትዮጵያም በምድብ ሰባት ከጋና፣ ደቡብ አፍሪካ እና ዚምባቡዌ ጋር ተደልድላ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ከሜዳዋ ውጪ ከጋና ጋር እንዲሁም በሜዳዋ ከዚምባቡዌ አቻዎቿ ጋር ማድረጓ የሚታወስ ነው። ጋና ላይ በጥቁር ከዋክብቱ1 ለ 0 የተሸነፈችው ኢትዮጵያ ከቀናት በኋላ ዚምባቡዌን በባህርዳር ስታዲየም አስተናግዳ 1ለ0 በሆነ ውጤት ማሸነፏ የሚታወስ ነው።
የምድቡ ሶስተኛው ጨዋታም ባላት ነጥብ ከምድቡ ቀዳሚ የሆነችው ደቡብ አፍሪካ ከኢትዮጵያ ጋር የምትጫወት ይሆናል። የደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድን በመጀመሪያ ጨዋታ ከዚምባቡዌ ጋር ተገናኝቶ ያለምንም ግብ የተለያየ ሲሆን፤ በሁለተኛው ጨዋታ ደግሞ ጋናን 1ለባዶ ማሸነፍ ችሏል። ከሁለት ሳምንት በኋላም ባፋና ባፋና ከዋሊያዎቹ እንዲሁም ጋና ከዚምባቡዌ የሚጫወቱ ይሆናል። ብሄራዊ ቡድኑ / ዋልያዎቹ/ መስከረም 26 ቀን 2014 ዓ.ም በሜዳቸው (በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም) ከአራት ቀናት በኋላ መስከረም 30 ቀን 2014 ዓ.ም ደግሞ ከሜዳቸው ውጪ በደቡብ አፍሪካ አቻቸውን የሚገጥሙ ይሆናል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተም ለዚህ ጨዋታ ዝግጅት ለማድረግ ለተጫዋቾቻቸው ጥሪ አድርገዋል። 25 አባላትን ያቀፈው ቡድኑ፤ ተጫዋቾች ዛሬ ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ በጁፒተር ሆቴል ተገኝተው ሪፖርት እንዲያደርጉ ጥሪ እንደተደረገላቸው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በድረ ገጹ አስነብቧል። የቡድኑ አባላት አስፈላጊውን የጤና ምርመራዎች ካደረጉ በኋላም ዝግጅታቸውን ከመስከረም 14 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በባህር ዳር ከተማ የሚያከናውኑ እንደሚሆንም ታውቋል።
በዚህም መሰረት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ግብ ጠባቂዎች፤ ተክለማሪያም ሻንቆ፣ ጀማል ጣሰው እና ፋሲል ገብረሚካኤል ጠርተዋል። በተከላካዮች በኩል ደግሞ አስራት ቱንጆ፣ ሱለይማን ሀሚድ፣ ረመዳን የሱፍ፣ ደስታ ዮሐንስ፣ ያሬድ ባየህ፣ አስቻለው ታመነ፣ ምኞት ደበበ እና መናፍ አወል ስብስቡን ተቀላቅለዋል። አማካዮች፤ አማኑኤል ዮሐንስ፣ ይሁን እንደሻው፣ ጋቶች ፓኖም፣ መሱድ መሀመድ፣ ሱራፌል ዳኛቸው፣ ታፈሰ ሰለሞን፣ ሽመክት ጉግሳ እንዲሁም ሽመልስ በቀለ ሆነዋል። የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ አማኑኤል ገብረሚካኤል፣ ጌታነህ ከበደ፣ አቤል ያለው፣ ቸርነት ጉግሳ እንዲሁም የሃዋሳ ከተማው መስፍን ታፈሰ እና የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር ደግሞ በአጥቂ መስመር የተመረጡ ተጫዋቾች ናቸው።
እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ደቡብ አፍሪካም ለመጪው ጨዋታ ለተጫዋቾቿ ጥሪ ማድረጓን ሶከር ኢትዮጵያ አስነብቧል። የቡድኑ አሰልጣኝ ሁጎ ብሮስ ለ34 ተጫዋቾቻቸው ጥሪ ማስተላለፋቸውን የሀገሪቱ ብዙሃን መገናኛዎች እየዘገቡ ይገኛሉ። የምድቡ መሪ የሆኑት ባፋና ባፋናዎች ለ34 ተጫዋቾች ጥሪ ቢያስተላልፉም በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም እና በ‹‹ኤፍ ኤን ቢ›› ስታዲየም ለሚያረጉዋቸው ወሳኝ ፍልሚያዎች የሚጠቀሟቸውን 23 ተጫዋቾች ከአራት ቀናት በኋላ እንደሚለዩ ተጠቁሟል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 12/2014